ከቦራ ጣቢያ እስከ ሀንጋሪ ቡዳፔስት

 አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ ትባላለች በ2023 በዳይመንድ ሊግ የአምስት ሺህ ሜትር የዓለም ክብረወሰን ይዛለች። በ2022 በኦሪገን በአምስት ሺህ ሜትር የዓለም ሻምፒዮን ሆናለች። በ2023 በቡዳፔስት በተካሄደው ውድድር በ10ሺህ ሜትር ወርቅ ለሀገሯ አምጥታለች። ሁለት ጊዜ የዓለም በቤት ውስጥ ሩጫ ሻምፒዮን ስትሆን በ1ሺ 500 ሜትር የራሷን ክብረወሰን ይዛለች። ሀገሯን ወክላ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ መሳተፍ የጀመረችው ከ16 ዓመቷ ጀምሮ ነው። የዓመቱ ምርጥ ሴት አትሌት 11 ዝርዝር ውስጥ እንዲሁ ገብታለች። በግሏ ባደረገቻቸው ውድድሮችም የራሷን ምርጥ ሰዓት በማስመዝገብ በአሁን ሰዓት በአትሌቲክሱ ከሚነሱ ምርጥ ሴት አትሌቶች በቅድሚያ ትጠቀሳለች። በዛሬው የሕይወት ገጽታ ዓምዳችን ስለ ሕይወቷ በሥራዋ ስለሚገጥሟት ፈተናዎች፣ ስለስኬቶቿ ጥንካሬዋና የሕይወት ልምዷን አጋርታናለች።

ትውልድና እድገት

ለቤተሰቦቿ የመጨረሻ ልጅ ናት የስሟ ትርጓሜም ጉዳፍ ማለት የእግዚአብሔር ስጦታ እንደማለት ነው። የተወለደችው በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በትግራይ ክልል ቦራ ጣቢያ በምትባል ቀበሌ ውስጥ ነው። አንድ እህትና ሁለት ታላላቅ ወንድሞች አሏት። ወደ ስፖርቱ የገባቸው ገና በልጅነቷ በመሆኑ በዚያን ወቅት አቅሟን ተረድተው ለዓለም አቀፍ ውድድር እድል ብታገኝም ተሳታፊ ለመሆን ግን አንድ ዓመት እድሜዋን መጨመር ነበረባት። የስፖርት መግለጫዋ 26 ዓመቷ ነው ሲል እሷ ደግሞ እድሜዋን ጨምራ ለውድድር የተሳተፈችበትን አጋጣሚ በማስታወስ 25 ዓመቷ እንደሆነ ትናገራለች።

አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማረችበት ቦራ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከቤቷ ብዙም አይርቅም ነገር ግን በባዶ እግሯ ብዙ ጊዜ ትምህርት ቤት ተመላልሳለች፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ለመማር ግን ከተወለደችበት አካባቢ ርቃ መሄድ ይጠበቅባት ነበር። ምክንያቱም የትውልድ ቀዬዋ ትንሽዬ ገጠር በመሆኗ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አልነበረም።

በልጅነት የትምህርት ቤት ቆይታ ውስጥ በተለያዩ የትምህርት ክፍለ ጊዜዎች በክፍል ውስጥ ተማሪዎች በሚኖራቸው እንቅስቃሴ መምህራን ተመልክተው ምን ላይ ይበልጥ ጎበዝ እንደሆኑ፣ አቅማቸው ምን ላይ እንደሆነ ይተነብያሉ እናም ወደፊት ምን ሙያ ላይ ቢሰማሩ ይሻላል የሚለውን ለተማሪዎቻቸው ይናገራሉ። አለፍ ሲል ደግሞ ወላጆች በችሎታቸው ላይ ተጨማሪ እገዛ እንዲያደርጉላቸው ምክር ይሰጣሉ። ጉዳፍም በትምህርት ቤት ቆይታዋ መምህራን አትሌት የመሆን ተስፋ እንዳላት አስቀድመው ገምተው ነበር። ‹‹መሆን ያለብሽ፤ አትሌት ነው›› ይሏት እንደነበርም ታስታውሳለች። ከልጅነቷ ጀምሮም ለስፖርትና ለአትሌቲክስ ፍቅር የነበራት ጉዳፍ በቦራ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የነበራትን ቆይታ ስትጨርስ ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ወደ መቐለ ከተማ አመራች።

