ወደ ጉዳይ ለመሄድ ማለዳ ብትነሱ መብራት የለም፣ ለመተጣጠቡም ቢሆን ከቧንቧው ጠብታ አይኖርም። ይህንን ተከትሎም ቁርስ አይኖር ይሆናልና እንዲሁ መንገድ ይጀመራል፤ ነገር ግን ታክሲም የለም። ከረጅም ጥበቃ በኋላ ቢመጣም ቅሉ «በዚህ በኩል መንገድ የለም» በሚል ምልክት አቅጣጫ ይቀየራል። «ታክሲ ለምን ጠፋ» ብለው ቢጠይቁ «ነዳጅ ስለሌለ» የሚል መልስ ይሰጥዎታል።
ለጉዳይ ማስፈጸሚያ ገንዘብ ማውጣት ቢፈልጉም በኔትወርክ አለመኖር መገልገል እንደማይችሉ ያሳውቅዎታል። እንደምንም እግርዎ ከጉዳይዎ ቢደርስም ደግሞ «ጉዳይ ፈጻሚው የለም» ይባላሉ። በብስጭትም ይሁን ተስፋ በመቁረጥ ከአንድ ስፍራ አርፈው፤ እህል ውሃ ሊሉ ቢፈልጉም ከግድግዳው የተለጠፈው የሚያስጎመጅ ምግብ እንደሌለ ይነገርዎታል።
ዓይኖን ከቴሌቪዥን መስኮት አሊያም ጆሮዎን ከራዲዮ ቢያዋድዱም ነገር ሁሉ በ«የለም» የታጀለ ሆኖ ያገኙታል። ሁሉም በየራሱ «ለውጥ የለም፣ የሥራ ዕድል የለም፣ የህግ የበላይነት የለም፣ የትምህርት ጥራት የለም፣ ሃገር ወዳድነት የለም፣ የሥራ ተነሳሽነት የለም፣ ፍትህ የለም፣ በጀት የለም፣ የሰው ኃይል የለም፣ …» ሲል ትታዘባላችሁ። እኔ ግን እላለሁ፤ ከየለም ባሻገር ያለውን መኖር የሚያይ ሁነኛ ሰው የለም።
አንድ ነገር በተለያዩ ምክንያቶች ላይገኝ አሊያም ሊጠፋ ይችል ይሆናል። ነገር ግን በነገርየው እግር ሊተካ የሚችል ሌላ አማራጭ መኖሩ የግድ ነው። አማራጭ ማየት ተስኖን ይሁን «የለም»ን ለምደነው እንጃ፤ «ለምን የለም?» አንልም። መብታችንና ከግዴታችን ተቀላቅሎብናል። መቼም ለጉዳይ በሄዳችሁበት ቢሮ «ኃላፊው የሉም» ተብላችሁ ሳትመላለሱ አልቀራችሁም።
ኃላፊነታቸው ሠራተኛን መምራትና ህዝብን ማገልገል ሆኖ ሳለ፤ የተሰጣቸውን ወንበር ቆልፈውበት ሲያበቁ «የሉም» ማስባል አያናድድም?ጤናችሁ ታውኮ ወደ ህክምና ስፍራዎች አቅንታችሁ የመብራት አለመኖርን እንደመንገር ቀለል ተደርጎ «ዶክተሩ የሉም፤ ነገ ተመለሱ» ተብላችሁ አታውቁ ይሆን? እስኪ አስቡት ከውጋትና ከከፍተኛ ስቃይ የሚታደገውን ለፈለገ ታማሚ ይህ ምን ማለት እንደሆነ።
ከህመሙ ብዛት ዓይኑን መግለጥ አቅቶት ተስፋን በጭላንጭል የሚመለከት በሽተኛ፤ ሞትን በቀጠሮ ያቆይ ይመስል «አድረህ ተመለስ» መባሉ አያቆስልም? ታዲያ ይህ ከእኛም አልፎ የውጭ ዜጎች ኢትዮጵያ ውስጥ ቆይታ ቢያደርጉ በቅድሚያ የሚለምዱት ቃል «የለም» የሚለውን ነው እየተባለም በማህበራዊ ድረ-ገጾች ይፌዛል።
ምክንያቱ ደግሞ «መብራት የለም፣ ውሃ የለም፣ ኔትወርክ የለም፣…» የሚሉትን በተደጋጋሚ ስለሚሰሙ ነው። አሁን አሁንማ «የለም» የሚለውን ምላሽ ከመደጋገማቸው የተነሳ ቋሚ መላ የዘየዱለትም አሉ። የእኔ የተመለከትኩትን ላውጋችሁ፤ እንደሚታወቀው የነዳጅ ማደያዎች ረጃጅም የመኪና ሰልፎችን ማስተናገድ ከጀመሩ ሰነባብተዋል።
