“የዓድዋ ድልና የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያንን በአንድነት ያቆሙ የዐቢይ ትርክቱ ተምሳሌት ናቸው”

ረዳት ፕሮፌሰር አየለ በክሪ (ዶ/ር) የታሪክ ምሁር

ትርክት ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ያለው ሚና አሉታዊም አዎንታዊም እንደሆነ ይነገራል። ለዚህም በምክንያትነት የሚቀመጠው እንደ ሕዝብ ለመተባበርም ሆነ ለመፎካከር፣ ግጭት ለመፍታትም ሆነ ለማባባስ እንዲሁም ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማምጣትም ሆነ ድህነትን ለመሸከምም የሚያገለግል በመሆኑ ነው፡፡

ትርክትን ዐቢይ እና ንዑስ ትርክት በሚል በሁለት የሚከፍሉ የዘርፉ ምሁራን፣ ዐቢይ የሚባለው ትርክት የጋራ ማንነትና የሁሉም ጉዳይ የሆነ መሆኑን እንዲሁም የጋራ ችግር ለሆነው ጉዳይ የጋራ መፍትሔ ማስገኘት የሚችል መሆኑን ያመላክታሉ፡፡ ንዑስ ትርክት ደግሞ ተናጥላዊ ነው። የጋራ ጉዳዮች ላይ አያተኩርም።

አዲስ ዘመን ከዚሁ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ስለትርክት ምንነትና ሀገራዊ አንድነትን በማጠናከር በኩል ያለውን ፋይዳ በተመለከተ ኢትዮጵያ ከታሪክ ምሁሩ ከረዳት ፕሮፌሰር አየለ በክሪ (ዶ/ር) ጋር ያደረገውን ቆይታ እንደሚከተለው አጠንቅሯል፡፡

አዲስ ዘመን፡- እንደ አንድ የታሪክ ምሁር ትርክት ምንድን ነው ይላሉ? ንዑስና ዐቢይ ትርት የሚባሉት ልዩነታቸው ምንድን ነው?

አየለ (ዶ/ር)፡- ትርክት ከታሪክ አንጻር ከወሰድነው የተከናወኑ ድርጊቶችን የምንረዳበት መንገድ ነው። አሊያም የተከናወኑ ድርጊቶችን ወደቃላት በመቀየር ለዚያ ጉዳይ ሕዝብን እንዲገዛ ማድረግ እና በሥርዓቱ እንዲተዳደር ማስቻል ነው፡፡

የትርክት አይነቶች ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛው ታላቁ ወይም ዐቢይ ትርክት የሚባለው ሲሆን፣ ብዙውን ጊዜ የሚሠራውና የሚሰራጨው የሀገር አንድነትንና አብሮነትን ለማስረጽ ነው። በሌላ በኩል የበላይነትን ለማስረጽም ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ለምሳሌ የአንድ ሀገር ንጉሥ ማስረጽ የሚፈልገውን ሀገራዊ ጉዳይ ደጋግሞ ወደሕዝቡ የሚያደርስ ከሆነ ትርክት ሊቀየር ይችላል፡፡ በተለይ ንጉሡ የራሱ ኃይል አይነኬ መሆኑን የሚያሳይበት መስመር ሊሆን ይችላል፡፡ ሌላ ምሳሌ ብንወስድ ምዕራባውያን አፍሪካን በሙሉ አሊያም ደግሞ አብዛኛውን ዓለም በቁጥጥር ሥር ስላደረጉ እኛ ነን ገናናዎች በሚል አስተሳሰቡን ከድርጊት ጋር ቀምረው ያስረጹት አይነት አካሄድ ነው፡፡

ከዚህ የተነሳ ምዕራባውያኑ የበላይ ነን የሚለው ጉዳይ መመሪያቸው አድርገው ይዘውት ቆይተዋል፡ እናም ከሌሎች ጋር ሊፈጠሩ የሚችሉ ግንኙነቶችን የበላይና የበታች እንዲሁም የደረጃ ጉዳይ አደርገውት እየኖሩ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ የተነሳም በዚህ መንፈስ ቀሪዎቹን የዓለም ሀገራትን ሊጫኑ ችለዋል፡፡

