ከኑሮ ውድነት ባሻገር

ኑሮ ተወደደ..ኑሮ ተሰቀለ የሁላችንም የዕለት ተዕለት ሰሚ ያጣ ጩኸታችን እንደሆነ ውሎ አድሮ ከቆመጠጠ ሰነባበተ። ኑሮ ተወደደ ተሰቀለ እያልን እዬዬ..ብንልም፤ዳሩ ግን የተሰቀልነው እኛ እንጂ እሱ አይደለም። ኑሮ መወደዱን እንዲያቆም እንመኛለን…ኑሮ ግን መቼም ቢሆን መወደዱን አያቆምም።

ሁላችንም እራሳችንን ከደሙ ንጹሕ እያደረግን የምናዋድደው እኛው ነንና እሱም መወደድን አይጠላም። መሣሪያ ይዞ እንደወረረን ጠላትም በክተት አዋጅ፤ በሽምቅ ውጊያም የምናሸንፈው አይደለም። መለስ ብለን እንደ ግለሰብ እያንዳንዳችን ኃላፊነታችንን እስካልተወጣን ድረስ የኑሮ ውድነትን ማሸነፍ ዘበት ነው።

ኑሮ ለምን ተወደደ? ስንል ሁሌም ከአፋችንም ከአዕምሯችንም የማይጠፉ ከጥያቄው ቀድመው የሚመጡልን ምላሾች አሉ። ነገር ግን ከእነዚህ ባሻገር በኑሮ ውድነት ውስጥ ሳናጤናቸው እጅና እግራችንን ጠፍንገው ስላሰሩን አንዳንድ ጉዳዮች እናንሳ።

ኑሮ ለምን ተወደደ? አዎን የምናውቃቸው እልፍ መንስኤዎች አሉ። በአጭር መንገድ ለመከበር በሚደረግ ሩጫ ክብረወሰን ሰባሪው ብዙ ሆኗል። ‘ማትረፍ’ ሳይሆን ‘መቦትረፍ’ የብዙ ሰው ስንቅ እራት ሆኗል። ዛሬ የምናየው የኑሮ ውድነት በዚህን ያህል ደረጃ ከፍ ማለቱ የእውነትም ለዚህ የሚያበቃን ምክንያት ኖሮ ሳይሆን ለራሱ ለማደላደል አጋጣሚዎችን የሚጠባበቅ ሰበብ ፈላጊ በመብዛቱ ነው።

በርግጥ ሁላችንም ነጋዴዎች ሆነናል። በአንድም ሆነ በሌላ በኑሮ ውድነቱ ውስጥ እጃችን አለበት። አስተዋፅዖ የምናደርግባት አንዲት ቦታም አለች። እኛ ሁላችንም አንደኛው ቦታ ላይ ገዢ፤ አንደኛው ቦታ ላይ ደግሞ ሻጭ ነን። ሻጭ ስንል የግድ በንግዱ ዓለም የተሠማራ ማለት አይደለም።

የኑሮ ውድነት ማለትም የቁሳቁስ ብቻ እንዳልሆነ ልንገነዘብ ይገባል። ትላንት ሻጭ የነበረው ሰው ዛሬ ገዢ ሆኖ እኛ ጋር ሊመጣ ይችላል፤ ይህ በኑሮ ቀለበት ውስጥ ሁሌም ያለ ነው። የኑሮ መወደድ መንስኤም የሚገኘው በዚሁ ቀለበት ውስጥ ነው። ቲማቲም ጨመረ ብሎ የሽንኩርት ዋጋ የሚጨምር፤ ጤፉ ከየት እንዳመጣው ባናውቅም ዶላር ጨመረ ብሎ የጤፍ ዋጋ የሚጨምር ነጋዴ ብቻም ሳይሆን ቆርቆሮና ሚስማር ተወደደ ብሎ ባረጀ ባፈጀው ቤት ላይ ዋጋ የሚጨምር የቤት አከራይም ተፈጥሯል።