የአትሌቲክስ ሕይወት ጅማሮ

‹‹እውነት ለመናገር በስፖርት እዚህ እደርሳለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም። ለስፖርት ፍቅር ቢኖረኝም እዚህ ደረጃ ደርሼ በዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ መንደር ታዋቂ እሆናለሁ፣ ከድህነት እወጣለሁ፣ ሀገሬን አስጠራለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር›› የምትለው ጉዳፍ በመቐለ ከተማ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ሳለች ለመጀመሪያ ጊዜ ከ 16 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎችን ወደ ውድድር የሚያስገባ እድል አገኘች። በዚህም ከሌሎች ሁለት መሰሎቿ ጋር በመሆን መስፍን ኢንደስትሪያል ኢንጅነሪንግ ውስጥ የአትሌቲክስ ሕይወትን አንድ ብላ ጀመረች።

ለስምንት ወራት ያህል በቆየችበት ጊዜም በምትቀርብባቸው እያንዳንዱ ውድድሮች ላይ የአንደኝነት ደረጃ ይዛ ነበር የምታጠናቅቀው። ከዚያ ብዙም ሳትቆይ ወደ አዲስ አበባ መጣች። አዲስ አበባ የስፖርት ሕይወትን ሙለ ለሙሉ ሥራዋ ያደረገችበትና ብዙ ስፖርታዊ እውቀቶችን የቀሰመችበት ስለመሆኑ ትናገራለች። ወላጆቿ በልጅነቷ ከነሱ ተነጥላ መሄዷን ባይደግፉትም እሷ ግን ለመሄድ ወስና ነበር። መምህር የሆነው ታላቅ ወንድሟም የወደፊቱ ስኬቷ ታይቶት ነበርና ሃሳቧን የሚደግፍ ሆኖ ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት ቻለች።

ወደ አዲስ አበባ ስትመጣም የተቀላቀለችው ክለብ የሱር ኮንስትራክሽን ሲሆን የአትሌቲክስ ሕይወቷ የሚጀምረው ጉዳፍ አሁን የደረሰችበት እና የተጓዘችበት ብዙ በመሆኑ ያለፈውን ለማስታወስ ጥቂት አሰብ ታደርጋለች። በሱር ኮንስትራክሽን ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የአትሌቲክስ ውድድር ያደረገችው ሁለት ሺህ ሜትር ሲሆን የሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቀቀች። ከዚያም በተለያዩ ውድድሮች፣ ፕሮጀክቶች ላይ ተሳተፈች። የሱር ኮንስትራክሽንን ከለቀቀች በኋላም እ.ኤ.አ በ2021 የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ላይ በአምስት ሺህ ሜትር በመወዳደር የኢትዮጵያን ክብረ ወሰን ሰብራለች።

ዓለም አቀፍ ውድድሮች

በሀገር ውስጥ ውድድሮች የበረታው ጉልበቷ ስለ ስፖርት ያላት ግንዛቤ ለአትሌቲክስ ሙያ ያላት ፍቅር እየጨመረ ከሀገር መሻገር ጀመረ። የተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮችንም መሳተፏን ቀጠለች። የመጀመሪያ ውድድሯ የነበረው በሆላንድ ሀገር ከ18 ዓመት በታች የ 1ሺ 500 ሜትር ውድድር ነበር፤ በዚህ ውድድርም ከአሸናፊነት ባሻገር ክብረወሰንን ለመስበር በቃች። በ16 ዓመቷ ኢትዮጵያን ወክላ እእአ በ2014 በዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮን በ1ሺ 500 ሜትር ተወዳደረች። በ17 ዓመቷ ደግሞ ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ውድድር ተሳትፋ የብር ሜዳሊያ ለራሷና ለሀገሯ አምጥታለች። እኤአ በ 2021 በፈረንሳይ የዓለም የቤት ውስጥ ውድድር በ1ሺ500 ሜትር ተወዳድራም አንደኛ በመውጣት አዲስ ክብረ ወሰን አስመዘገበች።

