ወርቃማ የዘመን ሙዳዮች

 ከጥበብ ጋር አድሮ ከጥበብ ያስጓዘን፣

ከዘመንም ዘመን አለ ወይ ቢመዘን?

ብዬ ጠየኩና በሃሳቤ ስባዝን፤

በእርግጥም አገኘሁ ያንን ወርቅ ዘመን።

ኑና ተመልከቱ ሂዱናም ጠይቁ፤

በዛሬ ወንጭፍ ላይ የኋልዮሽ ባርቁ፤

በጥበብ ትዝታ በላይ ተንፏቀቁ፤

ሙዳይዋን ይዛችሁ በትናንት ምጠቁ።

አዎን ዘመን አለ…

በጥበብ ተስሎ ለጥበብ የሾለ፤

ከእንቁ ጠቢባን ባንድነት የዋለ፤

ወርቃማው ወርቀጥቡ በእሳት የጋለ፤

አለ ወይ ካላችሁ…አዎን ዘመን አለ።

አብዛኛዎቻችን በምንስማማበት ዐረፍተ ነገር…ትናንት ከአንገቱ ላይ የወርቅ ኒሻን አጥልቆ በደስታ ጮቤ ሲያስረግጠን የነበረው የሀገራችን ኪነ ጥበብ፤ ዛሬ ከአንገቱ ላይ አጠንጥሎ የሚታየን ከብርም፣ የነሀስ ኒሻን መሆኑ ነው።

ይህንንም ለማየት ያልታደለ ብዙ አሉና፤ እሱንስ ማን አየበት ብለን ያለንን በደስታ ልንቀበል ግን የግድ ነው። እንዲህ ቢሆንም ቅሉ፤ በትናንትናና በዛሬ መካከል ያለውን እውነት አምነን ልንቀበል ያስፈልጋል።

የኛ ኪነ ጥበብ ዛሬ በደረሰበት ደረጃ ቢያኮራንም፤ ወርቁን ግን ለወርቃማው ዘመን መስጠታችንም አያስኮርፈንም። እንቁ ጥበባት በወርቃማ የዘመን ሙዳዮች ውስጥ የኖሩበትን የጊዜ ሀመልማል ከፍተው እየቆረሱ በትዝታ ማላመጡ አይከፋም። ዛሬ ላይ የጥበብ ሰዎችን ጨምሮ የምንወዳቸውንና የምናደንቃቸውን ጥበበኞች የምንመዘው አርባና ስድሳ ዓመታትን ወደኋላ ተስፈንጥረን ነው፡፡ ለምን? ምክንያቱም እነርሱ የወርቃማው ዘመን ፍሬዎች ናቸው። እኛስ? እኛ ደግሞ የእነርሱን እያደነቅን እንደ እነርሱን መሆን ግን ያልቻልን ምስኪኖች ነን።

ለመሆኑ ከዛሬና ከሌሎች ትናንቶች ለይተን ወርቃማ የምንለው የኪነ ጥበብ ዘመን ነበር? ጥያቄው አንዳንዶቻችንን አንገታችንን በአሉታ ያስነቀንቀን ይሆናል። በአዎንታ የሚያስወዘውዘንም ብዙዎች ነን። ጥያቄው በራሱ በጥቂቱም ቢሆን የሚመሳሰሉ ሁለት ጽንፎችን የያዘ ነው። ወርቃማ የኪነ ጥበብ ዘመን ሳይሆን ወርቃማ ጥበበኞች በየጊዜያቱ ብቅ ብለዋል በማለት ወርቁ እንጂ ዘመኑ ስለመኖሩ ትዝ የማይላቸው አንዳንዶች አሉ።

በእርግጥ እኛም ወርቃማ ዘመን ስንል በሌሎቹ ዘመናት ምንም አልነበረም ለማለት አይደለም። እንግዲህ ከእጅም እጅ ይመረጣልና ዛሬም ድረስ ከልባችን ማህደር የቀሩ ወርቃማ የጥበብ ሥራዎች የተሰነጉበት ለማለት ነው። አዳዲስ የፈጠራ ሃሳቦች በርክተው፤ የጥበብ መፍሰሻ ቦይ የተቀደደበት፤ ከዘመን ለይተን የምንረግጥበት ዘመን አለ። ይሄ የእውነተኛ የጥበብ አብዮተኞች ዘመን ነው።

