የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጉብኝት አመርቂ ውጤት የተገኘበት ነው

  • የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ በሌሎች ሀገራት እንደተሞክሮ ተወስዷል

 አዲስ አበባ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሰሞኑ ጉብኝትና የተለያዩ ጉባዔዎች ተሳትፎ አመርቂ ውጤት የተገኘበትና የኢትዮጵያን በጎ ገጽታ ከፍ ያደረገ መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) የአውሮፓና የዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ቆይታ አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰሞኑ ጉብኝትና የተለያዩ ጉባዔያት ተሳትፎ የተሳካ፣ አመርቂ ውጤት የተገኘበትና የኢትዮጵያ ክብር የታየበት ብሎም በጎ ገጽታዋ ከፍ ያለበት ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቆይታቸው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ዓመታዊ ጉባዔ፣ በአየር ንብረት ለውጥ የመሪዎች ጉባዔ እና በቼክ ሪፐብሊክ ይፋዊ ጉብኝት አድርገዋል ያሉት ዶክተር ለገሰ ፤ ከጉባዔው ጎን ለጎን ከተለያዩ ሀገራት መሪዎችና የዓለምአቀፍ ተቋማት መሪዎች ጋር ውጤታማ የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸውን አመላክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ዓመታዊ ጉባዔ ላይ በክብር እንግድነት ተጋብዘው መገኘታቸውን አስታውሰው፤ አካታችና ዘላቂ የኢንዱስትሪ ልማትን ለማረጋገጥ በተካሄደው ውይይት መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡

በጉባዔው የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያ በማድረግ ውጤታማ የሆኑ ሀገራት ልምድ ማቅረባቸውን ጠቁመው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያ አመርቂ ውጤት ማስመዝቧንና ሀገራት ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው መግለጻቸውን አስረድተዋል፡፡

ጉባዔው ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ ፣ በምግብ ዋስትና፣ በሌማት ትሩፋትና በሌሎች መስኮች ያደረገቻቸውን በጎ ልምዶች ለዓለሙ ማህበረሰብ ያካፈለችበት መሆኑን ዶክተር ለገሰ ተናግረው፤ በተለይም ከተመድ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ኢትዮጵያ አግሮ ኢንዱስትሪና ሌሎችን ለማስተሳሰር የምታደርገው ጥረት ለሌሎች ሀገራት ልዩ ተሞክሮ ሊሆን እንደሚችል አድናቆት ተችሮታል ብለዋል፡፡

የበለጸጉ ሀገራት እንደ ኢትዮጵያ ስኬታማ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ለሚገኙ ሀገራት ድጋፋቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማሳወቃቸውንና ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ ስኬትና ሂደት የምታሳይበት ኤክስፖ መክፈታቸውን ዶክተር ለገሰ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ከዓለም አቀፍ ጉባዔዎች ጎን ለጎን ከተለያዩ ሀገራት መሪዎችና የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነት አካሂደዋል ያሉት ሚኒስትሩ፤ በተለይም አጋርነት የማስፋት፣ የፋይናንስ ኢንቨስትመንት ላይ በመምከር አወንታዊ የሆኑ ምላሾች የተገኙበት ነው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቼክ ሪፐብሊክ በነበራቸው ይፋዊ ጉብኝት በተለይም በግብርና መካናይዜሽን፣ በኢንዱስትሪ፣ ለአየር ኃይል የአቅም ግንባታ ላይ ከሚሠሩ ተቋማትና ፣ ከባለሀብቶች ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፕሬስ ሴክሬታሪ ኃላፊ ቢለኔ ስዩም በበኩላቸው ፤ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)በቼክ ሪፐብሊክ በነበራቸው ጉብኝት በተለይም በቱሪዝምና በግብርናው ዘርፍ በጋራ ለመሥራት፣ በመከላከያ የአቅም ግንባታና የልምድ ልውውጥ፣ አየር ኃይልን ለማጠናከር አብሮ ለመሥራት ውይይት ማድረጋቸውን አመላክተዋል።

በተባበሩት ዓረብ ኢምሬትስ በተዘጋጀው የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ላይ ደግሞ ኢትዮጵያ የመካነ ርዕይ ማዘጋጀቷን በመግለጽ፤ የአረንጓዴ ዐሻራ ስኬቶችን፣ የግብርና፣ የምግብ ዋስት፣ ታዳሽ ኃይል ሥራዎችን ለመሪዎች ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኮፕ 28 ላይ ያቀረቡት ሃሳብ ተግባር ላይ ያተኮረ መሆኑን ጠቅሰው፤ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በርካታ ጥረቶች ይደረጋሉ ማለታቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ ተሞክሮ በሌሎች ሀገራት ላይ ተነሳሽነትን የፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በመከተል የተለያዩ ሀገራት የዛፍ ተከላ ኢኒሼቲቮችን ማስጀመራቸውን አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በነበራቸው ቆይታ የተለያዩ የሁለትዮሽ ውይይቶች ማካሄዳቸውን ጠቁመው፤ በተለይም ከቤልጂየም ጠቅላይ ሚኒስትር ፣ ቀጣናዊ አህጉራዊና በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ከኩባ ፕሬዚዳንት በትምህርት በጤና በቱሪዝም ላይ በጋራ ለመሥራት መወያየታቸውንና ከተለያዩ ሀገራት መሪዎችና የዓለምአቀፍ ተቋማት መሪዎች ጋር ተገናኝተው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውጤታማ ምክክር ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን   ኅዳር 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You