እነዚህ ታላላቅ ትርክቶች ጊዜው ደርሶ ደረጃቸው ዝቅ ያሉ ሕዝቦች አሊያም ደግሞ በሌላ አነጋገር በቅኝ አገዛዝ ስር የወደቁ ሕዝቦች ይህንን አካሄድ በሚገባ ከተገነዘቡ በኋላ እነርሱን ለመጨቆን የተፈጠሩ መሆኑን በማወቃቸው የምዕራባወውያኑ ዐቢይ ትርክት ፈተና እየገጠመው መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካ እስከ እኤአ 1950 ድረስ ጥቁሮች የበታች፤ ነጮች ደግሞ የበላይ ተብለው ዘልቀው ነበር። ነገር ግን ጥቁሮቹ “እኛ እንዴት የበታች እንሆነናለን? አይደለንም!” የሚለውን ጉዳይ ለማስረጽ ሲሉ የሚጠቀሙባቸው የበላይ የሆኑ ስልቶች አሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ አንዱ የሚደረጉ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ናቸው፡፡

ወይም ደግሞ ቅዱስ መጽሐፍን ሲረዱና ሲተረጉሙ በእነርሱ አይነት መልክ ያለ ጉዳይ መኖሩን ማስተዋላቸው ነው፡፡ ከዚህም ውስጥ አንዱ በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ያገኙት ነገር ሲሆን፣ ይኸውም ከ60 ያህል ጊዜ በላይ ኢትዮጵያ መጠቀሷ ነውና ያንን ይረዳሉ፡፡ በዚህም “ኢትዮጵያ ማለት ጥቁር ሕዝብ ያላት ሀገር ናትና እኛም እግዚአብሔር የፈጠረን ጥቁር ሕዝቦች ስለሆንን በምንም አይነት ሁኔታ ደረጃችን ዝቅ ያለ ሕዝብ አይደለንም” በሚል ወደታላቅ ትርክት ውስጥ የገቡ ናቸው፡፡

ከዚህም የተነሳ ዐቢይ ትርክታቸው “የነጭ የበላይነት የለም፤ ሁሉም እኩል ነው” በሚል እንቅስቃሴ ውስጥ ይገባሉ፡፡ በዚህ ዐቢይ ትርክታቸው አብዝተው የሚገልጹት ዋና ጉዳያቸው “ጥቁር ሕዝቦች ማለት የእግዚአበብሔር ምርጥ ሕዝቦች ናቸው” የሚለውን ነው፡፡ ለዚህም ዋና ማሳያቸው በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ኢትዮጵያ የሚለው ስም ደጋግሞ መገለጹን ጭምር ነው፡፡ በመሆኑም “ጥቁር በጣም ቆንጆ ነው” የሚለውን መፈክር አጥብቀው በመያዝ የራሳቸውን ታላቅ ትርክት መፍጠር የቻሉበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡

እናም ሀገር የሚታየው እንዲሁ ነው፡፡ ለምሳሌ የእኛ ዐቢይ ትርክት መሠረቱ ሲታይ ትልቁ ጉዳይ ከንግሥተ ሳባ ጋር የተያያዘ ጉዳይ ወይም ታሪክ ነው። በእርግጥ አንዳንዶቹ “ንግሥተ ሳባ የመናዊት እንጂ ኢትዮጵያዊት አይደለችም” ይላሉ፡፡ እንዲህ የሚሉ አካላት ሊገነዘቡ ያልቻሉት ነገር በቀደመው በጥንቱ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት በነበረው ዘመን ነው። ኢትዮጵያዊት አይደለችም የሚሉ ስህተታቸው ኢትዮጵያ የሚባለው ግዛት በወቅቱ ቀይ ባህርንም የሚጨምር መሆኑን አለመገንዘባቸው ነው፡፡ በዛ አካባቢ ያሉ የመንና ሳዑዲ አረቢያ በሚል ስያሜ የሚታወቁት በወቅቱ እነርሱም በኢትዮጵያ ስር መሆናቸውን “ንግሥት ሳባ ኢትዮጵያዊት አይደለችም” የሚሉ አካላት ይዘነጉታል። እንዲያም ሆኖ የንግሥት ሳባ ትርክት የተፈጠረበት የራሱ አካሄድ አለው። ጥበብን ፍለጋ ወደ ኢየሩሳሌም ስትሔድ የራሷም መንግሥት ሀብታም መሆኑን የሚያሳይ ስጦታ ይዛ የሄደች ንግሥት የነበረችም ናት።

