ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ስኬት እንደ ተሞክሮ !!

 እስካሁን ድረስ አንገብጋቢ ከሆኑና በቅጡ ካልተፈቱ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ችግሮች ውስጥ የመኖሪያ ቤት በዋናነት ይጠቀሳል። ከዛሬ ሀያና ሠላሳ ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ መኖሪያ ቤት ትልቅ ጉዳይ አልነበረም። ኅብረተሰቡ ከየትም ይምጣ ከየትም በቀላሉ የመኖሪያ ቤት ፍላጎቱን በተለያዩ አማራጮች ማሳካት ይችል ነበር።

በርግጥ በግዜው የነበረው የከተማዋ ነዋሪ ቁጥር እንደአሁኑ የበዛ አለመሆን፤ በግዜው ከነበረው በቂ የመሬት አቅርቦት ጋር ተዳምሮ የመኖሪያ ቤት ጥያቄ በቀላሉ እንዲመለስ አስተዋፅዖ ማድረጉ የሚካድ ሐቅ አይደለም። ሁኔታው በጊዜ ሂደት እየተቀየረ አሁን ላይ የከተማዋን ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለማርካት አስቸጋሪ ሆኗል ።

ችግሩን ለመፍታት ከተደረጉ ጥረቶችና እስካሁን በተለያዩ ችግሮች የተጠበቀውን ያህል መጓዝ ያልቻለው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ አንዱ ነው። ግንባታው ሲጀምር ብዙ የከተማዋ ነዋሪዎች ከፍ ያለ ተስፋ ጥለውበት እንደነበረም የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። በዚህም ከሁለት እስከ ሦስት መቶ ሺ የሚጠጉ የከተማዋ ነዋሪዎች ተመዝግበው በየወሩ በመቆጠብ በእጣ የቤት ባለዕድል ለመሆን በቅተዋል። እንዲያም ሆኖ ግን አሁንም በመርሐ ግብሩ ተመዝግበው በመቆጠብ ላይ የሚገኙ ነዋሪዎች ቁጥር ቀላል አይደለም ።

ከዚህ በተጨማሪም አቅም ያላቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ከመንግሥት መሬት በሊዝ በመውሰድ በራሳቸው ቤት ገንብተው የቤት ባለቤት የሚሆኑባቸው አማራጮችም ነበሩ። በዚህም ጥቂት የማይባሉት የከተማዋ ነዋሪዎች የቤት ባለቤት ለመሆን በቅተዋል። በአስር ዘጠና የቤት ፕሮግራም በርካታ አነስተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የቤት ባለቤት ለመሆን ችለዋል። በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙና ጎዳና ላይ ለወደቁትም ቢሆን ‹‹የደሃ ደሃ›› ለተሰኙ ኅብረተሰብ ክፍሎችም የቀበሌ ቤት የሚያገኙበት ሁኔታ በግዜው እንደተመቻቸ ይታወሳል።

እንግዲህ የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታን ጨምሮ በልዩ ልዩ አማራጮች ቤት አልባዎችን የቤት ባለቤት እንዲሆኑ የማድረግ እንቅስቃሴ ጥሩ ጅምር የነበረ ቢሆንም፤ ካለው የከተማዋ ነዋሪ የቤት ፍላጎት ቁጥር ጋር ሊመጣጠን ግን አልቻለም። የቤት ፈላጊውን ፍላጎትም በሚገባ ማርካት አልተቻለም።

ይህንን ተከትሎም በ2005 ዓ.ም አዲስ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ምዝገባ ተካሂዷል። በዚህ ሁለተኛው ዙር መርሐ ግብር ከ700 ሺ የሚልቁ ቤት ፈላጊዎች ተመዝግበዋል። እስከ 2008 ዓ.ም ድረስ መንግሥት በ1997 ዓ.ም ተመዝግበው ቤት ሲጠባበቁ ለነበሩት የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በመገንባት በዕጣ ሲያስተላልፍ ቆይቷል።

ከ2008 ዓ.ም በኋላ በአዲስ አበባ ዙሪያ በርካታ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በግንባታ ላይ የነበሩ ቢሆንም፤ በግዜው ኦሮሚያንና አዲስ አበባን በልማት ያስተሳስራል የተባለለት የተቀናጀ ማስተር ፕላን ይፋ ይሆናል መባሉን ተከትሎ በአዲስ አበባ ዙሪያ በተነሱ አመፆች ግንባታዎቹ ቆሙ። የተጠናቀቁትንም ለባለ ዕድለኞች የማስተላለፉ ሃሳብም እዚህ ላይ ተገታ።