አብዛኛውን ጊዜም አንዱን የነዳጅ ዓይነት ሊጨርሱ አሊያም ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት ላይሰጡ ይችላሉ። ይህንን ለአሽከርካሪዎች ለማሳወቅ በካርቶን አሊያም በተገኘው ቁስ ላይ «… የለም» የሚል ጽሑፍ አስፍረው አንዳች ነገር ላይ ይሽጡታል አሊያም በድንጋይ ደጋግፈው በሚታይ መልኩ ያስቀምጣሉ። እኔ ከምመላለስበት መንገድ ዳር የሚገኝ አንድ የነዳጅ ማደያ ታዲያ «የለም» ማለቱ ቢጸናበት ጎላ ባለ ባነር «ቤንዚን የለም» ብሎ ለማሳተም መብቃቱን ታዘብኩ።
ወገን ይህንን እንደቀልድ እናየው ይሆናል፤ ሳናስበው ግን አሉታዊ ነገርን በውስጣችን እያሰረጽን ነው። አሁን እያየነው ያለነው አለመኖር እየዋለ ሲያድር ከምን ይደርስ ይሆን? ነገስ ምን «የለም» እንባል ይሆን? የሚለው ያሳስባል እኮ። በእርግጥ እግረ መንገድ በሚሰጡ ማብራሪያ እና ትንታኔዎች ለጎደሉ ነገሮች ምክንያት የሃገሪቷ ወቅታዊ ሁኔታ አስተዋጽኦ አለው የሚል ሃሳብ ይነሳል።
ምክንያቱ ምንም ቢሆንም ግን፤ ከችግራችን አሻግረን መመልከት እንዳልቻልን ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል። ከግለሰብ እስከ ህዝብ፤ ከተቋማት እስከ መንግሥት አለመኖርን ተላምደንዋል። ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ «የለም» ሲባል ሲሉን እና ስንባል እንደ ተራ አሊያም እንደተለመደ ነገር መቀበላችን ነው። ድሮ ድሮ ተስፋ አሊያም መልካም ዜና ሲነገር ነበር ከአንገት ቀና ከድምጸትም ወፈር የሚደረገው። አሁን ነገሩ ሁሉ የተገላቢጦሽ ሆኖ መርዶ የመሰለን ዜና ከይቅርታ ሳያገናኙ መንገር ተለምዶ ሆኗል።
«ጽድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ» እንዲሉ «የለም» ባዮች ዓይናቸውን እንኳን ሰበር ቢያደርጉ ግን ምን አለ? ጥፋተኝነት ለምን አይጎበኛቸውም? በድክመታቸው አሊያም በስህተታቸው እንደፈጠሩት ቢያምኑስ ምን ይጎድልባቸዋል? ይቅርታ ጠይቀውን ትብብር እንድናደርግላቸው መጠየቅስ ስልጣኔ አይደለም? እኛም ብንሆን፤ በመንቀፍ፣ በማማረር፣ በማጥላላት፣ እምቢና የለም በማለት፣ … መቼም ቢሆን የተቃና ህይወትን ማግኘት አንችልም። አዳዲስ ሃሳቦችን በማመንጨት፣ ተነሳሽነትን በመፍጠር እንዲሁም መፍትሔ አመንጪ በመሆን «የለም»ን፤ በ«አለ» ስለመተካት መማር አለብን። ሳናስብ ከእሳቤያችን፣ ከእይታችን እና ከአንደበታችን የተዋህደውን አሉታዊ መልስ አርቀን ለመጣልም መጣር ይገባናል።
በየትኛውም ነገር ውስጥ መልካም ነገር መኖሩን እንዲያስብ አዕምሮን ማሰልጠንም ተገቢ ነው። መልካም እሳቤ አማራጭ የማይገኝለት የደስታ ምንጭ ነውና የማይበጀንን ከእኛ ወዲያ ማራቁን እንማር። ስኬታማ ሰዎች እርስ በእርሳቸው ይገነባባሉ፣ ይተጋገዛሉ፣ ይደናነቃሉም። እንዲሳካልን ከፈለግንም «የለም» ከማለታችን በፊት አማራጭ እንፈልግ፤ «የለም» ሲሉንም «መፍትሔውስ?» ብለን እንጠይቅ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2011
ብርሃን ፈይሳ