መፍጠን ያለበት የሳይበር መከላከል ሥራና ዝግጁነት

በዚህ የዲጂታል ዘመን የሀገሮች ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች የሚከወኑት በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ነው፡፡ የመረጃ ልውውጡ፣ ክፍያው፣ ሕክምናው፣ ትምህርቱ፣ ግብርናው፣ ግንባታው፣ ኢንዱስትሪው፣ ወዘተ… ከእዚህ ቴክኖሎጂ ውጭ ሊሆን አይችልም፡፡

ኢትዮጵያም የዲጂታል ቴክኖሎጂ አስፈላጊነትን በማመን በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያዋ የአስር ዓመት መሪ አቅድ ለምጣኔ ሀብቱ ምሰሶ አርጋ ከያዘቻቸው አምስት ዘርፎች መካከል ይህ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ አንዱ ነው፡፡ ሀገሪቱ በ2025 ዲጅታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ስትራቴጂ ነድፋ መሥራቱን ተያይዛዋለች፡፡ በመረጃ ለውውጡ፣ በክፍያው፣ የተለያዩ አገልግሎቶች በቴክኖሎጂው እንዲከናወኑ ለማድረግ እየተካሄዱ የሚገኙ ሰፋፊ ሥራዎችና ይህን ተከትሎ እየተከናወኑ ያሉ ተግባሮችም ይህንኑ ያመለክታሉ፡፡

ቴክኖሎጂውን የመተግበሩ ሥራ ከተለያዩ አካላት ሊደርስበት የሚችልን ጥቃት የመከላከል ሥራም እንዲሁ ሌላው በዘርፉ መከናወን ያለበት ተግባር ነው። በቴክኖሎጂው የሚፈለገው ስፍራ ለመድረስ አንዱ መከናወን ያለበት ተግባር የማይበገር የሳይበር ደህንነት አቅምን መገንባት ነው፡፡

የዲጅታል ኢኮኖሚ ግንባታው እየሰፋና እያደገ በመጣ ቁጥር የሳይበር ደህንነት ማስጠበቅ ደረጃ በዚያው ልክ እያደገ መምጣት ይጠበቅበታል፡፡ ይህም ደግሞ የሳይበር ደህንነት ጉዳይ የእያንዳንዱ ዜጋ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ አካል እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ለዚህም በየጊዜው ከሳይበር ምህዳር ጋር አብሮ የሚሄድ የሳይበር ግንዛቤ ያለው ዜጋ ማፍራትን ይጠይቃል፡፡

ኢትዮጵያ ዲጅታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እየሰራች ባለችበት በዚህ ወቅት የዜጎች የሳይበር ንቃተ ሕሊና ምን ይመስላል የሚለው መታየት ያለበት ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ለእዚህም የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ብሔራዊ የሳይበር ደህንነት ንቃተ ሕሊና ጥናት ውጤት በቅርቡ ይፋ አድርጓል፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ እንዳሉት፤ የጥናቱ ዋና ዓላማ በሀገሪቱ የሳይበር ተጠቃሚ ዜጎችን የሳይበር ንቃተ ሕሊና ደረጃን በማወቅ የታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት ቀጣይነት ያለው ሥራ ለመሥራት ነው፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ በሳይበር ንቃተ ህሊና ዙሪያ የሚሰሩት ጥናቶችን ዋቢ አድርገው ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ ከ80 እስከ 90 በመቶ የሳይበር ጥቃት የሚደርሰው በተጠቃሚዎች የንቃተ ሕሊና ክፍተት ነው፡፡ ይህ ጥናት መካሄዱ በሀገሪቱ ያሉት የንቃተ ሕሊና ክፍተቶች ተለይተው የሳይበር ደህንነትን ሊያስጠብቅ የሚችል ዜጋን ለመገንባት ያስችላል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ ሳይበር ሦስት ዋና ዋና ምሰሶዎች አሉት፡፡ እነርሱም ቴክኖሎጂ፣ የአሰራር ሥርዓት እና ሰው ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ በሆነው ሰው ላይ መሥራት ይገባል፡፡ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ሀገራዊ የሳይበር ደህንነት ባለቤትነትን በማረጋገጥ የሳይበር ምህዳርን ሊመሩ የሚችሉ የሕግ ማዕቀፎችና የአሰራር ሥርዓቶች በማዘጋጀት እንዲሁም የተቋማትና የዜጎችን ንቃተ ኅሊና ሊያዳብሩ የሚችሉ በርካታ ሥራዎች እየሰራ ይገኛል። የሳይበር ደህንነት ጉዳይ የሁሉም የጋራ ኃላፊነት ነው። የሀገሪቱን ዲጅታል ሉዓላዊነት የማስጠበቅና የማስከበር ሥራ በአንድ ተቋም ብቻ የሚሳካ ሳይሆን የሁሉንም ተቋማትና የዜጎች ቅንጅት ጥረት ይጠይቃል፡፡

