የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ስም በማጠልሸት ከተልዕኮው ማስቆም አይቻልም

 የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም ወዳድ ሕዝብ ነው፡፡ ከራሱ ሰላም አልፎም የጎረቤት ሀገራትን ሰላም የሚያስከብርና ወዳጅነትን አጥብቆ የሚፈልግ እንግዳ ተቀባይ ሕዝብ ነው፡፡የኢትዮጵያ ሕዝብ ተከባብሮ በመኖርና የሰላም ተምሳሌት ከመሆኑም ባሻገር ልዩነቶችን ጌጥ አድርጎ የሚቀበልና አብሮነትን የሚያስቀድም ድንቅ ሕዝብ ነው፡፡

ሆኖም የዚህን ኩሩና ሰላም ወዳድ ሕዝብ አኩሪ ዕሴቶች ለማምከን የተለያዩ ሴራዎች በውስጥና በውጭ ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ ሕዝቡ የመከባበርና የመቻቻል ዕሴቱን እንዲያጣ በብሔርና ሃይማኖት በመከፋፈልና በማናቆር ግጭት እንዲነግስና በሂደትም የተዳከመች ኢትዮጵያ እንድትፈጠር በርካታ አካላት ያለመታከት ሠርተዋል፡፡ ዛሬም እንቅልፍ አጥተው እየሠሩ ነው፡፡

ዛሬ ዛሬ ከኢትዮጵያውያን ባህል ባፈነገጠ መልኩ ፍላጎታቸውን በነፍጥ ማሳካት የሚፈልጉ ቡድኖች እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ ከውይይት ይልቅ ነፍጥ ማንሳት የሚቀናቸውና ሰላም ወዳዱን ሕዝብ የሚረብሹ፤አብሮነቱን የሚያውኩ ፤የኢትዮጵያን መረጋጋትና ሉአላዊነት የሚገዳደሩ ቡድኖች እዚህም እዚያም አቆጥቁጠዋል፡፡

እነዚህ ወገኖች በሚፈጥሩት ሁከትና ብጥብጥም ልማት ተደናቅፏል፤የሰዎች ወጥቶ መግባት ተስተጓጉሏል፤አለፍ ሲልም የሀገር ህልውናም አደጋ ላይ ወድቋል፡፡ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣በቤኒሻንጉልና በጋምቤላ አንዳንድ አካባቢዎች የሚታየው ሃቅም ይኸው ነው፡፡

የእነዚህን የግጭት ነጋዴዎች ሴራ ለማምከንና ብሎም አደብ ለማስገዛት ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ሕይወቱን ጭምር በመገበር ሌት ተቀን እየሠራ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የጀግንነት መገለጫ ጥግ ነው፡፡ ሠራዊቱ ከኢትዮጵያ ሕዝብ አብራክ የወጣ በመሆኑ እራሱን ለሕዝብና ለሀገር አሳልፎ ይሰጣል፤ የሀገሪቱን ሉአላዊነትን ለማስከበርና የዜጎችን ሰላም ለማረጋገጥ መስዋዕትነትን ይከፍላል፡፡ በዱር በገደሉ ይዋደቃል፡፡ደሙን ያፈሳል፤አጥንቱን ይከሰክሳል፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በጀግንነቱ ሁሉም በአንድ ድምጽ የሚስማማበት በሰላም ጊዜ የልማት አርበኛ ለድንገተኛ ክስተት የማይበገር ጀግና ሠራዊት ነው፡፡ ሠራዊቱ ድል የሚፈጥር፣ ሞትን የሚያሸንፍ፣ ለድንገተኛ ክስተት የማይበገር፣ ፍላጎቱን ለአላማው የሚያስገዛ፣ የነፃነትን ዋጋ ጠንቅቆ የሚያውቅ፣ ጨለማን ማሻገር የሚችል ልበ ሙሉ ነው። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሰላም ጊዜ የልማት አርበኛ በጦርነት ወቅት ጀግና ሆኖ በስኬት በመራመድ ላይ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሀገሩን ዳር ድንበር ከማስከበሩም ባሻገር በጎረቤት ሀገራት ጭምር ተልዕኮ በመውሰድ ሰላምን በማረጋገጥ ላይ ይገኛል፡፡ በሶማሊያ፤በሱዳን፤ቀደም ሲልም በላይቤሪያ፤በሩዋንዳና ቡሩንዲ ሀገራት ተሰማርቶ ሰላም ማስከበር የቻለ የሕዝብ ልጅ ነው፡፡ ይህም ብቃት ሊገኝ የቻለው ከሠራዊቱ ተፈጥሯዊ ባህሪ በሻገር በየጊዜው እየተደረገለት በመጣው አቅም ግንባታ ሥራዎች አማካኝነት ነው፡፡

በተለይም ባለፉት አምስት ዓመታት ሠራዊቱን ለማዘመን በተሠሩ የለውጥ ሥራዎች የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሯል፡፡ እራሱን በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ በማጠናከር ሳይዋጋ የሚያሸንፍበት ብቃት ላይ ደርሷል፡፡

የምድር ኃይልን በሰው ኃይልና የውጊያ አፈጻጸም በማጎልበት ከአየር ኃይልና ከሌሎች አቅሞች ጋር ያለውን ቅንጅት የማሳደግ ዕድል ፈጥሯል፡፡ በትጥቅና በመረጃ ግንኙነት አቅሙን በመገንባትም የማሸነፍ ብቃቱን አሳድጓል፡፡ ከአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲና ከተለያዩ የደህንነትና የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የባህር ኃይልን አቅም የማሳደግና የሳይበር ጥቃት ዝግጁነት /የሳይበር ዋርፌር/ ብቃትን በማሳደግ ከተለመደው የውጊያ ስልት ወጣ በማለት የሚቃጡ ዘመን አመጣሽ ጥቃቶችን የመከላከል ብቃቶችን ተጎናጽፏል፡፡

መከላከያ ከለውጡ ወዲህ በሠራቸው የሪፎርም ሥራዎች በቴክኖሎጂ አቅም ማሳደግ፣ በመከላከያ ምርምር ሥራዎች፣ በባህር ኃይል ዝግጁነትና ዘርፈ ብዙ ጉዳዮችን አከናውኗል፡፡በሀገር ውስጥና በውጭ አገራት የተቃጡ ውስብስብ ጥቃቶችን የመመከት ብቃቶችን አዳብሯል፡፡

ሆኖም የመከላከያ ሠራዊት መጠናከር ስጋት የሚሆንባቸውና ሴራቸውንም እንደሚያመክንባቸው ያወቁ ቡድኖችና ግለሰቦች ግብረ አበሮቻቸውን ሰብስበው በሰፊው ስም የማጥፋት ዘመቻ ውስጥ ይገባሉ፡፡ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ለብሶ ታላላቅ ድሎችን የተጎናፀፈውን ጀግና የመከላከያ ሠራዊታችንንም ስም በማጠልሸት ኢትዮጵያን ለማሳነስም በቀቢጸ ተስፋ ሲሯሯጡ ታይተዋል፡፡

ሆኖም የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት በወሬ የማይፈታ እና ለአፍታም ቢሆን በአሉባልታ የማይበገር መሆኑን ማመን ይገባል፡፡ሰላምን በማወክ ከግጭት ማትረፍ የሚፈልጉ አካላትም አዋጪው ሰላምና ፤ሰላም ብቻ መሆኑን መረዳት ይገባቸዋል፡፡

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You