የትምህርት ስብራቱን ለመጠገን የመምህራን ሚና

መምህርት ጽጌ ገብሩ (ለዚህ ፀሁፍ ሥሟ የተቀየረ) ላለፉት አስር ዓመታት በመምህርነት አገልግላለች። መምህርነት የምትወደው ሙያዋ ነው፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ከደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በእንግሊዝኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ አግኝታለች፡፡ ቋሚ መኖሪያዋን አዲስ አበባ ከማድረጓ በፊት በኢትዮጵያ የተለያዩ ገጠር አካባቢዎች ተዘዋውራ የማስተማር እድል ገጥሟታል፡፡

ዩኒቨርሲቲ ካገኘችው እውቀት በተጨማሪ የማስተማር ሥራ ላይ እያለች ከምታስተምርበት ቋንቋ ጋር የተያያዙ ክበባትን መሠረት ያደረጉ ሥልጠናዎች ወስዳለች፡፡

የመጀመሪያ ዲግሪዋን ወደ ሁለተኛ ዲግሪ ማሳደግ የምትችልበት እድል የነበረ ቢሆንም፤ ራሷን አሻሽላ በመምህርነት ሙያ የምታገኘው የደሞዝ ጭማሪ በቂ ነው ብላ አላሰበችም፡፡ ለዛም ነው የመምህርነትን ሙያዋን በሌላ ትምህርት መስክ ለመቀየር በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቷን እየተከታተለች ያለችው፡፡ ማስተማር በሷም ሆነ በባልደረቦቿ ዘንድ የሚወደድ ሙያ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በዚህ ሙያ ኑሮን መግፋት እየከበደ እንደመጣ ትናገራለች። የመምህርነት ደመወዟ ከዘጠኝ ሺ ትንሽ ፈቀቅ ያለ ቢሆንም ለቤት ኪራይ ብቻ አስር ሺ ብር ወጪ እንደምታደርግ ትገልፃለች፡፡

እንደመምህርቷ ገለፃ፣ መምህራን በደመወዛቸው ብቻ ወር ከወር መድረስ ስለማይችሉ ተጨማሪ ሥራዎችን ይሠራሉ፡፡ አብዛኞዎቹ የሥራ ባልደረቦቿ የግል ትምህርት ቤት ያስተምራሉ፣ ተማሪዎችንም ያስጠናሉ፡፡ እርሷ ግን ባለቤቷ የተሻለ ገቢ የሚያገኝ በመሆኑ ተጨማሪ ሥራ አትሠራም፡፡ ባለቤቷ ባይደግፋት ኖሮ ብቻዋን በምታገኘው የመምህርነት ደመወዝ ኑሮን መግፋት ከባድ ሊሆን እንደሚችል ትገምታለች፡፡

ተጨማሪ ሥራ የሚሠሩ ባልደረቦቿ የትምህርት ክፍለ ጊዜ እየተጋጨባቸው ለማስተማር ክፍል ሳይገቡ ሲቀሩና በተደጋጋሚ ሲያረፍዱ ታዝባለች፡፡ ይሄም በሱፐርቫይዘሮችና በመምህራን መሃል የጸብ መነሻ ሲሆን ተመልክታለች፡፡ በዚህ የተነሳ ተማሪዎች ማግኘት ያላባቸውን እውቀት ሳያገኙ እንደሚቀሩም አስተውላለች። ሆኖም የትምህርት አመራሮቹም የኑሮ ሁኔታውን ስለሚያውቁ ጫን ብው መምህራኖቹን ሲናገሩ አላየችም፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር የመምህራን እና ትምህርት አመራር ልማት አስተዳደር ዴስክ ኃላፊ ወይዘሮ አሰገድ ምሬሳ እንደሚናገሩት፣ ትምህርት ሚኒስቴር ብቁ ተማሪዎችን ለማፍራት የበቁ መምህራን ሚና የጎላ መሆኑን በመረዳት ደረጃውን የሚመጥን የትምህርት ዝግጅት ያላቸውን መምህራን ለማፍራትና ያሉትንም መምህራን ብቃት ለማሻሻል የሚያስችሉ ሥልጠናዎች በስፋት ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ በ39 የመምህራን ትምህርት ኮሌጆች ሥልጠናዎች በስፋት እየተሰጡ ይገኛሉ። ከ30 በላይ በሚሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች ውስት ባሉ የትምህርት ኮሌጆች በመጀመሪያ ዲግሪና በሁለተኛ ዲግሪ በመደበኛና በክረምት መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮችን በስፋት የማፍራት ሥራ ሲሠራ ቆይቷል፡፡

