ዘርፉን ከመንግሥት ጀርባ ለማውረድና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙን ለማጎልበት

ስፖርት በተለይ በአሁኑ ወቅት ለስሜት አሊያም በማዝናናት ብቻ አይወሰንም። ጤናማና አምራችና ትውልድ ከማፍራት በተጓዳኝ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍልን በቀጥታና ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ተጠቃሚ ያደርጋል። በርካታ ቢሊዮን ዶላር የሚንቀሳቀስበት ግዙፍ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ሆኖም የሀገራት ዋነኛ የኢኮኖሚ ምንጭና የምጣኔ ሀብት እድገታቸው መዘውር ሆኗል።

የተለያዩ ስፖርቶች በፍቅር ከሚወደዱባቸው ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ናት፡፡ በሀገሪቱ ዘመናዊ የስፖርት ውድድሮች መካሄድ ከጀመሩ አንድ ክፍለ ዘመን ሊሞላቸው ተቃርቧል። ይሁንና እነዚህን ሁሉ ዓመታት መመልከት ሳያስፈልገን የቅርቦቹን አስርና አስራ አምስት ዓመታት እንኳን ብንቃኝ የስፖርት ዘርፍ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ፈሰስ ይደረግለታል።

በመንግሥት ወጪ በርካታ የስፖርት መሰረተ ልማት አውታሮች እየተስፋፉ በተለይ የውድድር ማከናወኛ ግዙፍና ዘመናዊ ስታዲየሞች ተገንብተዋል። የአንዳንዶቹ ግንባታም ቀጥሏል። ከስቴዲየም ግንባታ በተጓዳኝ በተለያዩ ከተሞች የወጣት ስፖርት አካዳሚዎች ተከፍተዋል።

ይህ የሀገሪቱ መንግሥት ስፖርቱን የማጎልበት ዓላማና ሚና መሰረተ ልማቶችን በማስፋፋት ብቻ ተወስኖ የሚቆም ግን አይደለም። በሀገሪቱ የሚገኙ ፌዴሬሽኖች መካከል ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት በራሳቸው ገቢ መፍጠርና ማምጣት የማይችሉና ከዓመት ዓመት የሥራ ማስኬጃ ድጎማ ለመጠየቅ የመንግሥት በር ከማንኳካት ያልቦዘኑ ናቸው። ይህ እንደመሆኑም የሀገሪቱ መንግሥት በየዓመቱ በሩን ለሚያንኳኩ ፌዴሬሽኖች እጁን አያጥፈም።

ከፌዴሬሽኖች በተጓዳኝ በመንግሥት ተቋማት አሊያም ልማት ድርጅቶች ስር የሚገኙ ክለቦችም በየዓመቱ የዚሁ ድጎማ ተቋዳሽ ናቸው።የራሳቸውን ገቢ በራሳቸው መሸፈን እንኳን ያልሆነላቸው አንዳንድ የመንግሥት ጥገኛ ክለቦች በአንፃሩ ለአንድ ተጫዋች በሚሊዮን የሚቆጠር የፊርማና የወር ደሞዝ ይከፍላሉ። ከሀገር ውስጥ አልፈው ከውጭ ተጫዋች ያስመጣሉ።ከዓመት ከዓመት ከቀበሌ ጀምሮ የሚደረጉ ስፖርታዊ ውድድሮች ለማከናወን፤ ለስልጠና ለምልመላ፤ የስፖርት ትጥቆችን ለመግዛት እንዲሁም ለተዋናዮቹ የሚሆን አበል እየተባለ ረብጣ ገንዘብ ፈሰስ ይደረጋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ማንኛውንም ሀገር ከዓለም አቀፍ የስፖርት የሀብት ምንጭ ተጠቃሚ ከሚያደርጉ መንገዶች አንዱና ዋነኛው የስፖርት ኢንቨስትመንት መሆኑ ይታወቃል። የኢትዮጵያን የስፖርት ዘርፍ በዚህ መነፅር ከተመለከትነው ግን እንደ አንድ ኢኮኖሚና ኢንቨስትመንት ሆኖ አናየውም።

ዘርፉ «አክሳሪ አሊያም አትራፊ ነው» የሚለው በቅጡ አይታወቅም። ዘርፉ በሀገሪቱ አጠቃላይ ኢኮኖሚ ውስጥ ያለው ድርሻ ምን ያህል እንደሆነና ለኢንቨስትመንት ያለውን አመቺነት ለመረዳት በዚህ ረገድ የተጠኑ ጥናቶችን መኖር አለመኖራቸውን ማረጋገጥም እጅጉን ከባድ ነው፡፡

