‹‹የኃይል መቆራረጥ፤ የመለዋወጫ ችግር እና ስርቆት የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ድርጅትን እየፈተኑት ነው››አቶ አክሊሉ ሂቢሶ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ተወካይ

 የባቡር ትራንስፖርት በርካታ ሰዎችንና ዕቃዎችን ለማጓጓዝ ተመራጭ የትራንስፖርት ዘርፍ ነው:: ኢትዮጵያውያንም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ከሆኑ ሰንበትበት ብለዋል። የባቡር ትራንስፖርት የተጀመረው እኤአ በ1820 በእንግሊዝ ሀገር መሆኑ ይነገራል። ጅማሮው በእንግሊዝ አገር ይሁን እንጂ፣ ኢትዮጵያም በበኩሏ በባቡር ትራንስፖርት ተጠቃሚነት ከመቶ ዓመት በላይ ያስቆጠረ ታሪክ እንዳላት የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ።

ኢትዮጵያ በኢትዮ ጅቡቲ የባቡር መስመር ዝርጋታ በባቡር ትራንስፖርት በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረች ሲሆን፤ በኋላም በ2008 ዓ.ም የቀላል ባቡር የትራንስፖርት አገልግሎት በአዲስ አበባ ከተማ መሰጠት ተጀምሯል።

የቀላል ባቡር አገልግሎት መጀመሩ የትራንስፖርቱን ችግር ከመቅረፉ ባሻገር ለኢኮኖሚ እድገትና ለማኅበራዊ ለውጥም ጉልህ ፋይዳ እንዳለው በወቅቱ ተስፋ ተጥሎ ሲገለጽ ነበር።

የከተማዋን የትራንስፖርት እጥረት ለማቃለል ተገንብቶ አገልግሎት የጀመረው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት አገልግሎት CREC (China Railway Group Limited) ከተባለ የቻይና ኩባንያ ጋር EPC/Turn­key/ የግንባታ ስምምነት ተፈራርሞ ጥር 23 ቀን 2003 ዓ.ም የግንባታ ሥራውን መጀመሩም የሚታወስ ነው::

በ475 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የተገነባ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 85 በመቶ የቻይና የገቢ-ወጪ ባንክ (China EXIM bank) በብድር የተገኘ ሲሆን 15 በመቶ በኢትዮጵያ መንግሥት የተሸፈነ ነው:: ይህ የባቡር መስመር 34 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው በሁለት አቅጣጫዎች የሚጓዝ፤ የምሥራቅ-ምዕራብ መነሻ ከአያት አደባባይ መዳረሻው ጦር ኃይሎች ሆስፒታል ሲሆን 17 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው::

የሰሜን-ደቡብ መስመር መነሻ ከዳግማዊ ምኒሊክ አደባባይ መዳረሻው ቃሊቲ ሲሆን 16 ነጥብ 59 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው:: ሁለቱ መስመሮች ከመስቀል አደባባይ እስከ ልደታ ቤተክርስቲያን 2 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር የጋራ ሀዲድ ይጠቀማሉ::

የቻይና ስታንዳርድ ጌጅ 1 ነጥብ 435 ሚሊ ሜትር ስፋት ያለው ባለ ሁለት ሀዲድ በመሬት፤ በዋሻ ውስጥ እና በድልድይ የሚጓዝ ሲሆን የእግረኛ እና የመኪና ማቋረጫዎች አሉት::

የዲዛይን ፍጥነቱ 80 ኪሎ ሜትር በሰዓት የኦፕሬሽን ፍጥነቱ ደግሞ 70 ኪሎ ሜትር ነው:: 39 የመሳፈሪያ እና መውረጃ ጣቢያዎች ያሉት ሲሆን 27 በመሬት ላይ 9 በድልድይ ላይ 2 በከፊል ድልድይ እንዲሁም አንድ በዋሻ የሚገኙ ጣቢያዎችን ይዟል::

