የአንድ ሀገር ብዝሃነት በሃይማኖት እና በብሔር መጠን የሚገለፅ ነው፤ አንድ ሕዝብ በሃይማኖት የተለያየ የአምልኮ ሥርዓትን ሲከተል፣ ሕዝቡ የተለያየ ሃይማኖት አለው ይባላል:: በተመሳሳይ መልኩ በአንድ ሀገር ሕዝብ ውስጥ የተለያየ ማህበረሰብ ሲኖር እና እነዚህ ማህበረሰቦች የየራሳቸው ባህል፣ ቋንቋ እና የአኗኗር ዘይቤ ሲኖራቸው ብሔር እንደሚባሉ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ብያኔዎች ያመለክታሉ:: በዓለም ደረጃ በሀገራቸው ብዙ ብሔሮችን ከያዙ ሀገራት መካከል በቀዳሚነት ደረጃ ላይ የሚጠቀሱት ላይቤሪያ፣ ዑጋንዳ፣ ቶጎ፣ ደቡብ አፍሪካ ፣ ራሺያ እና ቤልጂየም የመሳሰሉት ናቸው::
ኢትዮጵያም ብዙ ብሔር እና የተለያየ ሃይማኖት ያለው ማህበረሰብ ካላቸው ብዝሃነትን እያስተናገዱ ከሚገኙ ሀገራት መካከል አንዷ ናት:: ይህ የተለያየ ሃይማኖት ያለው ማህበረሰብ መኖሩ እና ብሔሮች መብዛታቸው ፀጋ ነው ወይስ ስጋት? ስንል ለምሁራን ባቀረብነው ጥያቄ ብዝሃነት ፀጋም ሆነ ስጋት የሚሆነው እንደተያዘበት መንገድ ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተውናል::
ፖለቲካ ሳይንስ እና ፌዴራሊዝምን ያጠኑት የፌዴራሊዝም አስተምሮት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ሃይለየሱስ ታዬ (ዶ/ር) እንደሚናገሩት፤ ብዝሃነት ለአንድ ሀገር ቀላል ጉዳይ አይደለም:: ብዝሃነትን ማስተናገድ በጣም ትልቅ የፖለቲካ ዕውቀት እና አቅም የሚጠይቅ ነው:: ብዝሃነት ሲኖር ከጀርባው ብዙ የፖለቲካ ፣ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ሌሎችም ጥያቄዎች ይኖራሉ:: አንዱ የፖለቲካ፣ ሌላው የኢኮኖሚ አንዱ ደግሞ የማህበራዊ ጥያቄ ሊኖረው ይችላል:: ይህንን በደንብ ማስተናገድ እና ሀገራዊ አንድነት ላይም ሚዛኑን ጠብቆ መሄድ ካልተቻለ ብዝሃነት ስጋት ነው:: ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ሚዛን ጠብቆ ማስተናገድ ከተቻለ ግን ፀጋ ይሆናል::
ብዝሃነትን በትክክል ያስተናገዱ ሀገሮች ጠንክረው ወጥተዋል:: አስተካክለው ማስተዳደር ያቃታቸው አገሮች ደግሞ ብዝሃነት የግጭት ምንጭ ሆኖባቸዋል በማለት የዓለም ተሞክሮን በመጥቀስ በምሳሌ ሲያስረዱ፤ እንደማሳያ የድሮዎቹ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገሮች እስከ መፍረስ የደረሱት ብዝሃነትን በአግባቡ ባለማስተናገዳቸው ነው ብለዋል:: ዩጎዝላቪያን መጥቀስ ይቻላል ካሉ በኋላ፤ በሌላ በኩል ብዝሃነትን በአግባቡ በማስተናገድ ውጤታማ የሆኑ ሀገሮችንም አንስተዋል:: ሲውዘርላንድ ለብዙ ዓመታት የፌዴራል ሥርዓትን መሠረት በማድረግ ብዝሃነትን በማስተናገድ ጠንካራ ሆና መቀጠሏን አመላክተዋል:: ካናዳ እና ፈረንሳይንም የጠቀሱ ሲሆን፤ ቤልጂየም እና ስፔንንም በማንሳት ብዝሃነት ቢኖራቸውም የተሳካላቸው መሆኑን ተናግረዋል::
