ማዕከሉ ሕፃናትን በመታደግ ሥራዎቹ በእጅጉ ይጠቀሳል። በተለይ አሳዳጊ የሌላቸውን በርካታ ሕፃናትን ተቀብሎ እንደራስ ልጅ በማሳደግ እና ራሳቸውን እንዲችሉ በማድረግ ሥራው ይታወቃል። የማዕከሉ መሥራች በእዚህ በጎ ተግባራቸው ኢትዮጵያዊቷ ማዘር ቴሬዛ ለመባል በቅተዋል። ይህ የበጎ አድራጎት ተግባር ሀገራዊ ተምሳሌት መሆን ችሏል። ይህ ዛሬ በሕይወት የሌሉት የብዙዎች እናት እና የበጎነት ጥግ የክብር ዶክተር አበበች ጎበና የበጎነት ተምሳሌት እሳቸው በሕይወት ባይኖሩም በጎ ተግባራቸው ግን ተጠናክሮ ቀጥሏል።
እኚህ ታላቅ የሀገር ባለውለታ በርካታ ሴቶች በተለያዩ ችግሮች ሳቢያ የአብራክ ክፋይ ልጆቻቸውን ወልደው ለማሳደግ የአቅም ውስንነት እየገጠማቸው እስከመጣል ሲደርሱ ይመለከታሉ፤ ይሰማሉ፤ ሕፃናት ለሞት የሚጋለጡበት ሁኔታ ስለመኖሩም ይረዳሉ። ይህ ድርጊት በእጅጉ ያሳሰባቸው እኚህ በጎ አድራጊ በበጎ አድራጎት ድርጅታቸው አያሌ ሕፃናት ታድገዋል፤ የሴቶችንና የሀገርን ሸክምም አቅልለዋል።
የሕፃናት ችግር ከሴቶች ችግርም የሚመነጭ ነው የሚል እምነት እንደነበራቸው የሚነገርላቸው እኚህ የብዙዎች እናት፣ ሴቶችን ማብቃት የሕፃናትን ችግርም መቅረፍ ነው የሚል እምነት እንደነበራቸው ይገለጻል። በዚህ ሳቢያም ሴቶችን ከተለያዩ ችግሮች ይታደጋል ያሉትን ሴቶችን የማብቃት ፕሮግራም ያስጀምራሉ። በፕሮግራሙ በርካታ ተስፋ የቆረጡ እና መንገድ ላይ የቀሩ ለከፍተኛ ችግር የተጋለጡ ሴቶችን መታደግ ተችሏል፤ ይህም የበጎ አድራጎት ተግባር ስኬታማ ሀገራዊ ፕሮግራም እየሆነ መምጣቱን ከበጎ አድራጎት/ ቻሪቲ/ ማዕከሉ የተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የአበበች ጎበና ቻሪቲ የሥልጠና ማዕከል በዚህ ፕሮግራም አማካይነት ሴቶችን የማብቃት ሥልጠና ይሰጣል፤ በየስድስት ወሩ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ሴቶችን የማብቃት ፕሮግራም አለው። ባለፈው ሳምንት ለ36ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 130 ሴቶች አስመርቋል።
በዚህ ሥልጠና ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ወይዘሮ ዝናሽ ወንደወሰን አንዷ ናት። የአበበች ጎበና የ36ኛ ዙር ሰልጠኞች ተወካይዋ ወይዘሮ ዝናሽ፣ ለረጅም ጊዜ ስለ አበበች ጎበና የሴቶች ሥልጠና ስትሰማ ኖራለች። የሥልጠና እድሉን ያገኘችውም ወልዳ አራስ ቤት ባለችበት ወቅት ነው።
ወይዘሮ ዝናሽ የሥልጠና እድሉን በማግኘቷ ብትደሰትም፣ ልጅ ይዛ እንዴት አርጋ እንደምትሰለጥን ያሳስባት ጀመር። ቤተሰብ ትብብር አድርጎላት ተመዘገበች፤ ስድስት ወራት ሥልጠናውን ተከታትላም ለመመረቅ በቃች።
ሥልጠናው አምስት ዓይነት ዘርፎች እንዳሉት የምትጠቅሰው ወይዘሮ ዝናሽ፣ የልጅ እንዲሁም የቤት አያያዝ፣ መስተንግዶ፣ የባህላዊ እና ዘመናዊ የምግብ ዝግጅት ሁሉንም ባካተተ መልኩ አንድ ላይ የሚሰጥበት ነው። በውስጡም ለተቸገሩ ሴቶች የሚደረጉ ርዳታዎችን ጨምሮ የመረዳዳት እና የሰብዓዊ ድጋፎችን አስፈላጊነት የሚያስገንዝቡ ሥልጠናዎችም ተካተውበታል።