የሳይበር ደህንነት ጥቃት በሀገራችንም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ በዓይነት ሆነ በብዛት ፈጣን በሆነ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ እንደ ሀገር የሳይበር ጥቃት የመከላከል ሥራና ዝግጁነት ከሳይበር ጥቃት ባሕሪያትና ፍጥነት ጋር እኩል መራመድ ብቻ ሳይሆን መፍጠን ይኖርበታል ብለዋል፡፡ ለዚህም የተቋማትና የዜጎች የሳይበር ንቃተ ኅሊናን በቀጣይነት መገንባት የግድ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የጥናቱ አቅራቢ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የሳይበር ደህንነት ባለሙያ አቶ አየለ ሞሴ የሳይበር ደህንነት ንቃተ ሕሊናን የተመለከተው ጥናት ብዙ መነሻዎችን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት መሰራቱን ይገልጻሉ፡፡ ይህ ጥናት በኢትዮጵያ የሳይበር ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የሆኑ ዜጎችን የሳይበር ንቃተ ኅሊና ደረጃ በማወቅ በቀጣይ የንቃተ ኅሊና ፕሮግራሞችን ለመቅረጽ ግብዓት እንደሚሆን አመላክተዋል፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፤ በዓለም አቀፍም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ ባሉ ሀገራት የሳይበር ጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ ለመጨመሩ ምክንያቶች ተብለው ከተቀመጡት ውስጥ አንዱ የተጠቃሚዎች የንቃተ ኅሊና ደረጃ ዝቅተኛ መሆን ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የዲጅታል መሠረተ ልማቶች እድገት ነው፡፡ በኢትዮጵያ እንዲሁም ከጊዜ ወደ ጊዜ የሳይበር ጥቃት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ያለበት ሁኔታ መኖሩን የአስተዳደሩ ሪፖርቶችም እንደሚያመለክቱ አቶ አየለ ጠቅሰዋል፡፡

እስካሁን በኛ ሀገር የሳይበር ደህንነት ንቃተ ኅሊና ደረጃ ለማወቅ የሚያስችል ጥናት አልተሰራም ያሉት አቶ አየለ፤ ይህ ጥናት አጠቃላይ የተለያዩ ዓለም አቀፍ መረጃዎችን እና ባንኮችን አማካኝነት የተሰሩ ጥናቶችን መሠረት ተደርጎ የተሰራ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ይህ ደግሞ የሚያሳየው የሳይበር ደህንነት ንቃተ ኅሊና ጉዳይ ገና በጅምር ላይ እንደሆነ ነው ብለዋል፡፡ ለዚህም እንደ ምክንያት የሚነሳው ዝቅተኛ የሆነ የሳይበር ደህንነት ንቃተ ኅሊና መኖር እንደሆነ ጠቅሰው፤ ዝቅተኛ የሆነ የኢንዱስትሪው ተሞክሮ መኖሩ እና የሳይበር ደህንነት ስታንዳርድ፣ መመሪያዎች እና ፖሊሲዎች አለመኖራቸው የደህንነቱን ጉዳይ እንደጎዳው ያሳያል ብለዋል፡፡

