አምራቾችንና ሸማቾችን ያለ ደላላ ያስተሳሰረ መድረክ

ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የማዕድንና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ በሚሊኒየም አዳራሽ በቅርቡ መካሄዱ ይታወቃል። በኤክስፖው ላይ ሀገሪቱ በማዕድን ሀብት ባለጸጋ መሆኗን በሚገባ ያመላከቱ በርካታ የማዕድን ዓይነቶች ለእይታ ቀርበዋል። የወርቅ፣ የድንጋይ ከሰል፣ የብረት፣ እንደ ኦፓል ያሉ የከበሩ ማዕድናት በተለያዩ ኩባንያዎች ቀርበው ተጎብኝተዋል። ለመስታወት፣ ለብርጭቆ፣ ለሴራሚክ እቃዎች እንዲሁም ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች ግብዓት የሚሆኑ ልዩ ልዩ ማዕድናትም በኤክስፖው ከቀረቡት መካከል ይጠቀሳሉ።

በመድረኩ በኩባንያዎችና በማህበራት የቀረቡ የማዕድን ናሙናዎች ዓይነትና ብዛት የቀረቡበትን መንገድ በተመለከተ የማዕድን ሙዚየም የገባ ያህል ሊሰማው ይችላል፤ ናሙናዎቹ በራሳቸው የሚያስገነዝቡት እንዳለ ሆኖ፣ በምስልና በጽሑፍ የቀረቡ መረጃዎች እንዲሁም በየኩባንያዎቹ፣ ማህበራቱ፣ ወዘተ የተሰጡ ማብራሪያዎች የሀገሪቱን እምቅ የማዕድን ሀብትና ያንን ለማልማት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን የሚያስገነዘቡ ናቸው።

ከኅዳር 14 እስከ ኅዳር 18 ቀን 2016 ዓ.ም በተካሄደው በዚህ የማዕድንና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ ላይ አጠቃላይ ከ90 በላይ ኩባንያዎች፣ ማህበራት፣ ወዘተ መሳተፋቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። በስፍራው ተገኝተን ያነጋገርናቸው ተሳታፊዎች እንደገለጹት፤ በመድረኩ የተገኙት የማዕድናት አልሚ ኩባንያዎች፣ ለኩባንያዎች ግብዓት አቅራቢዎች፣ ገዥዎች የማዕድን ዘርፉ ቴክኖሎጂ አቅራቢ ኩባንያዎች፣ የክልል የማዕድን ቢሮዎች፣ በከበሩ ድንጋዮች ጌጣጌጥ የሚያመርቱ እንዲሁም እነዚህን ጌጣጌጦች የሚሸጡ ማህበራት፣ ወዘተ. ኤክስፖው ምርቶቻቸውንና አገልግሎቶቻቸውን ለማስተዋወቅ አስችሏቸዋል።

ተሳታፊዎቹ መድረኩን ትስስር ለመፍጠሪያነት ወይም ደንበኛ ለማፍሪያነት፣ ልምድ ለማጎልበቻነት፣ ቴክኖሎጂና እውቀት ለማሸጋገሪያነት ተጠቅመውበታል። ጥራት ያለው ምርት ለማምረት የሚያስችል ልምድ ለመጋራት እንዳስቻላቸውም ተናግረዋል። አብረው ለመሥራት ፍላጎት ያደረባቸው ጎብኚዎች ያጋጠሟቸው ኩባንያዎች ስለመኖራቸውም እነዚሁ ተሳታፊዎች ገልጸዋል። ተሳታፊዎቹ ኤክስፖው በቀጣይም ይበልጥ በተጠናከረ መልኩ እንዲካሄድም ጠይቀዋል።

የዘንድሮው መድረክ ከአምናው የተለየ መሆኑም ተጠቁሟል። የዘርፉ መልካም እድሎች፣ ፈተናዎችና መፍትሔዎች የተመላከቱባቸው ሲምፖዚየሞችም ከመድረኩ ጎን ለጎን ተካሂደው ውይይቶች ተደርገውበታል፤ ይህም መድረኩን የተለየ ካደረጉት መካከል አንዱ ነው።

የሀገር ውስጥ ማርብሎችን ከዋናው ከማዕድኑ ጀምሮ እስከ አለቀለት ምርት ድረስ የሚያቀርበው ሳምዳጆ ማርብልና ግራናይት ከእነዚህ ድርጅቶች አንዱ ነው። ያነጋገርናቸው የድርጅቱ ፕሮዳክሽን ማናጀር አቶ ዮናታን የምስራች እንዳሉት፤ ድርጅቱ ላይምስቶን እና ግራናይትን እያመረተ ለገበያ ማቅረብ ከጀመረ 10 ዓመታትን አስቆጥሯል፤ ማዕድኑን ወይም ዋናውን ጥሬ ዕቃ ከአቅራቢዎች በመረከብ ቃሊቲ በሚገኘው ማምረቻው እሴት ጨምሮ ለተለያዩ አገልግሎቶች እንዲውል አድርጎ ያመርታል።

ግራናይት ለደረጃ መወጣጫ እንዲሁም ለሌሎች በርካታ አገልግሎቶች የሚውል ነው። ጥሬ ድንጋዩን ቆርጦ፣ አጥቦና ለሚፈለገው አገልግሎት በሚውል መልኩ ለገበያ የሚያቀርበው ድርጅቱ፣ በሀገሪቱ ከሚገኙ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ጋር ትስስር በመፍጠር ለገበያ ያቀርባል። በአብዛኛው ከኮንስትራክሽን ኩባንያዎች ጋር እንደሚሰራ ነው አቶ ዮናታን የተናገሩት።

ኤክስፖው መዘጋጀቱ ድርጅቱን ከተቋራጮች ጋር በማስተዋወቅ የገበያ ትስስር ለመፍጠር እንደሚያስችል ጠቅሰው፣ ኤክስፖው ዓለም አቀፍ ኤክስፖ እንደመሆኑ በተለይም ከውጭ ድርጅቶች ጋር የመተዋወቅ ዕድል እንደሚፈጥርላቸው አስታውቀዋል። ሀገር ውስጥ ካሉና ተመሳሳይ ሥራ ከሚሰሩ ድርጅቶች ጋርም እንዲሁ የመተዋወቅ፣ የልምድ ልውውጥ በማድረግ ጥራት ያለው ምርት ማምረት የሚያስችላቸውን አጋጣሚ እንደሚፈጥርላቸው ነው ያመላከቱት።

እሳቸው እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ እምቅ የማዕድን ሀብት ያላት ቢሆንም በአግባቡ አልምቶ መጠቀም ላይ ገና ብዙ የሚቀሩ ሥራዎች አሉባት። ዓለም አቀፍ ኤክስፖዎች ሲዘጋጁ የማዕድን ሀብቱን የበለጠ ለመጠቀም ያበረታታሉ፤ በተለይ ሀገሪቷ ወደ ሀገር ውስጥ በምታስገባቸው በርካታ ሸቀጦች ምክንያት የምታጣውን የውጭ ምንዛሪ ለማስቀረት የማዕድን ልማት ወሳኝና ቁልፍ ሚና አለው። ከዚሁ ጋር በተያያዘም ኤክስፖው መንግሥትን ጨምሮ በማዕድን ዘርፍ የተሰማሩ አካላትን በሙሉ ያገናኘ በመሆኑ ለገበያ ትስስር ከሚፈጥረው ዕድል በተጨማሪ በርካታ ጠቀሜታዎችም አሉት።

በመድረኩ ከሚገናኙ አካላት መካከል አምራችና ገዢ ቀዳሚዎቹ ናቸው ያሉት አቶ ዮናታን፣ መድረኩ አምራችና ሸማቾችን ከደላላ ውጭ በቀጥታ ማገናኘት ችሏል ሲሉም አስታውቀዋል። ማዕድን የሚያቀርቡና የሚያወጡ ከአምራቹ ጋር በቀጥታ መገናኘት የቻሉበት መሆኑን ጠቅሰው፣ መንግሥትም በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ መረዳት የቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል። በማዕድን ዘርፉ ያለውን ግንዛቤ ለማስፋት መሰል ኤክስፖዎችን ማዘጋጀትና የማዕድን ዘርፉን ማሳደግ ለዘርፉ ዕድገት የሚኖረው ጠቀሜታ እጅግ የላቀ እንደሆነ አመላክተዋል።