ማዕከሉ የሚሰጣቸውን የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች በሚከታተሉበት ወቅትም በቀን 33 ብር የትራንስፖርት እገዛ እንደሚያደርግ ገልጻ፣ የሥልጠና አቅርቦቶቹንና የተለያዩ ግብዓቶችን ራሱ እያሟላ ሥልጠናውን እንደሚሰጥ አመልክታለች። ከሰልጣኞቹ የሚጠበቀው ፍላጎትና ተነሳሽነት ብቻ መሆኑንም ተናግረዋል።
ወይዘሮ ዝናሽ በሥልጠናው ተጠቃሚ በመሆኗ በእጅጉ ደስተኛ ናት፤ በከሰዓት እና በጠዋት ፈረቃ ከሰኞ እስከ ዓርብ ብቻ የሚሰጥ ሥልጠና መሆኑም የማያሰላች እንዲሆን እንዳደረገው ጠቁማለች። በቡድን መሰጠቱም እርስ በርስ ለመማር እድል የከፈተ በማለት አድንቃዋለች፤ በተመሳሳይ ሌሎች በየቤቱ የሚገኙ ሴቶችም የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሁም ጥሪ አቅርባለች።
ሴት ልጅ እንደምትችል የሚታይበት ማዕከል ነው ያለችው ወይዘሮ ዝናሽ፣ ተቀጥሮ መሥራት ብቻ ሳይሆን ራስን ችሎ ቤት ውስጥ ካለ ነገር በመነሳት መሥራት እንደሚቻል ሥልጠናው እንዳመላከታትና አቅም የፈጠረላት መሆኑንም ተናግራለች። ድርጅቱ ሰልጣኞችን ካስመረቀ በኋላም በቴሌግራም ቻናሉ በኩል የሥራ እድሎችን በመልቀቅ ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ መሆኑን በመግለጽ አመስግናለች።
የአበበች ጎበና ቻሪቲ የሥልጠና ማዕከል አስተባባሪ ወይዘሮ ወይንሸት ዳምጠው ሰልጣኞቹ በተመረቁበት ወቅት እንደተናገሩት፣ ዛሬ በሕይወት በሌሉት ነገር ግን ተግባራቸው ሲታወስ በሚኖረው በሩቅ አሳቢዋና የብዙኃኗ እናት የክብር ዶክተር አበበች ጎበና የተመሰረተው ይህ ማዕከል፣ ከሚያከናውናቸው ሰብዓዊና ማህበራዊ አገልግሎቶች መካከል የምግብ ዝግጅት፣ መስተንግዶ እና የሕፃናት እንክብካቤ ማዕከል አንዱ ነው። ሥልጠናው የሚሰጠውም በሁለት ፈረቃ ለስድስት ወራት ያህል ሲሆን፤ በእያንዳንዱ ፈረቃ በሳምንት ለአምስት ቀናት፣ በቀን ለአራት ሰዓታት ሥልጠናው ይሰጣል።
በነድፈ ሃሳብ 30 በመቶ እና በተግባር 70 በመቶ በሚሰጠው በዚህ ሥልጠና፣ በባህላዊና በዘመናዊ የምግብ ዝግጅት፣ በሕፃናት እንክብካቤ፣ በመስተንግዶ፣ በእንግዳ አቀባበል እንዲሁም የሥራ ሥነ ምግባር ላይ ሥልጠናዎች ይሰጣሉ። የመግባቢያ ቋንቋ ትምህርት፣ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከል፣ የጤና አጠባበቅ እና የሕይወት ክህሎት፣ ንግድ እንዲሁም መሠረታዊ የሕግ እውቀት ሥልጠናዎችም በፕሮግራሙ መካተታቸውንም ተናግረዋል።
ከሥልጠናው ጋር በተያያዘ በሥነ ምግባር ፕሮግራም ተጠቃሚ ከሆኑት እናቶች መካከል አንዳንዶቹ ሕፃናቱን በቀን ማቆያ (ዴይ ኬር) በማዋል የሙያ ሥልጠናውን ያለምንም ችግር እንዲከታተሉም እየተደረገ ነው፤ በዚህም በተከታታይ ስምንት ዙሮች 70 በመቶ እናቶች የእድሉ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ወይዘሮ ወይንሸት፣ ማዕከሉ በየዙሩ ከሰጣቸው ሥልጠናዎች ያለፉትን 15 የሥልጠና ዙሮች በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን ሙሉ የገንዘብ እና ሃሳብ ድጋፍ ላደረገው የሜንሽን ፎር ሜንሽን ሲውዘር ላንድ ድርጅት ወይዘሮ ወይንሸት ምስጋና አቅርበዋል።