ዘርፉ በሀገሪቱ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ውስጥ ትርጉም ያለው ገቢ ማስገኘት ችሏል ወይንስ ጨርሶ በኢኮኖሚ ገቢ ምንጭነት ደረጃ አልደረሰም ለማለትም በቂ መረጃ የለም፡፡ ይህ መረጃ የሀገሪቱን ስፖርት በበላይነት ከሚመራው ተቋም በሪፖርት መልክ ሲቀርብ አይታይም፡፡ አይሰማም፡፡

በእርግጥ አነጋጋሪ ቢሆንም ቀጥታም ሆነ ቀጥተኛ ባልሆነ መልኩ በሀገሪቱ ውስጥ የስፖርቱ ዘርፍ አበርክቶ ሙሉ በሙሉ የለም ማለት አያስደፍርም። በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከውድድርነት ተሻግሮ ታላላቅ የግንባታ ፕሮጀክቶች ለማስፈፀም የህዝብ ተሳትፎ ለማጠናከር በሚደረገው ርብርብ ላይ የማስተባበር ሚና እያበረከት ነው። ይህም እንደ አንድ ሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ ምንጭ ሊወሰድ የሚገባው ነው። ይሁንና ይህም ቢሆን ቦግ ጭለም የሚል እንደመሆኑ የዘርፉን አበርከቶ ውስን አድርጎታል።

ሌላው ከሥራ ፈጠራ አንፃር ነው። ስፖርት በሀገር እድገት ከሥራ እድል ፈጠራ አኳያ ያለው ፋይዳ በአንድና በሁለት ደረጃ ተጠቅሶ የሚቆም አይደለም። ለአብነት በኮንስትራክሽን ዘርፍ አንድ ስታዲየም ሲገነባ በአማካኝ ለብዙ ሺ ዜጎች የሥራ እድልን የመፍጠር አቅም አለው። ሥራ እጥነትን መቅረፍ በራሱ አንድ የኢኮኖሚ አስተዋጽኦ ነው። ይሁንና በሥራ እድል ፈጠራም ቢሆን የሀገራችን የስፖርት ሴክተር ምን ያህል ሰዎችን በስሩ አቅፏል ለምን ያህል ዜጎችስ የሥራ እድል ፈጥሯል የሚለው በቅጡ የሚታወቅ አይመስለኝም።

በእርግጥ ስፖርቱ ከተሞች እንዲለሙ ምክንያት እየሆነ ነው። ትላልቅና ዓለም አቀፋዊ ይዘትን የተላበሱ ስታዲየሞች ግንባታ መገንባት ሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ጎን ለጎን እንዲገነቡ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል። ይህም ትልቅ የልማት በርን በመክፈት የስታዲየሙ ግንባታ በሰፈረበት ከተማ ውበትና ኢኮሚኖሚያዊ እድገት የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚፈጥር የሚካድ አይደለም፡፡

ይሁንና እነዚህ የስፖርት መሰረተ ልማቶች ከሚሰጡት ስፖርታዊ አገልግሎት በተጨማሪ እንዴት ተጓዷኝ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም መስጠት ይችላሉ? እንዴትስ እየሰጡ ነው? የመሰረተ ልማቱን ያህል ስፖርቱን ኢኮኖሚ ማድረግ የሚችል ተመጣጣኝ አሰራርና አመራር እንዲሁም ስፖርተኛ አፍርተናል? ስፖርቱ ከሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊና ማህበራዊ እድገት አንፃር እየተጋዘ ነው ወይንስ ተንቀራፏል? የሚለውን ጥያቄ ለጠየቀ መልሱን ማግኘት ቀላል አይሆንለትም፡፡

በቅርቡ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ቆይታ ያደረጉት የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ቀጀላ መርዳሳም ይህን ታሪክ ለመለወጥና የስፖርት ዘርፉ ከድጋፍ ወጥቶ በሀገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ አስተዋጽኦ እንዲኖረው ለማድረግ አቅጣጫ ተቀምጦ ሥራዎች መጀመራቸውን አሳውቀዋል፡፡፡