ከኢትዮጵያ አንፃር ሲታይ፤ ቀደም ሲል በፊውዳል ዘመን አጠቃላይ ሕዝብን ከማየት ይልቅ ወደ ራስ ብሔር በማድላት፤ ሀገራዊ ጉዳዮች ይደረስባቸዋል በሚል የመተው ሁኔታ ነበር የሚሉት ሃይለየሱስ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓትን መተግበር ከተጀመረ ገና 30 ዓመታትን ብቻ ያስቆጠረ በመሆኑ፤ ጊዜው እንደሽግግር ጊዜ መታሰብ አለበት ብለዋል::
የሽግግር ጊዜ በመሆኑ እዚህ እና እዚያ ግጭቶች የሚታዩ መሆናቸውን በማመልከት፤ ነገር ግን ብሔር ብሔረሰቦች አኗኗራቸውን፣ ቋንቋቸውን እና ባህላቸውን ግልፅ በሆነ መልኩ የሚያሳዩበት መድረክ አግኝተዋል ብለዋል:: በመንግሥት ደረጃ ዕውቅና አግኝተው ራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደር እየሞከሩ ነው:: በዚህ ሂደት ሀገሪቷ ትፈርሳለች ተብሎ ቢሠጋም ግጭት ቢኖርም እስከ አሁን ኢትዮጵያ ሀገር ሆና ቀጥላለች ሲሉ ተናግረዋል::
‹‹የሽግግር ጊዜ መሆኑን ከማወቅ በተጨማሪ፤ ብዝሃነት ለኢትዮጵያውያን ተፈጥሯችን እና አብሮን የሚኖር በመሆኑ አምነን እንዴት አድርገን እናስተዳድረው በሚለው ላይ መነጋገር ይገባናል::›› ያሉት ሃይለየሱስ (ዶ/ር)፤ በኢትዮጵያ ለዚህ መልካም ሁኔታ መኖሩን አመላክተዋል:: ኢትዮጵያውያን በጋብቻ እና በሌላ በሌላውም የተሳሰሩ መሆናቸው በምቹነት ሊታይ እንደሚገባ አስረድተዋል::
ነገር ግን ፖለቲካው ላይ ጫፍ እና ጫፍ ይዞ መካረር እንደሚስተዋል አስታውሰው፤ ይህ እንደ ኢትዮጵያ ላለች ሀገር እንደማይጠቅም አስረድተዋል:: ፖለቲካው ከርሮ መጠፋፋት ላይ እንዳይደረስ የተማረው ማህበረሰብ ሀገርን እንዴት አድርጎ ዴሞክራሲ የሰፈነባት እና የበለፀገች ማድረግ እንደሚቻል ሊነጋገር ይገባል ብለዋል::
አንዳንድ ሰዎች በሀገሪቱ ብዝሃነት መኖሩን እንደሚዘነጉ በመጠቆም፤ በተለይ በንግግር በኩል ሰዎች የሚናገሩት ነገር ሌላው ማህበረሰብ ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ በደንብ መታሰብ አለበት ብለዋል:: በንግግር ብቻ ሳይሆን በተለይ በተግባር መጠንቀቅም ይገባል ሲሉ አመልክተዋል::
ብዝሃነትን ለማስተናገድ በከፍተኛ ጥንቃቄና በብቃት መሥራት የግድ መሆኑን አስታውሰው፤ የኢኮኖሚ ችግርም ሁኔታውን የበለጠ ሊያወሳስበው ስለሚችል ኢኮኖሚው ላይም ሊታሰብ ይገባል የሚል ምክራቸውን ለግሰዋል::
