ባለፉት ቀናት ሲካሄድ የቆየው 4ኛው ‹‹ፍሊንት ስቶን ሆምስ ለሁሉም ክፍት የሆነ እና የግል የበላይነትን የማስጠበቅ የቼስ ውድድር›› ከትናንት በስቲያ ፍጻሜውን አግኝቷል፡፡ ውድድሩ ከፍተኛ ፉክክር ማስተናገዱም ተጠቁማል፡፡ ውድድሩ ከዓለም የቼስ ፌዴሬሽን በድጋፍ መልክ በተገኘ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ በመታገዝ ‹‹ብሊቲዝና ራፒድ›› የተሰኙ የቼስ ጨዋታዎችን በማካተት በቀጥታ ስርጭት መካሄዱም ተገልጿል፡፡
ለሁሉም ክፍት የሆነ የግል የበላይነት የማስጠበቅ የቼስ ቻምፒዮናው ከህዳር 28 ጀምሮ ለተከታታይ ሶስት ቀናት በልደታ መርካቶ አዳራሽ በርካታ የቼስ ተወዳዳሪዎችን ያፋለመ ሲሆን፣ የውድድሩ አሸናፊዎችም ተለይተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቼስ ፌዴሬሽን ከዓለም አቀፉ የቼስ ፌዴሬሽን በድጋፍ ባገኘው የኤሌክትሮኒክስ ቼስ ቦርድ ( Digtal live chess) በመታገዝ የተካሄደ ሲሆን ከፍተኛ ፉክክር ማስተናገዱ ተገልጿል፡፡
ፌዴሬሽኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባው ዲጂታል የቼስ ቦርድ የዳኞች ጫናን ከመቀነስ በተጨማሪ ከዳኝነት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታዎችን የሚያስቀር መሆኑ ተጠቁማል፡፡ በተጨማሪም ውድድሩን በቀጥታ በማህበራዊ ድረ-ገጽ በሚለቀቅ ማስፈንጠሪያ አማካኝነት ለተመልካች እንደቀረበ ታውቀል፡፡
ውድድሩ በዓለም አቀፉ የቼስ ፌዴሬሽን እውቅና የተሰጠውና ልምድ ያላቸው እና ወጣቶች የተሳተፉበት በመሆኑ የተወዳዳሪዎቹን ወቅታዊ ብቃትና ደረጃቸውን እንዲያሻሽሉ እንዲሁም አዳዲስ ተወዳዳሪዎች እድል እንዲያገኙ ታስቦ እንደተካሄደ የኢትዮጵያ ቼስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡ በፍሊንት ስቶን ሆምስ የተሰየመው ይህ ውድድር የፌዴሬሽኑን ዓመታዊ ውድድሮች የተለያዩ ድርጅቶችና ተቋማት እንዲደግፉ በር ከፋች መሆኑም ተገልጿል፡፡ በዚህም ውድድር ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ከ70 በላይ ተሳታፊዎች የተመዘገቡ ቢሆንም ከ50 በላይ ተወዳዳሪዎች ብቻ መሳተፋቸው ተጠቅሷል፡፡
ቼስ የተለያዩ የውድድር ዓይነቶችን ያካትታል፤ እነዚህም የሚለያዩት በሰዓት አማካኝነት ሲሆን ክላሲካል፣ ብሊቲዝና ራፒድ የቼስ ጨዋታዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ክላሲካል የሚባለው የቼስ ጨዋታ ለእያንዳንዱ ተጫዋች አንድ ሰዓት ተኩል የሚሰጠው ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያለው የተጫዋቾች ብቃት የሚለካበትና ደረጃ የሚውጣበት ውድድር ከሆነ 30 ሰከንድ ጭማሪ ይኖረዋል፡፡
