አንድ ሀገር ሉዓላዊነቷን አስከብራ ለመቀጠልም ሆነ የሕዝቦቿን ሰላምና ደህንነት አስተማማኝ ለማድረግ ከሁሉም በላይ በመከላከያ ዘርፍ የሚኖራት ሁለንተናዊ ዝግጁነት ወሳኝ ነው። በዚህ ዘርፍ የሚኖር የትኛውም ዓይነት ክፍተት ሀገርን በግልጽም ይሁን በስውር ለከፋ አደጋ መጋበዝ የሚያስችል አቅም እንዳለው ይታመናል።
የቴክኖሎጂ ልህቀት የመከላከያ ኢንዱስትሪውን በከፍተኛ ደረጃ እያዘመነ ባለበት በዚህ ዘመን፤ ሀገራት ባላቸው አቅም መከላከያቸውን ማዘመን ካልቻሉ፤ የሀገራቱ ህልውናም ሆነ የሕዝቦቻቸውን ደህንነት በየትኛው ሰዓት ከእጃቸው እንደሚወጣ እርግጠኛ መሆን ይቻላል። ይህ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት በተጨባጭ እየታየ ያለ እውነታ ነው።
በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ውድቀታቸውን የሚሹ፤ እንደ ጥላ በየዘመኑ የሚከተሏቸው ጠላቶች ያሏቸው ሀገራት፤ ከጠላቶቻቸው የልብ መሻትና ሴራ ራሳቸውን መታደግ የሚችሉት ጠንካራና አስተማማኝ፤ ዘመኑን የሚዋጅ የመከላከያ ሠራዊት መገንባት ሲችሉና ይህንኑም በቀጣይነት አጠናክረው ሲቀጥሉ ብቻ ነው።
ይህን እውነታ በአግባቡ የተረዳው የለውጡ መንግሥትም ወደ ሥልጣን ከመጣ ማግስት አንስቶ የመከላከያ ሠራዊቱን ሁለንተናዊ አቅም ማሳደግ የሚያስችሉ የሪፎርም ሥራዎችን ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል። በዚህም የሠራዊቱ ሕዝባዊነት ሆነ አሁነኛ ግዳጅ የመፈጸም ብቃት በከፍተኛ ደረጃ አድጓል። የሀገርም የሕዝባችንም ብሄራዊ ክብር ምንጭ እየሆነም ይገኛል።
ሠራዊቱ እየታጠቃቸው ያሉ ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች፤ በተለያዩ ሥልጠናዎች እያካበታቸው ያሉ ሙያዊ ክህሎቶች፤ ኢትዮጵያዊ ከሆነው ጀግንነትና ልበ ሙሉነት ጋር ተዳምሮ ለጠላትም ሆነ ለወዳጅ ተገቢ መልዕክት ማስተላለፍ የሚያስችልበት ደረጃ ላይ ስለመድረሱ ባለፉት ሁለት ዓመታት እያስተዋልናቸው ያሉ እውነታዎች ማሳያ ናቸው።
ለዚህም በኢትዮጵያ አየር ኃይል ዙሪያ እየተደረጉ ያሉ የሪፎርም ሥራዎችን እና እየተመዘገቡ ያሉ አንጸባራቂ ስኬቶችን ማንሳት ይቻላል። የሀገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት ዋነኛ አካል የሆነው ይህ ተቋም ፤ በአፍሪካ ደረጃ በቀዳሚነቱ የሚጠቀስ ፤ በአየር ላይ ውጊያ ገድሎች ባለ ብዙ ታሪክ ነው። ብቁ ባለሙያዎችንም በማፍራት አንቱታ ያተረፈም ነው።
ከሀገር ውስጥ ባለፈ በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ግዳጆች የተሰጠውን ተልእኮ በስኬት በመወጣት የሀገርና የሕዝብ ኩራት ነው፤ በዚህም ዓለም አቀፍ እውቅና ጭምር የተቸረው ነው። በበረራ እና ጥገና ማሠልጠኛ ተቋሙም ብዛት ላላቸው አፍሪካውያን ወንድሞቻችን አቅም ምንጭ በመሆን በማገልገል ላይ ያለ፤ በዚህም ለአፍሪካውያን ሳይቀር ኩራት የሆነ ተቋም ነው።
ይህን የትናንት ታሪኩን ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሻገር ባለፉት አምስት ዓመታት በተቋሙ ሁሉን አቀፍ ሪፎርም ሲደረግ ቆይቷል። በዚህም የተቋሙን ጊቢ ለሥራ አመቺ እንዲሆን ከማስዋብ ጀምሮ፤ ዘመኑ ያፈራቸውን ትጥቆችን እንዲታጠቅና ሙያዊ ብቃቶችን እንዲላበስ ተደርጓል።
በዚህም የሀገሪቱን የአየር ክልል በአስተማማኝ ደረጃ መጠበቅ የሚያስችለውን አቅም ተጎናጽፏል። በየትኛውም የግዳጅ ወረዳ የሚሰጠውን ወታደራዊ ተልዕኮ በስኬት የሚወጣበትን ቁመና መላበስም ችሏል።
የተቋሙ የሪፎርም ስኬት ከዚህም ባለፈ ለሀገሪቱ ወዳጆች ሆነ ጠላቶች አሁናዊ መልእክት ማስተላለፍ የሚችል አቅም ሆኗል። በተለይም ሀገሪቱ እንደ ሀገር የጀመረችውን ልማትና በልማቱ እያስመዘገበች ያለውን ተስፋ ሰጪ ውጤት ለማሰናከል ለሚሹ ኃይሎች መልዕክቱ ከፍ ያለ፤ በሀገሪቱ እና በሕዝቦቿ ላይ የሚያስቧቸውን የጥፋት ሃሳቦች ደጋግመው እንዲያጤኑ የሚያስገድዳቸውም ጭምር ነው!
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 1 ቀን 2016 ዓ.ም