የአቬዬሽን ኢንዱስትሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢኖቬሽን ከፍተኛ እመርታ እያሳዩ ከሚገኙ ዘርፎች መካከል በዋነኝነት ተጠቃሽ ነው። ኢንዱስትሪው የአየር ትራንስፖርት አሁን ላለበት ሁለንተናዊ እድገት ትልቁ ባለውለታ ነው። በቀጣይ ለሚኖረው እድገትም ያለ አቬዬሽን የሚኖረው እገዛ የትየለሌ ነው።
በሀገር ውስጥ ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄዱ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቶች ያለ ችግር /ከአደጋ ነጻ በሆነ መንገድ / እንዲከናወኑ ፣ በቴክኖሎጂ ከመዘመን ጀምሮ ዓለም አቀፍ ሥርዓቶችን በማበጀት፤ ሥርዓቶቹ የሚገዙባቸውን ሕጎችና መመሪያዎች በማጽደቅ እና በማስፈጸም የሚታወቅ ነው።
ደረጃቸውን የጠበቁ ኤርፖርቶች መገንባታቸውን፤ ዘመኑ ባፈራቸው ቴክኖሎጂዎች ማዘመናቸውን ፤ ዘርፉ ለሚተዳደርባቸው ዓለም አቀፍ ሥርዓቶች ተገዥ መሆናቸውን በመቆጣጠር የአየር ትራንስፖርት ዘርፉ ደህንነቱን የተጠበቀና አስተማማኝ እንዲሆን ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ ነው።
ከዚህም ባለፈ የአንድን ሀገር ሉአላዊ የአየር ግዛት ከየትኛውም ሉአላዊነትን ከሚፈታተን ስጋት ነጻ መሆኑን በመከታተል እና በማረጋገጥ ሂደት ከሌሎች የሀገር ደህንነት ተቋማት ጋር በመሆን የሚያበረክተው አስተዋጽኦ መተኪያ የሌለው ነው።
ኢትዮጵያ የቀድሞውን “ሲቪል አቪዬሽን” የአሁኑን የኢትዮጵያ ሲቪል አቬዬሽን ባለስልጣን በ1944 ዓ.ም አቋቁሞና በዚሁ ዓመትም የዓለም አቀፉን የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ስምምነት ፈርማ ለዘርፉ እድገት የበኩሏን ሚና ተወጥታለች፤ እየተወጣችም ትገኛለች።
በኢትዮጵያ የአየር ትራንስፖርት አሁን ላለበት የላቀ ደረጃ መድረስ ሲቪል አቪዬሽኑ ተጠቃሽ ባለውለታ ነው። ኤርፖርቶችን ከመገንባት ጀምሮ ዘመኑን የሚዋጁ ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ ሀገሪቱ በዘርፉ በአለም አቀፍ ደረጃ አንቱታን እንድታተርፍ አስችሏል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀገርን በማስጠራት የሀገር ኩራት ከሆነው የኢትዮጵያ አየርመንገድ በስተጀርባ ገዝፎ የሚገኙ፤ አየር መንገዱ በሀገር ውስጥ ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች አስተማማኝ እና ተመራጭ እንዲሆኑ ከፍ ያለ ሚናን የተጫወተ በመሆኑ ምስጋናም የሚገባው የሀገር ኩራት የሆነ ተቋም ነው።
የአየር ትራንስፖርት በመላው ሀገሪቱ እንዲስፋፋ ኤርፖርቶችን ከመገንባት ጀምሮ ፤የኤርፖርት መሰረተ ልማቶችን በማሟላት እንደ ሀገር አሁን ለደረስንበት የአየር ትራንስፖርት እድገት በየዘመኑ አስፈላጊውን የአዋጅና የአደረጃጀት ማሻሻያዎችን ጭምር በማድረግ በኃላፊነት መንፈስ ሲንቀሳቀስ የነበረና አሁን በተሻለ መነቃቃት በመንቀሳቀስ ላይ ያለ ተቋም ነው።
እንደ አገር የመጀመሪያው የአቪዬሽን ትምህርት ቤት ከተከፈተበት 1951 ዓ.ም ጀምሮ ተቋሙ ከሀገር ውስጥ ባለፈ፤ ለአፍሪካውያን ወንድሞቻችን ሙያዊ ስልጠናዎችን በመስጠት፤ የአየር ትራንስፖርት በአፍሪካ የተሻለ እድገት እንዲኖረው ሙያዊ ድጋፍ በመስጠት ላይ ይገኛል፤ በዚህም በብዙዎች ዘንድ እውቅናና ከበሬታን ማትረፈ ችላል።
የሀገሪቱን ሉአላዊ የአየር ግዛት ለ24 ሰአታት በመጠበቅ፤ በሀገሪቱ የአየር ግዛት ውስጥ የሚደረጉ በረራዎችን ከመቆጣጠር ጀምሮ፤ ሉአላዊነትን የሚፈታተኑ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ መረጃዎችን ለሚመለከታቸው አካላት በማስተላለፍ ለሀገር ሉአላዊነት መከበርም ሌት ተቀን የሚተጋ ተቋም ነው።
በዓለም አቀፍ ደረጃም ሀገሪቱ በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ሊኖራት የሚችለውን ተሰሚነት በማስጠበቅ ፤እንደ ሀገር ማግኘት የሚገባትን ጥቅማ ጥቅሞች በማስከበር ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀገርና ሕዝብን ወክሎ የሚንቀሳቀስ ተቋም ነው። በቀጣይም የአየር ትራንስፖርቱ ለሚኖረው እድገት ዋነኝ ባለድርሻ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
በትናንትናው እለት በሳይንስ ሙዚየም የተከፈተውና የዘርፉን ተዋንያን ሥራዎች የሚያስቃኘው ኤክስፖ የዚህን የሀገር ባለውለታ ተቋም ሀገራዊ አበርክቶዎች ለማሳየት መልካም አጋጣሚ ነው።
ኤክስፖው በሀገሪቱ የአየር ትራንስፖርት ታሪክ ውስጥ የነበረውን እና አሁንም ያለውን ስፍራ በተጨባጭ ማሳየት ያስቻለ፤ ዜጎች ስለተቋሙ የተሻለ ግንዛቤ ኖሯቸው ለተቋሙ ተገቢውን ከበሬታ እንዲሰጡት የሚያስችልም ነው ። በተቋሙ ውስጥ ያለፉ አንቱታ ያተረፉ ባለሙያዎችን አውቆ ለመዘከርም እድል የሚሰጥ ታሪካዊ አጋጣሚ ነው።
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 2 ቀን 2016 ዓ.ም