የማዕከሉ የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙዩኒኬሽን ማናጀር አቶ ይትባረክ ተካልኝ እንደገለጹት፤ እ.አ.አ በ2002 ሐምሌ ወር ሥራውን የጀመረው ይህ የማዕከሉ ፕሮግራም፣ እስከ አሁን ሶስት ሺ 420 ሴቶችን በተለያዩ ሙያዎች አሰልጥኖ አስመርቋል፤ ሥልጠናው የሰልጣኞች ሕይወት እንዲሻሻል አግዟል። ማዕከሉ በአቅም ግንባታ ሥራዎቹ በጠቅላላው ከ129 ሺህ በላይ ሴቶችን ተጠቃሚ አድርጓል። በዋናነትም ከዓረብ ሀገራት የተመለሱና ለተለያዩ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር የተጋለጡ ሴቶችን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል። እነዚህን ሴቶች በመመዘገብም በልጅ እንዲሁም በቤት አያያዝ፣ በምግብ ዝግጅት እና በሆቴል መስተንግዶ ለስድስት ወራት በማስልጠን አብቅቷል።
ማዕከሉ ሴቶችን በተለያዩ የሙያ ሥልጠናዎች አስመርቆ መተው ብቻውን በቂ እንዳልሆነም ማዕከሉ ያምናል ያሉት አቶ ይትባረክ፣ ተመራቂዎቹ የሥራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር ትስስር በመፍጠር የሥራ እድል የሚያገኙበትን ሁኔታም እንደሚያመቻች ነው የተናገሩት። ሥራ ያገኙ እና የማብቃት ሥልጠናዎቹን የወሰዱ አሁን በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ክትትል እንደሚደረግም ጠቅሰው፣ ባለፉት 35 ዙሮች የተመረቁት አብዛኛዎቹ ሥራ መያዛቸውንም ገልጸዋል።
ሴቶች ለስድስት ወራት ሥልጠናውን ከወሰዱ በኋላም ለአንድ ወር ያህል የሥራ ላይ ልምምድ እንዲያደርጉ ወደ ተለያዩ ተቋማት እንደሚላኩ ጠቅሰው፣ አንዳንዴም በዚያው ሥራ የሚያገኙበት ሁኔታ እንዳለም ገልጸዋል። ማዕከሉ የሥራ ትስስር የሚፈጥርላቸው ሰልጣኞች እንዳሉም አመላክተዋል። የማዕከሉ ምሩቃን እይታቸው የተቀየረና መልካም ሥነ ምግባር እንዲኖራቸው እና ብቁ ባለሙያዎች እንዲሆኑ ብዙ የሚደከምባቸው መሆናቸውን ጠቅሰው፣ እነዚህን ምርጥ ባለሙያዎች የተለያዩ ተቋማት እየጠየቁ እየወሰዱ ናቸው ይላሉ።
በልጅ አያያዝ (በዴይ ኬር)፣ በሆቴል መስተንግዶ የሰለጠኑትን በር አንኳክተው የሚጠይቁ ተቋማት መኖራቸውን ጠቁመው፤ ኢንሳ፣ የኢትዮጵያ ፖስታ ድርጅት፣ የኢትዮጵያ የማህበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሥራ ትስስር ከተፈጠረላቸው በርካታ ተቋማት መካከል ይጠቀሳሉ ብለዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ በሥልጠና ቆይታቸውም ሰልጣኞች በልጅ አያያዝ፣ በምግብ ዝግጅት እና በመስተንግዶ ብቻ ሳይሆን፤ በሥራ ፈጠራ / ኢንተርፕሩነርሺፕ/ ላይም የተለያዩ አጫጭር ሥልጠናዎች ይሰጣቸዋል። በዚህ መሠረትም በየጊዜው በተሰራው ጥናት እና ክትትል መሠረት