በልጅነቷ በዓለም አቀፍ መድረክ የመወዳደርን እድል ባገኘችበት በአንድ ወቅት በዱባይ አየር ማረፊያ ቀጣይ በረራዋን ስትጠብቅ የቀረው ሀምሳ ደቂቃ ነበር። ለዚያም ሰዓቱ እስከሚደርስ ጎኗን አረፍ ስታደርግ በዛው እንቅልፍ ያሸልባታል፤ ከዚያም ከእንቅልፏ የነቃችው ከበረራዋ ከ15 ደቂቃ በኋላ ነበር። አጠገቧ የነበሩትም በሙሉ ትተዋት ሄደዋል። በወቅቱ ጉዳፍ በጣም አለቀሰች፤ ነገር ግን እድል ከእርሷ ጋር ነበርና አንድ ህንዳዊ አግዟት ከውድድሩ ሳትቀር መሄድ መቻሏ የማትረሳው ገጠመኟ ነበር።

እኤአ በ2022 ኦሪገን ኦሎምፒክ 5 ሺ ሜትር ላይ አንድ ብርና አንድ ወርቅ አምጥታለች። ያም ቢሆን ግን መላው ኢትዮጵያዊ ጉዳፍ በ10 ሺህ ሜትርም ታሸንፋለች የሚል ትልቅ ግምት ሰጥቷት ነበር። እሷም እምነቷን ላለመብላት በቦታዋ ተገኝታ ጠንካራ የውድድር ጊዜን አሳልፋለች።

እኤአ በ2023 በሀንጋሪ ቡዳፔስት በተካሄደው ውድድር ጉዳፍ በ10 ሺህ ሜትር ከሌሎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ማለትም ለተሰንበት ግደይና እጅጋየሁ ታዬ ጋር በመሆን ውድድር ላይ ነበሩ። በወቅቱ ግን ጉዳፍ በኪሎ ሜትሩ ላይ የመሮጥ ብዙም ልምድ ያልነበራት ቢሆንም ቀደም ብላ በሰራቻቸው ጠንካራ ልምምዶች በቡዳፔስት የ10 ሺህ ሜትር ውድድር ላይ በመጨረሻዎቹ ሰዓት ከተፎካካሪዋ ሲፈን ሀሰን ጋር ከባድ ትንቅንቅ አደረገች፤ ሲፈን በውድድሩ ማብቂያ ላይ ስትወድቅ ጉዳፍ እግሯ ላይ ጉዳት ገጥሟት እየደማችም ቢሆን የወርቅ ሜዳልያዋን ለሀገሯና ለራሷ ስለማምጣቷ ትናገራለች። ለተሰንበት ግደይና እጅጋየሁ ታዬም ተከታትለው በመግባት ብር እና ነሐስ ለሀገራቸው አመጡ። በማለት ሁኔታውን ታስታውሳለች። በኦሪገን አምስት ሺህ ሜትር ሻምፒዮን የሆነችው ጉዳፍ በ10 ሺህ ሜትርም በ31 ደቂቃ 27 ነጥብ 18 ሴኮንድ በመግባት ወርቅ አምጥታለች። በአምስት ሺህ ሜትር ውድድር ላይ ከዚህ ቀደም በኬንያ ተይዞ የነበረውን የዓለም ክብረወሰን የራሷ አድርጋለች። በወቅቱ በሀገሩ በነበረው ሙቀት ምክንያት በገጠማት ጉዳት ለማገገም ቀናት ቢወስድባትም በውድድሩ ማሸነፏ ደግሞ ትልቅ ብርታት እንደሆናት ትናገራለች።

የአምስት ሺህ ሜትር ሪከርድ ለመስበር ህልሟ የነበረው የ1ሺ500 ሜትር በምትወዳደርበት ጊዜ ነበር። በጊዜው በነበራት ብቃት አምስት ሺህ ሜትር ላይ ብትወዳደር ሪከርዱን መስበር እንደምትችል በራሷ አምና ያ ቀን እስኪመጣ ትጠብቅ ነበር አንድ ቀን እንደምታሳካውም ታውቃለች።

