“ሥራ ፈጣሪ መሆን ለአንድ ችግር መፍትሔ መስጠት መቻል ነው”- ወጣት ሲሃም ፈይሰል

በኢትዮጵያ በዓመት እስከ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ወጣቶች ወደ ሥራ ዓለም ይቀላቀላሉ ። ለዚህን ያህል ዜጋ በመንግሥት ወይም በግል ተቋማት እና ድርጅቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ባለመቻሉ ደግሞ አብዛኛዎቹ ለሥራአጥነት ይዳረጋሉ። ይህንን ችግር ለመፍታት ደግሞ ሥራ ጠባቂ ከመሆን ይልቅ ሥራ ፈጣሪ ሆኖ መገኘት የሚጠበቅ ሆኗል።

ሆኖም በኢትዮጵያ በርካታ ወጣቶች የሥራ ፈጠራ ባለሙያዎች ቢሆኑም የፈጠራ ሃሳባቸውን ወደ ተግባር ለማዋል የመሥሪያ ቦታ እጥረት፣ የብድር አቅርቦት አለመመቻቸት፣ የገበያ ትስስር አለመኖር እና የክህሎት ክፍተቶችና መሰል ችግሮች እንቅፋት ሆኖ ሲገጥማቸው ይስተዋላል።

አንድ ሰው የተሳካለት ሥራ ፈጣሪ ወይም ኢንተርፕረነር ለመሆን፣ የያዘው ሃሳብና ሃሳቡን ተግባራዊ ማድረጊያ ገንዘብ ወሳኝ መሆናቸው አይጠረጠርም። ሆኖም፣ እነዚህ ሁለቱ ብቻ ሥራ ፈጣሪው የተሳካለት የቢዝነስ ሰው እንዲሆን አያስችሉትም። ሥራ ፈጣሪው፣ ስኬትን መቀዳጀት እንዲችል ወይም ጉዞው ወደ ስኬት የሚገሰግስ እንዲሆን፣ ዓይነተኛ የሆኑ የሰብዕና መገለጫዎች ያስፈልጉታል። እንደ ሥራ ፈጣሪ፣ እነዚህ የሰብዕና መገለጫዎች ወይም ጠባዮች ካሉት ሊያዳብራቸው፣ ከሌሉት ደግሞ እንደ አዲስ ኮትኩቶ ሊያሳድጋቸው ይገባል።

ወጣት ሲሃም ፈይሰል ትበላለች። ትውልድ እና ዕድገቷ በኢትዮጵያውያን ብሎም በመላው ዓለም ሕዝቦች ዘንድ የፍቅር፣ የመቻቻል የመከባበርና የአንድነት ተምሳሌት ተደርጋ በምትነሳው ታሪካዊቷ ሀረር ከተማ ነው። ከመጀመሪያ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በዛው ተከታትላለች። በትምህርቷ ጠንካራ ከሚባሉ ተማሪዎች መካከል የነበረችው ሲሃም በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ጥሩ ውጤት በማምጣት ለከፍተኛ ትምህርት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መቀላቀል ችላለች።

ከሀረር አዲስ አበባ የደረሰችው ሲሃም ዩኒቨርስቲው ‹‹ምህንድስና የደረሳችሁ የህንፃ ዲዛይን ወይም የአርክቴክቸር ትምህርት ለመማር መወዳደር ትችላለሁ›› ብሎ ባሳወቀው መሠረት ተወዳድራ በጥሩ ውጤት ፈተናውን በማለፍ አምስት ዓመት ከግማሽ ትምህርቷን ተከታትላ በአርክቴክቸር ምህንድስና የመጀመሪያ ዲግሪ ከአንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማግኘት ችላለች።

ወጣት ሲሃም በብዙ መልኩ የዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ የተሳካ እንደነበር ትገልጻለች። የአርክቴክቸር ትምህርት ከሌላው የትምህርት አይነት በተለየ መልኩ ክብደት እንዳለው የምትናገረው ሲሃም፤ በዚህ ምክንያት ሌሊቱን ሙሉ በጥናት ከጓደኞቿ ጋር ቁጭ ብላ ታሳልፍ እንደነበር ታስታሳውሳለች። የምህንድስና ትምህርት በተለየ መልኩ ደግሞ አምስት አመት ከግማሽ ነበር የሚወሰደው። ሆኖም ከፈጣሪ ጋር ስኬታማ መሆን ስለመቻሏ ትናገራለች።