በቀጭን የጨረፍታ ዱላ ለመጠቆም ያህል እንጂ ለመቅዘፍ በማትሆነው በዚህች ጽሁፍ ውስጥ፤ የሃሳባችን ኮቴ በብዛት ሙዚቃው ላይ ቢያርፍም ሁሉንም የኪነ ጥበብ ዘርፎች በወርቃማው ዘንግ መነካካታችን አይቀርም።

የትናንትናውንና የዛሬውን የሀገራችንን ኪነ ጥበብ በዘመን መነጽር ውስጥ ስንመለከተው አንድ አይነት እይታ የለውም። ጸጉራቸውን አፍሮ አበጥረው፤ በካኪ ሱሪው ላይ የሳሪያም ኮት ደርበው ሽር በጥበብ ሲሉ በነበሩና ጸጉራቸውን ተተኩሰው፤ በቃሪያ ሱሪው፣ በማይክል ጃክሰን ኮት ኮፍያውን ደፍተው በተጠበቡት ትውልድ መካከል ብዙ የተለዩ ነገሮችን እንመለከታለን። በጊዜ ሂደትና በዘመናት እርቀት አዎን…ብዙ ነገሮች ሊለወጡ ይችላሉ። ትናንት ዛሬ አይደለም።

አፍሮ ጸጉርንም ሆነ ሳሪያም ኮትን ዛሬ ላይ ለምን አላየነውም ብሎ መጠየቅ የዋህነት የወለደው ሞኝነት ነው። የኛ ዘመናዊነትና ሥልጣኔ፤ ቱባ ማንነታችን የሆነውን ኪነ ጥበብን ከጋረደው ግን…ለምን ብለን መጠየቃችን ነቅቶ የተኛውን ማንቃት ነው።

በሙዚቃና ዘመን…በዘመንና ሙዚቃ መንገድ ስናዘግም በወርቅም፤ በአዳፋ ጨርቅም ላይ ተረማምደን አልፈናል። አዳፋው ጨርቅስ ይህ ነው ለማለት ባንችልም፤ ወርቃማውን ዘመን ግን አንዘነጋውም። በሀገራችን የሙዚቃ ዘመን መቁጠሪያ ውስጥ ወርቃማ ብለን የለየናቸው ዘመናት በሙዚቃ ሥራዎች ደረጃ፤ በድምሩ ከነበረው ስብስብ እንጂ በተናጠል ካየናቸው ወርቃማ ድምጻውያን አንጻር አይደለም። በየዘመናቱ ወርቃማ ሙዚቀኞችን አጥተን አናውቅም።

ዛሬም ድረስ የምናወሳቸው ሙዚቀኞች፤ በብዛት ፈልቀው ሙዚቃውን በጉልህ በሚታይ መልኩ የለወጡ አብዮተኞች የወጡት ከተመሳሳይ የዘመን ግንድ ላይ መሆናቸው ነው ዘመኑን ወርቃማ ያስባለው። ወርቃማው የሙዚቃ ጊዜ የምንለው ዘመን ሌላ የተለየ ነገር ቢኖረው፤ ይሄውም ወርቆቹ በግል ሳይሆን በኅብረት ተነስተው እንደ አንድ ያብረቀረቁበት ጊዜ በመሆኑም ጭምር ነው። ብዙ ሰዎች ወርቃማውን የሙዚቃ ዘመን ከዘመናዊው የሙዚቃ ጅማሮ ጋር ያያይዙታል። ጥንቱን የራሷ የሆነ ኖታና የሙዚቃ ስልት ያላትን ሀገር ወርቃማውን ዘመን ያገኘችው ከዘመናዊነቱ ነው ካልን ነገሩ ሁሉ ተበላሸ። ‘በጨው ደንደስ በርበሬ ትወደስ’ አይነት ይሆንብናል።