ኢሕአዴግ በአዲሱ የለውጥ መንግሥት ከተተካ በኋላ የከተማዋ ነዋሪዎች የቤት ጥያቄ ፍላጎት ይበልጥ ጨምሮ ታይቷል። አዲሱ የለውጥ መንግሥትም ገና ወደ ሥልጣን እንደመጣም የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዙሪያ ያለው ችግር ውስብስብ ከመሆኑ አንጻር ጊዜ ሊፈጅበት እንደሚችል የብዙዎች እምነት ነበር ።

የለውጡ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ተጀምረው የነበሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ በማፋጠን ለባለዕድለኞች ለማስተላለፍ ጥረት ማድረጉ አልቀረም። ችግሮቹን በመቅረፍ ስኬታማ ሥራዎችን ለመሥራትም ሲንቀሳቀስ ተስተውሏል ። ይህም ሆኖ ግን ችግሩ አሁንም የተጠበቀውን ያህል መፍትሔ እያገኘ አይደለም።

በለውጡ ማግስት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተቀሰቀሰው ጦርነት ለችግሩ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ በመሆን፤ በመንግሥት የተጀመሩ ጥረቶች እንዲቀዛቀዙ አድርጓል። ቤት ፈላጊው ኅብረተሰብም ከቤት ይልቅ የሀገር ሕልውና ጉዳይ ይቀድማል ብሎ የመንግሥትን አቋም ደግፎ፤ ቤቱን ረስቶ ፊቱን ወደጦርነቱ አዙሯል። መንግሥትንም በተለያየ መልኩ ደግፏል።

የከተማው አስተዳደር በጦርነቱ መሐል ቤት ፈላጊውን በአጭር ግዜ ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል የቤት ግንባታ ፕሮጀክት አቅዶ ተግባራዊ ለማድረግ ረጅም ርቀት ተጉዟል። ከነዚህ ውስጥ አንዱ ከአንድ የደቡብ አፍሪካ የቤቶች ግንባታ ኩባንያ ጋር የተደረሰው ስምምነት ተጠቃሽ ነው። በፍጥነት የሚጠናቀቁ ተገጣጣሚ ቤቶች በሙከራ ደረጃ ተሠርተው ታይተዋል ። የመንግሥት ሠራተኞች በፈለጉት አማራጭ የራሳቸውን ሥራ ተቋራጭ ቀጥረው ከመንግሥት ቦታ ተረክበው በማኅበር ቤት እንዲገነቡ ምዝገባ ተካሂዶም ነበር ።

በርግጥ እየጨመረ ከመጣው የከተማዋ ነዋሪዎች የመኖሪያ ፍላጎት አንፃር የመኖሪያ ቤት ችግሩን እንዲህ በቀላሉ መፍታት ይቻላል ተብሎ መገመት የሚቻል አይደለም። ችግሩ ጊዜና ሀብት የሚፈልግ ነው። ይህም ሆኖ ግን አሁን ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚታየው ፕሮጀክት አፈጻጸም አንጻር ተስፋ ሊጣልባቸው የሚችሉ ነገሮች እንዳሉ መገመት አያዳግትም።

የአንድነትና እንጦጦ ፓርክ፣ የወዳጅነት አደባባይ፣ የአብርኆት ቤተ መጽሐፍት፣ የመስቀል አደባባይና ሌሎችም የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ላይ የታየው፤ ፕሮጀክቶችን በጥራትና በፍጥነት የማጠናቀቅ አዲስ ልምድ፤ ለጋራ ቤቶች ግንባታ ስኬት/ውጤታማነት ትልቅ ተጨባጭ ተሞክሮ ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባ ነው ።

ከነዚህ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም በመነሳትም የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ግንባታ በፍጥነት እና በጥራት በመገንባት ለነዋሪዎች ማስተላለፍ የሚቻልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ተገቢ ነው። በተለይም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሆነ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ጽሕፈት ቤት ከዚህ ተጨባጭ ተሞክሮ ተገቢውን ትምህርት ሊወስድ ይገባል።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 5 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You