ከሰሜን ሸዋ መራቤቴ አካባቢ ከሚገኘው ኤምኤኬ ትሬዲንግ በኤክስፖው ላይ የሲልካ ሳንድ ወይም የሲልካ አሸዋ ይዞ ተገኝቷል። የድርጅቱ የሽያጭ ሠራተኛ አቶ ዘላለም ደምሴ ሲልካ አሸዋ ለመስታወት፣ ለብርጭቆና ለመሳሰሉት ዋና ግብዓት መሆኑን ይገልጻሉ፤ በተጓዳኝም ለቀለም፣ ለኮንስትራክሽን ግብዓትነትና ለሴራሚክ ማምረቻነትም እንደሚጠቀም ገልጸዋል።

ድርጅቱ በእዚህ ሥራ ላይ አምስት ዓመታትን ማስቆጠሩን የገለጹት አቶ ዘላለም፤ በወር አምስት ሺ ቶን የማምረት አቅም እንዳለውም ጠቅሰዋል። ድርጅቱ ለመስታወት፣ ለብርጭቆ፣ ለቀለም፣ ለሴራሚክ ፋብሪካዎች ለሚገኙበት አዲስ አበባን ጨምሮ ደብረብርሃን፣ ዱከም፣ ደብረዘይትና በሌሎች ከተሞችም ምርቱን እያቀረበ ይገኛል። በሀገር ውስጥ ያለውን የምርት ፍላጎት ማሟላት መቻሉን ጠቅሰው፣ ገበያው ውስን እንደሆነም አቶ ዘላለም ተናግረዋል።

ኤክስፖው መዘጋጀቱ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለውና በሚገባ እንደተጠቀሙበትም አስረድተዋል። ለሁለተኛ ጊዜ የተዘጋጀው ዓለም አቀፍ የማዕድንና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ የውጭ ገበያ ዕድል እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸውም አስታውቀዋል። በተለይ ለድርጅታቸው የውጭ ገበያ ትስስር እንደፈጠረላቸው የጠቀሱት አቶ ዘላለም፤ ከኤክስፖርት ኤጀንቶችና አብረው ሊሰሩ ከሚችሉ ሌሎች ከውጭ የመጡ ባለሀብቶችና ከኤክስፖርተሮች ጋር የመተዋወቅ ዕድል እንደፈጠረላቸውም አመልክተዋል። በዚህም ትልቅ የገበያ ትስስር እንደፈጠሩ፣ ምርቶቻቸውን ሊወስዱላቸው የሚችሉ ገዢዎችን እንዳገኙ ነው ያስታወቁት።

ሲልካ ሳንድ ወይም ሲልካ አሸዋ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በስፋት እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ በእሳቸው አካባቢም በበቂ መጠን እንደሚገኝ ይናገራሉ። ድርጅታቸው ሁለት ፈቃዶች በማውጣት ምርቱን በሁለት ቦታዎች ላይ እያመረተ መሆኑንም ጠቁመዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ አንደኛው ማምረቻ በሰሜን ሸዋ መራቤቴ አካባቢ እንሳሮ ወረዳ ይገኛል፤ የማምረቱ ሥራም በ12 ሄክታር መሬት ይከናወናል። ሁለተኛውም እዚያው መራቤቴ ወረዳ የሚገኝ ሲሆን፣ የማምረቱ ሥራም በ12 ሄክታር መሬት ላይ እየተከናወነ ነው።

