ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን ባለፈው ሳምንት ተከብራል። ኢትዮጵያም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮንቬንሽንን ተቀብላ ተግባራዊ ለማድረግ የተስማማች ሀገር እንደመሆኗ ይህንን በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች አክብራለች። አካል ጉዳተኝነትን በተመለከተ ቀኑን ከማክበር ባሻገር ብዙ ጉዳዮች ሊነሱ ከሚገባባቸው ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ነች። አካል ጉዳተኝነትን በተመለከተ እንደ ማህበረሰብ ያለው አመለካከት የተዛባ መሆኑ ተደጋግሞ ሲነሳ የቆየ ጉዳይ በመሆኑ ለዛሬ እንደ አዲስ አላነሳውም። ለጊዜው እንደ ክፍተት ላነሳቸው ከፈለኳቸው ጉዳዮች ግን አብዛኞች የሚመነጩት ከተዛባ አመለካከት ጋር በአንድም በሌላም መልኩ ሊያያዙ ይችላሉ።
የመጀመሪያው ከአካል ጉዳተኞች የሥራ ስምሪት ጋር ይያያዛል። አካል ጉዳተኞች በየትኛውም የሥራ መስክ ላይ ተሰማርተው ውጤታማ መሆን ይችላሉ። ለዚህ ደግሞ ከሥራ ቅጥር ጀምሮ የሚያስፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ ሊሟሉላቸው ይገባል። ይህ በሥራ ቀጣሪዎች በጎ ፍቃድ ላይ የተመሰረተ ጉዳይ ሳይሆን የአካል ጉዳተኞች ሰብዓዊም ህጋዊም መብት ነው። ያም ሆኖ በኢትዮጵያ የሚስተዋለው ነገር በተቃራኒው ሆኖ እናገኘዋለን። የግልም ይሁኑ የመንግሥት ተቋማት የአካል ጉዳተኞችን የሥራ ስምሪት በተመለከተ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ረገድ ያለባቸው ክፍተት አንድና ሁለት አይደለም። ለምሳሌ ያህል አንድ አካል ጉዳተኛ በሆነ ተቋም ውስጥ ሥራ ለመቀጠር ተወዳድሮ አለፈ እንበል፣ ይህ አካል ጉዳተኛ ሥራውን ለመጀመር ወደ ተቋሙ ሲሄድ ነገሮች ለእሱ ምቹ ላይሆኑ ይችላሉ። በዚህ ምክንያት ተቋሙ አካል ጉዳተኛው ሥራውን መከወን አይችልም ወይም ይከብደዋል ብሎ ሊያሰናብተው ይችላል። ይህ አካል ጉዳተኛ ጉዳዩን ወደ ሕግ ቢወስደው በደል የፈፀመበት ተቋም ሊቀጣ የሚችለው ሁለት ሺ ብር ነው። ይህ አስገራሚ ሕግ ነው። ሕጉ ለአካል ጉዳተኞች የሥራ ስምሪት ከለላ ይሰጣል ተብሎ ነው የወጣው፣ በተግባር ሲታይ ግን ሕጉ እንዴት አካል ጉዳተኛውን እንደሚጠቅመው ያስተዛዝባል። አንድ ተቋም ለአካል ጉዳተኛው ምቹ የሥራ ሁኔታን መፍጠር ባለመቻሉና አካል ጉዳተኛውን በማሰናበቱ የሚቀጣው ሁለት ሺ ብር ከሆነ ቅጣቱን ከፍሎ መገላገል ቀላሉ መንገድ እንደሚሆንለት ብዙ ማሰብ አያስፈልግም። ስለዚህ ይህን ሕግ ቀጣሪዎች እንዴት ሊፈሩት ይችላሉ? አካል ጉዳተኞችንስ እንዴት ሊጠቅም ይችላል?።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የግንባታ ፍቃድ ሕጉም አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያላደረገ ሰፊ ክፍተት ያለበት ነው። አንድ ሕንፃ የሚገነባ አካል ሊፍት(አሳንስር) ለማስገጠም የሚገደደው ሕንፃው ከአራት ፎቅ በላይ ከሆነ ነው። ይህ ለማንኛውም ሰው ችግር ላይሆን ይችላል። አንድ አካል ጉዳተኛ ግን በዚያ ሕንፃ ላይ ሥራ ተቀጥሮ ለመሥራትም ይሁን ሌላ ጉዳዩን ለማስፈፀም አይችልም ማለት ነው።
ከአካል ጉዳተኞች የሥራ ስምሪት ጎን ለጎን ትምህርትን በተመለከተ ያሉትም ክፍተቶች ጥቂት አይደሉም። ለአብነት ያህል ትምህርት ቤቶች አካል ጉዳተኝነትን በተመለከተ የሚይዙት በጀት ከአጠቃላይ በጀታቸው ከአንድ በመቶ የዘለለ አይደለም። በዚህ በጀት ለአካል ጉዳተኞች የመማር ማስተማር ሂደቱን የሚያቀሉ መሠረተ ልማቶችንና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን እንዴት ማሟላት እንደሚቻል ለማንም ግልፅ አይደለም። በእርግጥ በዚህ ረገድ በተለይም በአዲስ አበባ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ከተለያዩ የረድኤት ተቋማት ጋር በመሥራት ለአካል ጉዳተኞች አስፈላጊ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን ለማልማት ጥረት ሲያደርጉ ይታያል። ይህን ማድረግ ያልቻሉትስ በአጠቃላይ እንደ ሀገር ያሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች?