ዋና ቁም ነገሩ ሁሉም ሕብረተሰብ የየራሱ ታላቅ ትርክት እንዳለው መረዳቱና በዚያ ታላቅ ትርክት ተጠቃሚ ለመሆን መበርታቱ ነው፡፡ አለኝ የሚለው ትርክት ግን የተገነባበት መንገድ ምን ፍለጋ ነው የሚለው ላይ ማተኮሩ መልካም ነው፡፡ አንድ ሀገር አለኝ የሚለው ዐቢይ ትርክት ሕዝብን የሚያስተባብርና በማንነቱ እንዲኮራ የሚያደርግ ቢሆን ተመራጭ ነው። ችግሩ የአንዱ ትርክት የራሱን ማንነት ብቻ የሚያጎላ በመሆኑ ሌላው ላይ ለመጫን መፈለጉ ነው። በሌላ በኩል አንዱ ሀገር አለኝ የሚለውና አብዛኛውን ሕዝብ የሚያስማማ ዐቢይ ትርክት ሆኖ እያለ ሌላው አካል ግን “ይህን አልቀበልም” ማለቱ ላይ ነው፡፡ ይህ “አልቀበልም” ባዩ አካል ትርክቱ የተገነባበት መንገድን አለማስተዋሉ ነው። ከዚህም ሌላ ጉዳዩን ፖለቲካዊ ከማድረጉ በተጨማሪ አጥብቦ ማየቱም ሌላው ፈተና የሆነ ነገር ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- አንዳንዶች ዐቢይ ትርክት የሚገነባው በትውልድ ነው ይላሉ፡፡ ከዚህም የተነሳ እርስዎ ከጠቀሱት ዐቢይ ትርክት በተጨማሪ ጉዳዩን ከጊዜ አኳያ ቀረብ ስናደርግ የዓድዋ ድል እንዲሁም የበለጠ ስናቀርበው ደግሞ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እንደ ዐቢይ ትርክት ያነሳሉና ከዚህ አኳያ ይህንን እንዴት ይገልጹታል?

አየለ (ዶ/ር)፡- የዓድዋ ድልንም ሆነ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በምናስተውልበት ጊዜ የአንድነት ዐቢይ ትርክት ተምሳሌቶች ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው፡፡ ስለሆነም የዓድዋ ድልና የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያንን በአንድነት ያቆሙ የዐቢይ ትርክቱ ተምሳሌት ናቸው፡፡

በተለይ ዓድዋ አይነተኛ ዐቢይ ትርክት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ዓድዋ በትውልድ የተሠራና አሁን ላለንበት ማንነታችን መሠረት ያስቀመጠ ታላቅ ድል ነው። ለዘመናዊነታችንም መነሻ ነው፡፡ ምክንያቱም በወቅቱ የመጣው ጠላት እኔ የበላይ ነኝ በሚል መንፈስ ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት የመጣ ሲሆን፣ ሲሸነፍ አሸናፊው ከእሱ የተሻለ ሥልጣኔ እና ማንነት አለው ማለት ነው፡፡

ትልቁ ችግራችን ነው ብዬ የማስበው በተለይ ባለፉት 30 ዓመታት ያንን ጸጋ እና ታላቅ ድል ለአንድነታችን ማጠናከሪያ እንደ ድልድይ ከመጠቀም እና የተሻሉ ሁኔታዎችን ለሁላችንም ከመፍጠር ይልቅ ታሪክን ለማዛበት የተኬደበት ሙከራ መኖሩን ነው። በዐቢይ ትርክት ውስጥ ሌላ ያንን አይነት የሆነውን ትርክት ለማቃለል የሚደረጉ አካሄዶችም ነበሩ፡፡

ዓድዋ ዐቢይ ትርክት ነው፡፡ ዐቢይ ትርክት የሚያደርገው ዋና ነገር ደግሞ በወቅቱ ኢትዮጵያዊ የተባለው ሕዝብ ሁሉ የተሳተፈበት ጦርነት መሆኑ ሲሆን፣ የተገኘውም በኢትዮጵያውያን ትጋት መሆኑ ነው፡፡ ይህ ድል ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ዘመናዊነትና ወደፊት መገስገስ ታላቅ አርዓያ መሆን ያለበት ነው፡፡