ወርቃማው የሙዚቃ ዘመን በሀገራችን ልዩ መልክ የነበረው ሲሆን በየዘመናቱ ብቅ ጥልቅ ሲል ቆይቷል። በዚህም በባህላዊውም ሆነ በዘመናዊ ሙዚቃ ሁለት ወርቃማ ዘመናት ነበሩ። የመጀመሪያው መነሻውን ከ1950ዎቹ መጨረሻ አድርጎ እስከ 70ዎቹ መጀመሪያ ዘልቋል። በወቅቱ የሙዚቃውን አብዮት የቀሰቀሱ ሌላ ሁለት ምክንያቶች ነበሩ። የፖሊስ ኦኬስትራ የሙዚቃ ቡድኖች እና የቲያትር ቤቶች ኦኬስትራ። በሁለቱ መካከል የነበረው ትንቅንቅ ደስ የሚያሰኝ ቀዝቃዛ ጦርነት ነበር።

ጦርነቱ አሸንፎ የበላይነትን ለማሳየት ሳይሆን በአዳዲስ የፈጠራ ሥራዎች ለመቅረብ ነበር። ቀዝቃዛው የተሰጥኦ ጦርነትም በወላፈን የጋለውን ወርቅ ወልዷል። እያንዳንዱ ኦኬስትራ በአዳዲስ ሥራዎች አድማጭ ተመልካቹን ለማስደሰት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ፤ ሙዚቃ አካል ለብሳ እንድትቆም አድርገዋታል።

በዚህ መሃል ዘግየት ብሎ ደግሞ በ1960ዎቹ መጀመሪያ ዘመናዊ ባንድ የሚባል ነገር መጥቶ ከመሃከላቸው ተከሰተ። በዚህ የባንድ ሥርዓት ውስጥ የመጡ ሙዚቀኞች ምንጫቸው ከአንድ አቅጣጫ ነበር። በጊዜው የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት መከፈተን አስመልክቶ በርካታ ሙዚቀኞች እንደ አሸን ፈሉ። አሁን የባህል ኦኬስትራው ወደ አንድ ጎራ ተሰልፎ ፍጥጫው ከዘመናዊው ባንድ ጋር ሆነ። ቀደም ሲል በኦኬስትራዎቹ የነበሩት በልምድ የተዋጣላቸውና አንቱ የተባሉ ሙዚቀኞች ናቸው። ከያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት የወጡቱ ደግሞ ሙዚቃውን ከነሳይንሱ የቀመሱ ናቸውና የአብዮቱ እምብርት መገኛው እዚሁ አካባቢ ነበር።

የዘመናዊ የሙዚቃ መሣሪያዎችን ትውውቅ ተከትሎ ከቀድሞው ጋር ሳይጎራበጥ ከሀገራችን ሙዚቃ ጋር ተዋሃደ። በዚህኛው ወርቃማ ዘመን ከተገኙና በመካከል ከወጡት ኬኔዲ መንገሻ፣ አለማየሁ እሸቴ፣ ታምራት ሞላ፣ ሙሉቀን መለሰ፣ ጥላሁን ገሠሠ፣ ማህሙድ አህመድ፣ ንዋይ ደበበ እያለ በመቀጠል በነበሩበት የኪነት ባንዶች ውስጥ የሙዚቃውን አብዮት አቀጣጥለውታል። አረጋኸኝ ወራሽ፣ ኤፍሬም ታምሩ፣ ሀመልማል አባተ፣ አስቴር አወቀ እና ሌሎችም አስቀጥለውታል፡፡

በአልበም ሥራዎቻቸው የሙዚቃ ቅንብር ደግሞ አሊ ታንጎ አይዘነጋም። ማህሙድ ሙዚቃ ቤትንም አለማንሳት ነውር ነው። ሁለተኛውና ማሳረጊያ የመሰለውን ወርቃማ የሙዚቃ ዘመን ቀረብ ብለን በመጨረሻ እንመለስበታለን።