39 የትኬት መቁረጫ ቢሮዎች፣ 18 የኃይል መቀበያ ጣቢያዎች፣ 22 ሊፍቶች እና 12 እስካሌተሮች ያሉት ሲሆን ለ18 ሰዓታት በሦስት ፈረቃ አገልግሎት ይሰጣል::

በ2008 ዓ.ም መጀመሪያ የኦኘሬሽን ሥራውን በይፋ የጀመረው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት አገልግሎት ሸን ዘን ሜትሮ ግሩፕ የተባለ የቻይና ኩባንያ ለ3 ዓመታት የማስተዳደር እና ጥገና ውል ሥራ (ኮንትራት) ሠርተዋል:: አንድ ነጠላ ባቡር በአንድ ጊዜ 317 መንገደኞች ማጓጓዝ የሚችል ሲሆን በአጠቃላይ 41 ባቡሮች አሉት ::

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡት ትራንዚት አገልግሎት አሁናዊ ሁኔታን በተመለከተ ከተቋሙ የኦፕሬሽን ማዕከል ዳይሬክተርና የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ተወካይ ከሆኑት አቶ አክሊሉ ሂቢሶ ጋር ቆይታን አድርገናል::

 አዲስ ዘመን ፦ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት አሁናዊ ሁኔታ ምን መልክ አለው?

አቶ አክሊሉ፦ ሁላችንም እንደምናውቀው አዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት ድርጅት መስከረም 2008 ዓ.ም ጀምሮ በይፋ የትራንስፖርት አገልግሎቱን ለከተማው ትራንስፖርት ተጠቃሚዎች በመስጠት ላይ ይገኛል:: ላለፉት 9 ዓመታትም የትራንስፖርት አገልግሎቱን ለብዙኃን ተጠቃሚዎቹ ምቹ ቀልጣፋና አስተማማኝ በሆነ መልኩ በመስጠት በከተማው ውስጥ ያለውን የትራንስፖርት ችግር በማቃለል ላይ የሚገኝ ነው::

ይህ የትራንስፖርት አማራጭ በከተማዋ ዋና ዋና በሆኑ ሁለት መስመሮች ማለትም ከጦር ኃይሎች አያት እንዲሁም ከቃሊቲ እስከ ጊዮርጊስ ድረስ ባሉት መስመሮቹ ከፍተኛ የተሳፋሪ ቁጥርን በማመላለስ በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ የበኩሉን ጉልህ ሚናና ድርሻ እየተጫወተ ያለ ድርጅት ነው::

ድርጅቱ ሥራውን ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ተሳፋሪዎችን እያገለገለ ሲሆን ይህንንም በአኃዝ ለመጥቀስ በቀን ከ 150 ሺ በላይ የሚሆን ሰው አሁን ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች ቁጥሩ ዝቅ ብሎ እስከ 70 ሺ ሰው አገልግሎት እንዲያገኝ እየሠራ ነው:: በነገራችን ላይ የትራንስፖርት ድርጅቱ ሥራውን በሙሉ አቅሙ መሥራት ቢችል በቀን እስከ 2 መቶ ሺ ሰው ማጓጓዝ ይችል ነበር:: ይህንን የሚደግፍ መሠረተ ልማት የሰው ኃይልና ቴክኖሎጂ ቢኖረውም በአንዳንድ ምክንያቶች ግን የአቅሙን ያህል መሥራት እንዳይችል ሆኗል::

አዲስ ዘመን ፦ አሁን ላይ የትራንስፖርት ድርጅቱ የአቅሙን ያህል እየሠራ ላለመሆኑ ምክንያቶቹ ምንድን ናቸው?

