በቀጣናው የግብጽን የጥፋት ተልእኮ ለመመከት

የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስትራቴጂክ ከሚባሉ አካባቢዎች አንዱ እና ዋነኛው ነው።አካባቢው ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ጂቡቲ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያን የሚገኙበት ትልቁ የዓለማችን የባሕር ላይ ንግድ መስመር ነው። በቀይ ባሕር እና በኤደን ባሕረ ሰላጤ የሚገኘው የባብል ኤል-ማንደብ ሰርጥ የዓለማችን 15 በመቶ የሚሆን የንግድ መርከቦች እንቅስቃሴ የሚያደርጉበት ስፍራ መገኛ ነው። አካባቢው ከመካከለኛው ምሥራቅ፣ ከአፍሪካ እና ከእስያ ሀገራት የተለያዩ ምርቶች ወደ አውሮፓ እና አሜሪካ የሚተላለፉበት ወሳኝ መስመር ነው።

አካባቢው ካለው ከዚህ ስትራቴጂክ ጠቀሜታ አኳያም ከቀደሙት ዘመናት አንስቶ አካባቢው የብዙዎችን ቀልብ እየሳበ የሚገኝ ነው። ያደጉት ሀገራትም በአካባቢው ያላቸውን ብሔራዊ ጥቅሞች ተጨባጭ ለማድረግ በአካባቢው ከሚገኙ ሀገራት ጋር ወዳጅነትን በመመሥረት ተጽዕኗቸውን እና ቁጥጥራቸውን ለማጠናከር የሚሽቀዳደሙበት ነው።

አሜሪካ፣ ፈረንሳይ ሩስያ፣ ቻይና እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ በቀጠናው /በጅቡቲ የጦር ሠፈሮችን አቋቁመው ወታደሮቻቸውን በማስፈር አለኝ የሚሉትን ጥቅሞቻችውን ለማስጠበቅ እየተንቀሳቀሱ ይገኛል። ለምሳሌ ያህል አገራቱ የጦር ሠፈሮች፣ የባሕር ኃይል ወደቦች፣ አየር ኃይል እና ማሰልጠኛ ማዕከላትን ጭምር በጂቡቲ ገንብተዋል።

የአካባባው ሀገራት ሕዝቦች ግን ከቅኝ ግዛት ውርስ እና ከራሳችው ውስጣዊ ችግሮች በሚመነጩ የተለያዩ ምክንያቶች በሚቀሰቀሱ ጦርነቶች እና በድርቅ የእለት ተእለት ሕወታቸው ሲፈተን እና አለመረጋጋት እና የሰላም እጦት ሲዳረጉ ማየት የተለመደ ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

በተለያየ ወቅቶች በነዚህ ችግሮች የተፈተነችው፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ በቀደሙት ጊዜያት ከነበራት አንጻራዊ ሰላም እና ጠንካራ የመከላከያ ኃይል አኳያ፤ አስቸጋሪ በሚባሉ ወቅቶች ሳይቀር ለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት ግንባር ቀደም በመሆን ዓለም አቀፍ እውቅና ባገኘ መልኩ ስትንቀሳቀስ ቆይታለች፤ በዚህም ያበረከተችው እና እያበረከተች ያለው አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ነው።

የቀጠናውን ሰላም እና መረጋጋት በራሷ ሰላም እና ደህንነት ላይ የሚኖረው አዎንታዊ አስተዋጽዖ ግምት ውስጥ በማስገባት በጎረቤት ሀገራት የሰላም አስከባሪ ወታደሮቿን ልካ ብዙ መስዋዕትነት ከፍላለች፤ ዛሬም እየከፈለች ነው። ይህ በሀገራቱ ሕዝቦች የወንድማማችነት ታሪክ ውስጥ የጎላ ስፍራ እንደሚኖረው ይታመናል።

