የአልባሳት አምራቾቹ ፈተና- የግብዓት እጥረት

 የሀገራችን የአልባሳት ዘርፍ መነቃቃት እየታየበት ነው፤ በተለይ የባህል አልባሳት እና የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ምርቶች በስፋት እየተመረቱ ለገበያ እየቀረቡ ናቸው፤ በሀገር ውስጥ በሀገር ባህል አልባሳት አጠቃቀም ላይ የአመለካከት ለውጥ መምጣቱን ይጠቁማሉ፡፡ የአልባሳቱ ለተለያዩ አገልገሎቶች ተፈላጊ እየሆኑ መምጣት የምርቶቹን የሀገር ውስጥ ተፈላጊነት እየጨመረ መሆኑን እንደሚያመለክትም በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ይገልጸሉ፡፡

በዘርፉ የተሰማሩ ዲዛይነሮችና ባለሙያዎችም ዘመኑን በሚመጥን መልኩ የተዋቡና ያማሩ አልባሳት እየሠሩ የተጠቃሚውን ፍላጎት ለማሟላት ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። የባህል አልባሳትን በተለያየ መልክ እና ዲዛይን በማዘጋጀት ለበዓላት ወቅት፣ ለሰርግ እና ለተለያዩ ፕሮግራሞች የሚሆኑ ልብሶችን እያዘጋጁ ለገበያ እያቀረቡ ይገኛሉ። በሰርግ፣ በሃይማኖታዊ በዓላት፣ ወዘተ. ወቅቶች የባህል አልባሳት በስፋት ተለብሰው የሚታዩበት ሁኔታም አልባሳቱ በተለያዩ ዲዛይኖች በስፋት እየተመረቱ ለገበያ እንደሚቀርቡ ያስገነዝባል፡፡

እነዚህ አልባሳት ከሀገር አልፈው በዓለም ጭምር እየታወቁ መምጣታቸውንም አምራቾቹና ዲዛይነሮቹ ይገልጻሉ፡፡ በኦንላይን፣ በፖስታቤትና በተለያዩ የዲጂታል አማራጮችና በመሳሰሉት በኩል ምርቶቻቸውን በውጭ ሀገሮች ለሚገኙ ደንበኞቻቸው ተደራሽ እያደረጉ መሆናቸውን እንዳንድ አምራቾችና ዲዛይነሮች ይጠቅሳሉ።

ቀደም ሲል እናቶች እና ጥቂት በሸማ ሥራ የተሠማሩ አካላት ብቻ ይሳተፉበት የነበረ ይህ ዘርፍ ዛሬ በርካቶች የሚሠማሩበት መሆን ችሏል፤ ይህም አልባሳቱ በስፋትና እንደሚመረቱና ተፈላጊነታቸው እየጨመረ እንደመጣ ይጠቁማል፡፡

አሁን የሀገራችን የባህል አልባሳት አምራቾች ችግር እየሆነ የመጣው የገበያ ችግር እንዳልሆነም ባለሙያዎቹ ሲገልጹ ይሰማል፤ ባለሙያዎቹ ችግሩ ለአልባሳት ምርቱ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ማግኘት አለመቻል ወይም እጥረት  ነው፡፡ የባህል አልባሳት በዲዛይን አቅርቦት ደረጃም ይሁን በፍላጎት በጥሩ ሁኔታ እየተዋወቁ መሆናቸውን በአልባሳት ማምረት ሥራው የተሠማሩ ባለሙያዎች ጠቅሰው፣ የባህል ልብሶቹን ለመሥራት የሚጠቀሙባቸው አንዳንድ ግብዓቶች ላይ እጥረት እንዳለ ይጠቁማሉ፡፡

ዲዛይነር እጅጋየሁ ኃይለጊዮርጊስ በሙያው ላይ ከ30 ዓመት በላይ ልምድ አላት፤ ‹‹እጅግ ጥበብ›› የተሰኘ ድርጅት አቋቁማ የተለያዩ የባህል አልባሳትን ትሠራለች፡፡ በዘርፉ በገበያው እና በተጠቃሚዎች ዘንድ ጥሩ ፍላጎት እንዳለ የምትናገረው እጅጋየሁ፤ የባህል አልባሳትን ለመሥራት የሚውሉ የአንዳንድ ግብዓት እጥረት መኖሩ ለገበያ የሚቀርቡ የባህል አልባሳት ዋጋ የማይቀመስ እንዲሆን እያደረገ መሆኑን አመልክታለች፡፡