የትምህርት ሥራ ውጤት ለማግኘት ከታች ጀምሮ ለተማሪዎችን በቂ እውቀት እየሰጡ ማብቃት የሚችሉ ብቁ መምህራን ማፍራት ይጠይቃል፡፡ ይህንኑ መሠረት ያደረገ ሥራም እየተሠራ ነው፡፡

እንደ ዴስክ ኃላፊዋ መረጃ ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን መካከል 85 በመቶዎቹ በሰርተፍኬትና ከዛ በላይ የተመረቁ ናቸው፡፡ በዚህ ስሌት 85 በመቶዎቹ ለደረጃው የሚመጥን የትምህርት ዝግጅት አላቸው፡፡ ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ከሚያስተምሩ መምህራን ውስጥ 94 በመቶዎቹ ዲፕሎማና ከዛ በላይ የትምህርት ዝግጅት አላቸው፡፡

አዲስ በተዘጋጀው የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ መሠረት ከሰባተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል የሚያስተምሩ መምህራን የመጀመሪያ ዲግሪ ሊኖራቸው ይገባል። ሆኖም 30 በመቶዎቹ ብቻ የመጀመሪያ ዲግሪ ሲኖራቸው 70 በመቶዎቹ ከዲግሪ ያነሰ የትምህርት ዝግጅት አላቸው፡፡

የሁለተኛ ደረጃ መምህራን ለደረጃው የሚመጥን የትምህርት ዝግጅት እንዲኖራቸው በርካታ ሥራ ተሠርቷል፡፡ በተመሳሳይ የመጀመሪያ ዲግሪና ከዛ በላይ ያላቸው መምህራንን ለማፍራት በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ በዚህም 94 በመቶ የሚሆኑት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን የመጀመሪያ ዲግሪና ከዛ በላይ የትምህርት ደረጃ እንዲኖራቸው ተደርጓል። መምህራን አስፈላጊውን የትምህርት ዝግጅት መያዛቸው ብቻ በቂ ባለመሆኑ የሥራ ላይ ሥልጠና መርሀ-ግብሮች ተዘጋጅተው ሥልጠና ተሰጥቷቸዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት የመምህራንና የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል ሰፊ ሥራ ቢሠራም፤ የትምህርት ጥራቱ ላይ የሚፈለገው ውጤት አልመጣም፡፡ የትምህርት ጥራትን ችግር ለመፍታት ትምህርት ሚኒስቴር ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ የአጠቃላይ ትምህርት ለውጥ እያደረገ ነው። በሥልጠና ሥርዓቱ ላይ ያሉ ተግዳሮቶች ምንድናቸው? ለምን የተማሪዎች ውጤትን ማሻሻልና አስፈላጊውን ብቃት ማምጣት አልተቻለም? የሚለውን ምላሽ ለመስጠት በርካታ ጥናት ተደርጓል፡፡

የተጠኑ ጥናቶችን መነሻ በማድረግ አዳዲስ ስትራቴጂዎች ተዘጋጅተዋል፡፡ የተደረጉት ጥናቶች በክረምት የሚደረገው የመምህራን የትምህርት ማሻሻያ ውጤታማ አለመሆኑን በማመላከቱ መረሃ-ግብሩ ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል፡፡

የክረምት መርሃግብሩ መምህራን ሲገቡ ከሀምሌ 15 በኋላ መሆኑንና ሲወጡም ከነሀሴ 10 እስከ ነሀሴ 15 መሆኑንና አለፍ ሲልም ስሙ የክረምት ቢባልም አንዳንድ ጊዜ ከአስር ቀን ያልበለጠ የመማር ማስተማር ሥራ የሚከናወንበት ጊዜ መኖሩን በመናገር ወረቀትን ከማደል በስተቀር ወቅቱ የተቀመጡ ይዘቶችን ለመሸፈን የሚያስችል አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡ በዚህ የተነሳ ከአሁን በኋላ በክረምት መርሀ-ግብር መምህራንን ከዲፕሎማ ወደ ዲግሪ እንዲሁም ከዲግሪ ወደ ሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት ደረጃ ማሻሻያ ሥልጠና አይቀጥልም ብለዋል፡፡