በአትሌቲክስ ሕይወቷ አምስት ሺህ ሜትር ሪከርድን ይዛ ባደረገቻቸው የ10 ሺህ የአምስት ሺህ ሜትር ውድድር ሀገሯን ከማስጠራትም ባለፈ የነበራትን ዝቅተኛ ሕይወት ቀይራ እዚህ ደርሳለች። እናም በስፖርት ውስጥ ከባዱ ነገር ‹‹ጠንካራ የልምምድ ልማድን ማዳበርን አሰልጣኝ የሚያስቀምጠውን የልምምድ ፕሮግራም በብቃት በመወጣት አቅምን ማሳደግ ነው ›› ስትል የከፈለችውን ዋጋ ታስታውሳለች።

የአትሌቲክስ ውድድር በራሱ አድካሚ ጉልበትን የሚፈትን በመሆኑ ጉዳፍ ‹‹በስፖርት ውስጥ በተለይ ሴት ከመሆን ጋር በተያያዘ ተስፋ መቁረጥ ቀላል ነው። ተስፋ ቆርጣለሁ ከተባለ አሁንም ማድረግ ይቻላል፤ ትልቁ ጥንካሬና ከባዱ ነገር ጠንከሮ ሰርቶ ማሳየት ነው›› ስትል ትገልጻለች። ስፖርት በየእለቱ ጠንክሮ መሥራትን ብቁ ሆኖ መገኘትን ይጠይቃል፤ ይህም ሆኖ ግን ላይሳካ ይችላል፤ ስለዚህ ሽንፈትን ለሌላ ሥራ እንደመዘጋጃ አድርጎ መውሰድ ያስፈልጋል ‹‹ስሸነፍም ሳሸንፍም ትምህርት እወስዳለሁ። ጠንካራ በመሆኔ ለዚህ በቅቻለሁ ብዬ አስባለሁ›› በማለት ራሷን ትገልጻለች።

ጉዳፍ ከነበረችበት የሱር ኮንስትራክሽን ክለብ ከወጣች በኋላ የግል አስልጣኟ እንዲሁም ባለቤቷ ከሆነው ሕሉፍ ይህደጎ ጋር ረጅም መንገድን ተጉዘዋል። በእያንዳንዷ የውድድር ሂደቶቿ ላይም ከጎኗ አለ። በግሏ በምታደርጋቸው እንደ ዳይመንድ ሊግ የቤት ውስጥ ውድድርና ሌሎችም ውጤታማ ትሆን ዘንድ እሱም ይለፋል። ልፋቱን ሜዳ ያላስቀረችው ባለቤቱና ሰልጣኙም እነሆ እኤአ ከ2019 ጀምሮ የመሪነት ቦታውን ይዛ ቆይታለች።

ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገሯን ወክላ የተወዳደረችው እእአ በ2014 በኦሪገን ከ20 ዓመት በታች ባደረገችው ውድድር ነው። በዚህ ውድድርም የብር ሜዳሊያን አግኝታለች። በአትሌቲክስ ውስጥ አትሌቶች ማሳካት የሚፈልጉት ትልቁ ህልማቸው የዓለም ዋንጫና ኦሎምፒክን ድል ማድረግ ነው የምትለው ጉዳፍ እሷም እንደብዙዎቹ ይህ ህልም በውስጧ ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈችበት የኦሎምፒክ ውድድርም የነሐስ ሜዳሊያን አግኝታለች። አሁን እኤአ በ2024 በፓሪስ በሚካሄደው ኦሎምፒክ ውድድር ላይ የነሐስ ሜዳሊያዋን ወደ ወርቅና ክብረወሰን መስበር ደረጃ ከፍ ለማድረግም ጠንካራ ሥራ እየሰራች መሆኑን ትናገራለች።

‹‹ ለኦሎምፒክ የሚቀሩት ረጅም ወራት ናቸው የሚኖረው ልምምድ ከሌላው ጊዜ የተለየ ሊሆን ነው የሚሆነው ፤ በስፖርት ውስጥ ጉዳት፣ ህምም ሊደርስ ይችላል፣ ሆኖም ከአንድ አትሌት የሚጠበቀው ከዛሬ ነገ ራሴን ማሻሻልና በጥሩ ብቃት ላይ መገኘት አለብኝ የሚለው አስተሳሰብ ነው። ይህ ደግሞ ያለንን ብቃት በማሳደግ በራስ መተማመንን በመጨመር ወርቃማ ድል ላይ ያደርሳል›› ስትል ህልሟ ውስጥ ጠንክሮ