ልክ እንደሌሎቹ ሁሉ በኢትዮጵያ የሥነ ጽሁፍ ምህዋር ውስጥ የገዘፈ ዐሻራውን የጣለበት ወርቃማ ዘመን ነበር። ታሪክን ወደኋላ ስናሰናስን ኢትዮጵያ በሥነ ጽሁፍ ጥበብ ከዓለማችን ግንባር ቀደሟ ብትሆንም፤ ሥነ ጽሁፏ ግን በወርቃማው ሳጥን ውስጥ እንደተቆለፈበት ሳይደመጥ፤ ሳይገለጥ ነበር የኖረው። በታሪካችን ከሳጥኑ ሰብሮ የወጣው የመጀመሪያው የልቦለድ መጽሐፍ “ጦቢያ” ነው።

ዕድሜውን ወደኋላ ስንቆጥር ደግሞ መቶ ዓመታት ገደማ ነው። እንግዲ ከዚያ በኋላ ጦቢያን ተከትለው ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ። አንድ ሁለት እያሉም ጉዞ ወደ ወርቃማው ዘመን አደረጉ። ከ1950ዎቹ እስከ 1970ዎቹ የነበሩትን ጊዜያት ስለወርቃማነታቸው ማንም ኢትዮጵያዊ አይክዳቸውም። ዛሬ ላይ አንብበበን የማንረካቸው፤ ሰምተን የማንጠግባቸው የሥነ ጽሁፍ ሥራዎችና ጠቢባን የወጡት ከዚሁ የዘመን ቋጠሮ ውስጥ ነው። የሀዲስ አለማየሁ “ፍቅር እስከ መቃብር”፤ የዳኛቸው ወርቁ “አደፍርስ”፤ የበዓሉ ግርማ “ኦሮማይ”፤ የስብሐት ገብረእግዚአብሄር “ሌቱም አይነጋልኝ”፤ የአቤ ጉበኛ “አልወለድም”…ኧረ ስንቱን ዘርዝረው ይጨርሱትና…ሁሉም የተወለዱበትና እትብታቸው የተቀበረበት ወርቃማ ዘመን ይሄው ነበር።

ሥነ ጽሁፍና ሥነ ሥዕል ብዙ ዝምድናን በብዙ መዋደድ አብረው የተጋመዱ ናቸው፤ በተለይ ደግሞ ከግጥም ጋር። በሥዕል እያፈዘዙ በግጥም ሲያዋዙ የተመለከትናቸው ብዙዎች ናቸው። ለአብነትም ከገብረክርስቶስ ደስታ በላይ የምንጠራው እማኝ አይኖርም። የሥነ ጽሁፍ ጥበብ የወርቅ ካባ ለብሶ በተሞሸረበት ዘመን፤ የሥዕል ጥበብም አብሮት ከጎኑ ቆሞ ነበር። በሠገነቱ ከፍ ብሎ አድምቆ ደምቋል።

ሜትር አርቲስት ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ፣ እስክንድር በጎሲያን የወርቃማው ዘመን ፈርጦች ናቸው። ቲያትር በወርቃማው የዘመን ዙፋን ተቀምጦ የነገሠበት አርማው ጥበብ የነበረበት ዘመን ሌላኛው ወርቃማው ዘመን ነው። ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን፣ መንግሥቱ ለማ፣ ወጋየሁ ንጋቱ … የኢትዮጵያን የቲያትር መድረክ በወርቅ እንቁ ያንቆጠቆጡበት፤ ዛሬም በኩራት የምናወሳቸው ሥራዎችን የተከሉበት ድንቅ ዘመን ነበር። ዘመኑም ከሌሎቹ የራቀ አይደለም፡፡ 1960ዎቹ በተለየ ሁኔታ በሀገራችን የቲያትር ዐሻራ ያረፈበት ወርቃማ ዘመን ነው፡፡