ይህ የእኛ የኢትዮጵያውያን ዐቢይ ወይም ታላቅ ትርክት ነው የሚባለው የዓድዋ ድል በቅኝ ገዢዎች እጅ ሳንወድቅ ሙከራዎቻቸውን ሁሉ አክሽፈን በነጻነት መኖር መቻላችን ነው፡፡ ይህ ትግላችንና በአንድነታችን ያገኘነው ድላችን ዐቢይ ትርክታችን በመሆኑ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በአርዓያነት የሚጠቀስ ጭምር ነው፡፡ የዓድዋ ድል እነርሱም በሚፈጥሩት ዐቢይ ትርክት ላይ ይጠቃለላል። በዐቢይ ትርክታቸው ውስጥ ከመጨመር አልፎ ወደ ሌሎችም ይሄዳል። ምክንያቱም ዐቢይ ትርክት ሲገነባ እዛው የሚቀር ሳይሆን ከራስ አልፎ ለሌሎች የሚተርፍ ነው፡፡

የሌላው ዐቢይ ትርክት ጠቃሚ እስከሆነ ድረስ መውሰድ የሚቻል ነው፡፡ ለምሳሌ ፓን አፍሪካኒዝም ሲባል መላ አፍሪካን የሚያጠቃልል ነው፡፡ ስለዚህ መላ አፍሪካ ውስጥ ያሉ ጥሩ ናቸው፤ አርዓያ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ሊያሳድጉንና ሊያስተባብሩን ይችላሉ የሚሉትን መርጠንና አቀናጅተን ትርክት እንፈጥራለን። ከዛ ኅብረት የሚመጣው አንድነትም አፍሪካውያንን ያስተባብራል፡፡

ከዚህም የተነሳ ዓድዋ ከእኛ አልፎ ለሌሎች ሀገራት በሁለተኛ ደረጃ ብሎም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጭምር እንደ ታላቅ ትርክት የሚቆጠር ነው። በተለይ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አፍሪካ ሀገር በሆኑ በጋና እና ሴኔጋል የሚማሩት ጉዳይ ሆኗል፡፡ ለዚህ ትልቁ ምክንያት ምንድን ነው ከተባለ ሁሉም ነጻነቱን መሻቱ ነው፡፡ ይህን ነጻነት ኢትዮጵያውያን እንዴት ሊያስጠብቁ ቻሉ የሚለው ጉዳይ ቁልፉ መሠረት ነው። ከዚህ የተነሳ ዓድዋ የእኛ ብቻ የዐቢይ ትርክታችን መሠረት ሳይሆን በሌሎቹም ሀገራት ዐቢይ ትርክት ውስጥ ሊጨመር የቻለ ሆኗል። እንደሚታወቀው ትርክት ሲባል ታሪክ ላይ የተመረኮዘ ትርክት አለ። ይህ ማለት አንድ የተከናወነ ድርጊት ረጅም ጊዜ የሚያስቆጥር ከሆነ ወደ ታሪክ ይቀየራል ማለት ነው። ይህም የሚገነባው በትውልድ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ዐቢይ የሚባለው የትርክት አይነት ጥሩ እና አንድነትን ለመፍጠር አቅም ያለው ነው፤ ከዚህ በተቃራኒ ያለው ንዑስ የሚባለው የትርክት አይነት ዜጎች መግባባት ላይ እንዳይደርሱ የሚያደርግ ነው ይባላልና ይህንንስ እንዴት ያዩታል?

አየለ (ዶ/ር)፡- እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝብ ከሕዝብ ይጣላል? ይጋጫል? ብለን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ በእርግጥ ኢትዮጵያውያን አብዛኛው ታሪካችን የጦርነት ነው። በዚህ ታሪካችን ውስጥ ግጭት መኖሩ እንደተጠበቀ ሆኖ መስማማትም መግባባትም እንዳለ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ በመሆኑም ታሪካችን ውስብስብ እንጂ ወጥ ነው ማለት አይቻልም።

መረዳት ያለብን ነገር ቢኖር ግጭት ሲኖር የሚፈጠሩ ትርክቶች ይኖራሉ፡፡ እነዛን ትርክቶች ሆነ ብሎ አንዱን ሕዝብ ጠላት ሌላው ሕዝብ ደግሞ ጨቋኝ አድርጎ የማቅረብ ጉዳይ ነው፤ እሱ ደግሞ ሥርዓት እና የፖለቲካ አካሄድ ነው እንጂ ታሪካችን ሲታይ ግን ልክ በዓድዋ ጦርነት ጊዜ ያለው አይነት ኅብረት ያለው ነው፡፡ ነጩን በሀገር ወዳድ ስሜት ገጥመው ያሸነፉት ኢትዮጵያውያኑ ናቸው፡፡ እነዚህ ኢትዮጵያውያን ማን ናቸው የሚባል ከሆነ በቋንቋ እና በኃይማኖት የሚለያዩ፤ ነገር ግን ብዝሃነት ያላቸው ሕዝቦች ናቸው። የቱንም ያህል በዘር፣ በኃይማኖት የተለያዩ ቢሆኑም፤ በአንድ ሀገር ውስጥ “እኛ ኢትዮጵያውያን ነን” ብለው የኖሩ ሕዝቦች ናቸው፡፡