አቶ አክሊሉ፦ አሁን ላይ ድርጅቱ የሚሰጠው አገልግሎት እየቀነሰ በመምጣቱ የተሳፋሪዎቹም መጠን በዛው ልክ እየወረደ መጥቷል:: ይህም በዋናነት አገልግሎቱ ሲጀመር የተገዙ ባቡሮች ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት አገልግሎትን ቢሰጡም አስፈላጊው መለዋወጫ አልቀረበላቸውም፤ ይህ ሁኔታ ደግሞ በባቡሮቹ ላይ በጉልህ የሚታዩ የቴክኒክ ችግሮች እያመጣ ስላለ ባቡሮቹ አገልግሎት እንዳይሰጡ ተደርገዋል:: ይህ ሁኔታ ደግሞ አሁን ላይ የትራንስፖርት አገልግሎቱን በውስን ባቡሮች እንድንሰጥ አስገድዶናል::

ያለፉት ዘጠኝ ዓመታት አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩት ባቡሮች ደግሞ በጊዜ ሂደት መጠገን ስላለባቸው ይህንን ጥገና ደግሞ ለማድረግ ብዙ አሳሪ ምክንያቶች በተለይም የመለዋወጫው ጉዳይ አልባት ሊያገኝ ባለመቻሉ በውስን ባቡሮች እየሠራን ነው:: ጥቂትም ቢሆኑ አስተማማኝ ቴክኒካል ብቃት ላይ ናቸው ብለን ያመንባቸውን ብቻ በሥራ ላይ አውለን ኅብረተሰቡ አገልግሎት እንዲያገኝ እያደረገን ነው::

አዲስ ዘመን ፦ የባቡር ትራንስፖርት ዘርፉ በብዙ መንገዶች እየተፈተነ እንዳለ ነግረውናል፤ አሁን ላይ የባቡር ትራንስፖርቱ ፈታኝ ችግር ብለው ለይተው የሚያስቀምጡት ምንድን ነው?

አቶ አክሊሉ፦ ከላይ የጠቀስኳቸው ፈተናዎች በሙሉ ለድርጅቱ ከባድና የሕልውና ጥያቄ የሚያስነሱ መሆናቸው ሊሰመርበት ይገባል:: ባቡሩ ሥራውን ሲጀምር በ8 ደቂቃ ጣቢያዎች ላይ መድረስ ይችል ነበር፤ ከዛ ግን 10፣ 12፣ 15 ደቂቃዎች እየተባለ ተራዝሟል:: ዛሬ ላይ ግን በዚህ ደረጃ በጣቢያው ላይ የሚደርስ ባቡር ሊኖረን አልቻለም:: የዚህ ትልቁ ምክንያት ደግሞ የባቡሮች ቁጥር መመናመን ነው:: አሁን ላይ ከላይ እንደገለጽኩት በመለዋወጫ እጥረት የቆሙት ባቡሮች ቁጥራቸው 60 በመቶ ያህል ነው:: ይህንን ባብራራልሽ አገልግሎቱን ስንጀምር 41 ባቡሮች ነበሩን አሁን ላይ ሥራ እየሠሩ ያሉት 18 ብቻ ናቸው ሌሎቹ ቆመዋል:: በመሆኑም እንደ ድርጅት ዋና ችግር ብለን ከለየነው መካከል ይህኛው ተጠቃሽ ነው::

ሌላው በተደጋጋሚ የሚያጋጥመው የኃይል መቆራረጥ ሲሆን በዚህ ምክንያት ባቡሮች በመንገድ ላይ ይቆማሉ ፤ ተሳፋሪዎችም ይጉላላሉ:: ሌላው በመሠረተ ልማቶቹ ላይ እየደረሱ ያሉት የትራፊክ አደጋዎችና ስርቆቶች ናቸው:: በዚህም የኃይል ተሸካሚ ገመዶች ይሰረቃሉ፤ የመገናኛ ኬብሎችም ይወሰዳሉ የሚደርሱ የትራፊክ አደጋዎችም በባቡሩ እንዲሁም በሀዲዱ ላይ ከፍተኛ ጉዳትን ያስከትላሉ:: አሽከርካሪዎች አጥር ጥሰው ይገባሉ፤ መሠረተ ልማቱ ላይ ጉዳት ይደርሳል፤ አንዳንድ ማቋረጫዎች ላይ ከባቡር ጋር የመጋጨት ሁኔታዎች ይፈጠራሉ:: ይህ ሁኔታ ደግሞ በሁለት መንገድ ጉዳት ያደርሳል:: አንደኛው በንብረቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ ሲሆን፤ ሁለተኛ የአገልግሎት አሰጣጡ እንዲረበሽ ወይም እንዲስተጓጎል ያስገድዳል:: በዚህም ደንበኞች ከትንሽ ደቂቃ ጀምሮ እስከ ሰዓታት ድረስ ይጉላላሉ:: ተቋሙም የሚያጣው ገቢ ቀላል አይደለም::

አዲስ ዘመን ፦ ይህ እንግዲህ ከባድና ለድርጅቱም ፈተና የሚሆን ችግር ነውና ለመፍታትስ የተደረገው ጥረት ምን ይመስላል?