እሳቸው እንዳመለከቱት፤ ሌላኛው የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር መጨመር ነው፤ በኢትዮጵያ ያለው የኢንተርኔት ተጠቃሚ ቁጥር እ.ኤ.አ 2017/2018 22 ነጥብ 3 ሚሊዮን የነበረ ሲሆን፣ ይህ አሃዝ እስከ እ.ኤ.አ 2022 33ነጥብ9 ሚሊዮን እንደ ደረስ ከኢትዮ ቴሌኮም የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡ ይህም የኢንተርኔት ተጠቃሚ ቁጥር አሁን ላይ እየጨመረ መምጣቱ የዲጅታል ተጠቃሚነት በጨመረ ቁጥር ለሳይበር ጥቃት የመጋለጥ እድል በዚያው ልክ እየጨመረ የሚመጣ ለመሆኑ ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ጥናቱ በርካታ ፋይዳዎች ያሉት ሲሆን፣ አንደኛ በኢትዮጵያ ያለው የንቃተ ኅሊና ደረጃ ምን ላይ እንደሆነ በዳታ የተደገፈ መረጃ ለማግኘት ይረዳል፡፡ ሁለተኛ በኢንፎርሜሽን መረጃ ደህንነት አስተዳደር የንቃተ ኅሊና ግንባታ ለመስረጽ እየተካሄዱ ያሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞች ምን ያህል ውጤታማ እንደሆኑ ለመገምገም ያስችላል፡፡ ሦስተኛው ወደፊት በሀገር ደረጃ የሚሰጡ የንቃተ ሕሊና ሥራዎችን ለመቅረጽ ያግዛል፤ አራተኛውና የመጨረሻው በዚህ ጉዳይ ላይ ጥናት ለሚያደርጉ ሁሉ የመረጃ ምንጭ ሆኖ ማገልገሉ ነው፡፡

ጥናቱ በዋናነት በኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ላይ መሠረት ያደረገ ሲሆን፤ የሳይበር ንቃተ ሕሊና ደረጃን ለመለየት የሚያስችሉ የተጠቃሚዎች እውቀት ደረጃ፣ የአመለካከት እና አጠቃቀም ሁኔታዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ የተሰራ ነው፡፡ በዚህም በኢትዮጵያ የሳይበር ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ዜጎች አጠቃቀም (practice) ደረጃ ምን ይመስላል? የሳይበር ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ዜጎች አመለካከትስ ምን ደረጃ (attitude ) ላይ ይገኛል? የሳይበር ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ዜጎች የእውቀት (knowledge )ደረጃ ምን ይመስላል? የሚሉት በትኩረት ታይተውበታል፡፡

ጥናቱ የሀገሪቱን ክልሎችና ዋና ዋና ከተሞች እንዲያካትት ተደርጓል፡፡ የትምህርት ተቋማትን፣ የንግድ ስፍራዎችን፣ የተቋማት ቢሮዎችን፣ የመዝናኛ እና የመኖሪያ ስፍራዎችን ያካተቱ መረጃዎች የተሰበሰበበትም ነው፡፡

የጥናቱ መመዘኛ መስፈርቶች በዓለም አቀፍ ስታንዳርድ መሠረት የተቃኙ ናቸው የሚሉት አቶ አየለ፤ እያንዳንዱ መመዘኛ መስፈርት የሳይበር ንቃተ ኅሊናን ለመፈተሽ እንደሚያስችልም ይናገራሉ፡፡ ለአብነትም በእውቀት ደረጃ (knowledge) መመዘኛ መስፈርት ውስጥ የይለፍ ቃል፣ የፀረ ቫይረስ፣ የመተግበሪያዎች ዝመና፣ የሳይበር ጥቃት ክስተት፣ የነጻ ዋይፋይ አጠቃቀም፣ የኮምፒዩተር ቫይረስ፣ የኢሜል፣ የማህበራዊ ሚዲያ እና የመሳሰሉትን ተጠቃሚዎች ምን ያህል እንደሚያወቁ እንደሚጠይቅም አመላክተዋል፡፡