‹‹የብዙ ሀገራት ተሞክሮ የሚያሳየው ስፖርት የገቢ ምንጭ ሆኖ ሀገራዊ ጥቅም እያስገኘ ነው፡፡ መንግሥት ስፖርትን ከመደገፍ አልፎ ዘርፉ በራሱ መንግሥትን እንዲደግፍ መሥራት ያስፈልጋል።›› ያሉት አቶ ቀጄላ፤ በኢትዮጵያም ዘርፉን ለኢንቨስመንት ክፍት በማድረግ ተጠቃሚ ለመሆን እየተንቀሳቀሰች መሆኑንም ነው የጠቆሙት፡፡

እርሳቸው እንደነገሩንም፣ እስካሁን ሲሠራበት የቆየው ስፖርትን ማልማት በሚል አካሄድ ነበር። አሁን ግን ስፖርትን ለልማት ማዋል የሚቻልበት አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ በዚሁ መሠረትም በዘርፉ ለሚሰማሩ ኢንቨስተሮች ምቹ በማድረግ ስፖርቱ ከድጋፍ ወጥቶ በሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ አስተዋጽኦ እንዲኖረው እየተሠራ ነው፡፡

ይህ ስፖርቱን ከኢንቨስትመንት ጋር ለማስተሳሰር የተጀመረ እንቅስቃሴ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ይሁንና በተለይም ክለቦችን ከመንግሥት ጀርባ የማውረድ ተግባር ጊዜ ሊሰጠው የሚገባ እንዳልሆነ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ስፖርትን ወደ ኢንቨስትመንት ለመቀየር ከሚረዱ አማራጮች መካከልም ክለቦች በሕዝባዊ መሰረት እንዲታቀፉ ማድረግ አንደኛው ነው፡፡

እንደሚታወቀው ክለቦች በውድድር መድረኮች ለሚኖራቸው ውጤታማነትና ቆይታ በተለይም ለህልውናቸው ቀጣይነት የሚከተሉት የክለብ አደረጃጀት እጅግ ወሳኙን ድርሻ ይወስዳል። የክለቦችን አደረጃጃትና አመራር ቀጣይነትና መሰረት ባለው መልኩ ሕዝባዊ መሰረተን የተከተለ እንዲሆን ማድረግ ደግሞ ውጤታማነትን የላቀ የማድረግ አቅሙ ግዙፍ ነው፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ የወጣው የስፖርት ፖሊሲ፣ ክለቦች ደረጃ በደረጃ በሂደት ህዝባዊ አደረጃጀት እንዲኖራቸው ይደግፋል፡፡ የፖሊሲው ፍላጎትና የትኩረት አቅጣጫም የስፖርት አጠቃላይ እንቅስቃሴ፤ አደረጃጀትና አመራር ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው ነው።

ከዚህ በተጓዳኝ ስፖርቱ ከመንግሥት በጀትና ድጎማ ደረጃ በደረጃ የሚላቀቁበትና ራሱን የሚችልበት ምቹ ሁኔታ መፍጠርንም ይመለከታል። ይሁንና አሁን ላይ እንደሚታየው ከሆነ ጥቂት ከሚባሉት በስተቀር አብዛኞቹ የሀገሪቱ ክለቦች በመንግሥት ስር የተደበቁና ህዝባዊ አደረጃጀት የሌላቸው ናቸው።

ዘጠና በመቶ የሚሆኑት የሚተዳደሩም በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ስር ነው። ይህ እንደመሆኑም ከመንግሥት የገንዘብ ድጎማ የተላቀቁ አይደሉም። ከመንግሥት ከሚመደብላቸው ውስን በጀት ውጪ የራሳቸው የሆነ ቋሚ የገቢ ምንጭ የላቸውም። የራሳቸው ቋሚ ገቢ ለመፍጠር የሚያስችሉ አሰራሮችን የሚተገብሩም አይደሉም።

ለአብነት እግር ካስን ብንመለከት አብዛኞቹ በሀገሪቱ የሚገኙ ክለቦቹ በመንግሥት ድጎማ የሚንቀሳቀሱና ህልውናቸውና አደረጃጀታቸው የመሰረቱ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያትነት የመንግሥት ድጎማ ሲቀር የክለቦቹ አደረጃጀትም አብሮ ይቀራል። የመንግሥት መዋቅር ሲስተካከልና ሲለዋወጥ ክለቦቹም አብረው ይለወጣሉ። አሊያም ይፈርሳል።

