የግል ትምህርት ቤቶች «የግል ሥርዓተ ትምህርት»!

ታላቁ የነጻነት ታጋይና የፖለቲካ መሪ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ ለትምህርት የተለየ ፍቅር እንደነበራቸው ይነገራል። ብዙ ጊዜ ስለእርሳቸው ሲነሳ “ዓለምን መለወጥ የሚያስችል ብቸኛው መሳሪያ ትምህርት ነው” የሚለው አባባላቸው ሳይጠቀስ የማይታለፈውም ለዚሁ ነው። በርግጥም ትምህርት ራስን፣ አካባቢን፣ ሀገርንና ወገንን ከፍ ሲልም ዓለምን የመለወጥ ኃይል አለው። ይህንን የሚያደርገው ደግሞ የሰውን ልጅ የአስተሳሰብ አድማሱን በማስፋት፣ ዓለምን የሚመለከትበት ዕይታውን ወይንም አመለካከቱን በማስተካከልና ነገሮችን የመከወን ክህሎቱን በማሳደግ ነው።

ትምህርት የሰው ልጅ አዕምሮ ችግር ፈች በሆነ አስተሳሰብ እንዲሞላ ስለሚያደርገው አዳዲስ ነገሮችን የመፍጠር ብቃትን ያላብሰዋል። ዓለም በየጊዜው ያለፈችበት የለውጥ ሂደትና አሁን ላይ የደረሰችበት አጠቃላይ የሥልጣኔና የዕድገት ደረጃም የሰው ልጅ በትምህርት አማካኝነት በየጊዜው የሚገጥሙትን ችግሮች እየፈታና አዳዲስ ነገሮችን እየፈጠረ በአሸናፊነት ወደፊት መጓዝ የመቻሉ ውጤት ነው።

ለዚህ ደግሞ ትምህርት የሚጠበቅበትን ዓላማ ማሳካት እንዲችልና በትክክል የለውጥ መሳሪያ ሆኖ እንዲያገለግል የዜጎችን አካላዊና አዕምሯዊ የእድገት ደረጃ ያማከለና ሁሉንም እንደየፍላጎቱና አቅሙ ተጠቃሚ ሊያደርግ በሚችል ተገቢ ሥርዓተ ትምህርት ሊመራ ይገባዋል። ይሁን እንጂ በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በመዲናችን አዲስ አበባ ከመደበኛው የሀገሪቱ ሥርዓተ ትምህርት ውጭ የሆነ የራሳቸውን ማስተማሪያ መጽሐፍ አዘጋጅተው የሚያስተምሩ አንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን በተለያየ አጋጣሚ ሕብረተሰቡ በስፋት ሲያነሳው የሚሰማ ጉዳይ ነው።

ከሰሞኑ በአንድ አጋጣሚ በዚሁ ጉዳይ ላይ የታዘብኩትና እንደ አንድ ኃላፊነት የሚሰማው ኢትዮጵያዊ በጉዳዩ ላይ አሳሳቢ ሆኖ ያገኘሁትን ችግርና ጉዳዩ የሚመለከተው አካል መፍትሔ ይፈልግለት ዘንድ ሃሳቤን ላካፍላችሁ ወደድኩ።

ከሰሞኑ ወደ አንድ ጓደኛዬ ቤት ጎራ ብዬ ነበር። አዲስ አበባ ውስጥ በአንድ የግል ትምህርት ቤት ውስጥ አስተማሪ ነው። ታዲያ ቤት ውስጥ ተቀምጠን ስለሥራ፣ ኑሮ… የተለያዩ ጉዳዮችን እያነሳን እየተጨዋወትን እያለ በመሃል “አንተ እኮ እንግሊዝኛ ነው ያጠናኸው፤ እስኪ እነዚህን መጽሐፎች እያቸው” አለና ከኋላው ካለው ጠረጴዛ ላይ አራት የሚሆኑ የ“ኤ4” መጠን ያላቸው ትልልቅ ሞጁል መሳይ መጻሕፍቶችን አንስቶ ሰጠኝ። እርሱ በሌላ የትምህርት መስክ ተመርቆ ነው በትምህርት ቤቱ ውስጥ የእንግሊዝኛ ቋንቋ አስተማሪ የሆነው። ይህንንም ያዙልኝና ወደዋናው ጉዳዬ ልለፍ።