እሷ እንደምትለው፤ በዘርፉ የጥሬ እቃ ግብዓት እጥረት ያለ ሲሆን፣ ቁልፍ ፣ ክር ፣ ዚፕ እና ላስቲክ ፣ የልብስ ገበር በሽመናው ወቅት ደግሞ ድርና ማግ የመሳሰሉት ግብዓቶች እጥረትና ችግር በስፋት ይታያል፡፡ እነዚህን ምርቶች በሀገር ውስጥ የሚያመርቱ አምራቾች ዲዛነሮቹ በሚፈልጉት አይነትና መጠን ምርቶቹን አለመያዛቸው፣ አንዳንድ አምራቾች ደግሞ ለገበያ በሚያቀርቡበት ወቅት የሚያስቀምጡት የመጠን ገደብ እና አይነት ውስን መሆን ከሀገር ውስጥ እንዳይገዙ እንዳደረጋቸው ዲዛይነሯ ገልጻለች፡፡

ባለሙያዎቹ ከዚህ ቀደም እነዚህን መሰል ግብዓቶች ከቻይና፣ ከህንድ እና ከቱርክ ያስመጡ እንደነበር አስታውሳ፣ በአሁኑ ሰዓት በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ባለሙያዎቹ ግብዓቶቹን ማምጣት አልቻሉም በማለት አመልክታለች። ከውጭ ከሚያመጡ ነጋዴዎች መግዛት ዋጋቸው በጣም ከባድ መሆኑን አንስታለች፡፡

ዘርፉ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ይቻል ዘንድም ከውጭ ሀገር ምርቶች በሚገቡበት ወቅት አምጪዎች ላይ የሚጣለው ታክስ ማስተካከያ እንዲደረግበትም ዲዛይነሯ ጠይቃለች፡፡ ግብዓቶቹን በሀገር ውስጥ በስፋት ማምረት የሚቻልበት ሁኔታ መፈጠር እንዳለበትም ጠቁማለች፤ እነዚህን ግብዓቶች የሚያመርቱ የሀገር ውስጥ አምራቾች በቀጥታ ከባለሙያዎች፣ የባህል ልብስ ዲዛይነሮች ጋር የሚገናኙበት እድል እንዲፈጠርም የመፍትሄ ሃሳብም ዲዛይነር እጅጋየሁ ጠቁማለች፡፡

 የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ኢንቨስትመንት ፕሮሞሽንና የገበያ ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ስዩም ውጁራ፤ በገበያው ላይ የሚታየው የግብዓት እጥረት በሁለት መንገድ እንደሚከሰት ይገልጸሉ፡፡ በሀገር ውስጥ በፋብሪካ ውስጥ የሚመረቱ የጨርቃጨርቅ ምርቶች ላይ እጥረቱ መኖሩን ጠቅሰው፣ ከዚያም ባለፈ ባለሙያዎች ከውጭ የሚያስገቧቸው ምርቶች ወደ ሀገር ውስጥ በበቂ ሁኔታ እንዲገቡ አልተደረገም ሲሉም ገልጸዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ እነዚህን በጨርቃጨርቅ አልባሳት ላይ ያሉ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች ከውጭ የማስገባት ሥራን የሚሠሩት ጥቂት ናቸው፡፡ ምርቶቹ ወደ ሀገር ውስጥ ከገቡ በኋላ አላስፈላጊ ክምችት ተደርጎባቸው በውድ ዋጋ ለገበያ የሚቀርቡበት ሁኔታም አለ፤ በዚህ ጊዜም በነጋዴዎች እና ምርቶቹን በሚፈልጉት ባለሙያዎች መካከል የሚገባ ደላላ እጥረቱ እንዲፈጠር አንዱ መንስኤ እየሆነ ነው። በኢንተርፕራይዞች በኩልም ይህንን ችግር ለመቅረፍ በጥምረት ተጠናክሮ መሥራት ላይ የዝግጁነት ማነስ ይስተዋላል፡፡

ተቋሙ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ባለሙያዎችን በማቀናጀት በሀገር ውስጥ የሚመረቱና እጥረት የሚታይባቸውን ግብዓቶች በቀጥታ ከፋብሪካዎች የሚያገኙበትን መንገድ ለመፍጠር እንደሚሠራ ገልጸው፣ ከውጭ የሚመጡትን ደግሞ በበቂ ሁኔታ ከውጭ የሚመጡበትን መንገድ ለመፍጠር እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

 ከዚህም በተጨማሪ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን የሚያቀርበው የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት እነዚህን ግብዓቶች ለባለሙያዎች ለማቅረብ እየሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ በቅርቡም አዲስ ፕሮጀክት ቀርጾ በዘርፉ ተሰማርተው ለሚሠሩ እና እጥረት አለብን ብለው ላመለከቱ ባለሙያዎች ግብዓቶቹን ከውጭ የሚያመጡበትን መንገድ ለማመቻቸት ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለዚህም ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ የ25 ሚሊዮን ዶላር ብድር መመቻቸቱን ጠቅሰው፣ ተቋማቱ የሚፈልጓቸውን ግብዓቶች ከውጭ የሚያመጡበትን መንገድ እያመቻቸ ይገኛል ብለዋል፡፡  ይህ ተግባር ቀጣይነት ያለው ስለመሆኑም ነው ሥራ አስፈጻሚው ያረጋገጡት፡፡

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኀሣሥ 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You