የመምህራን ሥልጠና ሥርዓት ያለውን የትምህርት ስብራት መጠገን አለበት፤ የሚል ሃሳብ ተይዟል፡፡ የመምህራን የሥልጠና ሥርዓተ ትምህርቱን የመቀየር ሥራ እየተሠራ ይገኛል፤ በቅርብ ተጠናቆ ለትግበራ ይወርዳል። አዲሱ የመምህራን የሥልጠና ሥርዓተ ትምህርት ከዚህ ቀደም ካለው ሥርዓት የተለየ ነው፡፡

አንዱ መለያውም ተዛማጅነቱ የተጠበቀ መሆኑ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ተማሪዎች የሚማሩት ሥርዓተ ትምህርትና መምህራን የሚሠለጥኑበት ሥርዓተ ትምህርት የተዛማጅነት ችግር ነበረበት፡፡ ይሄንን ችግር ለመቅረፍም መምህራን ተማሪዎችን እንዲያስተምሩ የሚማሩት ሥርዓተ ትምህርትና ተማሪዎቹን በትምህርት ቤት የሚያስተምሩበት ሥርዓተ ትምህርት ተዛማጅ ሆኖ ተዘጋጅቷል፡፡

ዴስክ ሃላፊዋ እንደሚያብራሩት፣ ከዚህ ቀደም በሥራ ላይ ካሉና ከተመዘኑ መምህራን መካከል 24 በመቶው ብቻ ምዘናውን አልፈዋል፡፡ አሁን ያለውን መሠረታዊ ችግር ለመቅረፍ መምህራንን በአጫጭር የሥራ ላይ ሥልጠና ለማብቃት ታቅዷል፡፡ በዚህም ከዚህ ቀደም በክረምት መርሃግብር የተማሩትንና በቂ የትምህርት ክፍለ ጊዜ ያልተማሩትንም መምህራን መድረስ ይቻላል፡፡

የትምህርት ደረጃ ማሻሻያ ሲወስዱ ያልተካተቱ ርዕሰ ጉዳዮችና የተቀየረውን ሥርዓተ ትምህርት መነሻ ያደረጉ ይዘቶች እየተመረጡ ይሠለጥናሉ። ከመምህራን ደመወዝ አነስተኛነት ጋር ተያይዞ ለሚነሳው ጥያቄ በ2012 ዓ.ም ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጋር በመተባበር ‹‹ጂ ኤ ጂ›› ተዘጋጅቶ ተተግብሯል፡፡ በዚህም በወቅቱ የመምህራንም ሆነ የርዕሳነ መምህራን ደመወዝ የተሻለ ነበር፡፡ ሆኖም የዋጋ ግሽበቱ ደመወዙን ዋጋ አሳጥቶታል፡፡

ለዚህም መምህራን በዋናነት የመኖሪያ ቤትና መሥሪያ ቦታ እንዲያገኙ ማድረግ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ይገኛል፡፡ በዚህም ከ120 ሺ በላይ መምህራን የመኖሪያ ቤትና ቦታ አግኝተዋል፡፡ በቀጣይም ይህ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ከክልሎች ጋርም መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

በተጨማሪም መኖሪያ ቤት ለሌላቸው መምህራን ክልሎች አቅማቸውን ባገናዘበ መልኩ የቤት አበል እንዲያገኙ እየተደረገ ነው፡፡ በቀጣይ መምህራን የራሳቸውን ኢኮኖሚ የሚያዳብሩበት ሁኔታን ለመፍጠር የመምህራን ሕብረት ሥራ ባንክ ለመክፈት ጥናቶች እየተካሄዱ ነው፡፡ በባንኩና በሌሎች አማራጮች መምህራን የሚቆጥቡበት የሚበደሩበትና ኑሯቸውን የሚያሻሽሉበት ሥርዓት መዘርጋት ካልተቻለ በየጊዜው የመምህራንን ኑሮ ለማሻሻል ደመወዝ መጨመር ምንም ጥቅም የለውም፡፡ ስለዚህ ሌሎች አማራጮችን መፈለግ ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል፡፡

