የአርሶ አደሮች ቀን – ጠንካሮችን ለማበረታታት

ከኢትዮጵያ ሕዝብ 85 በመቶ ያህሉ አርሶ አደር መሆኑ ይነገራል፡፡ ይህ አርሶ አደር የሀገሪቷ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት በሆነው የግብርና ሥራ ይተዳደራል። መንግሥት የዚህን አርሶ አደር አመራረትና ሕይወት እየሠራ ይገኛል፡፡ አርሶ አደሩን ከእጅ ወደአፍ የማምረት ሂደት በማውጣት ትርፍ አምራች ለማድረግ የተለያዩ ድጋፎችን ያደርጋል፡፡

የግብርናው ዘርፍ እንዲዘምንና ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር በዘርፉ የተለያዩ ድጋፎችን ያደርጋል፡፡ ግብዓት በማቅረብ፣ ሜካናይዜሽን እንዲስፋፋ፣ የኩታ ገጠም እርሻ እንዲስፋፋ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን እውን በማድረግ አርሶ አደሩ በዓመት አንዴ ከሚያመርትበት ሂደት ሁለትና ሶስቴ ማምረት የሚችልበትን አድል እየፈጠረ ይገኛል፡፡

ይህን ሁሉ ተከትሎም የግብርና ሥራ እየተሻሻለና ምርትና ምርታማነት እየጨመረ መጥቷል፡፡ በዚህም የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን በማስፋፋት ስንዴ ከውጪ የሚመጣበትን ሁኔታ ማስቀረት ተችሏል፡፡ በሩዝ ልማትም እንዲሁ እየታየ ያለውን ለውጥ ተከትሎ ሩዝን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እየተሠራ ነው፡፡

ይሁንና የምርት እድገቱ ሀገሪቷ ካላት ዕምቅ አቅምና ጋር ሲነጻጸር የምርትና ምርትማነት እድገት አሁን ብዙ ይቀረዋል፡፡ ሀገሪቷ ከዘርፉ ከምትጠብቀው ምርትና ምርታማነት አንጻር ሲታይም ውጤቴ ብዙም የሚያኩራራ አይደለም፡፡ መንግሥት የግብርናው ዘርፍ እንዲያድግና እንዲዘምን ብሎም ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር በየዓመቱ የተለያዩ ድጋፎችን የሚያደርገውም ለዚሁ ነው፡፡

የአርሶ አደሩን ሕይወት ለመቀየር፣ ግብርናው እንዲዘምንና ምርትና ምርታማነትን ይበልጥ ለማሳደግ አርሶ አደሩ ይበልጥ ተበረታቶ የሚሠራበትን ሁኔታ መፍጠርም ይገባል፡፡ አርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነትን እያሳደገ ለመጣበት ሁኔታ እውቅና የሚሰጡና የሚያበረታቱ ሥራዎች እምብዛም አይስተዋሉም፡፡

በኢኮኖሚ የበለጸጉ እንደ አሜሪካ፣ ህንድ እና ቻይና ያሉ ሀገራት ተሞክሮን ስንመለከት አርሶ አደሩን የሚያበረታቱና ቅድሚያ እንዲያገኝ የሚያስችሉ ሁኔታዎች ስለመኖራቸው መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ለዚህም በየዓመቱ የተለያዩ ስያሜዎችን በመስጠት አርሶ አደሩ ዕውቅና የሚያገኝበትና የሚበረታታበት የአርሶ አደሮች ቀን ይሰየማል፡፡

በኢትዮጵያም በተመሳሳይ ምርትና ምርታማነትን ያሳደጉ፣ ኑሯቸውን ያሻሻሉ እና ለሌሎች አርሶ አደሮች አርአያ መሆን የቻሉ አርሶ አደሮችን በማበረታታት በሌሎች ዘንድ ተነሳሽነት መፍጠር የሚያስችል የእውቅና መርሀ ግብር ሲካሄድ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይህ የእውቅና መርሀ ግብር በ 1988 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ በባሕርዳር ከተማ ተካሂዷል፡፡ የእውቅና ሥነ ሥርዓቱ እስከ 2006 ዓ.ም ድረስ ሳይቆራረጥ ለዘጠኝ ተከታታይ ዓመታት ሲካሄድ ቆይቶ ተቋርጧል፡፡