አቶ አክሊሉ፦ ይህንን ከባድ ችግር ለመፍታት ለበርካታ ጊዜያት ከተለያዩ አካላት ጋር ሰፊ ውይይቶችን አድርገናል ቸግሮቹንም ለመቅረፍ ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ ነው:: በመሆኑም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቀው መለዋወጫ እስካልተሟላ ድረስ ግን አገልግሎቱን በሚፈለገው ልክ መስጠቱ የሚቻል አይመስለኝም:: የኃይል መቆራረጡን አልባት ለመስጠት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር እየተሠራ ያለ ሥራ አለ:: በመሠረተ ልማቱ ላይ እየደረሱ ላሉ ስርቆቶችንም ለመከላከል ከመጀመሪያ ጀምሮ የፖሊስ ጥበቃ የነበረ ቢሆንም በመካከል ተቋርጦብን ብዙ ሀብቶቻችንን አጥተናል:: ከግንቦት ወር ጀምሮ ግን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመነጋገርና በመስማማት በመሠረተ ልማቱ ላይ የ 24 ሰዓታት የፖሊስ ጥበቃ እንዲኖር ተደርጓል:: ለዚህም አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን 1ሺ 5 መቶ የሚሆኑ የፖሊስ አባላትን ለጥበቃ በማቆሙ አሁን ላይ ስርቆቱ በጣም ቀንሷል::

አዲስ ዘመን ፦ ከ 41 ባቡሮች መካከል አሁን ላይ አገልግሎት እየሰጡ ያሉት ከግማሽ በታች የሚሆኑት ናቸው ፤ እንደው ችግሩ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ በሥራ ላይ ያሉትስ ባቡሮች ላለመቆማቸው ዋስትና አለ?

አቶ አክሊሉ ፦ ትክክል ነው እነዚህ ባቡሮች ብቻቸውን ጫና እየበዛባቸው ነው፤ የመለዋወጫ እጥረቱ በዚሁ ከቀጠለ ደግሞ አንቺም እንዳልሽው ባቡሮቹ ላለመቆማቸው ዋስትና የለም:: ነገር ግን የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ድርጅት ከነሐሴ 13 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ወደከተማ አስተዳደሩ ገብቷል:: ከዛን ጊዜም ጀምሮ ከተማ አስተዳደሩ በተለያዩ መልኮች ድጋፉን እያደረገ ሲሆን ተቋሙን ሪፎርም ለማድረግ አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ያሉ ችግሮችንም ለመፍታት በጀት ከመመደብ ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ ነው:: በዚህም የቆሙ ባቡሮች መለዋወጫ ተገዝቶላቸው ተጠግነው ድርጅቱ በሙሉ አቅሙ አገልግሎቱን እንዲሰጥ የራሱን ጥረት እያደረገ ነው::

አዲስ ዘመን ፦ ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት የባቡር ትራንስፖርቱ በተለያዩ ፈታኝ ችግሮች ውስጥ ቢሆንም አገልግሎቱን አላቋረጠምና እንደው በዚህ ሥራ ውስጥ ጠንካራ ጎናችን ነበር ብለው የሚያነሱት ነገር ይኖር ይሆን?