ድርጅቱ በቋሚና በጊዜያዊ 450 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩንም አቶ ዘላለም ጠቅሰዋል። በቀጣይም የማምረትና የገበያ ተደራሽነቱን የማስፋት ዕቅድ እንዳለው ተናግረው፣ በተለይም ምርቱን በጥራትና በስፋት አምርቶ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ማቀዱንም አስታውቀዋል። አቅሙን ይበልጥ በማሳደግና እሴት በመጨመር የመስታወትና የብርጭቆ ፋብሪካ የመገንባት ዕቅድ እንዳላቸውም አመልክተዋል። ብርጭቆና መስታወት ለማምረት ሲልካ አሸዋ 75 በመቶ፣ ሶዳሽ 10 በመቶ፣ ላይም ስቶን 15 በመቶ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ 90 በመቶ ግብዓት በሀገር ውስጥ ሊሸፈን እንደሚችል አስታውቀዋል።

በኢትዮ ደላንታ ኦፓል እና የከበሩ ማዕድናት ኤክስፖርት ድርጅት ውስጥ ተቀጥራ የምትሰራው ወጣት ሰፊ አዳነ፤ የኦፓል ምርቶችን እንዲሁም ከሌሎች የከበሩ ማዕድናት የተዘጋጁ በርካታ ጌጣጌጦችን ይዛ ነው በኤክስፖው ላይ የተገኘችው። ድርጅቱ የጌጣጌጥ ምርቶቹን ለገበያ እንዲሁም ለማስተዋወቅ ነው ይዞ መቅረቡንም ገልጻለች።

በወሎ ደላንታ በስፋት የሚገኙትን እንደ ኦፓል፣ አማዞናይት፣ ብላክ ኦፕሲዲያ፣ አማቲስትና ሌሎች ጌጣጌጦችን ይዛ እንደቀረበች ጠቅሳ፣ ማዕድናቱ እጅግ ተፈላጊ እንደሆኑ ትናገራለች። ጌጣጌጦቹን ለማምረት አስፈላጊ የሆኑ የማዕድን ዓይነቶችን ከአቅራቢዎችና ከነጋዴዎች ገዝቶ እንደሚያመርት ገልጻለች።

ድርጅቱ ጌጣጌጦችን አምርቶ ለሀገር ውስጥ ገበያ ከማቅረብ ባለፈ የከበሩ ድንጋዮችን በጥሬው ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርብ ተናግራለች። ምርቶቹ በስፋት የሚላኩት ወደ ህንድ መሆኑንም አጫውታናለች። እሷ እንዳለችው፤ እንደ ደንበኞች ፍላጎትም እሴት የተጨመረባቸውንና ፖሊሽ የተደረጉ ምርቶችን ድርጅቱ ለገበያ ያቀርባል። ከዚህም ባለፈ ምርቶቹን ወደ ጌጣጌጥነት በመቀየር ለመዋቢያና ለጌጣጌጥነት እንዲውሉ እያደረገ መሆኑን ጠቅሳ፣ እነዚህ ምርቶች ሰፊ ገበያ እንዳላቸውም ጠቁማለች። ምርቶቹ በወሎ ደላንታ የሚዘጋጁ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ደግሞ የመሸጫ ሱቅ አለው።

እሷ እንዳለችው፤ ጌጣጌጦቹ የአንገት፣ የጆሮና የእጅ መዋቢያና ማጌጫ ናቸው። ከዚህ ቀደም ማህበረሰቡ ለከበሩ ድንጋዮች ዝቅተኛ አመለካከት ነበረው፤ ይህ አመለካከት አሁን እየተቀየረ መጥቷል። ምርቶቹን በስፋት የመጠቀም አዝማሚያ እየታየ ነው።

በማህበረሰቡ ዘንድ እየታየ ያለው ይህ ለውጥ የመጣው በተለያየ ጊዜ በሚዘጋጁ ኤክስፖዎች ምርቶቹን አውጥቶ ማስተዋወቅ በመቻሉ ነው። ኤክስፖው የገበያ ዕድሎችን የሚፈጥርና ምርቶቹን ለማህበረሰቡ ብሎም ለውጭ ገዢዎች ለማስተዋወቅ የሚያስችል እጅግ ጠቃሚ መድረክ መሆኑን አስታውቃለች።

