አብሮን ዘመናት እየተሻገረ ያለ የምርት ብክነት

ለዋጋ ግሽበት ምክንያት ናቸው ከሚባሉ ነገሮች አንዱ የምርት ብክነት ነው፡፡ የምርት ብክነት ማለት ሊገኝ ከሚገባው ምርት ውስጥ በአያያዝና አሰባሰብ ችግር ምክንያት መጠኑ ሲቀንስ ማለት ነው፡፡ ሊገኝ የሚገባው የምርት መጠን ቀነሰ ማለት የምርት ቅናሽ ተከሰተ ማለት ነው፡፡ የምርት መቀነስ ደግሞ የዋጋ ግሽበትን ያመጣል፡፡

የዋጋ ግሽበት የሚባለው በተወሰነ የጊዜ መጠን ውስጥ የምርት እና አገልግሎቶች ዋጋ መጨመር ማለት ነው፡፡ በሚፈለገው ልክ ማቅረብ አለመቻል ማለት ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች ሲከሰቱ ‹‹የኑሮ ውድነት›› ይባላል ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ምንም የተውሰበሰበ የምጣኔ ሀብት ትንተና ሳያስፈልገው፤ የአንድ ምርት ወይም አገልግሎት ዋጋ ከፍተኛ ይሆናል ማለት ነው፡፡

ምንም እንኳን አሁን በሀገራችን (በተለይም በከተሞች) የሚታየው የኑሮ ውድነት ምክንያቱ የምርት ብክነት ብቻ ነው ባይባልም ቢያንስ ግን አንዱ ምክንያት ነው፡፡ አሁን ወቅቱ በብዙ የኢትዮጵያ አካባቢዎች (በተለይም በማዕከላዊና ሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች) የመኸር ወቅት ነው፡፡

የኅዳር ወር በከፍተኛ ትጋት ሰብል የሚሰበሰብበት ወር ነው፡፡ በዚህ ወቅት ታዲያ ከፍተኛ የሆነ የምርት ብክነት ያጋጥማል፡፡ የምርት ብክነቱ የሚያጋጥምባቸውን ምክንያቶች ከመጥቀሴ በፊት ግን አንድ ገጠመኝ ላስታውስ፡፡

በ2010 ዓ.ም ይመስለኛል፡፡ በወቅቱ ስያሜው የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ወደ ቆቃ አካባቢ የፍራፍሬ ምርቶችን ለማስጎብኘት ወስዶን ነበር። በወቅቱ ባለሙያዎች ከነገሩን ነገር አንዱ ከፍተኛ የሆነ የምርት ብክነት እንደሚያጋጥም ነው፡፡ በአያያዝ ምክንያት በተለይም እንደ ቲማቲም፣ ማንጎና አቮካዶ የመሳሰሉ ምርቶች በተፈላጊው የምርት ጥራት አይላኩም፡፡ የመለየት ሥራው አስቸጋሪ ነበር፡፡

የሰብል ምርት የሆኑትን የግብርና ምርቶች ስናስተውል ደግሞ የበለጠ ከፍተኛ ብክነት ይታይባቸዋል፡፡ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት እስከማጠናቅቅበት ጊዜ ድረስ ከግብርና ሥራዎች አልራቅኩም፤ እኔ ንቁ የግብርና ተሳታፊ ባልሆን እንኳን ቤተሰብን በማግዝበት ሰዓት በትንሹ፤ ከዚያ ውጪ ደግሞ በአካባቢያችን የሚከናወኑ የግብርና ምርት አሰባሰብ ሂደቶችን በማየት ከፍተኛ ብክነት እንደሚፈጸም አስተውያለሁ፡፡

በብዙ አካባቢዎች የግብርና ምርቶች የሚሰበሰቡት በልማዳዊ መንገድ ነው፡፡ ለምሳሌ፤ ጤፍ የሚታጨደው በእጅ (በማጭድ) ነው። የጤፉን አገዳ ይዘው ጭንቅላቱ እየተወዛወዘ ችቧቸው እስከሚሞላ ያጭዳሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ የጤፉ ፍሬዎች ይወድቃሉ፡፡ የጤፍ ፍሬ በጣም ትንንሽ ከመሆናቸው የተነሳ መሬት ላይ አይታዩም። እንደሚባክን ግን ያውቃሉ፡፡ ቃሉን በጋዜጣ ለመጠቀም ባይመችም ጤፍ ሳይታወቅበት የሚባክን ምርት መሆኑን የሚገልጽ አባባልም አላቸው፡፡

እያጨዱ ችቧቸው ሲሞላ ከኋላ የታጨደው ላይ እያስቀመጡ ነው ወደፊት የሚሄዱት፡፡ ያ ማሳ ላይ በትንሽ በትንሹ (በችቦ ልክ) የተቀመጠ ጤፍ እንደገና ከፍ ወዳለ ስብስብ ይሰበሰባል፤ አሁንም እየፈሰሰ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ አሁንም ተሰብስቦ ክምር ይደረጋል፤ አሁንም እየፈሰሰ ነው። ማሳ ላይ የተከመረው ክምር ደግሞ ሰፈር አካባቢ ወደሚገኘው አውድማ በሸክም ይወሰዳል፤ አሁንም እየፈሰሰ ነው።

አውድማው ጤፍ ለማበራየት በሚያስችል ሁኔታ ተደርጎ ይዘጋጃል፡፡ የሚበራየውም በበሬ ነው፡ ፡ በሬ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ የጤፍ ፍሬዎች ከአገዳውና ከሙሉ ገለባው ተላቀው በኩንታል ውስጥ እስከሚታዩ ድረስ ያለው ሂደት ከ24 ሰዓት በላይ የሚወስድ ሥራ ስለሆነ ዘርዝረን አንጨርሰውም፤ በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ የጤፍ ፍሬዎች ይባክናሉ። ምንም እንኳን ሳይንሳዊ የተጠና ነገር ባይኖረውም ገበሬዎች በልማድ እንደሚናገሩት የሚባክነው ምርት ወደ ጎተራ ከሚገባው አይተናነስም፡፡