ከዚያም በጥያቄው መሠረት መጻሕፍቱን ተቀብዬ በጉጉት ማገላበጥ ጀመርኩ። ሁሉም የአራተኛ ክፍል ማስተማሪያዎች ናቸው። በእያንዳንዱ ሞጁል ላይ የተጻፈው የትምህርት ዓይነት ስም እንደ ወረደ አንደኛው “ኢንግሊሽ”፣ ሁለተኛው “ስፖክን”፣ ሦስተኛው “ሪዲንግ ስኪል” አራተኛው ደግሞ “ጀኔራል ሳይንስ” ይላል። እርሱ እንዳለው የተመረኩበት የትምህርት ዘርፍ እንግሊዝኛ ቋንቋ በመሆኑ ትኩረቴን እንግሊዝኛ ሞጁሎቹ ላይ አድርጌ ምልከታየን ቀጠልኩ። “ኢንግሊሽ” የሚለውን ሞጁል አንስቼ የመጀመሪያውን ገፅ ገልበጥ አድርጌ ማውጫውን ስመለከት በመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ “ፕሩፍ ሪዲንግ” የሚል ርዕስ ሳይ ክው ብዬ ደነገጥኩ።

ራሴን ማመን ስላቃተኝ በፍጥነት ሞጁሉን ዘጋሁትና እንደገና ጀርባውን አፍጥጬ ሳይ መጽሐፉ እውነትም ለአራተኛ ክፍል ተማሪዎች የተዘጋጀ ነው። ቀና ብዬ ጓደኛዬን በግርምት ተመለከትኩትና “እውነት ይሄን ለአራተኛ ክፍሎች ነው የምታስተምሯቸው?” በማለት ስጠይቀው “እኔን ግራ የገባኝና አንተ እንድታየው የፈለኩትም እኮ ለዚህ ነው” አለኝ። የአራተኛ ክፍል ሕጻናትን “ፕሩፍ ሪዲንግ” የሚያስተምር ትምህርት ቤት እንደ እውነታው “የዕውቀት ቤት” ሳይሆን “የውድቀት ቤት” በመሆኑ እዚያ አስተማሪ መሆን የሚጎዳው ትውልድን ብቻ ሳይሆን የአስተማሪውንም ኅሊና ጭምር ነውና በርግጥም ነገሩ ግራ ከማጋባት አልፎ የሚያሳዝንም ሆኖ ነው ያገኘሁት።

“ፕሩፍ ሪዲንግ” ማለት እኮ የንባብ የመጨረሻው ደረጃ ሲሆን ከፍተኛ የአዕምሮ ብስለትንና የማሰብ ችሎታን የሚጠይቅ ለአዋቂዎች ሳይቀር የሚከብድ ክህሎት ነው። ለአዋቂዎችም የሚከብድ ነው የሚባልበት ምክንያትም ትምህርቱ በእጅጉ አስተዋይነትንና ጥንቃቄ የሚፈልግ በመሆኑ ነው። ለአብነትም “kill him not, leave him” በሚለው ለቅጣት አስፈጻሚ ፖሊስ የተጻፈ የእንግሊዝኛ ዓረፍተ ነገር ውስጥ ኮማ የምትባለውን ሥርዓተ ነጥብ “not” ከሚለው ቃል በፊት ተሳስቶ ቢያስቀምጣት እንደማንኛውም ስህተት በይቅርታ ወይም በእርማት የሚታለፍ አይደለም፣ በመሳሳታችን ምክንያት ክቡር የሆነውን የሰው ሕይወት አጥፍተናልና! እንግዲህ እንዲህ ዓይነት ስህተቶችን የማስቀረት ክህሎት ነው “ፕሩፍ ሪዲንግ” የሚባለው።