ከሰልጣኞቹ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ወደ ሥራ ገብተዋል። በቀጣይም መቶ በመቶ የሚሆኑት ሥራ እንዲያገኙ ለማድረግ ታቅዷል። ሥልጠናዎቹ የሚሰጡት ሙሉ በጀት ተመድቦ ሲሆን፤ መምህራንን በመቅጠር፣ ከውጭ ለሚመጡ ተጋባዥ አሰልጣኞችም ክፍያ በመፈጸም ነው። ማዕከሉ ሴቶቹን የማብቃት ሥልጠና በሚሰጠበት ጊዜ የመማሪያ ግብዓቶችን አሟልቶ እንዲሁም ለሰልጣኞቹ በቀን 30 ብር የትራንስፖርት እገዛ በማድረግ ነው።
ሕጻን ልጅ ይዘው መንገድ ላይ የሚለምኑ በርካታ ሴቶች እንዳሉ የሚናገሩት አቶ ይትባረክ፣ እነዚህ እናቶች ወደ ማዕከሉ መጥተው ይህን እድል መጠቀም የሚችሉበት ሁኔታ ቀደም ሲል እንዳልነበረም ያስታውሳሉ። ማዕከሉ ይሄንን ችግር በመረዳት በማዕከሉ ከአምስት ዓመት በፊት የሕፃናት ማቆያ / የዴይ ኬር/ ማዘጋጀቱን ገልጸዋል። ይህ ሁኔታ እናቶች ለሥልጠና ወደ ማዕከሉ ሲመጡ ልጃቸውን ይዘው እንዲመጡ፤ ሲወጡም ልጃቸውን ይዘው እንዲወጡ የሚያስችል ሁኔታ መፍጠሩን አስታውቀዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ማዕከሉ አሁን እስከ 12 ሕፃናትን ብቻ የሚይዝ የሕፃናት መዋያ /ዴይ ኬሩ/ ነው ያለው፤ ይሁንና ይህ ብቻውን በቂ አይደለም፤ አሁንም በልጅ ምክንያት ሥልጠናውን የማይወስዱ ሴቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል። ማዕከሉ ተጨማሪ በጀት ካገኘም በርካታ በሕፃናት ምክንያት የመሰልጠን እድሉን መጠቀም ያልቻሉ እናቶችን ተቀበሎ ለማብቃት እና ሥልጠናውንም መከታተል ላልቻሉት እድል ለመስጠት ይፈልጋሉ።
ብዙ መሥራት የሚችሉ ወጣት ሴቶች ልጆቻቸውን እያሉ እና ልጆቻቸውን በክፍያ ሕፃናት ማቆያ /ዴይ ኬር/ ማቆየት ስለማይችሉ ልጅ ይዘው ይቀመጣሉ ያሉት አቶ ይትባረክ፣ እነዚህ እናቶች ልጅ የሚይዝላቸው ቢያገኙ ተሯሩጠው ሰርተው ልጃቸውን ማሳደግና መንከባከብ ይችላሉ ብለዋል። በዚህ ላይ መንግሥትም ሆነ ሌላ የልማት አጋር ድርጅቶች በስፋት ሊሰሩ እና እገዛ ሊያደርጉ እንደሚገባም ጠቁመዋል። ቢያነስ በተመጣጣኝ ዋጋ የሕፃናት ማቆያ /የዴይ ኬር/ አገልግሎቱ ቢስፋፋ እና አበበች ጎበና ቻሪቲ ማዕከል በመሳሰሉት ደግሞ በነጻ አገልግሎቱ በስፋት ቢኖር የተሻለ ለመሥራት እንደሚቻል አመላክተዋል።
የአበበች ጎበና ቻሪቲ የሥልጠና ማዕከል ከዚህ በፊት በአንድ ጊዜ እስከ 200 ሴቶችን አሰልጥኖ ማብቃት ደረጃ ላይ መድረሱን አስታውሰዋል። በኮሮና ወቅትም እንደ ሜንሽን ፎር ሜንሽን እና ዶምቦስኮ ከመሳሰሉት ድርጅቶች በሚያገኘው ፈንድ ሲሰራ እንደነበር አስታውሰዋል።
እንደ ሀገር የበጎ ሥራዎቹ ለማስፋት የበጀት እጥረት እና የአቅርቦት ችግር መኖሩን ጠቁመዋል። የበጀት ችግሩ እና የአቅድ ችግሮች ቢቀረፍ ማዕከሉ የረጅም ጊዜ ልምዱን ተጠቅሞ ሀገራዊ በጎ ተግባሩን ወደ ሌሎች ክልሎችም የማስፋት ፍላጎቱ አለው ብለዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ማዕከሉ ሴቶችን በእነዚህ ሙያዎች አሰልጥኖ የማብቃት ዑደቱም ቀጣይነት ያለው በመሆኑ ለቀጣይ 37ኛ ዙር ሴቶችን መዝግቦ የማብቃት ሥራውን እየቀጠለ ነው። ይህ ማዕከል ብቻውን በሴቶች ላይ የሚደርሱ ችግሮችን ሊፈታ አይችልም፤ ሌሎች ድርጅቶችም ይሄንን ተምሳሌትነት በመውሰድ ሴቶችን የማብቃት ሥራውን ማስፋት ይገባቸዋል።
