አብርሆት – ለልበ ብርሃኖች

በዓለም ከ46 ሚሊዮን ሰዎች በላይ ዓይነ ሥውራን መሆናቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ:: 235 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ ከፊል የእይታ ችግር ያለባቸው ናቸው:: በኢትዮጵያ ቁጥሩን ይህን ያህል ነው ብሎ ለማስቀመጥ ጥናቶች ባይኖሩም ቁጥሩ ቀላል እንደማይሆን ግን ይገመታል::

ዓይነ ሥውራን ስለሚገጥማቸው ችግር እንዲሁም መፍትሔዎችን ለማመላከት 31ኛው ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀንን ምክንያት በማድረግ “አብርሆት ለልበ ብርሃኖች” በሚል መሪ ቃል ለዓይነ ሥውራን በዓይነ ሥውራን የተዘጋጀ የውይይት መርሃ ግብር ሰኞ ኅዳር 24 ቀን 2016ዓ.ም በአብርሆት ቤተ መጻሕፍት ተካሂዷል::

የአብርሆት ቤተ መጻሕፍት ዋና ዳይሬክተር ባየሁ ማሞ (ኢንጂነር) በመርሃ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት፤ ከዚህ ቀደም የነበሩት ዓይነ ሥውራን ለመሠረታዊ ትምህርት ያልታደሉ ነበሩ:: በአሁን ወቅት ግን በብሬል እና በቴክኖሎጂ በመታገዝ ብዙ ፈተናዎችን አልፈው ውጤታማ የሆኑ በርካቶች ናቸው::

‹‹ዓይነ ሥውርነት ሰውን የሚገልጽ ባህሪ አይደለም፤ በቀላሉ ዕይታቸውን ብቻ የሚነካ ነገር ነው›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ነገር ግን በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው ውስጥ ብዙ ችግር እንደሚገጥማቸው ይናገራሉ:: በትምህርት፣ በሥራ እና በሌሎች የአካታችነት እጦት ሳቢያ ማህበራዊ ተስፏቸው ይገደባል:: በመሆኑም አሁን በመንግሥት እየተሠራ ያለው ሥራ የሚበረታታ ሲሆን፤ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር የሁሉም ኃላፊነት ነው:: በመሠረተ ልማት፣ በአካታች ትምህርት እና ልዩ ችሎታቸውን በመጠቀም የሥራ ዕድሎችን በመፍጠርም መደገፍ ያስፈልጋል:: ዓይነ ሥውራን በሁኔታቸው ከመገደብ ይልቅ በችሎታቸው የሚከበሩበትን ዓለም በመፍጠር የአብርሆት ቤተ መጻሕፍት ምሳሌ እንደሚሆን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ በቤተ መጽሐፍቱ ሦስተኛ ወለል ለዓይነ ሥውራን ቦታ በማዘጋጀት ብቸኛው ቤተ መጽሐፍት እንደሆነ ገልፀዋል::

የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ ዓለም አቀፉ የአካል ጉዳተኞች ቀን ለ31ኛ ጊዜ ሲታሰብ ‹‹ለአካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እና ለዘላቂ የልማት ግቦች ስኬት ትርጉም ያለው ትብብር›› በሚል መሪ ቃል መሆኑን አስታውሰዋል:: እንደ ሚኒስትራ ገለፃ፣ አካል ጉዳተኝነት ከተጠቃሚነት ሊገድብ አይገባም፤ አካል ጉዳተኝነት አለመቻል ሳይሆን ነገሮችን በተለየ መንገድ እና ሁኔታ መከወን መቻል ነው:: ማግኘት ያለባቸውን ጥቅም እንዲሁም ተሳታፊነታችን ለማረጋገጥ መሥራት ይገባል::

ለአካል ጉዳተኞች ተጠቃሚነት የተለያዩ ሕጎች፣ ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች ቢኖሩም የተበታተኑ ናቸው የሚሉት ሚኒስትሯ፣ እነዚህን ሰብሰብ በማድረግ የተጠቃለለ የአካል ጉዳተኞች ሕግ አስገዳጅ ሆኖ ሁሉም ሊተገብረው በሚገባ መንገድ ለማዘጋጀት እየተሠራበት እንደሚገኝ ተናግረዋል:: አክለውም ጉዳዩ የአካል ጉዳተኞች ብቻ መሆን እንደሌለበትና ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ትርጉም ያለው ትብብር ሲያደርጉ ውጤት ከማምጣት ባሻገር የአካል ጉዳተኞችን ተሳታፊነት ማረጋገጥ እንደሚቻል አብራርተዋል::

በመድረኩ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ ‹‹አካል ጉዳተኝነት አለመቻል አይደለም:: ይልቁንም በውስጥ ያለውን ችሎታ በልዩ ሁኔታ መከወን መቻል ነው:: ልዩ ችሎታቸውን እና ብቃትን ለመከወን ግን ድጋፎችን ማድረግ ብሎም ሁኔታዎችን ምቹ ማድረግ ያስፈልጋል::›› ሲሉ ተናግረዋል:: በምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚው የሆነው አብርሆት ቤተ መጻሕፍት ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ሁኔታን መፍጠሩ የሚበረታታ እንደሆነ የጠቆሙት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የማንበቢያ ቦታ ማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን በውስጣቸው ለሀገር የሚጠቅም በርካታ መጻሕፍትን ለአንባቢዎች ማቅረቡ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ነው:: እንደ ከተማ አስተዳደርም ሥራዎች አካታችነትን የሚተገብሩ ለማድረግ አዳዲስ ሕንጻዎች ዲዛይን ሲደረጉ እንዲሁም የቀድሞ ሕንጻዎች ቅርጻቸውን ሳይቀሩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እንዲሆኑ ተደርገው እየተሠሩ ናቸው:: በቀጣይም ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይገባል:: ሌሎችም እንዲህ ያለውን ሥራ መተግበር ይጠበቅባቸዋል::