ከዚህ ቀደም በማህበረሰቡ ዘንድ የከበሩ ድንጋዮችን በማውጣት አልምቶ የመጠቀም ባህሉ የዳበረ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ አብዛኛው ማህበረሰብ የከበሩ ማዕድናት ማልማት ላይ ፍላጎት እንዳልነበረው ወጣት ሰፊ ገልጻለች። በወሎ ደላንታ በስፋት የሚገኘውን የኦፓል ማህበረሰቡ አልምቶ እንዲጠቀም በማድረግ በኩል ሜዳ እምርታ የተሰኘው የካናዳ ድርጅት ፕሮጀክት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ተናግራለች። ፕሮጀክቱ ለዘርፉ ዕድገት ትልቅ አበርክቶ እንዳለው ጠቅሳ፣ በዚሁ ምክንያት ወደ ሥራ የገቡ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች መሆናቸውንም ነው ያመለከተችው።

የማዕድን ሚኒስቴር ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ በመድረኩ ላይ እንዳሉት፤ ማዕድን ብዙ ነገር ነው። ማዕድን ግብርና ነው፤ በሀገሪቱ የአፈር ማዳበሪያን ማምረት ካልተቻለ ግብርና ዘላቂነት አይኖረውም፤ የምግብ ዋስትናን በዘላቂነት ማረጋገጥም አይቻልም። ማዕድን ኮንስትራክሽን ነው፤ ያለ ሲሚንቶና ብረት ዘላቂ የሀገር ግንባታን ለማስቀጠል ቀላል አይሆንም። ማዕድን ኢንደስትሪ ነው፤ ማዕድን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ዋነኛ መሠረት ነው፤ የወጪና ገቢ የንግድ ሚዛን ካልተጠበቀ ዘላቂ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ማረጋገጥ አይቻልም።

መንግሥት ይህንኑ በመረዳት ከቀደሙት ጊዜያት በተሻለና በተለየ መንገድ ለማዕድን ዘርፉ ልዩና ከፍተኛ የሆነ ትኩረት መስጠቱን ሚኒስቴሩ ተናግረዋል። ኤክስፖው ኢትዮጵያ ያላትን የማዕድን ሀብት ለማስተዋወቅ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን አመልክተው፣ ባለሀብቶች ያለውን ሀብት ተመልክተው ወደ ሥራ እንዲገቡ የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል።

“የማዕድን ሀብታችን የነገ ተስፋችን” በሚል መሪ ሃሳብ በሚሊኒየም አዳራሽ የተዘጋጀውን ሁለተኛውን ዓለም አቀፍ የማዕድንና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ በንግግር የከፈቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ሀገሪቷ በሁሉም አካባቢዎቿ እጅግ አስደናቂ የሆኑ የማዕድን ሀብቶች ያሏት በመሆኑ ኤክስፖው ለተመራማሪዎችና ኢንቨስተሮች በዘርፉ ምን ዓይነት ሀብት እንዳለ ለማወቅ ዕድል ይፈጥራል። ኢትዮጵያን ከድህነት ለማውጣት በፈተና ጊዜም ቢሆን ችግሮችን ተቋቁሞ ማልማት ይገባል።

ሀገሪቱን ከታሰበው የእድገት ደረጃ ላይ ለማድረስ የኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ በግል ማምረትና ኢንቨስት ማድረጉን አቁሞ በጋራ መሥራት የሚቻልበትን እውቀት የሚሰባሰብበትን፣ ብልጽግና የሚመጣበትን መንገድ መፍጠር እንዳለበትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል። ከችግር ነጸ የሆነ የመልሚያ መንገድ እንደሌለም ጠቅሰው፣ በዘርፉ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ በመፍታት ወደ ብልጽግና ከፍታ መገስገስ እና ለተተኪው ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን ማስረከብ እንደሚገባም አስታውቀዋል።

 ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ህዳር 26/2016

Recommended For You