አንድ እውነት ስለመኖሩ ግን የሚያጠያይቅ ነገር የለም፡፡ ኢትዮጵያን በመሩ መንግሥታት መካከል ጥፋትም ልማትም መኖሩ አይካድም፡፡ ደግሞም እንደ አጠቃላይ ሲታይ በዓለም ላይ ሀገረ መንግሥት የምንለው በሚመሠረትበት ጊዜ ሰላማዊ በሆነ መንገድ አልፎ ያለምንም ጠብና ቆርሾ የተመሠረተ ሀገር አለ ብሎ ማለት አይቻልም፡፡ ይህ ሐቅ የሆነ የታሪክ ምስክር ነው ማለት ይቻላል፡፡ ዋናው መረዳት ያለብን ነገር ሕዝብ ሁልጊዜ የተሻለ ነገር ያለው መሆኑን ነው።

አንዳንዴ ሁለት የተጋጩ ትርክቶች ሲመጡ ይስተዋላል፡፡ ለምሳሌ የእስራዔልን እና የፍልስጤምን ጦርነት ብናስተውል በዚያኛው ወገን ያለው “መሬቱ የእኔ ነው ይላል” በእዚህኛው ወገን ያለውም “መሬቱ የእኔ ነው” ሲል ይደመጣል፡፡ በዚህኛውም ሆነ በእዚያኛው ወገን አንድ ሲነገር የቆየ ትርክት አለ ማለት ነው፡፡ በአንድ ጉዳይ ላይ የሚኖር እኩል አይነት ፍላጎት ግጭትን ያመጣል፡፡

በሀገራችን ኢትዮጵያ በተለያየ ምክንያት ሕዝብ ከአንድ ቦታ ወደሌላ ቦታ ይንቀሳቀሳል፡፡ ይህ የሚሆነው ምናልባት የሚያርሱት መሬት አንሷቸው ሊሆን ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ። በዚህ ምክንያት ወደ አዲስ አካባቢ ሲያቀኑ በተወሰነ መልኩ ግጭት ሊፈጠር ይችላል። ይህ የሚፈጠረው ደግሞ መግባባት እስካልተቻለ ድረስ ብቻ ነው፡፡

ነገር ግን አሁን አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ እያየን ያለው ነገር ወደየትኛውም ስፍራ ቢኬድ ጥርት ያለ አንድ ልዩ የሆነ ጎሳ እዚህ ቦታ አለ ሊባል አይችልም። ሁሉም ክልል የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ አለ፡፡ ለምሳሌ ትግራይ ክልል ትግርኛ ተናጋሪ ብቻ ነው ያለው ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም እዛም ሳሆ፣ ኩናማና ኢሮብ አሉ፡፡ እነዚህ በጣም አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ስለሆኑ ብዙውን ጊዜ አይጠቀሱም እንጂ በክልሉ ከጥንት ጀምሮ ያሉ ናቸው። እንዲያውም የሚነገረው የአክሱም አካባቢ የኩናማዎች እንደሆነ ነው፡፡ ከዛ ተገፍተው አሁን ያሉበት ቦታ እንደሄዱም ይገለጻል። ስለዚህ በኢትዮጵያ ባሉ የተለያዩ አካባቢዎች ብንሔድ የምናስተውለው ነገር እንዲህ አይነቱን ብዝሃነትን ነው።