በመጀመሪያ ወደ ሥራው ዓለም ስትቀላቀል ስለነበረው ሁኔታ ሲሃም ስትናገር፤ በተለያዩ የግልና የመንግሥት ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥራ ስለመስረቷ ታስረዳለች፤ “ተቀጥሮ መሥራት ለተወሰነ ጊዜ መጥፎ አይደለም፤ ተቀጥሮ መስራትን አልቃወምም። ምክንያቱም በአካዳሚክ የትምህርት ቆይታ አጠቃላይ የሆነ እውቀት ነው ይዞ መውጣት የሚቻለው። ወደ ተግባር የሥራ ዓለም ስንመጣ ልዩነት አለው። በተለይም ምህንድስና ደግሞ የተለየ ነው። ስለዚህ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ለመላመድ ተቀጥሮ መሥራት ጠቃሚ ነው። እኔ በግሌ በብዙ መልኩ ያስተማረኝ ልምድ ያገኘሁበት ነበር” ትላለች።

ሲሃም የራሷን ሥራ ለመስራት ከተቀጣሪነት ወጥታ ወደ ግል ሥራዋ ከመግባቷ በፊት የምትሰራውን ሥራ በግማሽ ቀን በማድረግ በቀሪ ሰዓት የግል ቢዝነሷን ማከናወን እንደጀመረች ታስረዳለች። “የራሴ ሥራ ሲኖረኝ ትርፍ ሰዓት አገኛለሁ ብዬ አስብ ነበር የምትለው ወጣቷ ይህ ግን ስህተት ነበር። ተቀጥሬ ስሠራ ከጠዋት 2 ሰዓት እስከ 11 ሰዓት ነበር የምሠራው። ወደ ራሴ ሥራ ከገባሁ ጊዜ ጀምሮ ግን 18 ሰዓት ነው የምሰራው›› ትላለች።

አሁን የተለያዩ ድርጅቶችን መሥርታ እየሠራች የምትገኘው ሲሃም ኢኖቮ የሚል ስያሜ በተሰጠው ድርጅቷ አማካኝነት በቤት ውስጥ ማስዋብ (inte­rior design) ሥራ ታከናውናለች። ከዚህ በተጨማሪ ክሬኤትቪ ጎጆ በተባለ የራሷ ኩባንያ በኩል የወዳደቁ የቆሻሻ ላስቲኮችን፣ ወረቀቶችን እንደገና በማስተካከል በማስዋብ የሚሸጥ ድርጅት እንደሆነ ትናገራለች።

አንድን ነገር ፈጠራ በተሞላበት መልኩ ወይም ከሌላ ሰው በተለየ መልኩ መሥራት ከተቻለ ውጤታማ መሆን ይቻላል የምትለው ሲሃም፤ የምንሠራው ሥራ አዲስ ነገር ያማከለ፤ ጥራት ያለው መሆን ከቻለ በሰፊ ገበያ ውስጥ ተሰማርቶ አሸናፊ መሆን ይቻላል ትላለች። በተለይ የኮንስትራክሽን ሥራ ጥራትን በእጅጉ ስለሚፈልግ ከምንም በላይ ለጥራት ቅድሚያ መስጠት አስፈለጊ ነው “እኔም ውጤታማ መሆን የቻልኩት በዚህ መርህ መጓዝ በመቻሌ ነው” ትላለች።

ወደ ግል ሥራ ለመግባት በዋናነት ምክንያት ስለሆኗት ነገር ወጣት ሲሃም ስትናገር፤ በግማሽ ቀን ሥራ በምትሠራበት ወቅት ማለትም ወረቀት (recy­cle) በማድረግ በምትሸጥበት ወቅት በመንግሥት ሥራ ከምታገኘው ደሞዝ የተሻለ ገቢ ማግኘት ቻለች። ይህ አዋጭ መንገድ መሆኑን በመረዳት በሙሉ ጊዜ የግል ሥራ ለመስራት እንደወሰነች እና ሁኔታው በራሱ ወደ ግል ሥራ እንደመራት ትናገራለች።

በኮንስትራክሽን ሥራው በዋናነት ችግር ሆኖ ያለው የዕቃ አቅርቦት ችግር እንደሆነ የምትገልጸው ወጣቷ፤ “የኮንስትራክሽን ዕቃ ለመግዛት አንድ ቦታ ስንሄድ የለም ነው የምንባለው በዚህ ምክንያት እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ድርጅቱም ይበልጥ ፈጠራ ላይ ትኩረት አድርጎ ስለሆነ ሥራውን የሚሰራው ሱቅ የማናገኘውን ዕቃ ውበቱን ሳያጣ በሌላ ዕቃ እንዴት መቀየር እንችላለን የሚለውን በመለየት በራሳችን ለመሥራት ጥረት እናደርጋለን በዚህ መልኩ ያጋጠሙ መሰናክሎችን ለመፍታት እየሠራን ነው ያለነው” ትላለች።