ሁለተኛው የሙሴን በትር መሳይ ወርቃማው የሙዚቃ ዘንግ የተዘረገባት ዘመን ከ1980ዎቹ አጋማሽ አንስቶ እስከ 90ዎቹ መባቻ ነበር። እነዚህኛዎቹ የዘመን ጥበበኞች ዘመናዊውን የጥበብ ጓዳ በኪነ ጥበብ ያንተከተኩ ከፖለቲካው የአብዮት አጥር እየዘለሉ የወጡ የጥበብ አብዮተኞች የሠፈሩበት የቅርብ ትውስታ ነው። የዚህኛው ወርቃማ የጥበብ ዘመን መነሻ፤ የፖለቲካ ድጥ የበዛበትና እግር ባነሱ ቁጥር እየተነሱ የሚፈርጡበት ነበር።

ፖለቲካው ማህበራዊ ሕይወትንም የበረዘበት ጊዜ በመሆኑ ጥበበኛው ብቻም ሳይሆን ማህበረሰቡም በድብርት ተውጦ ድባቴ እየወቃው አስተክዞት ነበር። አብዛኛው የጥበብ ሰው ከውጭ ያለው አስቀያሚ ሁኔታ እያንገሸገሸው በራሱ ውስጥ ተደብቆ ከውስጣዊ ስሜቱ ጋር በጥበብ ሲብሰለሰል ቆይቶ ነበርና የፖለቲካው ፍትጊያ ረገብ ብሎ ቦታ ቦታውን ሲይዝ የታመቁ ስሜቶች ሁሉ እየፈነዱ ግሩም የጥበብ መዓዛ መርጨት ጀመሩ።

ኪነ ጥበቡ እንደገና እየተነቃቃ፤ በተለይ ደግሞ ሙዚቃና ቲያትር መግነጢሳዊ በሆነ ፍጥነት እያቆጠቆጡ ወደ መንዠርገግ ገቡ። 1990ዎቹ እኩሌታ በወጣቱ የሙዚቃ አድማጭ ዘንድ ተወዳጁ ጊዜ ነበር። ቴዲ አፍሮ፤ ታምራት ደስታ፣ እጅጋየሁ ሽባባው(ጂጂ)፣ ጎሳዬ ተስፋዬ፣ ጌቱ ኦማሂሬ፣ ማዲንጎ አፈወርቅና ሌሎች ወጣትና አንጋፋ ድማጻውያንን ጨምሮ በእጅጉ የተለየ ስብስብ የነበረበት ጊዜ ነው። እንደዛሬው በነጠላ ሳይሆን በምርጥ የአልበም ሙዚቃዎች አድማጩን ያንበሸበሹበትም ነበር።

አብዛኛዎቹ አልበሞችም በወጣቱ የሙዚቃ አቀናባሪ ኤሊያስ መልካ የተቀመሙ ጥኡም ሥራዎች ናቸው። ጊዜው የ20ኛው ክፍለ ዘመን ማክተሚያ ብቻም ሳይሆን እስከ ዛሬ የነበሩት የወርቃማ የኪነ ጥበብ ዘመናት መባቻም ይመስላል። ወርቃማው ዘመን ከሚሊኒየሙ ርችት ጋር አብሮ ሳይፈነዳ አልቀረም። በግል ደረጃ ጭብጨባ የማይነፈጋቸው ቆንጆ ሥራዎችን ለማየት ብንችልም፤ እንዳለመታደል ሆኖ ቀደም ሲል የነበረውን አይነት ወርቃማ ስብስብ ለመመልከት ግን አይን ያዝ ያደርጋል።

ወርቃማ የኪነ ጥበብ ጉዟችንን ዛሬ ምን ሰለበው? በዘመን ከርሰምድር ውስጥ የነበረውን ወርቅ ሽጠን በላነው? ወይንስ…እኛኑ ቡዳ በላን? ውድ አንባቢያን ኪነ ጥበብ ከትናንቱ በተሻለ ተሟሙቆ አለን፤ ጥበብ ግን በርዷታል። ከዚህም ከዚያም እትቱ…የሚያስብላት የባህር ንፋስ በርክቶባታል። ዛሬ ሚዲያና ቴክኖሎጂው በየአይነቱ በዝቶ ጥበብ ለጠቢባን ብቻም ሳትሆን ለሁሉም ቅርብ ሆናለች።

