ሰሞኑን ጥበብና ግጥም ፍቅራቸው ጠንቶ በጫጉላ ቤት ያሉ ጥንዶች መስለዋል። ባለፈው ሳምንት ከብሔራዊ ቲያትር የጀመርነው ጉዞ ዛሬም ከሀገር ፍቅር ደጅ አድርሶናል። ጥበብ ውላ ትግባ እንጂ ማደሪያዋን አታጣም። የዛሬው ርዕሰ ጉዳያችን የሆነው “ጎልያድ እማን ፍታት” የተሰኘው የግጥም መድበል ደራሲዋ ማህሌት ጌታቸው(መልሕቅ) ደግሞ ሦስተኛውን የጥበብ ልጄን ተገላገልኩ ትለናለች። እኛም ‘እንኳን ጥበብ ማረችሽ’ ብለናል።
የማለዳዋ ጀንበር ከወደ ምሥራቅ ወጥታ ከሀገር ፍቅር ሰማይ ላይ የፀሐይ ብርሃኗን ቁልቁል መፈንጠቅ ተያይዛዋለች። ከሐረር የበቀለችው ደራሲዋ ማህሌት ጌታቸው የፀሐይዋን የተፈጥሮ ምህዋር ተከትላ የጥበብ ብርሃኗን በግጥም ሥራዎቿ ልትለግስ በሀገር ፍቅር ተገኝታለች። ለ3ኛ ጊዜ ወግ ማዕረጓን ለማየት የበቃችው ደራሲ ከዚህ ቀደም ሁለት ሥራዎች ጀባ ብላለች። በ2005ዓ.ም “የኔ” የተሰኘውን የግጥም መድብሏን አሰናድታ ለግጥም አፍቃሪያን አድርሳለች። ሁለተኛው ሥራዋ ደግሞ በ2010ዓ.ም በእውነተኛ ታሪክ ላይ ተመርኩዛ የጻፈችው “የቀለጠች ሻማ” የተሰኘው ሥራዋ ሲሆን በሴቶች ጥቃት ላይ የሚያጠነጥን መጽሐፍ ነው። ሴቶች በሴተኛ አዳሪነት ሕይወት ውስጥ የሚደርስባቸውን አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጥቃትን እያተተ ወደ አዲስ የሕይወት መስመር የሚገቡበትን መንገድ ጠቆም ያደርጋል። ይህን መጽሐፍ ለመጻፍ ያነሳሳት ነገር ‘ሜርሲ ቻፕልስ’ በተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ውስጥ በመምህርነት በምታገለግልበት ወቅት ካየችውና ካጋጠሟት ጉዳዮች መነሻነት ስለመሆኑ ትናገራለች። “ሴተኛ አዳሪዎቹን ቀርቦ ጓደኛ በማድረግ እንዲሁም ደግሞ ለምልከታ በእኩለ ሌሊት ብቅ እያልኩ በውጣ ውረድ የተሞሉ ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች አሳልፌ በመጨረሻም ለፍሬ የበቃ መጽሐፍ ነው” በማለት በወቅቱ ስለነበረው ሁኔታም ከማንሳት አልቦዘነችም። በእነዚህ ሁለት መጻሕፍት አልፋ፤ በሁለት እግሮቿ ለመቆም እየታገለች ደግሞ፤ ምርኩዝ የሆናትን 3ኛ ሥራዋን በግጥም ስንኞች አጅባ “ጎልያድ እማን ፍታት” ስትል መጥታለች። የግጥም መድብሉ የተዋቀረበት አካላዊ ቁመና በዋናነትም ፍቅር፣ ሰላም፣ ሀገርና ማህበራዊ ዳርቻዎቻችንን እየተሻገረ እልፍ ጉዳዮችን ያስመለክተናል። ከዚህ በተጨማሪም ደራሲዋ በሰዋሰው ማንነት ውስጥ እየጠለቀች አንዳንድ ጊዜ ከራስ፤ ከተፈጥሮና ፈጣሪ ጋር የሚደረጉ ውስጣዊ ግጭቶችን በጥያቄና ለምን በሚል ምላሽ ፍለጋ ውስጥ ስትዳክር እንገነዘባለን።
ለምን?