በተለይም በሶማሊያ የተሰማራው የኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪ ኃይል የሶማሊያን ሕዝብ እና መንግስት ከአልሸባብ እና ሌሎች ፅንፈኛ ኃይሎች በመታደግ ሂደት ወስጥ የነበረው የጎላ አስተዋጥኦ፤ በተለይም የችግሩ ዋንኛ ገፈት ቀማሽ በነበረው የሶማሊያ ሕዝብ ሕሊና ውስጥ በቀላሉ ሊፋቅ የሚችል አይደለም።

ይህ በብዙ የመስዋእትነት ደም የተጻፈ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የክፉ ቀን አጋርነት፤ አሁን አሁን በሶማሊያ መንግስት በኩል ተገቢውን ከበሬታ እያጣ፤ የሀገሪቱን ሕዝብ ዳግም ለከፋ አደጋ፤ ሀገሪቱንም ለተጨማሪ የመከፋፈል ስጋት የሚያጋልጡ እውነታዎች መታየት እና መሰማት ጀምረዋል።

በተለይም በኢትዮጵያ እና ሶማሌ ላንድ መካከል በወደብ እና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ የመግባቢያ ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ፤ በሞቃዲሾ መንግስት በኩል ከተሳሳተ ግንዛቤ በመነሳት እየተወሰዱ ያሉ የጠብ አጫሪነት እርምጃዎች ቀጣናውን ወደ አላስፈላጊ ቀውስ ሊወስዱ እንደሚችሉ እየተገመተ ነው ፡፡

የሶማሊያ መንግስት እየወሰዳቸው ያሉ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ጋር የሚጋጩ እርምጃዎችን፤ በተለይም የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ከሆነችው ግብጽ ጋር እየፈጸመ ያለው ያልተቀደሰ ጋብቻ፤ ለአካባቢው ሰላም እና መረጋጋት ተጨማሪ ስጋት እየሆነ ነው። በተለይም የኢትዮጵያ መንግስት ጉዳዩን በጥንቃቄ እንዲመለከተው እያስገደደው የሚገኝ ክስተት ሆኗል፡፡

ግብጽ በዋነኝነት በቀይ ባሕር እና የስዊዝ ቦይ (Suez Canal) ላይ ባላት ስትራቴጂካዊ ተፈላጊነት ምክንያት የቀይ ባሕር የፖለቲካ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በተጽዕኖዋ ስር እንዲሆን ትፈልጋለች። እነዚህ ፍላጎቶቿ የቀይ ባሕር የንግድ መስመሮችን መቆጣጠር፣ የባሕር በር ይዞታዋን ማስፋት፣ ጠንካራ የባሕር ኃይል እንዲኖራት መፈለግ ብሎም የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካን በራሷ ፍቃድ በሚዘወሩ መንግስታት እንዲከወን ማድረግ ዘመናት የተሻገረ ምኞቷ ነው፡፡

ከዚህም ባለፈ የአባይ ውሃ ምንጭ በሆነቸው ሀገራችን ሰላም እንዳይሰፈን ለማድረግ ከቅኝ ግዛት በተሻገረ ሕልሟ የአባይን ውሃ በብቸኝነት ለመጠቀም ትፈልጋለች። ይህንን ፍላጎቷ ለመፈፀም አሁን ላይ ኢትዮጵያ እና ሱማሌላንድ ያደረጉትን ስምምነት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ራሷን የሶማሊያ አጋር አስመስላ እየተንቀሳቀሰች ነው። ወደ ሶማሊያ እጇን ለማስገባት እየሞከረች ያለውም የቀጣናውን ሰላም ለማደፍረስ ብሎም ለኢትዮጵያ እድገት እንቅፋት ለመሆን ነው ፡፡

በሶማሊያ እና በግብፅ መካከል የተካሄዱ የትብብር ስምምነቶች፤ ወታደራዊ ስምምነትን ጨምሮ የዚሁ እውነታ አካል ነው። ወትሮም ቢሆን ሰላም በራቀው የአፍሪካ ቀንድ ላይ ከቀጣናው ፍላጎት ውጭ የሆነ ኃይል እጁን ሲያስገባ ይዞት ሊመጣ የሚችለው ቀውስ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ስምምነቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ጉዳዩ በብሔራዊ ጥቅሟ እና ሉአላዊነቷ ላይ ይዞ ሊመጣ የሚችለው ጫና በቀላሉ የሚታይ ባለመሆኑ በጥንቃቄ እየተከታተለች ትገኛለች።