አቶ አክሊሉ፦ ምንም እንኳን ድርጅቱ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ እያለፈ ቢሆንም አገልግሎቱ ግን በምንም መልኩ ሳይቆራረጥ ባሉት ባቡሮች ሥራው እየተሠራ ነው:: የሚገርመው ነገር ይህ አገልግሎት እየተሰጠ ያለው ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት አንድ መለዋወጫ እንኳን ሳይገዛ ነው:: ከዚህ አንጻር 70 ሺ ሰዎችን በ32 ከሚሎ ሜትር ላይ ማመላለስ ለእኛ የጠንካራ ጎናችን ማሳያ ነው::

በዚህ ከባድ ችግር ውስጥ ሆነን በቀን ለ70 ሺ ሰው አገልግሎት መስጠት ማለት እንደ ቀላል የሚወሰድ አይደለም:: የባቡር ትራንስፖርቱ በመለዋወጫ እጥረት ብቻ ሳይሆን እየተፈተነ ያለው በኬብል ስርቆት በመሠረተ ልማቱ ላይ እየደረሰ ባለው የትራፊክ አደጋ ነው::

ድርጅቱ ባለሙያዎችን እያበቃ በውስጥ አቅሙ የሚሰጣቸው የጥገና አገልግሎቶች በጠንካራ ጎንነት ሊነሱለት የሚገቡ ናቸው:: በዚህም እስከ አሁን ድረስ መለዋወጫዎችን በማሻሻል (ሞዲፋይ) በማድረግ እንዲሁም አንዱን በአንዱ በመተካት ባለሙያዎች እውቀታቸውን እየተጠቀሙ ጥገናዎችን እያከናወኑ ነው ድርጅቱን እዚህ ያደረሱት::

ሌላው አሁን ላይ የባቡር አገልግሎቱ በሙሉ በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች እየተመራ መሆኑም የጥንካሬው ማሳያ አድርጎ መውሰድ ይቻላል:: የአስተዳደር (ማኔጅመንት) አካላት በሙሉ ኢትዮጵያውያን ናቸው፤ ከውጭ አገር የመጣና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለውን ቴክኖሎጂ ወደ ሀገራችን በማምጣትና በማላመድ የባቡር ስምሪቱን ጥገናውን ኦፕሬሽኑን የጥንቃቄ መርሆዎቹን በጠቅላላ አስፈላጊ የሆኑትን በሙሉ ኢትዮጵያውያኑ ባለሙያዎች እንዲተገብሯቸው በማድረግ ላይ እንገኛለን::

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያውያን ባቡር አሽከርካሪዎች እንዲሁም ስምሪት ባለሙያዎችና የጥገና ሠራተኞች እንዲሁም የአስተዳደር አካላት እየሠራን እንገኛለን:: አሁን ላይ ምንም ቻይናውያን የሉም::

አዲስ ዘመን ፦ ችግሮቹን ለመቅረፍ ታዲያ ምን እያደረጋችሁ ነው?

አቶ አክሊሉ፦ የድርጅቱ ችግር ይታወቃል፤ ትኩረትም አግኝቶ በመሠራት ላይ ነው:: ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ አባላት ያሉበት የቴክኒካል ኮሚቴም የችግሩን አሳሳቢነት ተገንዝቦ የመጨረሻ የውሳኔ ሃሳቡን አሳልፏል:: ቦርዱም አቅጣጫ አስቀምጧል:: በዚህም የቆሙት ባቡሮች ወደ ሥራ እንዲገቡ ይሆናል ብለን እናስባለን:: ከዛ ውጪ ደግሞ ከቻይና መንግሥት ጋር በመነጋገር 7 አዳዲስ ባቡሮችን ለማግኘት ጥረቶች እየተደረጉ ነው:: የአዲስ ባቡር ግዢንም በተመለከተ አቅጣጫ ተቀምጦ ጥናቶች አሉ:: በዚህም ድርጅቱ አቅሙን አጎልብቶና ሙሉ ኃይሉን ተጠቅሞ በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ ያለውን ችግር ለማቃለል ይሠራል::

አዲስ ዘመን ፦ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ድርጅት አገልግሎቱን የማስፋት እቅድ አለው?