አሁን አሁን እየተደረገ ያለው በቋንቋ ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ አስተዳደር ውስጥ እንድንገባ ነው። እሱ ግን ሊሆን አይችልም ባይ ነኝ፡፡ ወደእያዳንዱ ቦታ በምንሔድበት ጊዜ አስቀድሜ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ጸዓዳ ነው ወይም ጥርት ያለ ነው የሚባል አንድ ቋንቋ ብቻ የሚናገር ሕዝብ የለም። እንዲያም ቢሆን ያ ሕዝብ እናገረዋለሁ የሚለው ቋንቋ ራሱ ሊቀየር ይችላል፡፡ ምክንያቱም ቋንቋ በባሕሪው ተለዋዋጭ ነው፡፡ ኦሮሚኛ ተናጋሪ የነበሩ ሰዎች አማርኛ ተናጋሪ ሊሆኑ ይችላሉ፤ በተመሳሳይ አማርኛ ተናጋሪ የነበሩ ሰዎችም ኦሮሚኛ ተናጋሪ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ከዚህ የተነሳ የኢትዮጵያውያን ብዝሃነት ስብጥርጥር ያለ ነው፡፡ እንዲህ አይነቱ ሕዝባዊነት ደግሞ ለምሳሌ እኔ ስለእኔነቴ ሳስብ ከጎኔ ያሉ ጎረቤቶቼን ካልጨመረ፤ ከጎኔ ያሉ ብሔሮችን ካላካተተ ያኔ ነው አገማመታችንና አሠራራችን ትክክል የማይሆነው። ያኔ ደግሞ አመለካከታችን ትክክል ስለማይመጣ ወደግጭት ያመራል እንጂ እንዲሁ ሕዝብ ከሕዝብ ጋር በምንም አይነት ሁኔታ አይጋጭም፡፡ ይልቁኑ ግጭት እንኳ ቢኖር ሕዝብ ከሕዝብ ጋር ሆኖ የሚፈልገው መፍትሔ ነው፡፡ ለዚህ ዋና ምሳሌ አድርገን ማንሳት የምንችለው በሁሉም ብሔር የራሱ የሆነ በሽምግልና የሚካሄድ የእርቅ ሥርዓትን ነው። ቅራኔዎችና አለመግባባቶች በጭራሽ አይኖሩም ብሎ መደምደም አይቻልም፤ በአንዳንድ አጋጣሚዎች የሚነሱ ግጭቶች ካሉ እነዚያን ግጭቶች ለማቃለልና ወደነበረው ሰለማዊ የአኗኗር ዘይቤ ለመመለስ ሁሉም እንደየባህሉ የእርቅ ሥርዓትን ይከተላሉ፡፡

ዋነኛ መገለጫ የሆነው የዓድዋው ጉዳይን ብንመለከት ሁሉም ኢትዮጵያዊ “ከብሔርነቴ ሆነ ከኃይማኖቴ የሚቀድምብኝ ኢትዮጵያዊነቱ ነው” በሚል የተቀበለው ጉዳይ በመሆኑ ዐቢይ ትርክት መሆን ችሏል። በወቅቱ የዓድዋ ጦርነት ላይ ለመሳተፍ የተንቀሳቀሱት በአብዛኛው ከ18 እስከ 25 የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ናቸው፡፡ እናም በዚያን ወቅት ይህ ኃይል ባለበት ቦታ ሆኖ እና ትዳር መስርቶ አርሶ አደሩም እያረሰ፤ አርብቶ አደሩም እያረባ መኖር ይችል ነበር። ነገር ግን እንዲህ አይነቱ ተደላድሎ መቀመጥ ዘላቂ ሊሆን እንደማይችል ከወዲሁ መረዳት የቻለ ኃይል ነው፡፡ በመተባበርና አንድነቱን ብሎም ብዝሃነቱንና ሀገሩ በመቀበልም በጦርነቱ ያላአንዳች ማቅማማት ሊሳተፍ በቅቷል፡፡

በመሆኑም ዓድዋ የእኛ ዋና እና ታላቁ ትርክታችን ብቻ ሳይሆን ለሌላ ተግባራችንም በዋናነት ተጠቃሽ መሆን የሚገባው ነው፡፡ ለምንሠራቸው የአንድነት ሥራችን ሁሉ ዋና ማጣቀሻችን ሊሆን የተገባው መሆን አለበት፡ ኢትዮጵያውያን ዓድዋ ላይ የከፈሉት መስዋዕትነት ለሁላችን ነውና ያንን ጉዳይ በቅጡ መረዳት መቻል አለብን የሚል አተያይ አለኝ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ዓድዋን የመሳሰሉ ዐቢይ ትርክቶች የሚገነቡት በትውልድ ነው፤ አሁን አሁን እየታዩ ያሉ አለመግባባቶች አሉና ከዚህስ በኋላ እንዲህ አይነቶቹ አለመግባባቶች መፍትሔ እንዲኖራቸውና ከእኔነት ወደእኛነት የሚያመጡን የትርክት አይነቶችን ይህ ትውልድ መገንባት የሚችለው እንዴት ነው?