እስከ አምስት ሺህ የሚደርሱ የግብፅ ወታደሮች በዓመቱ መጨረሻ አዲስ በሚደራጀው የአፍሪካ ሕብረት የሰላም አስከባሪ ኃይል ውስጥ እንዲቀላቀሉ ለማድረግ ያላት ፍላጎትም ለሱማሊያ አለመረጋጋት እና ለአፍሪካ ቀንድ ቀጣናዊ ተጨማሪ የግጭት ምንጭ ሊሆን እንደሚሆን በብዙዎች ዘንድ ስጋት የፈጠረ ነው፡፡

ለሶማሊያ ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያለውን አልሽባብ በመዋጋት ረገድ ቁልፍ አጋር ከሆነችው ኢትዮጵያ ይልቅ በችግሯ ጊዜ ምንም አስተዋጽዖ ካላደረገችው ግብጽ ጋር የጫጉላ ሽርሽር በሚመስል ሁኔታ ላይ መገኘቷዋ ግብጽ አካባቢውንም ለማመስ ላላት ፍላጎት ፈረስ ሁነው ለማገልገል ያላቸውን ዝግጁነት ያሳየ ነው፡፡

ግብጽ ከዚህ ቀደም ኢትዮጲያ በራሷ አቅም የምትገነባው የአባይ ግድብ ለማስቆም ተደጋጋዊ ጥረቶችን ስታደርግ ቆይታለች ፤ጥረቶቿ በኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት ጥንካሬ ከንቱ ሆኖ ግንባታው ፍጻሜ ላይ ደርሷል ፤ይህ ዛሬም ድረስ አልዋጥላት ያላት ግብጽ በሶማሊያ በኩል አካባቢውን ወደ ግጭት በመግፋት የአካባቢውን ሀገራት ህዝቦች የመልማት ፈግላጎት ፈተና መሆን ትፈልጋለች።

ይህን የግብጽ ወቅታዊ ስጋትነት ተቋቁሞ ለመሻገር ኢትዮጵያውያን እንደቀደሙት ዘመናት አንድነታቸውን አጠናክረው መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል። ለሀገራችን ብሄራዊ ጥቅም በጋራ መቆም ፤የውስጣዊ ችግሮቻችን በውይይት መፍታት ማስጠበቅ ይኖርባቸዋል ። ለዚህም ግብጽ በአፍሪካ ቀንድ ልትወስዳቸው የምትችላቸው ቀጣይ ተግባራት ምን ሊሆኑ ይችላሉ የሚሉ አንዳንድ ነጥቦችን በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ እሞክራለሁ።

ግብፅ አሁን እንደሚስተዋለው የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግስትን ለጥፋት ፍላጎቷ ማስፈጸሚያ አድርጋ መጠቀሟ የማይቀር ነው ።በርግጥ ግብጽ እራሷ በቀሰቀሰቻቸው ጦርነቶች በታሪኳ በአንዱም ኢትዮጵያን አሽንፋ አታውቅም ። ከዚህ ታሪካ እውነታ እና አሁን ላይ ኢትዮጵያ ያለችበትን አቅም በማጤን ከኢትዮጵያ ጋር የቀጥታ ጦርነት ውስጥ ትገባለች ተብሎ አይታሰብም ፡፡

ግብጽ ከኢትዮጵያ ጋር ወደ ቀጥተኛ ጦርነት ልትገባ የማትፈልገው ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ብሔራዊ አንድነት እና ነጻነት ምን ያህል ዋጋ እንደሚከፍሉ ስለምታውቅ ብሎም ተሳስታ የጦርነት ካርድን ብትመዝ ሊያስከትልባት የሚችለውን ከባድ አጸፋ ስለምታውቅ ነው።