በዚህ ውድድር ብሊቲዝና ራፒድ የቼስ ጨዋታ በዓለም አቀፉ የቼዝ ፌዴሬሽን የተመዘገቡ ውድድሮች ሲሆኑ ለእያንዳንዱ ተጫዋች የሚሰጠው ሰዓት ይለያያል፡፡ ለራፒድ የቼስ ጨዋታ 15 ደቂቃ ከተሰጠ በኋላ 10 ሰከንድ ጭማሪ ይኖረዋል፡፡ ብሊቲዝ የሚባለው ደግሞ በጣም ፈጣን እና ለእያንዳንዱ ተጫዋች 5 ደቂቃ የሚሰጠው ሲሆን የ3 ሰከንዶች ጭማሪ የሚደረግም ይሆናል፡፡
ውድድሮቹን በ5፣ 7 እና በ9 ዙሮች ማካሄድ የሚቻል ቢሆንም የተሻለ ፍክክር እንዲኖርና ጠንካራ ተወዳዳሪዎችን ለመለየት በእያንዳዱ 9 ዙሮችን የፈጀ ፍልሚያ ተደርጓል፡፡ በዚህም መሰረት በ9 ዙሮች ተወዳድሮ ጠንካራ ፍልሚያን በማከሄድ በድምር ውጤት አብላጫ ነጥብን ያስመዘገቡ ተወዳዳሪዎች የሜዳለያና የገንዘብ ተሸላሚ መሆን ችለዋል፡፡
በዚህም መሰረት ከፍተኛ የማሰብና የማሰላሰል ብቃትን በሚጠይቀው ውድድር በራፒድ ወንዶች ፉክክር ደሳለኝ ፍቀዱ፣ ያለምዘውድ መኮንን እና ዮሴፍ ክፍሌ የወርቅ፣ ብርና የነሐስ ሜዳለያ ተሸለሚ መሆን ችለዋል፡፡ በሴቶች ራፒድ ሊያና አመሀ፣ ሙላካ ፈቲ እና ወርዳ ፈቲ የተባሉ ተወዳዳሪዎች በተመሳሳይ ከ1-3ኛ በመውጣት ተሸልመዋል፡፡
በብሊቲዝ ወንዶች ውድድር በተደረገው ፉክክር ሚልኪ አብዲሳ፣ አዲስዓለም ተመስገን እና አቤል ሰይፉ የወርቅ፣ የብርና የነሐስ ሜዳለያን ሲሸለሙ፣ በብሊቲዝ ሴቶች ፉክክር ሙለካ ፈቲ፣ ሊያና አመሀ እና ወርዳ ፈቲ ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ በመያዝ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ ከሜዳለያ በተጨማሪ የገንዘብ ሽልማት የተበረከተ ሲሆን፤ በድምር ውጤት 1ኛ የወጣው ዮሴፍ ክፍሌ የ15 ሺ ብር ተሸላሚ መሆን ችሏል፡፡ ሶስት ተወዳዳሪዎች እኩል ውጤት በማስመዝገባቸው የ12 ሺ ብር ተሸላሚ ሆነዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቼስ ፌዴሬሽን ባለሙያ የዝና ሙኔ፣ ፌዴሬሽኑ በርካታ ውድድሮችን እንደሚያከናውን አስታውሰው የግል የባላይነትን የማስጠበቅ ውድድር ለ4 ጊዜ እንደተካሄደ ተናግረዋል፡፡ የዘንድሮውን የግል የበላይነትን የማስጠበቅ ውድድርን ለየት የሚያደርገው ስያሜ ከማግኘቱና ዓለም አቀፍ እውቅና የተሰጠው ከመሆኑ በተጨማሪ በዲጂታል ቼስ ቦርድ መታገዙ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡ ይህም ቴክኖሎጂ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ለውድድር ጥቅም ላይ እንደዋለ አስረድተዋል፡፡ ፍሊንት ስቶን ሆምስ ፌዴሬሽኑን ለረጅም ዓመታት እየደገፈ እንደቆየና ለዚህም ውድድር ሙሉ ወጪውን ሸፍኖ የውድድሩን ስያሜ እንደወሰደም አክለዋል፡፡ ይህንን አርአያ አድርገው ሌሎች ድርጅቶችም ዓመታዊ የፌዴሬሽኑን ቻምፒዮናዎች እንዲደግፉ በር ይከፍታልም ብለዋል፡፡
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሳስ 2 ቀን 2016 ዓ.ም