ታዲያ ማንበብ በደንብ የማይችል አንድ የአራተኛ ክፍል ሕጻን ማንበብ እንኳን ሳይችል በምን ተዓምር ነው ከማንኛውም ዓይነት ስህተት በፀዳ መንገድ ማንበብን እንዲማር የሚደረገው? እኔው ራሴ ተምሬ የተመረኩት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ሲሆን እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ድረስ “ፕሩፍ ሪዲንግ” የሚባል ነገር አላውቅም። ፕሩፍ ሪዲንግን የተማርኩት ዩኒቨርሲቲ ከገባሁ በኋላ ያውም መጨረሻ ዓመት ላይ ነው። እዚህ ግን ማንበብና መጻፍ እንኳን በደንብ ያለመዱ የአራተኛ ክፍል ሕጻናት ያለ አቅማችሁ ተማሩ ተብለው ሲጨነቁ ይውላሉ።

ይህን በማሳያነት አነሳን እንጂ ሌላም ብዙ ብዙ ነገር አለ። ከላይ እንደቀረበው አንዱ የእንግሊዝኛ ቋንቋ የትምህርት ዓይነት “ኢንግሊሽ”፣ “ስፖክን” “ሪዲንግ ስኪል” አንዳንዶቹ የግል ትምህርት ቤቶች አካባቢ ደግሞ “ራይቲንግ” ተብሎ አንዱን አራት ጊዜ ያስተምሯቸዋል። ተመልከቱ እንግዲህ ስፖክን፣ ሪዲንግና ራይቲንግ በቋንቋው ውስጥ የሚገኙ ክህሎቶች ሆነው እያለ የተለያየ የትምህርት ዓይነት ሆነው ሥርዓተ ትምህርት ተቀርጾላቸው መጽሐፍ ተዘጋጅቶላቸው ተማሪዎች እንዲማሩ ሲደረግ። እናማ እንግዲህ በእንግሊዝኛ ጻፍ ስትለው “በራይቲንግ ነው እንጂ በእንግሊዝኛ መጻፍ ይቻላል እንዴ? የሚል ትውልድን ቀርጸው እስከሚያስረክቡን በትዕግስት መጠበቅ ነው እንጂ ምን እንላለን።

ሌላም አለ። “ጀኔራል ሳይንስ” የትምህርት ዓይነታቸው ደግሞ እነዚህን የአራተኛ ክፍል ሕጻናት ልጆቻችንን ማወቅ ስለሚገባቸው ስለ አምስቱ የስሜት ህዋሳትና ስለ ዋና ዋና የአካል ክፍሎቻችን አገልግሎት ትተው ለሕጻናቱ ቀርቶ ስፔሻሊስት ሃኪሞች እንኳን በስንት ድካም የሚረዱትን ውስብስቡን የሥርዓተ ነርቭ ሳይንስ ያስተምሯቸዋል ማለቴ ያሰፍሩባቸዋል። ስለ ሥርዓተ ነርቭ የተማርኩት አስረኛ ክፍል ላይ መሆኑን በሚገባ አስታውሳለሁ፣ ከሥነ ሕይወት ትምህርት ብዙዎቻችን የሚከብደንም ይኼ እንደነበርም ትዝ ይለኛል።

እናም የተማሪዎችን ዕድሜ፣ የአዕምሮ ዕድገት ደረጃና አቅም ያላገናዘበ በአንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኘው የትምህርት ሥርዓት ችግር የሚፈታ ሳይሆን ትውልድን ለችግር የሚያጋልጥ አካሄድ ነው። ከዚህም ባሻገር በአንድ ሀገር ውስጥ የግል ትምህርት ቤት እንጂ የግል ሥርዓተ ትምህርት ሊኖር ስለማይችል ሁኔታው መፍትሔ ሊፈለግለት ይገባል።

 ሚዛን

አዲስ ዘመን   ኅዳር 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You