ይህም እንዳለ ሆኖ በሶማሊያ ያለው መንግስት ደካማ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ጸረ ኢትዮጵያ ኣቋም ያለው እንዲሆን እና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚጻረሩ የተለያዩ እርምጃዎችን እንዲወስድ በማድረግ የቀጣናውን ሰላም ለመበጥበጥ የጀመረችውን ጥረት አጠናክራ ልትቀጥልበት ትችላለች። ኢትዮጵያ በበሶማሊያ ያለው የማዕከላዊ መንግስት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም የማይጻረር እና ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር መስራት የሚችል መሆኑን ማረጋገጥ ቀዳሚ እርምጃዋ መሆን አለበት፡፡

ሌላኛው ጉዳይ ግብጽ የተለያዩ ጽንፈኛ አካላትን ልታስታጥቅ የምትችልበት እድል መኖሩ ነው። ይሄም በሶማሊያ አልሸባብን ጨምሮ የተለያዩ አሽባሪ ኃይሎችን በመደገፍ ቀጣናው የሽብርተኞች እና ወንበዴዎች መናሃሪያ ማድረግን ታሳቢ ያደረገ አካሄድ ሊኖራት ይችላል። ይሄም ግብጽ በኢትዮጵያ የሽብር ጥቃቶችን እንዲፈጽሙ በማድረግ የኢትዮጵያን ሰላም አደጋ ውስጥ ለመክተት ልትሞክር ትችላለች ፡፡

ክዚህ በተጨማሪ ግብጽ ልትከተለው የምትችለው ሌላው የጥፋት አማራጭ በኢትዮጵያ ላይ የኢኮኖሚ ጫና ለመፍጠር የሚደረግ ሙከራዎችን ማድረግ ነው። ግብጽ በውክልና ጦርነት የኢትዮጵያን ሰላም ለመበጥበጥ ከምታደርገው ጥረት በተጨማሪ ሌላኛው ጉዳይ የኢኮኖሚ ጫና ለመፍጠር የሚያስችሉ እርምጃዎችን ለመውሰድ የምታደርገው ጥረት ሊኖር ይችላል፡፡

በተለይም ከሶማሊያ በዘለለ ግብጽ ወደ ጅቡቲ በመጠጋት የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ አሻጥሮችን ልትፈጽም የምትችልበት እድል እንዳይኖር ከጅቡቲ ጋር ያለን ግንኙነት አሁን ካለበት በላይ ማጠናከር የሚያስችል ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ስራ መስራት ያስፈልጋል፡፡

የግብጽን እኩይ ሴራዎች ለመከላከል ቀጣናዊ ጥምረቶችን በማጠናከር ከጎረቤት ሀገራት ጋር ሊፈጠሩ የሚችሉ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ በውይይት ለመፍታት የምትከተለውን መንገድ አጠናክራ መቀጠል፤ በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስት (ኢጋድ) በኩል ቀጠናዊ ችግሮች ለመፍታት የምታደርጋቸውን ጥረቶችን አጠናክሮ መቀጠል ይኖርባታል።

በኢጋድ ውስጥ ያላትን አዎንታዊ አስተዋጽዖ በማሳደግ ከሀገሪቱ የሰላም እና ደህንነት ሁኔታ በዘለለ ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ ሰላም እና የኢኮኖሚ ትብብር እንዲጎለብት ማድረግ፤ (ኢጋድ) በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን ፖለቲካዊ ውጥረት በድርድር ለመፍታት የጀመረውን ጥረት በማገዝ ፖለቲካዊ ትኩሳቱ እንዲቀዛቀዝ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ከዓለም አቀፍ አጋር አካላት ጋር በተለይም እንደ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ሕብረት እና የአፍሪካ ሕብረት የመሳሰሉ ተቋማት አዎንታዊ ድጋፍ እንድታገኝ ያላሰለሰ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በማድረግ የግብጽን ጸብ አጫሪ ድርጊቶች ማምከን ያስፈልጋል።

ኤልያስ ጌትነት

አዲስ ዘመን መስከረም 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You