የአጥብቆ ጠያቂዎች ነገር…

ከቀናት በአንዱ ነው፡፡ ከጓደኛዬ ጋር ለቅሶ ቤት ተገኝተናል፡፡ ገና ወደ ድንኳኑ ስንገባ እጄን ጎተት አደረገችኝ፡፡ ለካ የምናውቃትን አንዲት ሴት በቅርብ ርቀት ተመልክታት ወደ እርሷ እንዳንሄድ ለመከልከል ኖሯል፡፡ ምነው? የሚለውን ጥያቄ ገና ከማስከተሌ፤ በድንኳኑ ፊት ለፊት ባየችው ክፍት ወንበር ላይ በፍጥነት ተቀመጠች፡፡ እኔም እንድቀመጥ ጋበዘችኝ፡፡ የማይመች ቦታ ስለሆነ ደጋግሜ ‹‹ለምን እዚህ ጋር ?›› ስል ጠየቋት፡፡ ‹‹እኔ ከሷ ጋር መቀመጥ አልፈልግም፣ በጥያቄ ታሰለቸኛለች›› የሚል ምላሽ ሰጠችኝ፡፡

በአንድ ሰው ምክንያት ምቾት ማጣትን የደረሰበት ያውቀዋል፡፡

የማሕበራዊ ሕይወት አንዱ ከአንዱ እንዲነጋገር መንገድ ከፋች ነው፡፡ ማሕበራዊ ሕይወቱ የሚጀመረው ከሥራ ቦታ ወይም ከመኖሪያ አካባቢ ሊሆን ይችላል። ሰዎች ስለሰዎች የሚያውቁት አንድም ሌሎች ከሚነግሯቸው ተነስተው፤ አልያም ጥያቄዎችን በመጠየቅ ሊሆን ይችላል፡፡

አንዳንዶች በአንድ አጋጣሚ ያገኙትን ሰው በጥያቄ ማጣደፍ ልማዳቸው ነው፡፡ በጥያቄ የሚያሰለቹ ሰዎችን ገና እንዳገኙን አገባህ? ወለድክ? ደገምክ? ምን ሆነህ ነው ያረጀኸው? ሚስትህ ምንድ ነው የምትሠራው? ልጅህን ትምህርት ቤት አስገባሃት? ሲሉ ያዋክባሉ። ድንገት ተጠያቂው ሚስቴ ‹‹ሥራ የላትም›› የሚል ምላሽ ከሰጠ ደግሞ እንዴት በዚህ ጊዜ ቤት ትሆናለች? በማለት የሰውን ቤት ጓዳ ጎድጓዳ ሚስጥር ለማወቅ የማይፈነቅሉት የለም፡፡

 ችግሩ እንዲህ አይነት ሠዎች ችግራቸው ቢነገራቸው ለመለወጥ በጣም ቀርፋፎች መሆናቸው ነው፡፡ ምክንያቱም ስለሰው እንጂ ራሳቸው ለመስማት ፍላጎቱም፣ ወኔውም የላቸውምና ፡፡

እነርሱ ስለ ሰው ሲወራ በጣም ሰፊ ገለጻ በመስጠት የሠዎችን ትኩረት በቀላሉ መሳብ ይችላሉ። ነገር ግን ምን ያህል የሌሎችን ግላዊ ነጻነት እየገፈፉ ስለመሆናቸው ፈጽሞ ማሰብ አይፈልጉም፡፡ ወይም ነገሬ ነው አይሉትም። አንዳንዶቹ ደግሞ ለወሬ ፍጆታ እንኳን ባያውሉት ለምን እንደሆነ ሳይገባቸው አሰልቺ ጥያቄዎችን ከመጠየቅ አይቦዝኑም፡፡

ብዙ ሰዎች የሚዘነጉት ነገር ቢኖር የሚጠየቁ እና የማይጠየቁ ጥያቄዎች መኖራቸውን ነው፡፡ ሁሌም ቢሆን ሰዎች በፈቃደኝነትና እንደ ሁኔታዎች አስገዳጅነት ስለራሳቸው ቢናገሩ መልካም ነው፡፡ አንዳንዶች የማያገባቸውን በመጠየቅ ስለሚያሰለቹ ብዙ ሰዎች ከእነርሱ መሆንን አይፈልጉም፡፡ በአስገዳጅ ሁኔታ ከነዛ ሰዎች ጋር ቢገጣጠሙ እንኳን ውሏቸው በጭንቀት የተረበሸ አድርገው ይቆጥሩታል፡፡

እነዚህ ሰዎች ጥያቄ በመጠየቅ ብቻ አወቅን ያሉትን ሁሉም እንዲያውቀው ከሁሉም ቤተኛ ይመስሉ እንጂ አይደሉም፡፡ እንደውም በተቃራኒው በብዙ ሰዎች ዘንድ ይሸሻሉ፡፡ ጠይቀው ያወቁትን ሁሉም እንዲያውቀው ስለሚያጋሩም በሰዎች ዘንድ ክብር አይሰጣቸውም፡፡ ሁሌም እንደ ምስጢር አባካኝ ይቆጠራሉ፡፡

አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ጥያቄያቸው ከንጽጽር ጋር ይያዛል፡፡ የራሳቸውን ነገር ከሌላው ጋር አወዳድሮ ለማሳነስም ይሁን ለማግዘፍ ይጠቀሙበታል፡፡ ለምሳሌ ‹‹ልጅሽ ስንት ወሩ ነው? ወይም ስንት አመቷ ነው? ሲሉ ይጠይቁና መልሱን ተከትሎ እንዲህ

