የሰው ልጅ ጸባይ እንደየመልኩ ሁሉ የተለያየ ነው። አንዳንዶች ቁጡና በሆነ ባልሆነው ግንፍል ማለት ሲቀናቸው ሌሎች ደግሞ እጅግ የተረጋጉና በአድራጎታቸው ሰው የማያስከፉ ይሆናሉ። እንዲህ ዓይነት ሰዎች ቢገናኙ ግን ምን የሚፈጠር ይመስላችኋል? ምናልባት አንዱ ሲቆጣ ሌላው እየቻለ አሊያም እያረጋጋ ይኖሩ ይሆናል ትሉ ይሆናል።
ግን ግን የሰዎች ትዕግስት እስከ ምን ሊጓዝ ይችላል? ኦዲቲ ሴንትራል ከሰሞኑ ያስነበበው ዜና ለዚህ ምላሽ ይሆን ይሆናልና እንካችሁ። ባለ ታሪኮቹ ቻይናዊያን ወጣት ጥንዶች ናቸው። ታዲያ እነዚህን ፍቅረኛሞች በሃገራቸው መነጋገሪያ በእኛ ዘንድ ደግሞ ዜና ለመሆን ያበቃቸው ጉዳይ የእርሷ ብስጭት እና የእርሱ ታጋሽነት በአደባባይ በመታየቱ ነው።
ነገሩ እንዲህ ነው፤ በቻይናዊያን ልማድ መሰረት የተያዘው የፈረንጆቹ ወር ሊጠናቀቅ 10 ቀናት ሲቀሩት «የፍቅረኛሞች ቀን» ይከበራል። ጥንዶችም ስጦታ በመለዋወጥ፣ አብሮ በማሳለፍና ፍቅራቸውን በማጠናከርም ያሳልፋሉ ዕለቱን። ከቀናት በፊት በተከበረው በዚህ በዓል ግን በአንድ አካባቢ ያልተለመደ ነገር ታይቷል። ይኸውም ወጣቷ ፍቅረኛዋ የሆነን ወጣት በተደጋጋሚ በጥፊ ስትመታው፤ እርሱም አጸፋውን በትዕግስት መቀበሉ ነበር።
ታዲያ ነገሩ እየሆነ ያለው የተጓዦች እግር በሚበዛበት ግልጽ ስፍራ ነበርና የመንገደኞችን ቀልብ የሚስብ ነበር። ቀስ በቀስ ሰዎች እየተሰባሰቡ ከበው ቢመለከቷቸውም ግድ የሌላት ወጣት ግን አድራጎቷን አላቋረጠችም ነበር። እንዲያውም ማንም በዙሪያቸው የሌለ ያህል በፍቅረኛሞች ቀን ዘመናዊ ተንቀሳቃሽ የስልክ ስጦታ ሊሰጣት እንዳልቻለ እያነሳች ትወቅሰው እንደነበር በዘገባው ተመልክቷል።
የመንገደኞችን መሰብሰብ ያየው ፖሊስም በቦታው ደርሶ ወጣቷ በምስኪኑ ፍቅረኛዋ ላይ ስታደርስ የቆየችውን ጥቃት ለማስቆም ችሏል። ፖሊስ ከጅምሩ በቦታው ባይደርስም ግን ወጣቱ በፍቅረኛው ከ52 ያላነሰ ጥፊ ሳያርፍበት እንዳልቀረም ጠቁሟል። ነገሩን ለማብረድ ፖሊስ ከመሃላቸው በገባ ጊዜም ወጣቱ ለፍቅረኛው ጥብቅና ሲቆም ታይቷል፤ የምትፈልገውን ስልክ ሊገዛላት አለመቻሉ የእርሱ ስህተት እንደሆነም ነበር የሚገልጸው።
ንዴቷን ሊያበርድ የሚችለውም ይህ በመሆኑ እንድትመታው የፈቀደላት ራሱ መሆኑንም አስረድቷል። በፖሊስ ጣቢያ ቆይታ ካደረጉ በኋላም በተረጋጋ መንፈስ እንደ ሰለጠነ ሰው ችግራቸውን በንግግር መፍታት እንዳለባቸው ተምረዋል። በቦታው የነበሩ የዓይን እማኞች ሁኔታውን በተንቀሳቃሽ ምስል በመያዝ በማህበራዊ ድረገጾች ለጥፈውታል።
ኦዲቲ ሴንትራልም ዘገባውን «ማየት ማመን ነው» በሚል ከተንቀሳቃሽ ምስሉ ጋር አያይዞታል። ተንቀሳቃሽ ምስሉን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የተመለከቱት ሲሆን፤ ወጣቱ ይህንን ያህል ዱላ ሲያርፍበት በእርጋታ መቀበሉንም አድንቀዋል። እናሳ ጥፊና ትዕግስት እስከምን እንደሚዘልቁ አልተመለከታችሁም?
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2011
ብርሃን ፈይሳ