ከኑሮ መወደዱ ይልቅ የኛ ማዛመዱ በዛ። አንዲት ኑሮ ውድነት በኛ ሰበብ እየተባዛች ብዙ እጥፍ ትወልዳለች። ትልቁ ችግራችን እራስ ወዳድነት ነው። በአንዱ ያጣነውን በሌላ ለማካካስ ስንማስን ሙሉ ገበያው እሳት በእሳት ይሆናል። ከአንዲት ቦታ በተለኮሰች እሳት ወደ ሁሉም እየተሰራጨ የሰደድ እሳት ይሆናል።

አንዱ የጅምላ አከፋፋይ የጨመረውን ሂሳብ የለመዱትን ትርፍ ማጣት የማይፈልጉት ተረካቢዎችም፤ የተቀበሉትን ጭማሪ ወስደው ለገዢዎቻቸው በችርቻሮ ያከፋፍሉታል። የስኳርን የዋጋ ጭማሪ የሰማችው ያቺ ምስኪን የጨው ዕቃ እያልን የምናላግጥባት ጨው እንኳን፤ እኔስ ከማን አንሼ ስትል ትከተላለች።

እንግዲህ ማን ቀረ? በአንዲት የበርበሬ መወደድ ምክንያት በድስቱ ውስጥ የሚገኙ አባላት በሙሉ ተባብረው ወጥ ሳይሆን የእሳት እረመጥ ይሆናሉ። ከጤፉ የምትወለደው እንጀራም ምሕረት የላትም ትቀጥላለች። ይህን ከመሰለው የውስጥ ለውስጥ ፍትጊያዎቻችንን አለፍ ስንል፤ የኛ ኑሮ እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ እኛኑ እንዲውጠን ካደረጉን ነገሮች መካከል ሌላ ውጫዊ ተውሳክም አለብን።

የኛን ኑሮ በቁሙ እየገዘገዘው ኑሮ ውድነቱን ያከናነበን ሌላኛው ጉዳይ ‘ሜድ ኢን ፈረንጅ’ መሆናችን ነው። ሥልጣኔ ይሁን የስንፍና መቅኔ ከጉልበታችን ገብቶ ውጭ ውጪውን ማየት አብዝተናል። ከኛ እውቀት የፈረንጅ እውቀት፤ ከኛ ጥበብ የፈረንጅ ጥበብ፤ ከኛ የወይን ጠጅ የፈረንጅ ሀሞት፤ ከኛ ብዕር ይልቅም የፈረንጅ እርሳስ አድምቆ የሚጽፍ መስሎ ይሰማናል። ታዲያ እኛ የፈረንጅ የሆነ ነገር ሁሉ ሲያምረን ኑሮስ ለምን መወደድ አያምረውም?።

የባሕላችንን ብቻ ሳይሆን የአኗኗር ዘያችንንም አመሳቅለነዋል። የኛ የሆነውን ከማምረትና ከመጠቀም ይልቅ የእነርሱን ማከፋፈልና መሸቀጥ አብዝተናል። ገንዘብ ስላለን ብቻ ምንም ሳይመስለን እንደቀልድ የምናደርጋቸው ነገሮች፤ ከኛ አልፈው ማኅበረሰባችንንም መጠራረግ ጀምረዋል። በሀገር ውስጥ የሚመረቱትን ምርቶች እኛ ካልተጠቀምናቸው ማንስ ሊጠቀማቸው ነው?

ለመብላቱም…ለመልበሱም…ለመዋቡም ዓይናችን የሚያየው፤ ልባችንም የሚወደው ባሕር አቋርጦ የመጣውን የሩቅ ተጓዥ ነው። በወርቅ ከተለበጠው ‘ሜድ ኢን ኢትዮጵያ’ ይልቅ በነሐስ በተለበጠው ‘ሜድ ኢን ፈረንጅ’ ኩራት ይሰማናል። ጫማው ቬትንሃም፣ ካልሲውም የጆርዳን፣ ሱሪው ደግሞ ታይላንድ፣ ሹራቡ ከአሜሪካ፣ ቲሸርቱ ካናዳ፣ ኮፍያው ከጀርመን ካልሆነ በቀር ለብሶም የለበሰ የማይመስለው ስንት አለ…በአልባሳቱ ብቻም ሳይሆን በሌላውም። ዓይንና ልባችን በምንዛሪና በግዙፍ ታክስ በሚገቡት ላይ ከሆነ እንዴትስ ኑሮ አይወደድ?