ከሰሞኑም ለአርሶ አደሩ እውቅና መስጠት ላይ የመከረ መድረክ በግብርና ሚኒስቴር፣ በቀድሞ የሀሮማያ ኮሌጅ ተመራቂ ተማሪዎች ማህበር እና በአሊያንስ ፎር ሳይንስ የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት አባላት አማካኝነት ተካሂዷል፡፡ የአርሶ አደሩ ተወካዮች፣ ተመራማሪዎች፣ ከፍተኛ የግብርና ባለሙያዎች እና የሚመለከታቸው አካላት በመድረኩ ተሳትፈዋል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር የእርሻና የሆልቲካልቸር ኤክስቴንሽን ዘርፍ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ የኔነሽ ኤጉ እንዳሉት፤ መድረኩ የተቋረጠውን የአርሶ አደር ቀን በዓል ለማስቀጠል ያለመ ነው፡፡ ቀኑ ጠንካራ አርሶ አደሮች የሚሸለሙበት እና ወደኋላ የቀሩ አርሶ አደሮች ደግሞ የሚበረታቱበት፣ አርሶ አደሩን የተመለከቱ መልዕክቶች የሚተላለፉበት፣ መሪዎችና ፖሊሲ አውጪዎች ከአርሶ አደሮች ጋር የሚመክሩበት ነው። እንደዚህ አይነት መድረኮች ቀጣይነት እና ወጥነት ባለው መልኩ መካሄድ ባለመቻሉ በቀጣይ የአርሶ አደሮች ቀን እንዲኖር ለማድረግ ያስችላል፡፡

‹‹የአርሶ አደሮች ቀን አርሶ አደሩን የምናበረታታበትና የምንሸልመበት፣ ጠንካሮችን በደንብ አጠናክረን ወደ ኢንቨስትመንት የምናስገባበት እና ሌሎች ወደኋላ የቀሩ አርሶ አደሮችን የምናበረታታበት ነው›› ያሉት ወይዘሮ የኔነሽ፣ ከዚሁ ጎን ለጎን ኤግዚቢሽኖች እና የተለያዩ ፕሮግራሞች የሚካሄድበት መሆኑንም አብራርተዋል። መድረኩም በጋራ ለመወሰን የሚያስችል እንደሆነም አመላክተዋል፡፡

የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት የሆነውን የግብርና ዘርፍ ዋና ተዋናይ አርሶ አደር ማበረታታት ትልቅ ፋይዳ አለው ያሉት ወይዘሮ የኔነሽ፤ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ትልቁ ባለድርሻ አርሶ አደሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደሩን ማበረታታት እውቅና መስጠት በተለይ ውጤታማ የሆኑትን መሸለም ወደ ኋላ የቀሩትን ለማነቃቃት ጠቃሚ እንደሆነም አመላክተዋል፡፡

የግብርናው ዘርፍ ችግሮች ምላሽ የሚያገኙበት አንድ መድረክ እንደሚሆንም ወይዘሮ የኔነሽ፤ አመላክተዋል። ድርቅ፣ በሽታ እና በመሳሰሉት በርካታ ጉዳዮች ዙሪያ ለሚነሱት ችግሮች የፖሊሲ፣ የስትራቴጂ እና በተለያየ መልኩ ምላሽ የሚሰጥበት እንዲሁም አርሶ አደሩ የቴክኖሎጂ እና የገበያ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ የበኩሉን ሚና ሊጫወት እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር መለስ መኮንን እንዳሉት፤ አርሶ አደሩን የማመስገን ጉዳይ ዘላቂነት ባለው መልኩ መፈጸም ይኖርበታል፡፡ በዚህም ሂደት የመጀመሪያው ተግባር ቀኑ የሚከበርበትን ሁኔታ ለመወሰን የሚያስችል አንድ ግብረ ኃይል መቋቋም አለበት፡፡ ይህ ግብረ ኃይል አርሶ አደሩን ለማመስገን የሚያስችሉ ቀደም ሲል የተሠሩ ሥራዎችንና ሌሎች ተሞክሮዎችን በደንብ ተንተኖ ለውሳኔ ሊሆን የሚችሉ ሃሳቦች አዘጋጅቶ ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡

የቀድሞው የአርሶ አደሮች ቀን ብዙ መልካም ጎኖች እንደነበሩት ያስታወሱት ሚኒስቴር ዴኤታው፣ ይህን ቀን እንደገና መመልከትና ወቅቱ ከሚፈልገው አኳያ መቃኘት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል፡፡ አንዳንድ መስተካከል እና መቅረት ያለባቸው ነገሮች እንዳሉም ጠቅሰው፣ በአርሶ አደሮች ቀን አርሶ አደሮች ተለውጠዋል፣ ባለሀብት ሆነዋል ተብለው የሚመረጡባቸው መንገዶች አንዳንድ ችግሮች እንደነበሩባቸው አስታውሰዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት ሕይወታቸው ያልተለወጠ አርሶ አደሮች ጭምር ባለሀብት /ሚሊየነር/ ሆነዋል ተብለው ይቀርቡ እንደነበር ነው፡፡ በእውነቱ የተለወጡ እንዳሉ ሆነው እንደዚህ አይነት ስህተቶች እንዳይደገሙ ማድረግ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ አሁን መሆን አለበት? የሚለው በጥልቀት ታይቶ ውሳኔ ለሚሰጡ አካላት መቅረብ እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡ ‹‹የአርሶ አደሮች ቀን ብለን ስናከብር ሌላ አዲስ ነገር የምንጀምርበት ሳይሆን፣ የቀደሙ ጥሩ ተሞክሮዎችን በመቀመር፣ የማይጠቅሙትን በመተው፣ ቀኑ እንዲከበር የሚደረግበት ነው›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ይህንን ሥራ በባለቤትነት የሚመራው የግብርና ሚኒስቴር ነው፡፡ ያሉት ሚኒስትሩ ለአርሶ አደሩ የሚሠራ ስለሆነ አርሶ አደሩን የሚጠቅም የትኛውንም ተግባር ያከናውናል፡፡ ይህ ሲባል ደግሞ የግብርና ሚኒስቴር ብቻውን ይሠራል ማለት አይደለም፤ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር፣ የንግድ ሚኒስቴር፣ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እና ሌሎች የግብርና ቤተሰብ የሆኑ ተቋማትም ጉዳዩ ይመለከታቸዋል፡፡ ግብረ ኃይሉ የአርሶ አደሮች ቀን በምን መልኩ መከበርና እንዴት መከበር እንዳለበት ሁሉንም ሠርቶ የሚያቀርብ ይሆናል፡፡ የግብርና ሚኒስቴርም ይህን ጉዳይ ሰፋ አድርጎ በመመልከት ቀጣይነት ያለው ተግባር ያከናውናል፡፡