የዓለም አቀፍ ፖለቲካ ሳይንስ እና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ዓለምአየሁ ገብረማርያም፤ ቤተ መጻሕፍቱ ከተገነባ ጀምሮ በርካታ ማሕበራዊ ኃላፊነቶችን እየተወጣ እንደሚገኝ በመግለጽ፤ ማኅበረሰቡ አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ ከአስተሳሰብ ጀምሮ ቃላት አጠቃቀም ላይ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባው ይናገራሉ:: ፕሮፌሰሩ እንደገለፁት፤ በ2020 በወጣው የስታቲስቲክስ መረጃ መሠረት 8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሰዎች በተለያየ ደረጃ የማየት ችሎታቸው ቀንሷል:: ይህን አስመልክቶ በኅብረተሰቡም ይሁን በመንግሥት በኩል አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ይገባል::

በኢትዮጵያ ዓይነ ሥውራን ብሔራዊ ማህበር የአካቶ ትምህርት አሰልጣኞች አስተባባሪ አቶ ከተማ ባየልኝ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ መሠረት፤ ዓይነ ሥውራን ለማንበብ ከሚጠቀሙባቸው መንገዶች መካከል ብሬል፣ ኮምፒውተር፣ የድምጽ ቅጂዎች ይጠቀሳሉ:: ነገር ግን በትምህርት ቤቶች ‹‹የልዩ ፍላጎት መምህራን ናቸው›› ተብለው ብሬል የሚያሰለጥኑ አሰልጣኖች ብቃት አጠያያቂ በመሆኑ መሻሻል ይገባዋል::

ሌላው የብሬል ተደራሽነት ቁጥር አናሳ ሲሆን ፍላጎትና አቅርቦቱን ማጣጣም ይገባል:: ከዚህ በተጨማሪም የብሬል ሕትመት ዋጋ መናር ለብሬል ተደራሽነት እንደ አንድ ችግር መሆኑን በመጥቀስ፤ በብሬል ተደራሽነት የመንግሥት ተሳትፎ አናሳ መሆኑ እንዲሁም ዓይነ ስውራን ተማሪዎች የኮምፒውተር ትምህርት እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት እየተማሩት ባለመሆኑ ለእነርሱ አመቺ የሆኑ ሶፍትዌሮችን በመጠቀም ትምህርቱ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ያስረዳሉ::

አቶ ፋሲካ አጌና በአዲስ አበባ ፍትህ ቢሮ አቃቤ ሕግ ናቸው:: እርሳቸው ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ ዓይነ ሥውራንም ይሁኑ ሌሎች የማንበብ ችግር ያለባቸው ሰዎች እንደ ማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል የማንበብ እና የማወቅ ፍላጎታቸው ከፍተኛ ነው:: ነገር ግን አብዛኛው መጻሕፍት ተደራሽነት ይጎድላቸዋል:: በየዓመቱ ከሚታተሙ መጻሕፍት መካከል ለዓይነ ሥውራን እና የንባብ ውስንነት ላለባቸው ተደራሽ የሚሆኑት ከሰባት በመቶ ብቻ እንደሆነ ዓለም አቀፍ ጥናት እንደሚያመላክት በመግለጽ፤ በዚህም ከንባብ የተገፋ ሰፊ ማኅበረሰብ እንዳለ አመላካች ነው ይላሉ:: ክፍተቱን ለማጥበብ አካቶ እና ተደራሽ አድርጎ መሥራት ይገባል::

እንደ አቶ ፋሲካ ማብራሪያ፤ መንግሥት ‹‹የማራካሽ ስምምነት›› ፈርሞ አጽድቋል:: ስምምነቱም መጻሕፍት ተደራሽ እንዳይሆኑ የሚከለክሉ የቅጂ መብቶች ሕጎች ላይ ገደቦች እንዲሁም ልዩ ሁኔታዎች እንዲካተቱ የማድረግ ዓላማ ያለው ነው:: ይህም የሕትመት ውጤቶች በተለይም ለዓይነ ሥውራን እና የንባብ ችግር ላለባቸው ልዩ በሆነ መንገድ እንዲያዘጋጁ የሚያስገድድ ነው:: ስምምነቱ መፈረሙ ይበል የሚያሰኝ ሲሆን፤ ከመፈራረም የዘለለ ሥራ ግን ከመንግሥት ይጠበቃል::

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋ እና የሥነ ጽሑፍ አራተኛ ዓመት ተማሪ ኃይለ ልዑል ምስጋናው፣ ብሬል ማንበብ የቻለው በራሱ ብርቱ ጥረት መሆኑን ይናገራል:: እርሱ እንደሚለው፣ ሥርዓተ ትምህርቱ መፈተሽ አለበት፣ ለንባብ አመቺ የሚባሉ ሁኔታዎችም መፈጠር አለባቸው:: የብሬል ተደራሽነት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማረም፤ ራሱን የቻለ ሥርዓተ ትምህርት መቅረጽ እንደሚገባ የመፍትሔ ሃሳብ ያቀረቡት አቶ ፋሲካ፤ የብሬል ትምህርት ለዓይነ ሥውራን እና ዓይነ ሥውራንን ለሚያስተምሩ መምህራን መስጠት ቢቻል ችግሩን ያቀለዋል::

 እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን   ኅዳር 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You