የትምህርት ስብራቱ የሚጠገነው በዋናነት መምህራንና የትምህርት አመራሮች በሚያደርጉት ርብርብ ነው፡፡ ሌሎች ባለድርሻዎች ተሳትፎ ቢኖራቸውም ዋናው ቁልፍ በክፍል ውስጥ ባለው መማር ማስተማርና በትምህርት ቤት አመራር የትመህርት ስብራቱ ሊጠገን የሚችለው። በየደረጃው ያሉ መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች የተፈጠረውን የትምህርት ስብራት ለመቀልበስ የሚያስችል ሥራዎችን ባለው አቅም አጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት መምህር ሽመልስ አበበ በበኩላቸው እንደሚናገሩት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የነበረው የተማሪዎች ውጤት ልክ እንዳሁኑ ‹‹ይሄን ያህሉ አለፈ ይሄን ያህሉ ወደቀ›› ተብሎ ቢለይ ኖሮ ከዚህ የተሻለ ውጤት ይመዘገብ ነበር የሚል እምነት የለኝም፡፡

ከዚህ ቀደም 101 ያመጣ ተማሪ ዩኒቨርሲቲ ይገባ የነበረበት ሁኔታ እንደነበር በማንሳት ‹‹ስንት በመቶው ነው ከ50 በመቶ በላይ ስንቱስ ከ50 በመቶ በታች ውጤት አመጣ የሚለው›› በደንብ አይለይም ነበር ብለዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ተማሪዎች ተረጋግተው እየተማሩ ያለበት ሁኔታ አለመኖሩ የኮቪድ መከሰት፣ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ጦርነት መኖሩን ተከትሎ ተማሪዎች በአንድ ሃሳብ ተረጋግተው የሚያጠኑበትና የሚፈተኑበት ሁኔታ አለመኖሩ ለውጤቱ ማነስ አሉታዊ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

ፈተና በራሱ የተረጋጋ አካባቢ ይፈልጋል። ተማሪዎቹ ፈተናውን ለመፈተን ከመኖሪያ አካባቢያቸው ርቀው ሄደዋል፡፡ አብዛኛው ተማሪ ከ20 ዓመታች በታች መሆናቸውና አዲስ ቦታ ፍራቻ ነበረባቸው፡፡ በዚህ ላይ የብቃቱ ችግር ተደምሮ ያለፉት ተማሪዎች ሦስት ነጥብ ሁለት በመቶ ብቻ ናቸው፡፡ ተማሪዎች በደንብ የተዘጋጁበት ሁኔታ ቢኖር ከዚህ የተሻለ ውጤት ይመዘገብ ነበር፡፡

ያም ሆኖ ግን የትምህርት ጥራት ከጊዜ ወደጊዜ እየወረደ መጥቷል፡፡ ለዚህ እንደምክንያት የተቀመጡት ተማሪዎች ትኩረት ሰጥተው እየተማሩ አለመሆናቸውና በመምህራንም በኩል የተለያዩ ችግሮች መኖራቸው ነው። የመምህራን ጥቅማጥቅም ይከበር የሚለውም ሌላው ምክንያት ነው፡፡

እንደ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ማብራሪያ፤ የኑሮ ውድነቱን ተከትሎ በክልሎች ባጃጅ እየነዱ የሚያስተምሩ መምህራን፣ አናጺ ቤት እየሠሩ የሚያስተምሩ መምህራንና፣ በገጠር አካባቢ እርሻ እያረሱ የሚያስተምሩ መምህራን አሉ፡፡ ሆኖም መምህር ሆኖ ተጨማሪ ሥራ መሥራት እንደማይቻልና መምህር የመምህርነትን ሥራ ብቻ መሥራት እንዳለበት መግባባት ላይ ተደርሷል። በዛው ልክ ተማሪም የሚጠበቅበትን ድርሻ መወጣት ካልቻለ ችግሩ አይፈታም፡፡ የትምህርት ጥራት ጉድለት አሳሳቢ ነው። ስለዚህ የወደቀውን ትምህርት ማንሳት የሁሉም ሕብረተሰብ ድርሻ መሆን አለበት፡፡

የመምህራንን የጥቅማጥቅም ጥያቄ መጠየቅ የሚቻለው የመማር ማስተማሩ ሥራ ላይ ውጤት ሲመዘገብ ነው፡፡ መምህር ሙሉ ጊዜውንና እውቀቱን አውጥቶ የመማር ማስተማር ሥራ ላይ አውሎ የተጣለበትን ኃላፊነት መወጣት መቻል አለበት። ሆኖም በዘርፉ ሰፊ የመልካም አስተዳደር ችግሮች አሉ፡፡ ስድስት ወር ድረስ ደሞዝ ያላገኙ መምህራን መኖራቸውንና ደሞዛቸው ከፍቃዳቸው ውጪ እስከ 18 በመቶ የሚቆረጥባቸው አካባቢዎችም አሉ፡፡ አልፎ አልፎም መምህራን በራሳቸው ደሞዝ የማያዙበት ሁኔታ በመኖሩ ይህ የመልካም አስተዳደር ችግር ሊቀረፍ ይገባል፡፡ በዛው ልክ መምህራንም ሙሉ አቅማቸውን ይዘው ማስተማር ይጠበቅባቸዋል፡፡