በመድረኩ ላይ ቀኑ እንዲከበር በማድረግ በኩል ግብርና ሚኒስቴር የሚያከናውነው ተግባር እንዳለ ሆኖ፣ የአርሶ አደሮች ማህበር የማቋቋም አስፈላጊነትም ተጠቁሟል፡፡ ሚኒስትር ዴኤታው የተነሳው ሃሳብ ትክክል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ጥናት ማድረግ እንደሚገባ አመልክተው፣ የአርሶ አደሮች ማህበር ወደፊት የአርሶ አደሮች ቀን በዓል አንዱ ባለቤት እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው እንዳሉት፤ የአርሶ አደሮች ቀን ከአርሶ አደር የሥራ ባህሪ ጋር የሚሄድ መሆን አለበት፡፡ የአርሶ አደሩ የሥራ ባህሪ አንድ ቀን ላይ ብቻ እንዲተኮር አያደርግም፡፡ እንዲከበር የሚፈለገው የአርሶ አደሮች በዓል ስለሆነ ከመሬት ባለቤትነት ባሻገር ብዙ ነገሮች ሊነሱበት ይችላሉ፤ ቀኑ መቼ መከበር አለበት የሚለው በደንብ መታየት ይኖርበታል፡፡ በዓሉ ለአንድ ቀን ብቻ ሳይሆን ለአንድ ወር የሚከበርበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፤ ሌሎች አማራጮችም በጥልቀት መታየት አለባቸው፡፡

አርሶ አደሩ ቀኑን ሲያከብር ምርቶቹን የሚያቀርብበትና ብዙ ጥያቄዎቹ ምላሽ እንዲያገኙ የሚሠራበት እንዲሆን ተደርጎ መታየት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዝርዝር ሥራዎችን በማካተት ግብረ ኃይሉ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ማብራሪያ፤ የአርሶ አደሩን ቀን ለማክበር የተመረጠው ግብረ ሃይሉ በጥናት ላይ ተመሥርቶ መሥራት ይኖርበታል፤ ሥራውን በደንብ ተንትኖ የሚያቀርብ ይሆናል፡፡ በሥራው ሂደት ሌሎች ግብዓቶች ካስፈለጉም ተጨማሪ መድረኮችን ማዘጋጀት ይቻላል፤ በዚህም የሚያቀርበውን ሃሳብ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመገናኘት የበለጠ እንዲበለጽግ ማድረግ ይችላል፡፡ ግብረ ሃይሉ በተሰጠው አጭር ጊዜ በዚህ መድረክ ላይ የተነሱትን ሃሳቦች በደንብ በመተንተን የቤት ሥራውን አጠናቅቆ ለውሳኔ ያቀርባል፡፡

የአርሶ አደሮችን ቀን ለማክበር የሚከናወነው የሥራ ሃላፊነት ከፍተኛ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የቀድሞው የአርሶ አደሮች ቀን ያኖረውን ዐሻራ በመውሰድ፣ መካተት ያለባቸውን በማካተት ቀኑ እንደገና መከበር እንዲጀምር የማድረጉ ሥራ ብዙ ጥረት ማድረግን እንደሚጠይቅም አመልክተዋል፡፡ በደንብ የተደራጀና ዘላቂነት ባለው መልኩ የሚከበር የአርሶ አደር በዓል እንዲኖር ለማድረግ በሚኒስቴሩ በኩል በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል፤ ቀኑ እንዲከበር የመነሻ ሃሳብ ያነሱትን የቀድሞ የሀሮማያ ኮሌጅ ተመራቂ ተማሪዎች ማህበር አባላትን እና አለያንስ ፎር ሳይንስ የተሰኘውን ግብረሰናይ ድርጅትም አመስግነዋል፡፡

በመድረኩ ላይ ከተገኙ አርሶ አደሮች ወጣት አርሶ አደር ትዕግስት ከበደ አንዷ ናት፡፡ ‹‹የገበሬ ልጅ ነኝ፤ እኔም ገበሬ ነኝ›› ያለችው አርሶ አደር ትዕግስት፣ ቀደም ሲል ገበሬ የሚለው ቃል ለስድብ የሚውል ነበር፡፡ አሁን ግን ገበሬ ሲባል ሀብታም እንደሆነ ይታሰባል። ገበሬው ገበሬ መሆኑን ሲናገር በራሱ ኩራትን ያጭራል›› ትላለች፡፡