አቶ አክሊሉ፦ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት ድርጅት የመሠረተ ልማት ዝርጋታው ሁለተኛ ክፍል (ፌዝ 2 ) አለው:: ይህም ማለት እስከ 70 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባቡር መሠረተ ልማት ዝርጋታ ነው:: ነገር ግን ከአራት ዓመት በፊት ጥሩ ሂደት የነበረው የቻይና ኤግዚም ባንክም ብድር እያመቻቸ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ሀገራችን በገባችባቸው የተለያዩ ችግሮች ምክንያት ሥራው ቆሟል::

በጠቅላላው ግን ይህ ክፍል ሁለት ግንባታ ሲከናወን አሁን በሥራ ላይ ያሉ ባቡሮችም ይሁኑ አዳዲስ የሚገዙትን እንጠቀማለን:: በነገራችን ላይ ነባሮቹ ባቡሮች የቆይታ ጊዜ አላቸው ምን ያህል ኪሎ ሜትር ድረስ ነው ማገልገል የሚችሉት የሚለውም ይታወቃል:: ያ እስኪደርስ ባሉት እንጠቀማለን ማስፋፊያው ሲጠናቀቅ ደግሞ ሌሎችንም አዳዲስ ባቡሮችን እናሰማራለን::

አዲስ ዘመን፦በቀጣይ የሚገነባው ሁለተኛና ሦስተኛ ምዕራፍ የባቡር መሠረተ ልማቶች ከዚህኛው የሚለዩበት ሁኔታ ይኖር ይሆን?

አቶ አክሊሉ፦ አዎ ይለያሉ ፤ለምሳሌ ሁለተኛው ምዕራፍ የሚሠራው በሜትሮ ስታይል ከመሬት በታች ሆኖ ነው :: ለምሳሌ ፒያሳ ላይ ያለው ሽሮሜዳ ድረስ ይዘልቃል፤ አያት የሚያበቃው እስከ ለገጣፎ እንዲወጣ ይሆናል፤ በተመሳሳይ ጦርኃይሎች ላይ የሚያበቃው እስከ ጀሞ እንዲሁም የቃሊቲው ቂሊንጦ ድረስ አገልግሎቱን እንዲሰጥ ተደርገው እንደሚገነቡ ነው ፕላኑ የሚያሳየው::

የባቡር ኢንዱስትሪ ለአንድ ሀገር እድገት ወሳኝ ሚና ያለው ከመሆኑ ጋር በተያያዘ እንዲሁም እድገትን ተከትለው የሚመጡ የትራንስፖርትና የመንገድ መሠረተ ልማት ፍላጎቶችን ለመመለስ የሚጠቅም ከመሆኑ አንጻር ይህ የባቡር ማስፋፊያ ፕሮጀክት ሥራው እንዲጀመር አጥብቀን እንፈልጋለን::

ብዙ ሰዎችን በአንዴ የሚያመላልስ፤ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን የሚጠቀም፤ ነዳጅ የማይፈልግ ከመሆኑ አንጻር ዶላርን በማስቀረት የአየር ብክለትን ከመከላከል አንጻር ሚናው የጎላ በመሆኑም ባቡር መስመሩ መገንባት አለበት:: በእርግጥ ከፍ ያለ የአገር አቅምን የሚጠይቅ ቢሆንም ይገነባል የሚለው ተስፋችን ግን ሙሉ ነው::

አዲስ ዘመን፦ አሁን ላይ የባቡር አገልግሎቱን ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን እየተዳደረ ከመሆኑ አንጻር የባለሙያዎችን አቅም በማሳደግ እና ቴክኖሎጂዎችን በማላመድ በኩል የተሄደበት ርቀት ምን ያህል ነው?

