በሀገራችን አብዛኛዎቹ ሰዎች ለማጌጥ ከሚመርጡት የማዕድን ዓይነቶች ወርቅና ብር በብዛት ይጠቀሳሉ። ሆኖም ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ የማዕድን ዓይነት ለጌጣጌጥ ይውላሉ። ማዕድናቱ የተለያዩ ዓይነት ሲሆኑ ጌጣጌጦችን በማስዋብ ሥራ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች ወቅቱን በሚፈልገው መልኩ አስውበው ለገበያ ያቀርባሉ። ከወርቅና ከብር በተጨማሪም እንደ ኦፓል፣ ኤመራልድ፣ ዳይመንድ፣ ቶፓዝ፣ አስፓየር እና ሳፋየር ከመሳሰሉ ማዕድናት ጌጣጌጦች ይሰራሉ። እነዚህም አብዛኛዎቹ ማዕድናት በሀገራችን በተለያዩ ቦታዎች ይገኛሉ።
በቅርቡም የማዕድን ሚኒስቴር ሀገራችን ያላት እምቅ የማዕድን ሀብት ለማስተዋወቅ ያለመ የማዕድን ኤክስፖ ማዘጋጀቱ ይታወሳል። ለአምስት ቀናት በቆየው ኤክስፖ ላይ በሀገራችን ያሉ የተለያዩ ዓይነት ማዕድናት ለእይታ ቀርበዋል። በኤክስፖው ላይ በዘርፉ የተሰማሩ የማዕድን አምራቾችና ላኪዎች ማህበራት ተሳትፈዋል።
በኤክስፖ ከተሳተፉት ‹‹ቱ ጄ ጄምስቶን›› የተሰኘ የማዕድን አምራችና ከማዕድን የሚሰሩ ጌጣጌጦችን ለዓለም ገበያ የሚያቀርብ ድርጅት አንዱ ነው። የድርጅቱ የጌጣጌጥ ሽያጭ ክፍል ባለሙያ ወጣት ሳራ ደጀኔ ከወርቅና ከብር ውጭ ከማዕድን ለሚሰሩ ጌጣጌጦች በሀገራችን ያለው ተቀባይነት እምብዛም መሆኑን ትናገራለች። ለዚህም ምክንያቱ እነዚህ ማዕድናት በመዋቢያ በጌጣጌጥ መልክ ተሰርተው ሲቀርቡ ብዙም የተለመደ ባለመሆኑ ማህበረሰቡ ማዕድናት ያላቸውን ጠቀሜታ እንዳልተረዳው ትናገራለች። ከዚህም በተጨማሪ በገበያው ላይ ያሉት በማዕድናት የተሰሩ ጌጣጌጦች የሚሸጡበት ዋጋ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ያማከለ አለመሆን ብዙዎች ሲጠቀሙበት አይታይም ትላለች።
በማዕድን የሚሰሩ ጌጣጌጦችን ለሁሉም ተደራሽ በሆነ መልኩ ለማቅረብ ሁሉም ግብዓቶች በሀገራችን እንደሚገኙ የምትጠቆመው ወጣት ሳራ፤ ድርጅታቸው ከማዕድን የተሰሩ ጌጣጌጦችን ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ያማከሉ እንዲሆኑ ለማድረግ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጻለች። ይህ የማዕድን አምራች ድርጅት በሀገራችን የማዕድን ሀብት ክምችት ስሙ በትልቁ ከሚነሱ አካባቢዎች ውስጥ በሻኪሶ ከተማ የራሱ የማዕድን
ስፍራ ያለው ሲሆን በማዕድን የሚሰሩ ጌጣጌጦችን ከማቅረብ ባሻገር የተለያዩ ማዕድናትን ያቀርባል።
ሀገራችን በተለያዩ ተፈጥሯዊ ሀብቶች የበለጸገች ስትሆን በዓለም ላይ ካሉ የከበሩ ማዕድናት አብዛኛው እዚሁ ሀገራችን ውስጥ ይገኛሉ የምትለው ወጣት ሳራ፤ ነገር ግን በማዕድን ጌጣጌጥ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ እና ማዕድን አምራቾችና ባለሙያዎች የሚቸገሩት ግብዓቶቹን እንደልብ አለማግኘት፣ ማዕድኑን አውጥቶ ለሚፈለገው አገልግሎት ለማዋል በሚጓጓዝበት ወቅት የሚገጥሙ የተለያየ ችግሮች ስለመኖራቸው ትገልጻለች። በሀገራችን ያለው የማዕድን አውጥቶ ለመጠቀም የሚያስችለው ቴክኖሎጂ ማሽነሪዎች በበቂ ሁኔታ አለመኖር እና የማዕድን ቴክኖሎጂ በሀገራችን የሚገኝበት ደረጃ በቂ እና ከጊዜው ጋር የሚሄድ አለመሆን በሥራው አንድ ተግዳሮት መሆኑን አንስታለች።
ወጣት ሳራ እንደምትለው፤ ድርጅቱ የማምረታቸው የማዕድን ጌጣጌጦችን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ያቀርባል፤ በፋሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ ፋሽኑን የጠበቀ ከዘመኑ ጋር የሚሄድ የሚለው ርዕስ የተለመደ ሲሆን የሚሰሩ ጌጣጌጦችም እንዲሁ ወቅቱን የሚመስሉ እንዲሆኑ በደንበኞች ዘንድ ይፈለጋል። የመዋቢያ ጌጣጌጦችም የሚሰሩት ምንም እንኳን ከማዕድናት ቢሆንም በተለያየ ጊዜ እና ወቅት የሚኖራቸው ዲዛይን የሚፈለጉበት ዓይነትና ስሪታቸው ከጊዜ ጊዜ ይቀያየራል። በመሆኑም የማዕድን ጌጣጌጥ ሙያ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች ከዘመኑ ጋር የሚሄድ ዘመኑን የሚመጥኑ ጌጣጌጦች ከመሥራት ባሻገር ለሁሉም የእድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ደንበኞች የሚሆኑ ጌጣጌጦችን ለወጣቶች፣ ለሴቶች፣ የሚሆኑትን በማጥናት አዳዲስ ዲዛይኖችን ያቀርባሉ። በተጨማሪም ደግሞ ከማዕድን የተሰሩ ጌጣጌጦች ተቀባይነት እንዲያገኙ ለእይታ ቀለል ያሉ እና የሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ኪስ በማይጎዳ መልኩ ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ በሚያመሩ ዲዛይኖችን ጌጣጌጦች ይሰራሉ።
እነዚህን የማዕድን ጌጣጌጦች ወደ ገበያ ለማቅረብ በአብዛኛው ከደንበኞች ጋር በአካል በመገናኘት የገጽ ለገጽ ግብይትን የሚጠቀሙ ሲሆን ደንበኞች ወደ መሸጫ ሱቃቸው እና ቢሮአቸው በመምጣት የሚፈልጉትን የጌጣጌጥ ዓይነቶች እንደሚገዙ ትናገራለች። ስለማዕድን ጌጣጌጦች ሰዎች ያላቸው አቀባበል ብዙም ባለመሆኑ ጌጣጌጦቹን የሚያውቁ የረጅም ጊዜ ደንበኞች በማንኛውም ጊዜ ወደ ሱቃቸው በመምጣት የሚገበያዩ መሆኑን ጠቅሳ፤ የማዕድን ኤክስፖው ከሌሎች ባለሙያዎችና ድርጅቶች ጋር ልምድ እንዲለዋወጡ እድል እንደፈጠረላቸው ትናገራለች።
ሌላኛው በኤክስፖው ሲካፈል ያገኘነው ወጣት እያዩ ግዛው ‹‹ብራይተን›› ከተሰኘ የማዕድን አምራች የመጣ ሲሆን የጌጣጌጥ የማስዋብ ሥራ ባለሙያ ነው። ጌጣጌጦችን በማስዋብ ሥራ የ13 ዓመት ልምድ አለው። በኤክስፖው የተለያዩ ማዕድናትን ለእይታ ይዞ ቀርቧል። በሀገራችን ከማዕድን የተሰሩ ጌጣጌጦች ሽያጭ ብዙም ያልተለመደ በመሆኑ ድርጅታቸው ‹‹ብራይተን›› የሚሰሯቸውን ከማዕድን የተሰሩ ጌጣጌጦች በአብዛኛው ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ ናቸው። ጌጣጌጦችን በተለያዩ ቅርጻና ዲዛይን ከማምረት ባሻገርም ራሳቸው ማዕድናቱንም በተለያየ ቅርጽ በማዘጋጀት ከከሰል ድንጋይ ጀምሮ ኦፓል ኤመራልድ፣ እና የመሳሰሉ ሌሎች ማዕድናትን ያቀርባሉ። በማህበረሰቡ ዘንድ ያለውን ተቀባይነትም ለማሻሻልና ከማዕድን የተሰሩ ጌጣጌጦችን እንዲለመዱ እየሰሩ ይገኛሉ።
ጌጣጌጥ ሲባል ተፈላጊነቱ ለመዋብ ውበትን ለማጉላት በመሆኑ የገዢዎች በመጀመሪያ ሲያዩት ዓይናቸው ሊወደው ይገባል የሚለው ወጣት እያዩ፤ በመሆኑም የደንበኞችን ፍላጎት ለማሟላት ወቅታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ በሥራው የተሰማሩ ባለሙያዎች የራሳቸውን ልምድ በማከልና ክህሎታቸውን በማሳደግ አዳዲስ የጌጣጌጥ ዲዛይኖችን እንደሚያቀርቡ ይናገራል።
እንደ እያዩ ገለጻ፤ በኤክስፖው ላይ መገኘታቸው ለጎብኚዎች ማስታወሻ በመጣላቸው ግንዛቤ ስለመፍጠራቸው አንስቷል። ከሌሎች ተቋማት ጋር የልምድ ልውውጥ ከማድረግ ባሻገር ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የገበያ ትስስር የመፍጠር እድልን አግኝተዋል።
ኢትዮጵያ ያላትን የማዕድን ሀብት በመጠቀም ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ መንግሥት ዘርፉ ላይ ከዚህ በበለጠ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራትና የሚያስተዋሉ ሕገ-ወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩ አካላትን በማስቆም፣ በግብይት ሂደቱ ላይም ያለውን እንቅስቃሴ ማሳደግ ይገባል ብሏል። በተጨማሪም በዘርፉ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ባለሙያዎችን የሚያበረታታ የፖሊሲ ማሻሻያዎች በማድረግ አሁን ካለበት ደረጃ ከፍ ማድረግ እንደሚቻል ተናግሯል፡፡
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ኅዳር 24 ቀን 2016 ዓ.ም