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ አቶ አሮን ደጎል በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ አንድ ዓይነት ነገር ያሰለቻል:: አንድ ዓይነት ከመሆን ይልቅ ብዙ ዓይነት መሆን ያስደስታል:: ስለዚህ ብዝሃነት ውበት እንጂ ስጋት መሆን የለበትም:: የኢትዮጵያ ብዝሃነት በምንም መልኩ ለኢትዮጵያውያን ለራሳቸውም ሆነ ለሌሎች ስጋት ሆኖ አያውቅም:: ስጋት ሊሆን አይገባም፤ እንደውም ዜጎች በውበትነት ሊቀበሉት የሚገባ ፀጋ ነው:: እንደስጋት የሚታሰበው የአያያዝ ሁኔታው ነው::
‹‹ብዝሃነት የሚስተናገድበት መንገድ ሁሉንም አንድ ላይ በማምጣት ለኢትዮጵያ ዕድገት እና ለልማት የሚውልበትን መንገድ ካላወቅንበት እንደስጋት ሊታሰብ ይችላል:: ብዝሃነቱ እውቅና አግኝቶ መብቶች ካልተከበሩ እና ሰዎች በእኩልነት ካልታዩ ስጋት ሊሆን እና ብዝሃነት የፀብ ምክንያት ሊሆን ይችላል::›› ብለዋል:: እንደሃይለየሱስ (ዶ/ር) ሁሉ አቶ አሮንም፤ ብዝሃነት ያለባቸው ብዙ ሀገሮች አሉ:: አውሮፓ ውስጥ እነቤልጂየም እነሲውዘርላንድ እና ሌሎችም የአውሮፓም ሀገሮች ብዝሃነትን የያዙበት እና ያስተዳደሩበት መንገድ በፀጋነት እንዲቀበሉት ያደረጋቸው መሆኑን አስረድተዋል::
ብዝሃነት የቱሪስት መስህብ መሆን አለመሆን ብቻ አይደለም:: ብዝሃነት ብቻውን በርካታ ጥቅሞች አሉት:: ብቻውን ስጋት መሆን አይችልም ያሉት አቶ አሮን፤ ነገር ግን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የሚቆጠረው እንደስጋት መሆኑን አብራርተዋል:: ዋናው ነገር ስጋት ያደረገው የመሪዎች ችግር መሆኑን በመጠቆም፤ አሁን ድረስ ብዝሃነት ለመሪዎች እንደስጋት የሚታይ መሆኑን አብራርተዋል:: ነገር ግን ከሕዝቦች አንፃር እንደውም ኢትዮጵያ በጣም መልካም ለሌሎች ምሳሌ መሆን የሚችል ባህል ያላት መሆኑን አስታውሰው፤ አብሮ መኖር፣ አብሮ መብላት፣ መተዛዘን እና መተሳሰብ የሚችል ሕዝብ ያላት ሀገር በመሆኗ ብዝሃነትን እንደስጋት ከማየት ይልቅ በፀጋነት መቀበሉ አዳጋች እንደማይሆን ተናግረዋል::
ሕዝቡ ጠንካራ የአብሮነት ባህል ስላለው ብዝሃነት ችግርም ሆነ ስጋትም አይሆንበትም:: ያሉት አቶ አሮን፤ ነገር ግን መሪዎች በተለይ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱት የፖለቲካ መሪዎች፣ የማህበረሰብ አንቂ ነን የሚሉ፤ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች እና የመንግሥት ባለሥልጣናት እና የሃይማኖት መሪዎችን ጨምሮ ሁሉም በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ማህበረሰብን የሚመሩ አካላት የሚፈጥሯቸው ችግሮች ብዝሃነት ስጋት እንዲሆን የራሳቸውን ሚና ይጫወታሉ ብለዋል:: እነዚህ መሪዎች ሊያራምዷቸው የሚፈልጓቸውን የግል አመለካከቶቻቸውን ሕዝቡ ላይ ለመጫን ሲሞክሩ ብዝሃነትን በስጋትነት ይመለከቱታል ብለዋል:: የፖለቲካ መሪዎች አመለካከታቸው ቢስተካከል እና አቃፊዎች ቢሆኑ፤ ፖለቲካው ቢስተካከል እና ቁርጠኝነት ቢታከል በትክክል ብዝሃነት ፀጋ መሆኑን ማረጋገጥ ይቻል እንደነበር አስረድተዋል::
በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ በሆነ ወቅት አንዱ ሌላውን የበታች የሚያደርግ አመለካከት ሊያሳይ ይችላል:: ነገር ግን መሪዎች ይህንን ማስቆም አለባቸው ያሉት አቶ አሮን ለምሳሌ ዳግማዊ ምኒልክ አዋጅ አውጥተው እንደነበር አስታውሰዋል:: አንድን ሰው ወይም ማህበረሰብ ለይቶ እንዲህ ነህ እንዲያ ነህ ማለትና በተለይም ሥራውን እና ሙያውን መሠረት አድርጎ ዕውቅና ሊያገኝበት የሚገባውን ልዩ ሙያ እና ክህሎት አናንቆ መጥራት እንደሚያስቀጣ አዋጅ አውጥተው እንደነበር እና ይህንንም በሰነድ ማረጋገጥ ይቻላል ብለዋል::
በፊውዳል ዘመን በነበረው ችግር የገዢው መደብ አካላት በወቅቱ የነበሩ ባላባቶች እና ገዢዎች ለአንዳንዱ ማህበረሰብ የሠጡት ስያሜ ነበር:: ይሄ የተወሰኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ብቻ ሳይሆን ስያሜ ያልተሰጠው ማህበረሰብ የለም:: አማራውን፣ ትግሬውን ፣ ኦሮሞውን፣ ሃድያውን፣ ከንባታውን ለሁሉም ስያሜ ተሰጥቶት ነበር:: ይህንን ስያሜ የሠጠው የፊውዳሉ አካል ሲሆን፤ ከዛ ወደ ማህበረሰቡ ወርዷል:: ይህንን ለማስተካከል መሥራት ያለበት መንግሥት ነው:: መንግሥት አሉታዊ ተፅዕኖ ሲኖር ሚናው መከልከል እና ሥርዓት ማስያዝ ነው:: ይህን መሥራት ሲኖርበት ለጥፋቱ በዝምታ ካለፈው ዕውቅና ሰጥቷል ማለት ነው:: ስለዚህ ብዝሃነት ፀጋ እንዲሆን መሪዎች ሚናቸውን መወጣት አለባቸው ሲሉ አሳስበዋል::
ሕዝብ የሚከተለው መሪውን ነው:: መሪ የግድ ለሌሎች ምሳሌ እና አርአያ መሆን አለበት:: መሪው ትክክለኛ ነገር ሲሠራ እና ስብዕና ሲኖረው፤ ለራሱ ክብር እና ሀገራዊ ራዕይ ሲኖረው ሕዝብም እንደዛው ይሆናል:: በተቃራኒው መሪው በተሳሳተ መንገድ ሲሔድ ሕዝብም በተመሳሳይ መልኩ ይሔዳል:: ብዝሃነት ስጋት እንዳይሆን መሪዎች ሀገራዊ ራዕይ ኖሯቸው ለሕዝብ ክብር መስጠት አለባቸው ብለዋል:: መሪዎች ላደጉበት እና ለመጡበት ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለእያንዳንዱ ሰው ክብር መስጠት እና መሥራት እንዳለባቸው አመላክተዋል::