“እኔ እንኳን የሀገር ውስጥ ምርት ብዙም አልጠቀምም…” በማለት የውጭ ምርትን መጠቀም እንደ ልዩ ክብር አድርገው ሲናገሩ የሚታዩና የሚሰሙ ጥቂት አይደሉም። ክፋቱ ያለው የውጭ ምርት መጠቀማችን ላይ አይደለም። ነጋዴውም ሆነ አምራቹ ሁሌም ትርፍን ይፈልጋሉ። የተጠቃሚው ፍላጎት የውጭ ምርቶች ላይ ከሆነ፤ ፍላጎቱን ተከትለው እነርሱም ፊታቸውን ወደ ውጭ ምርቶች ያዞራሉ።

የዛኔ መውጫ መግቢያውን ያጣው የሀገር ውስጥ ምርት ቀስ በቀስ ከገበያው ጨዋታ ውጭ ይሆናል። የሀገር ውስጥ አምራችና ምርትን መገፍተር ማለት በሌላኛው መልኩ የገዛ ገንዘባችንን ከኪሳችን እየገፈተርን ኑሮ በውድነት የምትበስልበትን እሳት ማቀጣጠል ማለት ነው።

የሀገርና የራስ ምርትን አናንቆ በካልቾ እየጠለዙ ኑሮ ውድነት እንዲቀንስ መሻት፤ የሲኦል በር ላይ ቆመው ገነትን እንደመመኘት ነው። የኑሮ ውድነት እንዲባባስ የሚያደርጉት ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ብቻም ሳይሆኑ አላግባብ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባው የውጭ ሀገር ገንዘብም ሌላኛው የቀውሱ መንገድ ነው።

በሌላ መንገድ ሀገራችን የምትከተለው የነፃ ገበያ ሥርዓት መሆኑ ይታወቃል። ነገር ግን በነፃ ገበያ ጥላ ስር ተቀምጠው “ይሄ እኮ ነፃ ገበያ ነው…ካልተመቸህ መተው ትችላለህ” እያሉ፤ የሕዝብን ኪስ የሚያኝኩትን ነፃ ዘራፊዎችን መንግሥት አንድ ሊላቸው ይገባል። በነፃ መተሳሰብና ፍቅር የኖረን ሕዝብ በነፃ ገበያ ሲመነተፍ እያዩ ዝምታ አያሻም።

አሁን አሁን በእጅጉ አሳሳቢ እየሆነ የመጣው የደላሎች ነገር ደግሞ ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ነው። በገበያው መግቢያና መውጫ ቆመው ሁሉንም ያለ እኔ አይሆንም በማለት ገዢና ሻጭ፤ ፈላጊና ተፈላጊ በቀጥታ እንዳይገናኙ በማድረግ ውድነቱን አፋፍመውታል።

በቤት ኪራዩ ብንመለከት፤ ከአከራዩ ምስጋናና ተጨማሪ ጉርሻ ለማግኘት ሲል በእጅ እግር እየገባ ቀድሞ ከታሰበው በላይ እንዲከራይ የሚያደርግ ብዙ ነው። እንግዲህ ከዚያን ወዲህ ኑሮ ሽቅብ እንጂ እንደ ውሃ ቁልቁል አይፈስም፤ ይህን የሰማ ጎረቤትም ይቀጥላል።

ኑሮ ውድነት በየትኛውም ዓለም ውስጥ ያለና የሚኖር ቢሆንም ድህነታችን የባሰውን ገልጦ አሳይቶናል። ኑሯችን፤ ኑሮ ውድነት ምን እንደሆነ ሰምተው ከማያውቁት ጋርም ጭምር ነውና ከመተሳሰቡ ይልቅ መተዛዘብ አብዝተናል።

እንግዲህ ብለነዋል ፤ ማናችንም ሁሉም ቦታ ላይ ገዢ፤ ሁሉም ቦታ ላይ ሻጭ አይደለንም… ስለዚህ አንተም ተው እኔም ልተው ተባብለን በብልሃት መኖር ስንችል፤ ተያይዞ ማደግ ይመስል ተያይዞ በኑሮ ውድነት መዋደቅን ምን አመጣው?!።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን   ኅዳር 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You