አየለ (ዶ/ር)፡- ይህ በጣም ጥሩ ነጥብ ነው፤ በአሁኑ ወቅት እኔ እንዳስተዋልኩት ከሆነ እየነገሰ ያለው እኔነት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ባልተገባ መንገድ የተዛባ ትርክት አምጪው በዝቷል፡፡ በአቋራጭ መንገድ የሚመጣው የተዛባ ትርክት ቶሎ ለመክበርና ሀብታም ለመሆን በሚያስቡ አካላት ነው፡፡ በእንዲህ አይነት መልኩ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ስለመኖራቸው ምንም አይነት ጥርጣሬ የለውም፡፡ ሌላው ቀርቶ ነጻ አውጪዎች ነን በሚል በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ አሠራራቸው ሁሉ የተመሠረተው ገንዘብ ላይ ነው። አሁን አሁን እንዲያውም የአንድ ነጻ አውጪ አባል ለመሆን ገንዘብ እስከመክፈል የተደረሰበት ሁኔታ እንዳለም በመነገር ላይ ነው፡፡

መገንዘብ ያለብን አንድ ነገር ቢኖር ብዝሃነት መመሪያችን እስከሆነ ድረስ ያ ብዝሃነት ሁላችንንም ሊያግባባን ይችላል፡፡ ብሎም የዴሞክራሲ ሥርዓትንም ሊያመጣ ይችላል፡፡ ስለራሳችን ስናስብ ስለጎረቤቶቻችን እና ከእኛ ቋንቋ ውጭ ስለሚናገሩትም ሆነ ከእኛ ኃይማኖት ውጭ ስለሚከተሉት አማኞች ወገኖቻችን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ያንን ሳናደርግ ስንቀር ግጭት ይመጣል፡፡

የግጭት መንስዔ እንዳይኖር ማድረግ ተገቢ ነው። መቼም ቢሆ ኢትዮጵያ ውስጥ ‹‹ያለሁት እኔ ነኝ፤ ከእኔ በቀር ኢትዮጵያን ሊገዛት የሚችል ብሔር የለም›› ብሎ ማሰብ በጭራሽ የማያስኬድ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ ይህን ተረድተን ኢትዮጵያ የሁላችን ሀገር እንደመሆኗ እንዴት አድርገን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ልንጠቀም እንችላለን? እንዴት ለሁላችንም የሚበጅ አስተዳደር ልንፈጥር እንችላለን? በሚል መንፈስ እስካተንቀሳቀስን ድረስ ግጭቶቹ ይቀጥላሉ፡፡

አዲስ ዘመን፡- የጋራ ትርክት በአግባቡ ይገነባ ዘንድ የፖለቲከኛው ሚና ምን መሆን አለበት ይላሉ?

አየለ (ዶ/ር)፡- የፖለቲከኛው ዋና ኃላፊነት መሆን አለበት ብዬ የማምነው ሰፋ ያለ አመለካከት እንዲኖረው ነው፡፡ ነገሮችን በሚያይበት ጊዜ ሰፋ አድርጎ ለማየት መሞከር አለበት፡፡ ከጠባብ አስተሳሰብ ራሱን ማራቅም ይጠበቅበታል፡፡

አንድ ፖለቲከኛ ወደፖለቲካው የመቀላቀሉ ምስጢር ሀብት ለማካበት ከሆነ በፖለቲከኛው ዘንድ የሚሰበከው ሥርዓትና አሠራሩም ሁሌም ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ለማጋጨት ይሆናል፡፡ ይህ አመለካከት የሚመጣው ደግሞ ጠባብ አስተሳሰብ ካለው ፖለቲከኛ ነውና በዚህ ላይ በመሥራት አመለካከትን ማሻሻል የሚጠይቅ ይሆናል፡፡

ጠባብ በሆነ መንገድ ሁኔታዎችን ሁሉ የሚተረጉም ፖለቲከኛ ሀገርን ወደባሰ ችግር ውስጥ ይጨምራል እንጂ ለሰላምም ሆነ ለእድገት የሚሆን መፍትሔ ሊያመጣ አይችልም፡፡ ፖለቲከኛው አስተሳሰቡ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ሰፋ ያለ መሆን ይጠበቅበታል። የሕዝብን ፍላጎት ለመጠበቅ የሚችልም መሆን አለበት፡፡