አርሶ አደር ትዕግስት አሁን ድረስ አብዛኛው የግብርና ሥራ ከባህላዊ አስተራረስና አመራረት አለመላቀቁን ጠቅሳ፤ አብዛኛው ገበሬ በበሬ የሚያርስ በመሆኑ የአርሶ አደሩን ሕይወት የሚያሻሽል የተሻለ አሠራር ሊኖር የግድ መሆኑን ጠቁማለች፡፡ የአርሶ አደሩን ቀን ለማክበር ስንነሳ ይህ ከግንዛቤ ውስጥ መግባት አለበት ብላለች፡፡

አርሶ አደሩን መሸለም ብቻውን በቂ እንዳልሆነም ጠቅሳ፣ የአርሶ አደሩን ችግሮች ከመሰረቱ ሊፈቱ የሚችሉ ነገሮችን አብሮ ማሰብን ይጠይቃል ብላለች። አርሶ አደሩ ለፍቶ ያመረተውን ለሸማቹ በአግባቡ የሚያቀርብበት የገበያ ትስስር መፈጠር ያለበት መሆኑን አብነት በመጥቀስ አንስታለች፡፡ አሁን ላይ ባለው አሠራር አርሶ አደሩ ምርቶቹን በቀጥታ ለህብረተሰቡ የሚያቀርብበት ሁኔታ አለመኖሩን ጠቅሳ፤ ይህ በመሆኑም ተጠቃሚዎቹ በመሀል ያሉ ደላሎች መሆናቸውን አመላክታለች፡፡

እሷ እንዳለችው፤ የአርሶ አደሮች ቀን ሲከበር አርሶ አደሩ ችግሮቹን አውጥቶ የሚናገርባቸው የውይይት መድረኮችም ጎን ለጎን መዘጋጀት ይኖርባቸዋል፤ በዚህም ከአርሶ አደሩ ጋር መመካከር ያስፈልጋል፡ አርሶ አደሩን መደገፍና በሁሉም መስክ ተሰማርቶ ውጤታማ እንዲሆን ማስቻል ያስፈልጋል፡፡

ሌላው በመድረኩ የተገኙት አርሶ አደር አቶ ተስፋዬ በዳዳ ናቸው፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ አርሶ አደሩ አሁን የሚያመርተው ጤፍና ስንዴ ብቻ አይደለም፤ የግብርና ሥራው እጅግ ሰፍቷል፡፡ አርሶ አደሩ በሁሉም የግብርና ሥራዎች ላይ እንዲሠማራ ለማስቻል እውቅና መስጠትና ማበረታት ይገባል። በዚህም ጠንክሮ የሠራው አርሶ አደር ሲበረታታ፣ ወደኋላ የቀረው ይነቃቃል ነው ያሉት፡፡

የአርሶ አደሩ ሕይወት የሆነው የግብርና ሥራ ሊደገፍና ሊበረታታ የሚገባው ጉዳይ እንደሆነ ያነሱት አቶ ተስፋዬ፤ ለእዚህም የአርሶ አደሮች ቀን መከበር አንዱ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡ ቴክኖሎጂ እየተስፋፋ ባለበት በዚህ ጊዜ ግብርናውን በማዘመን አርሶ አደሩን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚችሉ ሥራዎችን መሥራት ይጠይቃልም ብለዋል። ግብርናውን የሚያሻሽሉ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ ማቅረብ ላይ በተጠናከረ መልኩ መሠራት እንደሚገባ ገልጸው፤ የግብርና ሚኒስቴርም ሆነ በዘርፉ የሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለአርሶ አደሩ በአጠቃላይ ለግብርናው ዘርፍ የሚያደርጉት ድጋፍ ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመላክተዋል።

መድረኩ የአርሶ አደሮችን ቀን ለማክበር የቅድመ ሁኔታ ሥራዎችን የሚሠራ ከግብርና ሚኒስቴርና ከሚመለከታቸው አካላት የተውጣጡ ሰባት አባላት ያሉት ኮሚቴ አዋቅሮ ተልዕኮ በመስጠት ተጠናቅቋል።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኀሣሥ 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You