 መሥራት እና በአቋም መገኘት ከፈጣሪ ጋር መልካም ነገር ለመሥራት መፈለጓን ተስፋ ቆራጭ አለመሆኗን ትናገራለች።

የሷ አርአያ

ጉዳፍ ታላላቅ ከሆኑ አትሌቶች እጅግ የምትወዳት የሙያ አጋርዋ የአትሌት መሠረት ደፋር አድናቂ ናት። የአትሌት መሠረት ደፋር እልህ፣ ጥንካሬ፣ አልሸነፍ ባይነት አብዝቶ እንደሚማርካት ነው የምትገልጸው። በአትሌቲክስ ውስጥ ሁልጊዜ ማሸነፍ የለም የምትለው ጉዳፍ ሰዎች በየትኛው ዘርፍ ቢሸነፉም በድጋሚ ጠንክረው ሰርተው አቅማቸውን ማሳየት እንደሚችሉ ታምናለች። ጥንካሬና እልህ፣ የረጅም ሰዓት ልምምድ፣ በውድድር ላይ ባለው የመጨረሻዎቹ ደቂቃ ላይ በሚደረግ ትንቅንቅ ጉልበት የሚሰጥ ነገር መሆኑንም ታብራራለች።

ጉዳፍ አብዝታም አትሌት መሠረት ደፋርም ሆነች ሌሎች ታላላቆቼ የምትላቸው አትሌቶች እርስ በእርስ ያላቸው መደጋገፍና ደግነት እንደሚገዛት ትናገራለች።

በሌላ በኩልም ጉዳፍ ሳትጠግባቸው የተለየቻቸው እናቷም ለስኬቷ መሠረት መሆናቸውን ትገልጻለች። “እናቴ አትሌት እንድሆን ከመገፋፋት ባሻገር የሕይወት ውጣ ውረዶቼ ሁሉ ደጋፊ ነበረች” በማለት በሕይወት ያጣቻቸውን እናቷን ውለታ ታነሳለች። “

ኢትዮጵያን በስፖርት በተለይም በአትሌቲክስ ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንድታተወቅ ያደረጓት አትሌቶች ለረጅም ጊዜ ክብራቸውን አስጠብቀው በአሸናፊነት የመቆየታቸው ሚስጥር ጠንክረው መሥራታቸው ነው የምትለው ጉዳፍ ‹‹በአትሌቲክስ ውስጥ ታይቶ ወዲያው መጥፋት ሳይሆን ጠንክሮ በመሥራት ሀገርን ማስጠራት ከጎናችን ላሉ ሰዎች ሰርቶ መቀየር እንደሚቻል ማሳየትና ለሌሎች ትምህርት መሆን በራሱ ትልቅ ነገር ነው›› ትላለች። ጉዳፍ ታግሎ ማሸነፍን ፈጣሪዋን በሥራዋ ላይ አስቀድማ መሥራትን ባህሪዋ ያደረገች ስትሆን ደግነት መልካምነት ይነበብባታል። ከታላላቅ የኢትዮጵያ አትሌቶችም ጭምር የምትወስደውና የምትወደው ያላቸውን ደግነት፣ እርስ በእርስ መተባበራቸው ነው ‹‹ ሰው ለመርዳት ግዴታ ሌሎች ሰዎች ሊያውቁብሽ አይገባም የድሮ አትሌቶችን በሩጫቸው ብቻ ሳይሆን በቅንነታቸውም ጭምር አደንቃቸዋለሁ›› ትላለች።