ለዚህ ደግሞ አንድ ማሳያ አለ፡፡ ‹‹ምርትና ግርድ›› የሚሉት፡፡ ምርት ማለት በትክክል የተጣራው ሲሆን ግርድ ደግሞ የተራረፈው ማለት ነው፡፡ በምርትና በግርዱ መካከል የጤፍ ፍሬዎች ልዩነት የላቸውም፤ ልዩነቱ ግርዱ ከገለባው ጋር ያለው መሆኑ ነው፡፡ ከአቅም በላይ ሆኖ ያመለጠው ማለት ነው፡፡ ይህ አውድማ ላይ ብቻ የሚባክነው ነው፡፡

እንደ ማሽላ እና ጥራጥሬ ያሉ የሰብል አይነቶች ከተሰበሰቡ በኋላ ልጆች ‹‹ቃርሚያ›› በሚል ማሳ ውስጥ ይሄዳሉ፡፡ በምርት አሰባሰብ ሂደት ውስጥ ከቁጥቋጦ ውስጥ፣ ከእርከን ሥር፣ ከቦይ አካባቢ የተራረፉትን ለመሰብሰብ ማለት ነው፡፡ እንደማሳው መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ ሁኔታ ልጆች ብዙ ምርት ያገኛሉ፡፡

ያንን ያገኙትን ምርት ቤተሰብም ሆነ የማሳው ባለቤት አይጠይቃቸውም፡፡ ሸጠው ብሩ ለራሳቸው ነው፡፡ ልጆች እንደዚያ ካላደረጉ ደግሞ የወዳደቀው (የባከነው) ሰብል የአራዊት ይሆናል ማለት ነው፡፡

ከማሳ እስከ ጎተራ ባለው ሂደት ውስጥ ይህ ሁሉ ብክነት ያጋጠመው አሰራራችን ዛሬም ያው ነው፡፡ በኮምባይነር ምርት የሚሰበስቡ አካባቢዎች እጅግ በጣም ጥቂት ናቸው ፤ ጥቂት መሆናቸው ብቻ ሳይሆን የኮምባይነር አገልግሎት የሚያገኙት አብዛኞቹ ኩታ ገጠም አካባቢዎች እና የስንዴ ማሳዎች ናቸው ፡፡ በኢትዮጵያ በሰፊው ለምግብነት የሚውለው የጤፍ ምርት በዘመናዊ መንገድ መሰብሰብ አለመቻሉ /ብዙ ብክነት ማስተናገዱ ምን ማለት እንደሆነ ለመገመት አይከብድም፡፡

የምርት ብክነት የሚያጋጥመው በእነዚህ የአገዳ እህሎች ላይ ብቻ አይደለም፡፡ በአትክልትና ፍራፍሬ ጭምር ነው ፤እንዲያውም ችግሩ የከፋ ሳይሆን አይቀርም፡፡ በተለይ እንደ ቲማቲም ያሉ ፍራፍሬዎች በቀላሉ የሚበላሹ ስለሆኑ በከፍተኛ ሁኔታ ይባክናሉ። የሚባክኑት በአያያዝና አሰባሰብ ችግር ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለባለቤቱ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገርም ኪሳራ እየሆነ ነው ፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ‹‹የምርት እጥረት አለ›› ብሎ መናገር አሳፋሪ መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም በየትኛውም አካባቢ ቢሄዱ ቢያንስ ከአንዱ አካባቢ ያለው ሌላ አካባቢ ላይኖር ይችላል እንጂ በሁሉም ቦታዎች የምርት አይነቶች አሉ። ዳሩ ግን የግንዛቤ እጥረት አለ፡፡ የግንዛቤ እጥረት ነው የምርት እጥረት ያመጣብን፡፡

አፈሩ እጅግ ብዙ ምርቶችን ያፈራል፤ ዳሩ ግን ወደ ተጠቃሚ የሚደርሰው ከግማሽ በታች የሚሆነው ሊሆን ይችላል፡፡ የተቀረው እዚያው ባክኖ ይቀራል፡፡ በዚህ ምክንያት ባለ ምርቱ ሸጦ ሊያገኘው የሚገባውን ገንዘብ ሳያገኝ ይቀራል ነው፤ ሸማቹ የኅብረተሰብ ክፍል ተፈላጊውን ጥራት ብቻ ሳይሆን ያንኑም ጥራቱን ያልጠበቀውን ሳይዳረስ ይቀራል ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም ይመጣል፤ ይህ ደግሞ የዋጋ ግሽበት፤ ቀጥሎም የኑሮ ውድነት ያስከትላል ማለት ነው፡፡

ስለዚህ የምርት እጥረት እንዳያጋጥም የግንዛቤ እጥረትን እናስተካክል! ለዚህ ደግሞ የዘርፉ ባለሙያዎች ወደ አምራቹ የኅብረተሰብ ክፍል በመጠጋት በችግሩ ዙሪያ ያለውን እውነታ ሊያሳውቁት እና ሊያስተምሩት የተሻሉ መፍትሔዎችን አብረውት ሊያፈላልጉ ያስፈልጋል፣ መንግሥትም ለዚህ የሚሆኑ ሁኔታዎች ሊያመቻች፤ አስፈላጊ ግብዓቶችን ሊያቀርብ ይገባል!::

ሚሊዮን ሺበሺ

አዲስ ዘመን   ኅዳር 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You