የማህበረሰቡ ችግሮች አንድም በሴቶች ላይ ከሚደርሱ ችግሮች እንደሚመነጭ ጠቅሰው፣ ሌሎች የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ሀገራዊ የበጎነት ሥራቸውን በዚህ ላይ ካጠናከሩ ሀገሪቱና ማህበረሰቡ በብዙ መልኩ ይጠቀማሉ የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል። ሆቴሎች እና ሌሎች ተቋማትም ተመራቂ ሴቶችን በመቅጠር እንዲተባበሩም ጠይቀዋል።
የሜንሽን ፎር ሜንሽን ስዊዘርላንድ የኢትዮጵያ ተጠሪ አቶ ጌታቸው ዘውዱ በበኩላቸው እንደተናገሩት፣ ድርጅቱ ለአበበች ጎበና ቻሪቲ የሥልጠና ማዕከል በዋናነት የሚያደርገው ድጋፍ ወላጆቻቸውን ያጡ ታዳጊ ሕፃናት ቤተሰብ ውስጥ ሆነው ሲያድጉ ሊያገኙ የሚገባቸውን እንዲያገኙ ለማድረግ የሚረዳ ነው። እንዲማሩ፣ ጤንነታቸው እንዲጠበቅ እንዲሁም ሌሎች የሚያስፈልጋቸው ግብዓት እንዲሟሉላቸው ይደረጋል። በየስድስት ወሩ እየሰለጠኑ የሚወጡ በትንሹ ከ140 የማያንሱ በአብዛኛው ከዓረብ ሀገር ተመላሽ የሆኑ ሴት እህቶችን በሙያ በማብቃትም ራሳቸውን ችለው ለሀገርም ለወገንም ለቤተሰቦቻቸውም እንዲተርፉ ድርጅቱ እገዛ እያደረገ ይገኛል።
በማዕከሉ ባለው ተጨማሪ ፕሮግራሙም ማዕከሉ በሚገኘበት አካባቢ ኑራቸው ዝቅተኛ በሆኑና ልጆቻቸው ከሶስት ዓመት በታች የሆኑ ለመወንጨር የተጋለጡ ሕፃናትን የመታደግ ሥራም ይሰራል። በተለይም በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ ያሉ የቀነጨሩ፣ የጤንነት እና የምግብ እጥረት ያለባቸው ሕፃናትን በስድስት ወር ውስጥ እንደማንኛውም ሕጻን ሊኖራቸው የሚገባውን ክብደት እንዲያገኙ በማድረግ የመመገብ ሥራ እያከወነ መሆኑንም ተናግረዋል። መቀለብ ብቻም ሳይሆን ቤታቸው ይዘው የሚሄዱትን ስንቅ በመስጠት፣ ወደ ማዕከሉ በመጡ ቁጥር ልጆቻቸውን በትናንሽ ነገሮች እንዴት መመገብ እንደሚገባቸው በሙያው በሰለጠኑ ባለሙያዎች የትምህርት አገልግሎት እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል።
በዚህም በአበበች ጎበና ማዕከል ብቻ በዓመት በአማካኝ ከ300 ያላነሱ ሴቶች ሲመረቁ በተመሳሳይ መልኩም ከ300 ያላነሱ ሕጻናት በምገባ ፕሮግራም ውስጥ ያልፋሉ ብለዋል። በምገባ እና በሥልጠና ፕሮግራሞቹ እንዲሰሩም የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል። ቡራዩ በሚገኙ ሕጻናት መዋያዎች ለሚገኙትም ድጋፍ እንደሚደርግ አስታውቀው፣ ሜንሽን ፎር ሜንሽን ድርጅት ከአበበች ጎበና ጋር ከሚሰራው ውጪም በኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉም ክልሎች ላይ ሰፊ የበጎ ተግባር ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ኅዳር 28 ቀን 2016 ዓ.ም