ሁለት ስሜት አንድ ሁነት

በኦሪገን በነበራት ውድድር ላይ ስታሸንፍ በሀገራችን በነበረው ሁኔታ ጉዳፍ በተወለደችበት ቦራ የሚገኙ ወላጆቿ ሩጫውን እንደሌላው ኢትዮጵያውያን መከታተል አልቻሉም ነበር። በጊዜውም ጉዳፍ ድምጻቸውን ከሰማች ወራት ተቆጥረው የነበረ በመሆኑ ውድድሩን ስታሸንፍ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ ደስታ ቢሆን እሷም ከህልሞቿ ውስጥ አንዱን እና ትልቁን ብታሳካም ደስታዋ ግን ሙሉ እንዳልነበር ነው የምትናገረው። በዚህም ምክንያት በደስታ እና በሀዘን ውስጥ ነበረች። ከዚያ በኋላ በነበራት ውድድር ቤተሰቦቿ የደስታዋ ተካፋይ መሆን በመቻላቸው ደስታዋን ሙሉ እንዳደረጉላት አሁንም እየሳቀች ትናገራለች።

አትሌቶች በዓለም መድረክ ለሀገራቸው ከፍተኛ የሚባል ውጤት አምጥተው ወደሀገራቸው ሲመለሱ በጎዳናው ላይ እና በወከሉት ሕዝብ መካከል የተደረገላቸው አቀባበል ለስፖርት ያለው ወዳጅ ውጤት ባልተገኘባቸው ውድድሮች ላይ የሚያሳየው ብርታት እና ሞራል ለጉዳፍ እጅግ ልዩ ትርጉም እንዳለው ትናገራለች።

ስኬትና ውድቀት በስፖርት ዓለም

በስፖርት ውስጥ ቋሚ የሆነ የልምምድ ወቅት ራስን በአካልም በመንፈስም ለውድድር ዝግጁ ማድረግ የተለመደ ቢሆንም በዛው ልክ በልምምድም ሆነ በውድድር ሰዓት ጉዳት ሊገጥም የሚችልበት ሁኔታ ይፈጠራል የምትለው ጉዳፍ ይህ በስፖርት ውስጥ ያለ ፈተና ስለመሆኑ ትናገራለች። ‹‹በጣም በጥሩ አቋም ላይ ሆኜ እግሬ ላይ ጉዳት አጋጥሞኝ ያውቃል። ታዲያ ይህንን ጠንክሮ ማለፍ የስፖርቱ አንዱ መለኪያ ነው። በዓለም ዋንጫ 10 ሺህ ሜትር ላይ በሙቀት ምክንያት እግሬ ላይ ጉዳት አጋጥሞኝ ነበር። የአምስት ሺህ ውድድር በነበረኝ ሰዓት ደግሞ ሌላ ሰው መተካት የማይቻልበት ሰዓት ነበር። የምትለው ጉዳፍ ጓደኞቿን ለማገዝ ቢሆን ከአንድ ሳምንት ባነሰ ልምምድ ወደ ውድድሩ ገብታ ሪከርድ መስበር ችላለች። ህመም ካልገጠማት በቀር ልምምዷን አንድም ቀን የማታቋርጠው ጉዳፍ ይህ የጥንካሬዋ ውጤት ስለመሆኑ ትናገራለች።

በርካታ አትሌቶች የሚሳተፉበት የጎዳና ላይ ውድድር እና ማራቶን በስፋት የሚጠብቃት መሆኑን የምታነሳው ጉዳፍ አሁን ባለችበት ደረጃ ሌላ ውጤት ሌላ ታሪክ ለሀገሯ የመሥራት ፍላጎት እንዳላትም ትገልጻለች።

ትዳርና የሙያ አጋርነት

በአሁን ሰዓት ኢትዮጵያን ወክለው እየተወዳደሩ ከሚገኙ ሴት አትሌቶች ውስጥ ጉዳፍ ፀጋይ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት ውስጥ ነች። ሁሉም አትሌቶች በሚያደርጓቸው ልምምዶች አቅማቸውን እና ችሎታቸው ከፍ ለማድረግ በሚሰሯቸው ሥራዎች ውስጥ መንገዳቸውን የሚመሯቸው የሚያግዟቸው አብረዋቸው በቅርበት የሚሰሩ አሰልጣኞች አሏቸው። ታዲያ ይህ የሥራ ሂደትና ውጤት በጉዳፍ እና በአሰልጣኟ ሕሉፍ ይሕደጎ መካከል የአሰልጣኝና የአትሌት ጥምረት ብቻም ሳይሆን ሁለት በትዳር የተጣመሩ ጥንዶች ጭምር ነው።