ለምን ወሰደክብኝ ብቻዬን ፈለከኝ፤
እንዲህ ነው ምትወደኝ?
ቀናተኛ አምላክ መሆንክን አውቃለሁ፤
እንዲህ ከወደድከኝ ውሰደኝ ብያለሁ።
ምክንያቱን አትጠይቀኝ ሁሉን አውቀህ ሳለህ፤
ከልቤ ልኬት ውስጥ ያለውን እያየህ።
አቅቶህ አይደለም ሉዓላዊ እኮ ነህ፤
መልስልኝ ባክህ ባክህ ልለምንህ!
በሱሙ እንዳልጠራው ሰዎች ያውቁብኛል፤
አምላኬ ብቻውን ለኔ ይበቃኛል፤
እንዳልል ሰው ነኝ ሰው ያስፈልገኛል፤
መልስልኝ ባክህ እጅጉን ከፍቶኛል፤
የሆነ ጉድለቴ ህመም ሆኖብኛል፤
ህመም በርትቶብኝ ማውራት ተስኖኛል።
ከሆነ አጥንት ላይ እኔን የፈጠርከው፤
እንድሞላው ነበር እሱን ያጎደልከው፤
መሙላት የተሳነኝ ምን ብትሳሳት ነው።
….
ወይ እኔን ውሰደኝ ለእርሱ ካጎደልኩት፤
ኧረ እንዲያውም ይቅርብኝ ፍቅርን ቱ! አልኩት።
ኅዳር 22 ቀን ረፋድ በሀገር ፍቅር ቲያትር በነበረው በዚሁ የመጽሐፍ ምረቃ ላይ በአሁኑ ሰዓት “የቀድሞ የሐረር ሙዚቀኞች ማህበር”ን መስርተው በ4 ኪሎ የከተሙት የቀድሞው የሰሜን እዝ ኪነት ቡድን አባላትን ጨምሮ አርቲስት ሥዩም ተፈራ፣ ትዕግስት ባዩ፣ ሕይወት አራጌ፣ ቃቂ ተስፋዬና ሌሎች የጥበብ ሰዎችም ታድመውበታል። ጀማሪ ገጣሚያንና ድምጻውያንም የተለያዩ ሥራዎቻቸውን በማቅረብ የመድረኩ ጌጥ ሆነዋል። ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ ተግባር በመጠቀም ለኪነ ጥበቡና ማህበራዊ ጉዳዮቻችን መነቃቃትን እየፈጠሩ ካሉ የቲክቶክ መንደር ጌቶችም ሌላ ውበት ነበሩ። ሌላው የመድረኩን ድባብ ሞልቶ ዓይን ሳብ ልብ ወሰድ የሚያደርገው የታዳጊ ሕጻናቱ የፋሽን ትርኢት ነበር። በቆንጆ ዲዛይን በተሸመኑ አልባሳት አሸብርቀው ወዲያ ወዲህ ሲሽሞነሞኑ ታይተዋል።
ደራሲዋ ማህሌት ጌታቸው(መልሕቅ)ና “ጎልያድ እማን ፍታት” የተሰናሰኑበት የሕይወት ገጽታ ከመቅድሞቿ በተለይ መንገድ ነው። “ይህን መጽሐፍ ስጽፍ ሀዘን ጥላውን አጥልቶብኝ…በመከፋት የልብ ስብራት ውስጥ በአንድ ዓይኔ ሆኜ ነበር የጻፍኩት” በማለት በሕይወት ጊዜ ውስጥ የተቀዳውን መራራ ጽዋ፤ ዛሬ በጣፋጭና በመልካም የደስታ መዓዛ ተለውጦ ለማየት ስለመብቃቷ ታወሳለች። ግጥም ለገጣሚው ያበጠውን የውስጣዊ ስሜት ማስተንፈሻ የሰላም መርፌ ነው። ከሌሎች የጥበብ ሥራዎች በተለየም ውስጣዊ ማንነትና ስሜትን በማንጸባረቅ እኔነትን አጉልቶ የማሳየት ባህሪ አለው። በገጣሚው ግጥም ውስጥ የራሳችንን የሆነው የሕይወት እንዝርት ሲሾር እንመለከትበታለን። የደራሲዋ የግጥም ስብስቦች በብዛት ከራሷ ሕይወት የቀዳችው ቢሆንም እያንዳንዳችን እራሳችንን እናገኝባቸዋለን። በየጊዜው ውስጣዊ ስሜቶቿን በግጥም ስንኞች እያሰፈረች በማህበራዊ ሚዲያው የቲክቶክ መንደር ብቅ በማለት ስሜቷን ለተከታዮቿ ታጋራቸው ነበር። ይህም በሚያዩዋት ዘንድ መልካም አጋጣሚና እድልን ፈጥሮላታል። ሦስተኛ ልጇ የሆነውን ይህን የግጥም መድብል ለመጽሐፍነት እንዲበቃ የረዷትም እኚሁ በቲክቶክ መንደር የሚያውቋትና የሥራዎቿ አድናቂ የሆኑ ወጣቶች ስለመሆናቸው ተናግራለች። በወቅቱ ከነበረችበት የድባቴ ዓለም የልብ ስብራቷን ተመልክተው፤ እነዚህ የግጥም ሥራዎችሽ እንደ ንፋስ ላይ አቧራ በነው መቅረት የለባቸውም በማለት፤ ሊያ ግሩፕና ሞዴል ዞላን ጨምሮ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ በርካቶች ተሰባስበው የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ “ጎልያድ እማን ፍታት” ታትሞ ለዚህ ወግ ማዕረግ ሊበቃ ሆነ።
ሰሞነኛው የግጥምና የጥበብ ፍቅር ጠቢባኑን ብቻም ሳይሆን በተለያዩ ጊዜያት የሀገር ባለውለታ የነበሩ ጀግኖችንም በድጋሚ ያስታውሰን ይዟል። በመጽሐፍ ምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት የቀድሞው የምሥራቅ እዝ የኪነት ቡድን አባላት ስለመገኘታቸው ከላይ ጠቆም ለማድረግ ሞክረን ነበር። ታዲያ እዚህ የመገኘታቸው ምስጢር ግብዣ ብቻ አልነበረም። ‘ጀግና ጀግናን ይወልዳል’ እንዲሉ የደራሲዋ ወላጅ አባት ድምጻዊ ጌታቸው ተሰማ የኪነት ቡድኑ አባል የነበረ በመሆኑ ነው። በመድረኩ ከታደሙ ከእነዚህ አባላቱ መሃከል አንዱ የነበረው ወልደ አማኑኤል ዱባለ እንዲህ ሲል በጥቂቱ ያስታውሰዋል፤ “ከዛሬ 40 ዓመታት በፊት የምሥራቅ እዝ የኪነት ቡድን ለሀገር የሚዋደቁ ጀግና የጦር ሠራዊቶችን ብቻም ሳይሆን በኪነ ጥበቡ አንቱ የተባሉ የጥበብ እንቁዎችንም ሲያፈራ የነበረ ነው። የመንግሥት ለውጥ ሲመጣ ግን እንደቀልድ የቀድሞ የደርግ ሠራዊት ተብለን ተበታተን። ከጊዜያት በኋላም አንድ አስደንጋጭ ነገር ገጠመን። በወቅቱ ኮከብ ድምጻዊና የቡድኑ የመድረክ ፈርጥ የነበረው ግርማ ከበደ፤ ዞር ብሎ የሚያየው አጥቶ ከጎዳና ወድቆና በመጨረሻም ሞቶ ተገኘ። አስክሬኑ ምኒልክ ሆስፒታል ከተመረመረ በኋላ ማዘጋጃ ሊቀብረው ሲሰናዳ ሕልፈቱን ሰማንና ተሰባስበን መጣን። በክብር ግብዓተ መሬቱን