ከአስር ለሚበልጡ ሰዎች በድርጅቶቿ በኩል የሥራ ዕድል መፍጠር እንደቻለች የምትናገረው ሲሃም፤ ከዚህ በተጨማሪ አራት እናቶች በቤታቸው ሆነው እየሠሩ ገቢ እንዲያገኙ መደረጉን ትገልጻለች። እናቶች በቤት ሆነው ለተለያዩ የቤት ማሳመሪያ የሚሆን ዕቃዎችን ማለትም ወረቀት፣ ፕላስቲክ የመሳሰሉትን ለድርጅቱ ያቀርባሉ። እነዚህ ዕቃዎች ለቢሮ ማሳመሪያ ለተለያዩ አገልግሎት መዋል እንዲችሉ ተደርገው ይሠራሉ። በዚህም እናቶች ገቢ ማግኘት እየቻሉ ነው ትላለች።

‹‹ሥራ ፈጣሪ ወይም የቢዝነስ ባለቤት መሆን ለአንድ ችግር መፍትሔ መስጠት መቻል ነው ብዬ ነው የሚወስደው›› የምትለው ወጣት ሲሃም፤ መጀመሪያ ከችግሩ ከልተነሳን እና መፍትሔ ለዚያ ችግር መስጠት የማንችል ከሆነ እና ሰው የሚያደርገውን ነገር፣ ሰው የፈጠረውን መፍትሔ የምንደግም ከሆነ ሥራ ፈጣሪ መሆን አንችልም። ውጤታማም አንሆንም፤ ስለዚህ መጀመሪያ መፍታት የምንፈልገው ችግር ምንድነው የሚለውን ከያዝን እና ከእሱ ከጀመርን ስኬታማ መሆን የማንችልበት ምክንያት የለም›› በማለት ወጣቶችም ሥራ ፈጣሪነትን በዚህ መልኩ ሊረዱት እንደሚገባ ትናገራለች።

አንድ ሥራ ፈጣሪ ወደ ስኬት ለመድረስ ቆስቋሽ ሳያስፈልገው የራሱ ተነሳሽነት ሊኖረው ይገባል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የበለጠ ኃላፊነትን መውሰድ ይጠበቅበታል። በዙሪያው የሚያበረታቱ ሰዎች ቢኖሩ መልካም ነው። ባይኖሩም ግን ከማንም በላይ “ለራሳችንን ሞራል የምንሰጠው” እና የምናነሳሳው ራሳችን መሆን እንዳለብን ወጣት ሲሃም ትናገራለች።

ወጣት ሲሃም እንደምትናገረው፤ አደጋን ለመጋፈጥ ፈቃደኛ መሆን የስኬታማ ሥራ ፈጣሪ ቁልፍ መለያ ነው። አዲስ ቢዝነስ ጀምሮ ስኬት ላይ ለመድረስ፣ ወይም ያለንን ቢዝነስ ለማሳደግ እየፈለግን በሌላ በኩል ደግሞ ምንም ዓይነት አደጋ መሰል ነገር ማሰብ አንፈልግም ማለት አብሮ አይሄድም። በሚገባ አሰላስሎ፣ አውጠንጥኖ፣ ግራ ቀኙን ተመልክቶ አዲስን ነገርን የመጀመርና የመሞከር “አደጋን” ለመጋፈጥ ፈቃደኛ መሆን እንደሚያስፈልግ ትናገራለች።

ሲሃም እንደምትናገረው፤ በትምህርት፣ ቴክኖሎጂ፣ በግብርና እና በሌሎችም የኢትዮጵያን ዕድገት በሚያሳልጡ ዘርፎች ሁሉ የኢትዮጵያ ወጣቶች በሥራ ፈጠራ ላይ ተሰማርተው እየሠሩ ቢገኙም ያላቸውን ርዕይ ወደ ተግባር ላይ ለመለወጥ በርካታ ተግዳሮቶች ይጋፈጣሉ። ስለዚህ ችግሮችን ለመፍታት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ትገልጻለች።

ልንሰማራ ባሰብንበት መስክ፣ አስተማማኝ የሆነ ችሎታ እንዳለን በራሳችን መተማመን ያስፈልገናል የምትለው ሲሃም፤ በጠራ አእምሮ ስናስብ የሚታየን የችሎታ ክፍተት ካለብን፣ ራሳችንን ከማታለል ይልቅ ችሎታችንን ለማዳበር መነሣት ወይም ሌላ የሚስማማንን የሥራ መስክ መምረጥ ይኖርብናል። ነገር ግን፣ ችሎታው እንዳለን ካወቅን በፍፁም ልንዘናጋ እንደማይገባ ትናገራለች።