ጉዳፍ ለሷ እዚህ መድረስ የባለቤቷና አሰልጣኟ ሚና በቀላሉ የሚተው አይደለም ምክንያቱም ገና ልጅ በነበረችበትና ወደ አትሌቲክሱ ለመምጣት በመስፍን ኢንደስትሪያል ውስጥ ሥራ በጀመረችበት ወቅት የተሻለ እንድትሰራ አቅሟን በመረዳት ወደ አዲስ አበባ ለመምጣቷ ምክንያት የሆነውም አሰልጣኟና ባለቤቷ አቶ ሕሉፍ ነው። ‹‹በስፖርት ውስጥ ስኬታማ ለመሆን ትልቁ ሚስጥር ጠንክሮ መሥራት መሆኑን የተማርኩት ከሱ ነው። ለኔም ብቻ ሳይሆን ለሌሎች አትሌቶች ትልቅ ደረጃ መድረስ ምክንያት ነው። ›› ስትል በአትሌቲክስ ሕይወቷ ውስጥ የትዳር አጋሯና አሰልጣኟ ያለው ድርሻ ትልቅ መሆኑን ትናገራለች። አሰልጣኝ ሕሉፍ ይሕደጎ ከስምንት ዓመታት በላይ በዚህ ሙያ የቆየ ሲሆን እንደ አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ ፣ አትሌት ብርቄ ኃየሎም ያሉ ትልልቅ አትሌቶችን ያፈራ አሰልጣኝ ነው።

የወደፊት ህልም

በአትሌክስ ተሳትፎዋ ከልጅነቷ ጀምሮ በማሸነፍ እና ከተወለደችበት ቦታ አንስቶ ብዙ ተስፋ እየተሰጣት እዚህ ደርሳለች። ወደ ውድድር ከመጣች በኋላም የኢትዮጵያውያንን ቀልብ ስባ በሥራዋ የብዙዎችን ድጋፍ አግኝታለች። በአትሌቲክስ ውስጥም ስሟን በትልቁ ማስጠራት የምትፈልግበት ታሪኳን መትከል የምትፈልግበት ብዙ ውጥኖች አሏት። በቀጣይም በሀገሯ ላይ ልጅ ሆና ትመኛቸው የነበሩትን ቢቀረፉ ብላ የምትላቸው ችግሮች የሚያስቀሩ ዘርፎች በሀገሯ ኢንቨስት አድርግ ደግሞ በዚህ ዘርፍ የወጣችበትን ሕዝብ የሞራል ብርታት የሚሆናትን ሕዝብ የመደገፍ ህልም አላት። ‹‹ጀማሪ በነበርኩበት ወቅት አንጋፋ አትሌቶች ያደርጉልኝ የነበረው ድጋፍ ውለታም ብቻ ሳይሆን ደግነትን ጭምር እንድማር አድርጎኛል›› የምትለው ጉዳፍ ጊዜው ሲደርስ ደግሞ በስፖርት ውስጥ ስኬታማ መሆን የሚፈልጉ ወጣቶችና ታዳጊዎችን መደገፍ በህልሟ ውስጥ አለ።

‹‹ ፈተና የሌለበት ሥራ የለም። ዋናው ነገር ፈተናውን አልፎ ጥንካሬን ማሳየት ነው። በሥራ ውስጥ መውደቅ ያለ ነው። ተስፋ ልቁረጥ ካልኩ አሁንም እችላለሁ ተስፋ መቁረጥ ቀላል ነው። ከባዱ ነገር ይቻላል ብሎ የራስ ጥንካሬን ማሳየት ነው። ›› ከሰዎች የሚያስደስታት ነገር የምታያቸውን ጥሩ ጎን ወደ ሕይወቷ መውሰድ ነው።

ጉዳፍ ፀጋይ በተለያየ ፈተና ውስጥ እና ልምምድ ጠንካራ ሠርታ እዚህ ስትደርስ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውስጥ የሚመለከታቸው አካላት ክልሎች ላይ ትኩረት ሰጥተው ቢሰሩበት የሚል እይታ አላት።

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ኅዳር 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You