አብዛኞቹ ክለቦችም በመንግሥት የልማት ድርጅቶች የሚተዳደሩ እንደመሆናቸው ለአብነት የአንድ ፋብሪካ መዋቅር ሲቀየር ክለቦቹም አብረው ይቀየራሉ። አሊያም ስለስፖርት ጥሩ አመለካከት የሌለው አመራር ወደ ፋብሪካ በአመራርነት ከመጣ በግለሰብም ፍላጎት ሳይቀር ህልውናቸው አክትሞ ሊፈርሱ ይችላሉ። በዚህ ሂደት ለመፍረስ የበቁም አሉ። ለዚህ ደግሞ በርካታ ክለቦች ምሳሌ ይሆኑናል።

አሁን ላይ በሀገሪቱ በሁሉም ክልሎች የከነማ ክለቦች አሉ። የእነዚህ ክለቦችም አደረጃጀትም ተመሳሳይ ነው። ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ የራሳቸው የሆነ ቋሚ ገቢ የሌላቸውና የክልል ከተማ አስተዳደር በቀጥታ ኢንቨስት የሚያደርግባቸው ናቸው።ከድጎማና ጣልቃ ገብነት የተላቀቁም አይደሉም።

የዚህ የክለቦችና የመንግሥት ያልተገባ ጥምረት መቀጠልም በርካታ ምክንያቶች ይነሳሉ፡፡ በተለይ መንግሥት ክለቦችን ምን ያህል እየደጎመ ማቆየት እንደሚቻል ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ አለመኖሩ ዋነኛው ተጠያቂ እንዲሆንና ለችግሩ ዘላቂነት የጎላውን ድርሻ እንዲወስድ ያደርገዋል። ይህ ድክመቱም፤ ክለቦች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ልክ ቀጣይ አደረጃጀታቸውን የሚመለከት አቅጣጫ እንዳይቀይሱና ባሉበት ደረጃ ሁሌም እንዲመላለሱ አብይ ምክንያት ሆኗል።

ክለቦችም ቢሆን የመንግሥት ድጎማ ተመችቷቸዋልና ሌሎች አማራጮችን ላለመመልከት አይናቸውን ሸፍነዋል። የህልውናቸው ቀጣይነት የሚመሰረተው በመንግሥት ድጎማ የተለቀቀ አደረጃጀት ሲከተሉ መሆኑን ረስተዋል።በዚህም ምክንያት አደረጃጀታቸውን የሚመለከት ቀጣይ አቅጣጫ ሲቀይሱ አይስተዋልም።

ዘላቂ ውጤት ባለው መሰረት ላይ የተሻለ ሕዝባዊ አደረጃጀት፤ አሰራር ሥርዓትና የራሳቸው ቋሚ የገቢ ምንጭ ለመፍጠር አይንቀሳቀሱም፡፡ ስፖርቱን ከኢንቨስትመንት ጋር ለማስተሳሰርና ኢኮኖሚያዊ አበርክቶውን ከፍ ለማድረግ ከተፈለገ መሰል ችግሮች ልዩ ትኩረትና መፍትሄ ሊሰጣቸው የግድ ነው፡፡

ስፖርቱ ባለበት ስለመርገጡ ስለተደረገው፤ ያልተደረገው አሊያም የማይደረገው ጥያቄ ሲነሳ መልሳችን ሰበብ ከሆነ በሞተ ትናንትና ባልተወለደ ነገ መሃል መሆናችንን መረዳት አለብን። ከዚህ ቅርቃር ለመውጣት ደግሞ ዘርፉ እንዴት ይለወጣል?የሚለውን ብቻ ሳይሆን ክፍተቱንም ለመመልከት ዝግጁ መሆን እና የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት የግድ ይለናል፡፡

ከሁሉ በላይ መንግሥት እየደጎመ የሚያወዳ ድራቸው ክለቦች ከጥገኝነት ተላቀው ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ አለበት። መንግሥትም ክለቦችን እየደጎመ መቀጠል የለበትም። ስፖርቱን ሕዝብና ክለቦቹ በጋራ እንዲመሩት ማድረግ ይኖርበታል። መስራት ያለበት እነዚህ አካላት የሀገሪቱን ህግና ደንብ አክበረው የሚሰሩበትን እድል መፍጠር ነው። ክለቦችም ከመደጎም የሚላቀቁበት የመውጫ ስትራቴጂ ሊያዘጋጁ የግድ ይላል። ክለቦች ሕዝባዊ አደረጃጀቶች ለመተግበር መንቀሳቀስና የራሳቸው የሆነ የገቢ ምንጭ በአስተማማኝ ሁኔታ መገንባት ላይ ትኩረት ሠጥተው ሊሠሩ ይገባል።

ታምራት ተስፋዬ

አዲስ ዘመን   ኅዳር 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You