በትራፊክ አደጋ ከ506 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት ደርሷል

አዲስ አበባ፡- በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሦስት ወራት በትራፊክ አደጋ ምክንያት ከ506 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ባላቸው ንብረቶች ላይ ጉዳት መድረሱን የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፈትያ ድድገባ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳስታወቁት፤ በበጀት ዓመቱ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት በደረሰ የትራፊክ አደጋ ምክንያት ግምታዊ ዋጋው 506 ሚሊዮን 305 በላይ ብር የሚሆን ንብረት ወድሟል፡፡

እንደ ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ገለጻ፤ በተሽከርካሪ ቴክኒክ ጉድለት፣ ከፍጥነት በላይ ማሽከርከር እና ደርቦ ማለፍ ለተከሰቱት ለአደጋዎች መንስዔ ከሆኑት መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በትራፊክ አደጋ የደረሰው የንብረት ውድመት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ቀንሷል ያሉት ወይዘሮ ፈትያ፤ ያለፈው ዓመት የንብረት ውድመት 989 ሚሊዮን በላይ ብር እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ በቅንጅት እየተሠራ ነው ያሉት ኃላፊዋ፤ የግንዛቤ ማስጨበጫ በሁሉም ክልሎች መሠራቱን ጠቅሰዋል፡፡

የአደጋ መከላከሉን ውጤታማነት ለመጨመር በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብና ሲዳማ ክልሎች ላይ 52 ለአደጋ አጋላጭ የሆኑና የመንገድ ምልክት የሌለባቸው አካባቢዎች ተለይተዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

እንደ ፈትያ ገለጻ፤ በኢትዮጵያ የመንገድ ዳር ምልክቶች የወጥነት ችግር አለባቸው፡፡ ምልክቶቹን ወጥና ብቁ ለማድረግ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው፡፡

መንገድ የሚሠራው ተቋራጭ መንገዱን ሲሠራ አብሮ ምልክቱን የመሥራት ኃላፊነት እንዳለበት ጠቅሰው፤ ይህም ተፈጻሚ ለማድረግ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ፈትያ ተናግረዋል፡፡

እ.ኤ.አ ከ2021 እስከ 2023 የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ በተሠሩ ሥራዎች በሀገሪቱ በ10 ሺህ ተሽከርካሪ 34 ነጥብ ስድስት የነበረው የሞት መጠን 27 ለማድረስ ታቅዶ 25 ነጥብ አምስት ማድረስ መቻሉን አያይዘው ገልጸዋል፡፡

ፈትያ አክለውም፤ 2016 በጀት ዓመትም በ10 ሺህ ተሽከርካሪ ከ25 ነጥብ አምስት ወደ 24 ዝቅ ለማድረስ እቅድ ተይዞ እየተሠራ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ በአስር ዓመት 10 ሺህ ተሽከርካሪ 10 ሰው ለማድረስ እቅድ ተይዟል ብለዋል፡፡

መንገድ ሲሠራ ለተሽከርካሪ ብቻ ታስቦ መሆን የለበትም ያሉት ፈትያ፤ ለአካል ጉዳተኛ፣ ለሕጻናት እንዲሁም እግረኞችን ታሳቢ ያደረገ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You