ለእያንዳንዱ ማህበረሰብ ክብር እና ዕውቅና ካልተሰጠ ስለኢኮኖሚ ልማት እና ስለሀገር እድገት መናገር አይቻልም:: መጀመሪያ ሕዝብ የሚለውን መስማት፣ ሕዝብን መታዘዝ እና ለአጠቃላይ ሕዝቡ መቆም ያስፈልጋል ብለዋል:: ሌላው ትልቁ ነገር ኢትዮጵያን የመሰለች ብዝሃነት ያለባትን ሀገር ለመምራት የፖለቲካ ቁርጠኝነት እና አእምሮን ሰፋ አድርጎ ማዘጋጀት እንዲሁም ከብልሃት ጋር ቅንነት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል:: እንደዚህ ካልሆነ የፈለገውን ያህል ዕውቀት እና ክህሎት፣ የበዛ ሀብት እና ፀጋ ቢኖርም ሀገርን ከችግር ማውጣት እንደማይቻልም ነው የተናገሩት::
ከዚህ በፊት የተፈፀሙትን ስህተቶች እየነቀሱ ወደ መድረክ በማምጣት ቁስልን ማከክ ወይም በሰው ቁስል ላይ እንጨት መስደድ ሳይሆን ያንን በይቅርታ ረስቶ አዲስ የሕይወት ምዕራፍ ለመጀመር መነሳት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል:: መሪዎች ቅንነት፣ ሰፊ ልቦና እና በዋናነት ደግሞ ያለምንም መድልዎ እና ልዩነት ለሕዝብ ክብር መስጠት እንዳለባቸው በማስታወስ፤ መሪዎች ራሳቸው ላለፈው ይቅርታ አድርገው እና ሕብረተሰቡም እርስ በእርሱ ይቅር እንዲባባል አመቻችተው መሪነታቸውን መቀጠል እንዳለባቸው አመላክተዋል::
ከኢትዮጵያውያን ብዝሃነት አንፃር አሁን በተያዘው መንገድ የሚቀጥል ከሆነ እና ካልተስተካከለ የወደፊቱ ያስፈራል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል:: በየቦታው ከብሔር ጋር የተያያዙ ብዙ ችግሮች መኖራቸውን፤ በየቦታው ሰዎች የሚታፈኑ፤ የሚታገቱ እና የሚሞቱ መሆኑን በማስታወስ፤ ይሄ ሁሉ ሲካሄድ በየአካባቢው በየቦታው ያለው አስተዳዳሪ ምን እንደሚሠራ እስከ ፌዴራል ድረስ ችግሩን ለማስቀረት የተከናወነው በሙሉ መታወቅ አለበት ብለዋል::
የኢትዮጵያ መፃኢ ዕድል መልካም እንዲሆን እና አብሮ መኖር እንዲቻል በየደረጃው ሃላፊነት ያለባቸው መሥራት አለባቸው ብለዋል:: በተቃራኒው ሚናቸውን ካልተወጡ እና እነርሱም የችግሩ አካል ከሆኑ እና ችግሩን ካስቀጠሉት የወደፊቱ ተስፋ ብሩህ አይሆንም ሲሉ ተናግረዋል::
አሁን ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሟል፤ እንደ ቀደመው የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ወይም የድንበር እና የማንነት ኮሚሽን ተቋቁሞ የሰዎችን ጊዜ፣ የመንግሥትን በጀት ወስዶ የታለመለትን ዓላማ ከግብ ካላደረሰ ሁኔታው ከባድ እንደሚሆን አመልክተዋል:: አሁንም ብሔራዊ ምክክሩ የተሳካ እንዲሆን መንግሥት ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል::
አቶ አሮን እንደገለፁት ሁሉ ሃይለየሱስ (ዶ/ር)ም እንደሚናገሩት፤ በእርግጥም ላለው ችግር ብዝሃነት ፀጋ እንዲሆን መሪዎች መሥራት አለባቸው:: ነገር ግን ለብዙ ችግር እኩልነት መኖሩ መፍትሔ ቢሆንም እኩልነት በራሱ ብዙ ትርጉም እንዳለው መረሳት የለበትም:: በሕዝብ ደረጃ ሁሉም እኩል ነው ቢባልም በኢኮኖሚ በኩል ሲታይ ለሁሉም እኩል ዕድል መስጠት የግድ መሆኑን ተናግረዋል:: በዚህ ላይ የፌዴሬሽ ምክር ቤት በሚያስቀምጠው ቀመር መሠረት በጀት ይመደባል:: ነገር ግን በአንድ ጊዜ የሁሉም ኢኮኖሚ እኩል ይሁን ማለት እንደማይቻል በመጠቆም፤ በዋናነት መፍትሔው ትብብር መሆኑን አስረድተዋል::