በዚህም ረገድ የሳይበር ንቃተ ኅሊና እውቀት የሌላቸው 29 ነጥብ 23 በመቶ ሲሆኑ፣ ዝቅተኛ እውቀት ያላቸው 35ነጥብ 60፣ መካከለኛ እውቀት 11 ነጥብ75 እና ከፍተኛ እውቀት ያላቸው 23 ነጥብ 40 በመቶ ያህል መሆናቸውን ጥናቱ ያመላክታል፡፡ ይህም በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የሳይበር ደህንነት ንቃተ ኅሊና እውቀት ያላቸው 35 በመቶ እንዲሁም 65 በመቶ ያህል ዜጎች ደግሞ እውቀት የሌላቸው መሆናቸውን እንደሚያሳይ አመልክተዋል፡፡

የሳይበር ደህንነት ንቃተ ኅሊና የአመለካከት ደረጃን (attitude) በተመለከተ በተዘጋጀው የሳይበር ጥቃት ሪፖርት፣ የይለፍ ቃል መቀያየር፣ የአካውንት ደህንነት አጠባበቅ፣ ጠንካራ የይለፍ ቃል መጠቀም የሚሉትና የመሳሰሉት መመዘኛ መስፈርቶች የተካተቱበት ነው። በዚህም በኢትዮጵያ የሳይበር ደህንነት ንቃተ ኅሊና አመለካከት ደረጃ አጠቃላይ 47 በመቶ ያህሉ አዎንታዊ አመለካከት ያላቸው ሲሆን ፤ 53 በመቶ ያህሉ አሉታዊ አመለካከት ያላቸው መሆናቸው ተመላክቷል፡፡

በኢትዮጵያ የሳይበር ደህንነት ንቃተ ኅሊና አጠቃቀም (practice) ደረጃ በተመለከተም እንዲሁ በጥናቱ የተለያዩ መመዘኛዎች ቀርበዋል፤ የሳይበር ጥቃት ሪፖርት፣ የኢሜል ደህንነት፣ የይለፍ ቃል አጠቃቀም እና የመሳሰሉትን ተካተውበታል፡፡ በዚህ ዙሪያ በተካሄደው ጥናት በኢትዮጵያ የሳይበር ደህንነት ንቃተ ኅሊና አጠቃቀም 50ነጥብ 2 በመቶ አዎንታዊ ልምምድ ያደረጉ ተጠቃሚዎቹ ሲሆኑ አሉታዊ ልምምዶች ያደረጉት ተጠቃሚዎች 48 ነጥብ 9 በመቶ ያህሉ ናቸው፡፡

በአጠቃላይ ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ንቃተ ኅሊና ደረጃ የሳይበር ደህንነት እውቀት፣ አመለካከት እና ልምምድ የታየበት ነው ያሉት የጥናቱ አቅራቢ፣ በጥናቱ የተገኘው ውጤት የሳይበር ደህንነት ንቃተ ኅሊና እውቀት ያላቸው ዜጎች 35 በመቶ መሆናቸውን ማመላከቱን ጠቅሰዋል፤ 65 በመቶ ያህል ዜጎች እውቀቱ እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡

በአመለካከት በኩልም አዎንታዊ አመለካከት ያላቸው 47 በመቶ ያህል መሆናቸውን ጠቅሰው፣ 53 በመቶ ያህሉ አሉታዊ አመለካከት ያላቸው ናቸው ብለዋል። አጠቃቀም እንዲሁም አዎንታዊ ልምምድ ያደረጉ ተጠቃሚዎች ቁጥር 50 ነጥብ 2 በመቶ መሆናቸውን ገልጸው፣ አሉታዊ ልምምዶች ያደረጉት ተጠቃሚዎች 48 ነጥብ 9 በመቶ ያህሉ መሆናቸው ጥናቱ አመላክቷል ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ያለው የዜጎች የሳይበር ደህንነት ንቃተ ኅሊና ደረጃ 65 በመቶ ክፍተት እንዳለበት በጥናቱ መታወቁን አመልክተዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ የጥናቱ ተሳታፊዎች የትምህርት ደረጃ በአጠቃላይ ሲታይ 77 ነጥብ 3 ያህሉ ዲፕሎማ፣ ዲግሪ፣ ማስተርስ እና ፒኤችዲ ያላቸው ናቸው። ከእነዚህም 87 ነጥብ 5 ያህሉ ከ14 እስከ 35 ባለው የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ በመሆኑም አብዛኛዎቹ የተማሩ ተጠቃሚዎች ሆነው ሳለ ለምን ይህንን ያህል የሳይበር ንቃተ ኅሊና ክፍተት ሊመዘገብ ቻለ የሚለውንም ለማየት ተሞክሯል።