ከፈጸምን በኋላ ለምን ቡድኑን ዳግም አናቋቁመው የሚል ሃሳብ ተነስቶ፤ ዳግም ወደምንወደው ሕዝብና ሙያ ተመለስን። ከአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮም እውቅናን አግኝተን ዛሬ በአራት ኪሎ፤ በራሳችን ቤት ውስጥ ተሰባስበን በመሥራት ላይ እንገኛለን። ይህ የመጽሐፍ ምረቃ ለኛ ትልቅ ትርጉም አለው። የእርሷ አባትና የኛ ጓደኛ የነበረው ጌታቸው ተሰማ…ምን ነበር ኖሮ ይሄን ባየ…ሁለገብ የጥበብ ልጅ ነበር። በመረዋ ድምጹ ብቻ ሳይሆን በሙዚቃ መሳሪያውም በኦርጋን፣ በክራር፣ በጊታር፣ በድራምና ሳክስፎኑ ሁሉ ችሎታው ወሰን አልባ ነበር። ነገር ግን 1979ዓ.ም የኪነት ቡድኑ ለኤርትራው ጦርነት ቅስቀሳ ወደ ሰሜኑ ሄዶ ከተገደሉ 17 ሰዎች መሃከል፤ አንዱ እርሱ ሆነና እንደወጣ ሳይመለስ ቀረ። ልጁ ልጃችን ናትና ደስታው የኛም ጭምር ነው…” ሲል፤ ሁሉንም ከትዝታ ቀድቶ በእውነተኛ የስሜት ቋጠሮ ገለፀው።
ደራሲ ማህሌት ጌታቸው በ”ጎልያድ እማን ፍታት” ክንብንብ አምራና አሸብርቃ፤ በግጥም ሥራዎቿም ተሞሽራ ብትታይም፤ መድረኩ ግን የእርሷ ብቻ አልነበረም። ጀማሪና እውቅ ገጣሚያን በመድረኩ ተፈራርቀውበታል። ግሩምና አንጀት አርስ የግጥም ሥራዎች ተደምጠዋል። በዚህ ወቅት ከታዳሚነቱ ባሻገር የተሳታፊነቱንም ዕድል በማግኘት ጥቂት ነገሮችን ለማለት የቻለው አንደኛው የጥበብ ሰው ገና ስንመለከተው የ90ዎቹ የሙዚቃ ጠረን ትውስ እያለን በትዝታ ወደኋላ እንድንጓዝ የሚያደርገንና የደራሲዋ አብሮ አደግ የሆነው ድምጻዊ ቃቂ ተስፋዬ ነበር። መቼም አዳራሹ በሐረር ክዋክብት፤ በድሬ ጠበብት ደምቋልና ቃቂ ተስፋዬም ስለ ሐረር አውርቼ እንዳልጠግብ ሰምቼ እንዳልረካ የሚያደርጉኝ ብዙ ምክንያቶች አሉኝ ሲል “ያልተበረዘች ሀገር፤ ያልተበረዘች ኢትዮጵያ ናት። አባቴ ክርስቲያን እናቴ ሙስሊም…ፍቅር አካል ለብሶ የቆመባት…ሀገር በግጥም ይገነባልና” በማለት እንዲህ ሲል ስለ ሐረር ገጠመላት፤
ሰው ሲሆን ለሀገሩ እንግዳ፤
ታውቃለች ሁሉን አቅርባ አላምዳ።
የሀረሯ ወጣት ቆንጂት፤
ቤት ለንግዳ ስትል አቤት።
ድሪያው ሽርጡ ሲያምርባት፤
ውብ ክንብንብ ጸጉሯ ሸፍኗት።
ሥርዓት ባህሏን አክባሪ፤
አየሁኝ ቆንጆ ከሐረሪ።
ከድሬ ብንወጣም ከሀረር ብንርቅም፤
እንደ አለማያ ሀይቅ ፍቅራችን አይደርቅም።
በምሥራቅ ፀሐይ ጀንበር ደምቃ፤
በጀጎል ግንብ ስር ተደብቃ።
የኖረች ሐረር ውብ ከተማ፤
ውሃ እንጂ ማን ፍቅር ሊጠማ።