ለዚህም ይመስላል የተመኛት ሁሉ አንስቶ እንደ ዋንጫ እየሳመ ፊቷን ጭርት በጭርት ማድረጉ። እነዚያን ዘመናት ወርቃማ እያልን እንድንናፍቃቸው ካደረጉን ነገሮች አንዱ የቄሳርን ለቄሳር…የሚገባውንም በሚገባው ሥፍራ ብቻ ስላገኘነው ነው። የቴክኖሎጂው መርቀቅ…የሚዲያው መብዛት እሰየው! የሚያስብል ቢሆንም ዳሩ ግን ጣፋጩ የወይን ጠጅ ውሃ ተከለሰበት። ‘ከብዛቱ ጥራቱ’ እንልም የለ…አሁን አሁን በኪነ ጥበቡ ውስጥ ባሉት ጣፋጭ ሥራዎችና ጠቢባኑ ላይ፤ ውሃ ውሃ…እጅ እጅ የሚሉ ነገሮች እየበዙባቸው፤ ሁሉንም በጅምላ እንድንወቅጥ የሚገፋፉን ነገሮች ከውስጣችን ቢፈጠርም ማጥራቱ ግን የግድ ነው።

አሁናዊው የኪነ ጥበብ ጠረን ልክ ሀገራችን ያለችበትን ሁኔታ መስሏል። ሁላችንም በግላችን፤ ሀገራችንን የምንወድና ያለኔ ማን አላት የምንል አይነት ነን፤ እንደ ሀገር ግን ሁላችንም ከሥፍራው የለንም። ወርቅ ድምጻውያን፣ እንቁ ሰዓሊያን፣ ምጥቁ ደራሲያን፣ ጀግና ተዋንያን ዛሬም አሉ። ክብር ለሚገባቸው ክብርን እየሰጠን እናመሰግናቸዋለን! የእያንዳንዱ የግል ችሎታ ትልቅ ዋጋ አለው፤ ይህ አይካድም። እንደ ሀገር ግን በአንድ ጎበዝ ብቻ አሸናፊ ለመሆን የሚቻለው በሩጫ ትራክ ላይ እንጂ በእግር ኳስ ሜዳ ዘበት ነው። አሸናፊ የሚያደርገን በምርጥ ስብስብ የተቃኘ ቡድን ሲኖረን ነው።

ወርቃማ ዘመን እያልን ወደኋላ ማሽተታችን፤ በእያንዳንዱ የግል ችሎታ ብቻ ሳይሆን በዋናነት በጥምረቱ ውስጥ የነበረው መዓዛ ስላወደን ነው። በሙዚቃው ከዘመነ ወርቅ እያፈነገጥን ወደ ዘመነ ነጠላ ገብተናል። ነጠላውም አድፎብን በጥለት ብቻ እንዳንቀር ነው ፍራቻው። በወርቃማው ዘመን የነበሩና አሁንም ያሉ አብዛኛዎቹ ዝምታን አብዝተዋል። ጊዜውን በተራ በነጠላ ዜማ አባዜ ናላው ለዞረው ለቀውለት ይሁን ደክሟቸው አይታወቅም። ችሎታው ሳይከዳን እሩቅ ናፋቂ የሥልጣኔና የዘመናዊነት ጥላችን፤ ወርቃማውን ዘመን እንዳናስቀጥል አሊያም እንዳንደግም አድርጎ አስሮናል።

በግል የምንሮጠው ሩጫ እኛን እንጂ የሀገራችንን ኪነ ጥበብ ለማንገሥ ተስኖታልና ቀኝ ወደኋላ ዞረን ትናንትናን እንመልከት። ወርቃማውን ዘመን እንደወርቃማዎቹ!!

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You