በአጠቃላይ የትምህርት ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ንቃተ ኅሊና ተለምዷዊ የሆነውን የሥነ ትምህርት በማሳደግና በማስፋፋት ብቻ ችግሩን መቅረፍ እንደማይቻል አቶ አየለ ጠቅሰው፣ በሀገራችን ይህ ከፍተኛ የሆነ የሳይበር ደህንነት ንቃተ ኅሊና ክፍተት ለሁሉም ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ዜጋ እኩል ስጋት እንደሆነ ያመላክታል ብለዋል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ የትምህርት ደረጃ ብቻውን የሳይበር ደህንነት ንቃተ ኅሊናን ለማረጋገጥ በቂ አለመሆኑን እንደሚያሳይ ጠቅሰው፣ ሁሉም ዜጋ የሳይበር ደህንነት ጉዳይን የራሱ ጉዳይ አድርጎ የሳይበር ምህዳሩ የሚያስፈልገውን ፕሮቶኮል አሟልቶ መጓዝ እንደሚያስፈልግ ማሳያ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

አቶ አየለ እንደሚሉት፤ ከጥናቱ ምክረ ሃሳቦች አንዱ በሳይበር ንቃተ ኅሊና ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ነው፡፡ ሌላኛው የሳይበር ደህንነት ጉዳይ ሜይንስትሬም መደረግ መቻል ያለበት መሆኑ ነው፡፡ ይህንንም በፖሊሲ፣ በሕግ ጸድቆ የግልም ሆነ የመንግሥት ተቋማት የሳይበር ደህንነት ጉዳይን ሜይንስትሪም አድርገው ካልሰሩበት አሁንም የሳይበር ንቃተ ኅሊና ክፍተቱ ሊቀጥል ይችላል፡፡

ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ አንደኛ የሳይበር ደህንነት ጉዳይ በየተቋማቱ በመዋቅር ደረጃ ሜይንስትሪም መደረግ አለበት፡፡ ሁለተኛ ለዚህም አስፈላጊውን የቴክኖሎጂና የሰው ኃይል አሟልቶ ወደ ሥራ መግባት ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ የመንግሥትና የግል ተቋማት እንዲሁም በተለየ መልኩ የሚዲያ ተቋማት ትኩረት አድርገው መሥራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ አቶ አየለ አጽዕኖት ሰጥተው አስታውቀዋል፡፡

ይህ ሁሉ ከተደረገ በኋላ እንዴት ነው ንቃተ ኅሊናን በማስፋት ግንዛቤ ማምጣት የሚቻለው የሚለውን ለማየት ብዙ ዓይነት መንገዶች መጠቀም ይቻላል የሚሉት አቶ አየለ፤ ከእነዚህ መንገዶች ውስጥ ለኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ በሚሆን መልኩ የምንፈልገውን ዓይነት የሳይበር ንቃተ ኅሊና ለማምጣት የሚያስችሉ ስልቶች መጠቀም ይገባል ብለዋል፡፡

እንደ ሀገር የሳይበር ንቃተ ኅሊና ክፍተት ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ በተወሰነ ፕሮግራም ብቻ ሰዎች ማንቃት አይቻልም ብለዋል፡፡ ለዚህም የሳይበር ምህዳሩ የሚፈልገው እውቀትና አተገባበር እንዲኖር ከግለሰብ ጀምሮ በየደረጃው ያለው ሁሉም አካል በቅንጅትና በትብብር መሥራት ይጠበቅበታል ሲሉ ምክረ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን   ኅዳር 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You