በእርግጥ የሕዝብን ፍላጎት በተቻላቸው ሁሉ ለማስጠበቅና የሕዝብን መብት ለማረጋገጥ የሚጥሩ ፖለቲከኞች መኖራቸው የሚካድ አይደለም፡፡ እነርሱን ማበረታታት እና አቅም በፈቀደ ሁሉ ከእነርሱ ጋር መሥራት ይጠበቅብናል ባይ ነኝ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያን ወደሰላሙ ጎዳና ሊያሻግራት የሚችል ዐቢይ ትርክት ምን መሆን አለበት ይላሉ? በአሁኑ ወቅት አብሮነትን ለማጽናት አስፈላጊው ምንድን ነው?

አየለ (ዶ/ር)፡- እኛ ኢትዮጵያውያን በጣም ሰፊ የሆነ ታሪክ ያለን ሕዝብ ነን፡፡ በዛ ታሪክ ውስጥ አንድ ሁልጊዜ መሠረታዊ የሆነው ነገር ቢኖር ነጻነታችንን አስከብረን ከትውልድ ትውልድ እየተሸጋገርን ዛሬ ላይ መድረሳችን ነው። ከዚህ የተነሳ ነጻ ሕዝብ መሆን መቻላችን አንድ ራሱን የቻለ ጉዳይ ነው፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን ከጊዜ ወደጊዜ ለአንድነታችን መሠረት እየሆኑን የመጡ ትልልቅ ድልድዮች አሉን። እነዚህም ከአንድ ብሔርም ኃይማኖትም በላይ ሊያሳትፉ የሚችሉ ተግባራትንም ማከናወን የቻልንና የምንችል ሕዝብ ነን፡፡ እንደእነርሱ አይነት ትልልቅ የአንድነት ድልድይ ናቸው የሚባሉ ተግባራትን ለመፈጸም በሚደረገው ሒደት አብሮነት በጽኑ ገመድ መታሰር ይጀምራል፡፡ ሕዝብ ደግሞ የበለጠ የመተዋወቅ እድልም እንዲኖረው ያደርጋል፡፡ አካል ለአካል ተቀራርቦ ለመሥራት መነሳሳቱ አንዱ ከሌላው የሚማረውና የሚረዳውም ነገር እንዲኖር ያስችላል፡፡

ለአብነት ግልጽ የሆነ ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ሥራ ለመሥራት የተሰባሰበው ሰራተኛ ከመላ ኢትዮጵያ ሲሆን፣ የተውጣጣውም ከተለያየ ብሔር እና ኃይማኖት ነው። ይህ ሠራተኛ በሥፍራው እያሳለፈ ያለው ጊዜ ረዘም ያለ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አንዱ የሌላውን ማንነት የማወቅ እድሉ ሰፊ ነው። መተዋወቅ ሲኖር ደግሞ መከባበር አብሮ ይመጣል፡፡ መደጋገፍም ይከተላል፡፡

ይህን መሠረት አድርገን እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አይነት አስርና አስራ አምስት ሥራ መሥራት ቢቻል እና በዚህ መልኩ ከሁሉም ኢትዮጵያውያን የተውጣጣ ሠራተኛ በሥራው ቦታ ቢሰማራ ሥራዎቹ ራሳቸው የሚያስተሳስሩን ይሆናሉ። በመካከላችን ያለውን አለመግባባትም ለማስወገድ መፍትሔ ይሆናሉ። ትልልቅ ሥራ በሕዝብ መካከል ያለውን መገፋፋት አርቆ ለአንድነት ድልድይ የሚፈጥር ይሆናል፡፡ እንዲህ አይነቱ ሥራ እንዲሠራ በተለይ በአመራር ደረጃ ያሉ ሕዝቡን ቢያበረታቱ መልካም ነው እላለሁ፡፡ ምክንያቱም እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያለ ሥራ ዐቢይ ትርክት እንደመሆኑ ሕዝብን በሀገሩ ጉዳይ በአንድነት እንዲቆም ማድረግ የቻለ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- የሁልጊዜ ተባባሪያችን ረዳት ፕሮፌሰር አየለ ለሰጡን ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

አየለ (ዶ/ር)፡– እኔም አመሰግናለሁ፡፡

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኀሣሥ 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You