አቶ አክሊሉ፦ የቻይናው ሼንዘን ሜትሮ ተቋም ድርጅቱን ሲያስተዳድር በነበረበት ጊዜ የኦፕሬሽንና የጥገና አገልግሎትን ነበር በኮንትራት የወሰደው:: በዚህም ለሦስት ዓመት ያህል ቆይቷል፤ እኛ ደግሞ የመጀመሪያው ዓመት ላይ አብዛኞቹን ቴክኖሎጂዎች ለመቆጣጠር ችለን ነበር:: ለምሳሌ የባቡር ስምሪቱ የጊዜ ሰሌዳ የሚባለውን 95 በመቶ በኮምፒውተር የተደገፈና ማዕከል ላይ የሚሠራ ከመሆኑ አንጻር በመጀመሪያው ዓመት ነው ልጆቻችን የተማሩት፤ በአሁኑ ወቅትም ራሳችን የምንሠራው ሥራ ሆኗል::

የባቡር ማሽከርከርን ሙያን ሙሉ ለሙሉ በመጀመሪያው ዓመት አውቀናል:: ዋናውና መሠረታዊውን ጥገናም ቢሆን በራሳችን ልጆች ሙሉ በሙሉ እያሠራን ከመሆኑም በላይ አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎችንም እንዲሠሩ እየተበረታቱና እየሠሩም ነው:: በዚህም ሽግግሩ ትልቅ አቅም የፈጠረልን ነው ማለት ይቻላል::

አዲስ ዘመን፦ እንደ ድርጅት ከገቢ አንጻር የታለመለትን ግብ እየመታ ነው ማለት ይቻላል ?

አቶ አክሊሉ፦ ባደጉትም ሆነ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ሲሰጡ ዋና ዓላማቸው የዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎችን ኢኮኖሚ ወይም እንቅስቃሴ ማሳለጥ ነው:: በተለይም በታዳጊ አገሮች ላይ የብዙኃን ትራንስፖርት ኢኮኖሚውን ለማሳለጥ የሚሠራ እንጂ ትርፍ ይገኝበታል ተብሎ አገልግሎት ላይ የሚውል አለመሆኑ ሊታወቅ ይገባል:: በመሆኑም አብዛኞቹ በመንግሥት ድጎማ የሚኖሩ ናቸው:: መንግሥት ደግሞ እነዚህን ድርጅቶች የሚደጉምበት ዋና ዓላማው ዜጎች ምቹ በሆነ ትራንስፖርት አማራጭ ተጠቅመው በሥራ ገበታቸው ላይ በሰዓቱ መገኘታቸው ለእሱ ትልቅ ትርፍ በመሆኑ ነው::

ከዚህ አንጻር እንደ ከተማ ከየትኛውም የትራንስፖርት አማራጭ የቀነሰ ክፍያን የሚያስከፍለው ባቡር ብቻ ነው:: ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት የተለያዩ የታሪፍ ማሻሻያዎችን አድርገናል ይህም ቢሆን ግን በክፍያ ረገድ ከሁሉም ትንሹ ባቡር ነው::

አዲስ ዘመን፦ በሠራተኞች አያያዝ ላይ የሚነሱ አንዳንድ ቅሬታዎች እንደነበሩ እናውቃለንና እነዚህን ከማረም አኳያ እንደ ማኔጅመንት ምን ተሠራ?

አቶ አክሊሉ፦ኢንዱስትሪው አዲስ ከመሆኑ አንጻር አዲስ ባለሙያዎችና እውቀት ያለበት ተቋም ነው:: አብዛኛው ሰው ወጣት በመሆኑም የተሻለ እውቀትም ያላቸው ናቸው:: እንደ ተቋም ደግሞ ለእነዚህ ባለሙያዎች የተሻለ ነው የሚለውን ሁሉ ይሰጣል:: ለባለፉት ዘጠኝ ዓመታትም የባቡር ትራንስፖርት ተሞክሮ ተብሎ የጣሊያንና የስዊዲን መንግሥት መዋቅር ሠርተው በዛም ሠራተኞች ተበረታተው እንዲሠሩ የሚያስችል ማበረታቻዎች ተደርገዋል:: አሁንም ትራንስፖርት ቢሮ በበላይነት እየመራው በመሆኑ በሚሠራው ሪፎርም ውስጥ አስገብቶታል:: በዚህም የሠራተኞች ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም እየተሻሻለ ይሄዳል ተብሎም ይጠበቃል:: በመሆኑም ኢንዱስትሪውን የሚመጥን ለሠራተኛውም ምቹ የሆነ የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታም የጠበቀ ሥራን ለመሥራት እየጣርን ነው::

አዲስ ዘመን፦ድርጅቱ ካለው ሰፊ ጠቀሜታ አንጻር በእቅዱ መሠረት አገልግሎቱን ያዳርስ ዘንድ ከማን ምን ይጠበቃል ይላሉ?