ሌላው አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ለማድረግ ከቀረጥ ነፃ ተሽከርካሪዎች ቢፈቀድም አፈፃፀሙ ላይ ያለው ውጣ ውረድ ነው። ይህም እንደ ሌሎቹ ሕጎች አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ የታሰበ ቢሆንም ሕጉ የሚፈፀምበት ውስብስብ ሂደት አካል ጉዳተኞች እንዲጠቀሙበት ሳይሆን እንዲሸሹት የሚያደርግ መሆኑ ነው። እነዚህንና ሌሎች ያልተጠቀሱ የአካል ጉዳተኛ ሕጎች መከለስ ወይም ድጋሚ መታየት አለባቸው።
80 በመቶ የሚሆኑት የዓለማችን አካል ጉዳተኞች የሚገኙት ባላደጉት ሀገራት ውስጥ ነው። በኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ምን ያህል የህብረተሰብ ክፍል እንደሆኑ በትክክል የሚገልፁ ጥናቶችን ማግኘት ከባድ ነው። እኤአ 2007 ላይ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ቁጥር 1ነጥብ 9 በመቶ እንደነበር አንዳንድ መረጃዎች ይጠቁማሉ። የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ የ2013 መረጃ ደግሞ 2ነጥብ 5 ሚሊየን ገደማ እንደሆኑ ያስቀምጣል። የዓለም ጤና ድርጅትና የዓለም ባንክ የ2011 መረጃ ደግሞ 17.6 ሚሊየን ናቸው ይላል። በተመሳሳይ ዓመት 2011 ላይ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ቁጥር እስከ 20 ሚሊየን እንደሚደርስ የዓለም አካል ጉዳተኞች ሪፖርት ያስቀምጣል። የኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኛ መብት ተቆርቋሪ ሆነው የሚሰሩ ድርጅቶች ቁጥሩ ከዚህም ሊልቅ እንደሚችል ይገልፃሉ። በተለይም በቅርብ ዓመታት በሀገሪቱ በነበሩ ጦርነትና ግጭቶች የተጎዱ ዜጎች ቁጥር ይህን አሃዝ በእጅጉ ሊያሳድገው እንደሚችል ይገመታል።
በቁጥራዊ መረጃዎቹ ላይ አንድ መደምደሚያ ላይ መድረስ ባይቻል እንኳን አማካኙን ብቻ ከተመለከትን ቀላል አይደለም። ይህም የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ የጥቂቶች ብቻ ሳይሆን የሰፊ ማህበረሰብ ጉዳይ አድርገን እንድንመለከተው ያስገድደናል።
የአካል ጉዳተኞችን መብቶች ለማስጠበቅ እንደ ሀገር የተጠቃለለ የአካል ጉዳተኞች ሕግ ይወጣል ከተባለ ሶስት ዓመት አልፎታል። ያ ሕግ የት ደረሰ? ሚዲያዎችም ጠያቂ መሆን አለባቸው።
ማንም ሰው ነገ አካል ጉዳተኛ እንደማይሆን ምንም መተማመኛ የለውም። ስለዚህ የአካል ጉዳተኞችን መብት የማስከበር ጉዳይ ለአካል ጉዳተኛው ብቻ መተው የለበትም። ሁሉም ሰው ነግ በኔ ብሎ ለአካል ጉዳተኞች የተሻለ ነገር ለመፍጠር ያገባኛል ማለት አለበት።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ኅዳር 29 ቀን 2016 ዓ.ም