በርግጥም ቃቂ አልተሳሳተም። እንኳንስ ሕዝቧና በንፉግነትና በአስቀያሚነት የምንስላቸው ጅቦችም እንኳ የሐረርን አፈር እረግጠው አየሯን ሲምጉ በፍቅር ውቃቢ ተለክፈው ፍቅር ፍቅር ይሸታቸዋል። መሶብሽ መሶቤ፤ ኪስህ ኪሴ ነው እያሉ ተሳስቦ የመኖርን ኢትዮጵያዊነት ዛሬም ቢሆን ከሐረሮች ማጀት አልተንጠፈጠፈም። ፍለጋ ብንወጣ ምናልባትም የምናገኘው እዚያ ይሆናል።
በእለተ ቅዳሜዋ ረፋድ፤ የጥበብ ሰዎችንና ወዳጅ ዘመዱን ከሀገር ፍቅር ያሰባሰበው ዋነኛ ጉዳይ የ”ጎልያድ እማን ፍታት” የግጥም መድብል ምረቃ ስለመሆኑ አይዘነጋም። ከነበሩ በርካታ ዝግጅቶች መገባደጃ ላይ የምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ተካሂዷል። አንጋፋውን የኪነ ጥበብ ደጀን ሥዩም ተፈራን ጨምሮ ሌሎች መራቂ የክብር እንግዶችም በጋራ ሆነው ከታዳሚው ፊት በመቆም መጽሐፉን መርቀው ከመልካም ምኞት ጋር አብስረውታል። “ከመሞቴ በፊት አሥር መጽሐፍትን የመጻፍ እቅድ አለኝ” ስትል በቀልድ ቢጤ የታጀበውን እውነተኛ ሕልሟን ጠቆም ያደረገችው ደራሲ ማህሌት ጌታቸው፤ በሴትነቷ በበቀሉ መንጠቆዎች ሳትያዝና ለስንክሳሮቿ ሳትረታ፤ ሰፊውን የጥበብ አድማስ ዛሬም አሻግራ ትመለከታለች። ከዚህ በኋላ በርካታ መጻሕፍትን ጽፋ የማበርከት ተስፋን እንደሰነቀች አሁን አንድ በጅምር ያለ ሥራ ስለመኖሩ ተናግራለች። የሴት ልጅ ጥቃት የሚያንገበግባት በመሆኗ፤ በጅምር ያለው ይህ መጽሐፏም በዚሁ ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው። አሁን ብዙ የሞራል ስንቅና ተስፋን ተሞልቻለሁና እስከ አንድ ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ አራተኛውን ልጄን እታቀፋለሁ ስትል በልበ ሙሉነት ገልጻለች።
ጥበብ ውበትና ፍካት ለጥበብ እጆች፤ ዳርቻ አልባ ፍቅር ወሰን አልባ ሰላም ለሀገር ልጆች፤ የማይነጥፍ ብዕር የማያልቅ ማህደር ለጥበብ ደጆች…በማለት ብሩህ ተስፋና ለምለም ምኞታችንን በማስከተል፤ በስተመጨረሻም ከ”ጎልያድ እማን ፍታት” የግጥም መድብል አንደኛውን ገጽ በመግለጥ ይቺን ግጥም ጋበዝናችሁ።
አትሳቅ
የጥርስ ነጸብራቅ ከሩቅ እየጠራ፤
እንደ ሰብአ ሰገል ያመጣል እያበራ።
ስለዚህ አትሳቅ ፈገግታህ ያመኛል፤
ልትሔድ ነው እያለ ያመላልሰኛል።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ኅዳር 27 ቀን 2016 ዓ.ም