ስኬታማ ኢንተርፕረነሮች ከዛሬው እንቅፋት፣ ውጣ ውረድ ወይም ጊዜያዊ ድል ይልቅ የወደፊቱ ጊዜና የሚደርሱበት ከፍታ የሚታያቸው ናቸው። ሁልጊዜም ከወራት፣ ከዓመታት በኋላ ሥራችን የት እንደሚደርስ በማሰብ መቃኘት ይኖርብናል። ራዕይና ዓላማችንን ስናስብና የወደፊት ግባችንን መላልሰን የምናስብ ስንሆን፣ ዛሬ የሚገጥሙንን እንቅፋቶችም ሆነ “ማታለያዎች” ለማለፍ አቅም ይኖረናል።

አዲስ ሥራ ስንጀምር፣ እየሠራንም ከሆነ ሥራችንን ለማስፋት ስናስብ ነገሮች ሁሉ አልጋ በአልጋ ይሆኑልናል ብሎ መጠበቅ ዘበት ነው። ያለን ገንዘብ፣ የሰው ኃይል፣ የሥራ ቦታ፣ የገበያ ትስስር ወዘተ በምንፈልገው “ሃሳባዊ” ልክ የመሆን ዕድሉ አነስተኛ ነው። ስለዚህ ያሉንን ነገሮች ቅደም ተከተል በማስያዝና በሁነኛ መንገድ በማቀናጀት መሥራት መቻል አለብን። እንዲህ ማድረግ እንድንችል ደግሞ ነገሮችን የማቀናጀትና ውጤት የማምጣት ክህሎትን ማዳበር ያስፈልገናል።

በእርግጥ አንድ ቢዝነስ ህልውናው ሊቀጥል የሚችለው አትራፊ ከሆነ፣ በሌላ አባባል ከወጪው ይልቅ ገቢው ከበለጠ ነው። የዚህ ዋናው መለኪያ ደግሞ የተስተካከለ የገንዘብ ፍሰት ነው። ይሁን እንጂ፣ አንድ ቢዝነስ ትርፋማ ለመሆንና ላለመክሰር መጠንቀቅ ያለበትን ያህል ዋና ግቡን እንደው ዝም ብሎ ገንዘብ ማጋበስ እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ስለዚህም፣ “በፍጥነት” ከምንሰበስበው ገንዘብ ይልቅ፣ በምርታችን ወይም በአገልግሎታችን ለምንጨምረው እሴት ዋጋ መስጠት ይኖርብናል። ለጥራት፣ ለአገልግሎት ርካታና ለመሳሰሉት እሴቶች ከፍተኛ ዋጋ የምንሰጥ ከሆነ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተዓማኒነታችን ከፍ እያለና ትርፋችን እየጨመረ መሄዱ አይቀሬ ነው።

ወጣት ሲሃም እንደምትናገረው፤ በፈጠራ ሥራ ውጤታማ ለመሆን በገበያው ውስጥ የቆዩ የንግድ ድርጅቶች ወይም ኢንተርፕራይዞች ከሚሰጡት አገልግሎትና ከሚያቀርቧቸው ምርቶች በመነሳት ምን መሻሻሎች ብናደርግ ብቁ ተወዳዳሪ ሆነን ልንቀርብ እንችላለን? የሚሉና ሌሎች ተመሳሳይ ጥያቄዎችን በአእምሮአችን በማምጣት በራሳችን በርካታ አዳዲስ የንግድ አማራጮችን ማመንጨት እንችላለን ትላለች። ከዚህ በተጨማሪ ነባር ምርቶችን ተጨማሪ አገልግሎቶች እንዲሰጡን አድርጎ በማሻሻል አዳዲስ ምርቶችን ወደ ገበያ መምጣት ይቻላል፤ በዙሪያችን የሌሉ ነገር ግን በሌሎች አካባቢዎች የተለመዱ የምርትና የአገልግሎት አይነቶችን በመለየት ለአካባቢው በሚሆን መልኩ በማቅረብ ስኬታማ መሆን እንደሚቻል ትገልጻለች።

በመጨረሻም ወጣት ሲሃም ባስተላለፈችው መልዕክት፤ ወጣቶች ብዙ ፈተና ሊያጋጥማቸው ይችላል። ነገር ግን እጅ ባለመስጠት እስከመጨረሻው መጓዝ አለባቸው። ኢትዮጵያን ጨምሮ ታዳጊ ሀገራት ከወጣት አምራች የሰው ሃይላቸው ብዙ ስለሚጠብቁ ወጣቶች የራሳቸውንና የሀገራቸውን ነገ የተዋጣለት ለማድረግ መሥራት አለባቸው ስትል መልዕክቷን አስተላልፋለች።

ክብረአብ በላቸው

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 5 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You