አቶ አክሊሉ፦ አዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት ድርጅት በጣም ጠቃሚ ፕሮጀክት ነው:: አንድ ሀገርም ከባቡር ትራንስፖርት ውጪ መኖር እንደማይችል ማሰብ አለብን:: በምሥራቅ አፍሪካም የእኛ ቀላል ባቡር የመጀመሪያው ነበር:: የከተማዋን እንቅስቃሴ በማሳለጥ ኢኮኖሚውን በማመጣጠን በኩልም የሚኖረው ሚና በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም:: ስማርት ሲቲ የሚለውንም ከማምጣት አንጻር ሚናው የጎላ ነው::

ነገር ግን ይህንን ያህል ጥቅም ያለው ተቋም ሥራው በታሰበው ልክ እየሄደ ካለመሆኑም በላይ የአቅሙን ያህል አገልግሎት እንዳይሰጥም እየሆነ ነው:: የዚህ ድርጅት ችግር እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድረስ የሚታወቅ ነው፤ በመሆኑም ከመለዋወጫዎቹ በተጨማሪም ይገባሉ የተባሉት 7 ባቡሮች በቶሎ ወደሀገር ቢገቡ አገልግሎቱን በማሳለጥ በከተማዋ የሚስተዋለውን የትራንስፖርት ችግር እንፈታበታለን፤ ሕዝባችንንም የማገልገል አቅማችንን ያሳድግልናል::

በጠቅላላው ቻይናን ጨምሮ የአደጉ አገራት በሙሉ የእድገታቸው መሠረት ባቡር ነው:: ትልልቅ የመንግሥት ባለሥልጣናት ባቡር ነው የትራንስፖርት መጓጓዣቸው:: በመሆኑም የእኛንም አገር ባቡር ትራንስፖርት እዛ ላይ ማድረስ ያስፈልጋል:: ከመሠረተ ልማቱ ጀምሮ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ ግን ደግሞ ችግሮቹ የሚታወቁ በመሆናቸው ዛሬ ተነስተን መሠረተ ልማት ወደማፍረስ አንሄድም፤ ግን ችግሮቹን ፈተን የተሻለ ተቋም ለማድረግ ሁሉም የመንግሥት አካላት በጋራ መሥራት ይኖርባቸዋል::

አዲስ ዘመን ፦ ቀረ የሚሉት መልዕክት ካለ?

አቶ አክሊሉ፦ በሌሎች አገሮች የባቡር ትራንስፖርት ባለባቸው አካባቢዎች ላይ ሰውም ሆነ ተሽከርካሪ ወደመሠረተ ልማቱ እንዲገባ በምንም መንገድ አይፈቀድም:: አጥሩ ውስጥ አይጸዳዱም፤ አይነግዱም፤ ተሽከርካሪም አይገባም:: ለዚህ ደግሞ ዋነኛው አደጋው ከባድ በመሆኑና መሠረተ ልማቱም እንክብካቤ የሚፈልግ ስለሆነ ነው:: ወደእኛ ሀገር ስንመጣ ደግሞ የዚህ ተቃራኒ ነው የሚስተዋለው:: ሰዎች የባቡሩን ጡሩንባ እየሰሙ እንኳን ዳር ይዘው ለማሳለፍ አይፈልጉም፤ አሽከርካሪዎችም ለመተባበር ፍቃደኛ አይሆኑም፤ ንግዶች ይነገዳሉ፤ በመሆኑም መሠረተ ልማቱ የሁላችንም መሆኑን በመገንዘብ ከእኩይ ድርጊቶቻችን ብንታቀብ ጥሩ ነው ::

አዲስ ዘመን፦ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ::

አቶ አክሊሉ፦እኔም አመሰግናለሁ

እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን   ኅዳር 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You