የኢትዮጵያ ችግር የፖለቲካ ሥርዓቱም በብሔር ላይ የተመሠረተ ነው:: ዝቅተኛ ቁጥር ያለው ብሔር አለ:: ብዝሃነት ፀጋ እንዲሆን ዝቅተኛ ቁጥር ያለውም መስተናገድ እና የሚሳተፍበት ሥርዓት መበጀት አለበት:: ብዙ የአሠራር ሥርዓት እና ሕጎች እንዲሁም ፈፃሚ ተቋማት ያስፈልጋሉ:: ሕግ አውጪውን እና አስፈፃሚውን የሚከታተሉ ተቋማት መኖር አለባቸው ብለዋል::
ሃይለየሱስ (ዶ/ር) እንደሚናገሩት፤ ብዝሃነት ሲባል በፌዴራል ደረጃ ባለው ሥልጣን ላይ ብቻ ሳይሆን በቀጥታ በአገልግሎት አሰጣጥ ከሕዝቡ ጋር የሚገናኘው ቀበሌ ላይ መሠራት አለበት:: ማንኛውም ነገር መነሻው ቀበሌ ላይ በመሆኑ የተማረ እና በአስተሳሰብ ማንም ይሁን ማን ማገልገል አለብኝ ብሎ የሚሠራ የተማረ ሰው እንዲሠራ መደረግ አለበት:: እስከ አሁን ድረስ እንዴት ሔድን? ወደፊትስ እንዴት እንቀጥላለን ? በሚለው ላይ በጣም ሰፊ ውይይት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል::
አቶ አሮን በበኩላቸው፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥረት የሚያደርጉት መሪ ለመሆን ነው:: ነገር ግን የሚመራ ሕዝብ ከሌለ መሪ መሆን አይቻልም:: ስለምርጫ፣ ስለሥልጣንም ሆነ ስለሃይል መነጋገር የሚቻለው ሀገር ሲኖር ነው:: ተቃዋሚ ፓርቲዎችም መጀመሪያ ሕዝቡ ጫና ሳይበረታበት በትክክል ኑሮውን እንዲኖር ሚናቸውን መወጣት አለባቸው:: ሕዝብ ሲኖር ወደ ሥልጣን ጥያቄ ይገባሉ:: ይህንን አርቀው ሊያስቡ ይገባል:: ሥልጣናቸውን እና ኑሯቸውን ብቻ ሳይሆን የነገውን ሕዝብ ጉዳይ አርቀው ሊያስቡት ይገባል:: ማህበረሰብ አንቂዎችም የሚያነቁት ሕዝብ እንዲኖር በሕዝብ ጉዳይ ላይ ማሰብ አለባቸው:: የሃሰተኛ መረጃ እና የጥላቻ ንግግር አዋጅ ወጥቷል:: የወጣበት ምክንያት እነዚህ አንቂ የተባሉ አካላት በሚያሰራጩዋቸው ሃሰተኛ መረጃዎች ሕዝብ አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ነው:: ስለዚህ አዋጁን በትክክል መተግበር እና ለሕዝብ ማደር ከሁሉም ይጠበቃል::
እንደምሁራኑ ገለፃ፤ ብዝሃነት ስጋት አይደለም:: ስጋት የሚሆነው ብዝሃነትን በተሳሳተ መንገድ ለማስተዳደር መሞከር ነው:: ብዝሃነትን በአግባቡ ማስተናገድ ከተቻለ ከስጋትነት ይልቅ ፀጋ መሆን ይችላል::
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሳስ 2 ቀን 2016 ዓ.ም