ያደርጋል ? እንዲህ ይሞክራል? ሲሉ ይቀጥላሉ። ‹‹የእኔ ግን እንዲህ ማድረግ ይችላል፡፡ ‹‹ያንቺስ እንዲህ ትሆናለች? እንዴ እንዲህማ ካላደረገች በጣም ዘግይታለች›› ይላሉ፡፡ ያስከትሉናም ለምን ወደ ህከምና አትወስጃትም እያሉ ሰው ያላሰበውን እንዲያስብ በማድረግ ጭንቀት ውስጥ እንዲገባ ያስገድዳሉ፡፡

ምናልባትም ይህ ምሳሌ በልጅ ሆነ እንጂ ራሳቸውን ከእኛ ጋር በማነጻጸር ጥርጣሬ ላይ እንድንወድቅ ያደርጉናል፡፡ ታዲያ እንደነዚህ አይነት ሰዎች በድርጊታቸው ምንም ይሉኝታ አያውቁም። እንዲህ አይነቶቹ ጠያቂዎች በማያልቀው ጥያቄያቸው እያታከቱ ሰዎች የረሱትን ሕይወት ዳግም በመቀስቀስ ወደ ኀዘን እና ድባቴ ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋሉ፡፡ የትምህርት ቤት ጓደኛችን ለአባቷ ያላት ፍቅር በጣም የተለየ ነበር፡፡ አባቷ በድንገተኛ አደጋ ነበር ያለፉት፡፡ ኀዘን በጣም ጎድቷታል፡፡ ታዲያ ይህች ጓደኛችን ወደቀደመው ማንነቷ ለመመለስ ብዙ ጊዜ ፈጅቶባታል፡፡ በወቅቱ እኛ እንዳይሰማት በማሰብ ተሳስተን እንኳን ስለራሳችን አባት አናወራም፡፡

በአንድ አጋጣሚ ግን ፈጠን ያለች ጓደኛ ተዋወቅን። በቃ! የማትጠይቀው፣ የማታነሳው ጉዳይ የለም። ስለራሷ አባት እስኪበቃን እና እስኪሰለቸን ነገረችን። ቀጥላ ደግሞ ጥያቄዋን ጀመረች። እንደፈራነው ትኩረቷ ጓደኛችን ላይ አረፈ፡፡ ‹‹አባትሽ ምንድነው የሚሠራው?›› ልጅቷ የምትሆነው ጠፋት፡፡ ፈጣኗ ጓደኛችንም ‹‹ኦው በሕይወት የለም? ይቅርታ ›› የሚል አጭር ምላሽ ሰጠች፡፡ አዎ እንዲህ ያሉ ሰዎች የማይነካ ጉዳይ በመነካካት፤ የተዳፈነው እሳት ከቆሰቆሱ በኋላ ምላሻቸው ከንፈር መምጠጥ ይሆናል፡፡ ምን ዋጋ አለው ከንፈር መምጠጥ? ምን  ዋጋ አለው ልብን ካደሙ ካቆሰሉ በኋላ ‹‹በጣም አዝናለሁ፡፡›› ብሎ ምላሸ መስጠት ?

ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ በአንድ አጋጣሚ ራዲዮ እየሰማሁ ፕሮግራም አዘጋጆቹ ርዕሰ ጉዳያቸው ሰዎች ስለሰዎች ካላወሩ የሰዎች ንግግር ውስንነት ያጋጥመዋል የሚል አይነት ሆነ፡፡ አንደኛው ጋዜጠኛ እንዲህ አለ። ‹‹በእኛ ቤት ውስጥ አንድ ሙከራ ሞከርን፣ እርሱም ማንም ሰው ‹‹ስለ ሰው›› እንዳያወራ ነበር፡፡›› ይህን ከመነጋገራቸው በፊት ግን ቤታቸው በጨዋታ ሲደምቅ፣ ሲሞቅ ቆይቷል፡፡

ከደቂቃዎች በኋላ ያጋጠመው ግን ተቃራኒ ነበር፡፡ ሁሉም ለረዥም ጊዜ በዝምታ ተዋጡ፡፡ ቆይተው ጉዳዩን ሲረዱ ለካ በቤታቸው በአብዛኛው የሚያወሩት ስለ ሰዎች ነበር፡፡ ይህ በጥሩም ይሁን በመጥፎ ሊሆን ይችላል፡፡ ወሬዎቹ የሚደምቁት ደግሞ ከንግግር ልውውጥ በዘለለ በጥያቄ ጭምር ታጅቦ ነው።

በእርግጥ ለሁሉም ነገር ልክ እና ቦታ አለው። ‹‹ካለመጠየቅ ደጃዝማችነት ይቀራል›› የሚባለው አባባል ያለቦታው ሲውል ትርጉም አልባ ይሆናል፡፡ ሰዎች አይነኬ የሚሉት የራሳቸው ነገር ይኖራቸዋል። እንዲህ ማድረግ መብታቸው ነው፡፡ እንደውም አንዳንዶቹ በእንዲህ አይነቶቹ ሰዎች የተነሳ ሰው መቅረብ አይፈልጉም፡፡ በራሳቸው ዓለም ብቻ እንዲኖሩና ሽሽትን እንዲመርጡ ያስገድዳቸዋል። እናም ሰው መንገር ሲፈልግ ይናገር። ብዙ ሰው ማስታወስ የማይፈልገው የኋላው እና የቅርብ ታሪክ አለው፡፡ ጥያቄን ለትክክለኛ ጠያቂዎች እንተውላቸው። ዝም ብሎ ከመጠየቅ ‹‹የምጠይቀው ጥያቄ ተገቢ ነው?›› ሲሉ ማሰብ ምን ይከብዳል?

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኀሣሥ 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You