ምንም እንኳን በኢትዮጵያ ለመምህራን የሚከፈለው ክፍያ ዝቅተኛ ቢሆንም መምህራኖች ሥራ ሊሠሩ የሚገባው በቂ ክፍያ ሲከፈላቸው ብቻ መሆን የለበትም፡፡ አንዴ የተገባበት የውድድር ሜዳ እንደመሆኑ ውድድሩን አሸናፊ ሆኖ መውጣት ግድ ይላል፡፡ ማህበሩ የመምህራንን ጥያቄ ለማስመለስ የማይደርስበት ቦታ የለም፡፡ እንደዛም ሆኖ መምህራን ባላቸው አቅም ልክ ማስተማር መቻል አለባቸው የሚለው ጉዳይ ላይ መግባባት ተደርሷል፡፡

ከዚህ ውስጥ የመምህራንን የመኖሪያ ቤት ጥያቄ በ2007 ዓ.ም ለቀድሞው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ቀርቧል፡፡ በአዲስ አበባ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው የጋራ ኮንዶሚኒየም የተሰጣቸውና በስማቸው የዞረላቸው አምስት ሺ መምህራን እንዳሉ ይታወሳል፡፡ በተመሳሳይም በክልሎች ከሦስተኛ ወገን ክፍያ ነጻ የሆነ በማህበር ለተደራጁ 120ሺ መምህራን የመኖሪያ መሥሪያ ቦታ ተሰቷቸዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል በ2016 ዓ.ም ቦታ ላልደረሳቸው መምህራን ቦታ ለመስጠትና ትምህርት ቤት ላይ በመመላለስ ጊዜ እንዳይባክንና መምህራን ላልተገባ ወጪም እንዳይዳረጉ ገጠር ላይ ለሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች የመምህራን ማረፊያ ቤት እሠራለሁ ብሎ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ በመኖሪያ ቤት ረገድ ጥሩ ደረጃ ላይ እንዳለና ማህበሩም ይበልጥ ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ የማስታወስ ሚና ይጫወታል፡፡

‹‹ለመምህር መኖሪያ ቤት ቤቱም ቢሮውም ነው›› ያሉት መምህር ሽመልስ፤ የመማር ማስተማር ሥራ እንደሌላ ሥራ ከቢሮ ወጣሁ በማለት ጠረጴዛ ላይ ተትቶ የማይወጣና ዝግጅት የሚፈልግ ነው ይላሉ። ለመምህራን ሁለንተናዊ ዝግጅት የመኖሪያ ቤት ያስፈልጋል፡፡ የመኖሪያ ቤት ማግኘታቸው ቢሮም ቤትም በሆነው ቤታቸው መምህራን ተነቃቅተው እንዲሠሩ ያግዛል፡፡ በዚህ የተነሳ ለመምህራን የመኖሪያ ቤት ማግኘት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆን አለበት፡፡

አዲስ አበባ መኖሪያ ቤት ላላገኙ መምህራን የቤት አበል መጀመሩና የከተማ ባስ ትራንስፖርት ነጻ መደረጉ የሚበረታታ ነው፡፡ ይሄን ተሞክሮ ሌሎችም እየወሰዱት ነው፡፡ የመምህራን ጥቅማጥቅም ጥያቄ አለ ግን የማህበሩ አመራሮች ባለሥልጣናት ዘንድ ይሄን ጥያቄ ይዘው ሲቀርቡ ‹‹ትምህርቱ ያለበትን ታውቃላችሁ ወይ?›› እየተባልን አንገታችንን እየደፋን ነው የሚሉት መምህር ሽመልስ፤ ማስተማር የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን በማንሳት የወደቀውን ትምህርት ለማንሳት መምህራን ምንም ቅድመ ሁኔታ ሳያስቀምጡ ባላቸው አቅም በሙሉ እንዲያስተምሩ አደራ ብለዋል፡፡

ቤዛ እሸቱ

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኀሣሥ 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You