‹‹ሜቴክ ያሳረፈው ጠባሳ የከፋ ቢሆንም፤ ተቋማትን ትርፋማ ማድረግ ተችሏል››የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱለይማን ደደፎ

ስለሙስናና ምዝበራ ሲነሳ ቀድሞ ከሚታሰቡ ተቋማት ውስጥ የቀድሞው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን(ሜቴክ) አንዱ ነው። ሜቴክ ከተቋቋመበት ዓላማ በተጻራሪ መልኩ በበርካታ መዝበራና ብልሹ አሰራር ውስጥ በመውደቁ ለትውልድ የሚተርፍ ዕዳ አውርሶ ሄዷል። በቅርቡ በመገናኛ ብዙሃን ይፋ እንደተደረገውም በሜቴክ አማካኝነት ከባንክ ወጥቶ ምን ላይ እንደዋለ የማይታወቅ 65 ቢሊዮን ብር በመንግሥት እንዲሰረዝ መደረጉ የዚሁ አንድ ማሳያ ነው።

የለውጡ መንግሥት እንደመጣ በመጀመሪያ ከተቃወማቸውና ስር ነቀል ለውጥ ያስፈልጋቸዋል ብሎ አቋም ከወሰደባቸው አሰራሮች ውስጥ የመጀመሪያው የሜቴክን መዋቅር እና አሰራር ማፍረስ ነው። ይህን ሕገ ወጥ አሰራር ሲሰሩ የነበሩትን ወደ ሕግ ከማቅረብ ጀምሮ በስሩ የነበሩ ተቋማትን ለሁለት በመክፈል አዲስ አደረጃጀት ለመፍጠር ተችሏል። ወታደራዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን በመከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ ማካተት የመጀመሪያው ሲሆን ለሕዝብ የዕለት ተዕለት አገልግሎት የሚሰጡትን ቀሪዎቹን ተቋማት በአንድነት በማደራጀት ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸዋል።

የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም በአዲስ መልክ ከተቋቋመውና የኢንዱስትሪውን ዘርፍ በበላይነት እንዲመራ ተልዕኮ ከተሰጠው ከኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱለይማን ደደፎ ጋር ቆይታ አድርጓል። መልካም ንባብ።

አዲስ ዘመን፡- የቀድሞው ሜቴክ የአሁኑ ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ሲቋቋም አላማው ምን ነበር ?

አምባሳደር ሱለይማን ደደፎ:- ሜቴክ የተቋቋመበት ዋነኛ ዓላማ የሀገሪቱን የኢንዱስትሪ ዘርፍ እንዲመራ ነው። በፈጠራ እና በቴክኖሎጂ ሽግግር በሀገሪቱ ያሉትን ኢንዱስትሪዎች እንዲደግፍና የጥናትና ምርምር ሥራዎችን እንዲያካሂድ ታልሞ የተቋቋመ ግዙፍ ድርጅት ነው።

በሀገሪቱ ተበታትነው የነበሩ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪዎችን በማስተባበርና በመምራት ለሀገሪቱ የኢንዱስትሪ እድገት አስተዋጽኦ የማበርከት ኃላፊነት የተጣለበት ተቋም ነበር። በአጠቃላይ ሜቴክ የሚባለው ተቋም የተሰጠው ኃላፊነት ሰፊና ሀገሪቱንም በኢንዱስትሪው ዘርፍ እምርታ እንድታመጣ ታልሞ የተቋቋመ ትልቅ ተቋም ነበር። ይህ ግዙፍ ተቋም ከሀገሪቱ ኢንዱስትሪ ባሻገር የመከላከያ ሠራዊትን በተለያዩ ፈጠራዎች የማጠናከር ተልዕኮም ተሰጥቶታል።

ሀገር የሚያድገው በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ዘርፍ በመሆኑ፤ ይኸው ድርጅት የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ተቋም ሆኖ እንዲቋቋም መንግሥት ሲወስን ኢትዮጵያን በኢንዱስትሪው ዘርፍ ወደፊት ያራምዳል ከሚል እምነት ነበር።

በሀገር ውስጥ የማይመረቱ እና በሕዝብ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶችን በማምረት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የመተካትም ሚና ነበረው።

በተለይም ለመከላከያው ዘርፍ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ ሀገሪቱ በወታደራዊው ዘርፍ ልቃ የምትወጣበትን ሁኔታ ማመቻቸትም የተልዕኮው አንዱ አካል ነበር። የተለያዩ ትጥቆችን፤ መሳሪያዎችን እና ለወታደራዊ ተልዕኮ አጋዥ የሆኑ ልዩ ልዩ ልማቶችን እንዲያካሂድም ኃላፊነት የተጣለበት ተቋም ነው።

ሆኖም በነበሩ ብልሹ አሰራሮች እና አስተሳሰቦች የተሰጠውን ተልዕኮ ከግብ ሳያደርስ ተኮላሽቶ ቀርቷል። አካሄዱም እጅግ አደገኛና ሀገርንም ለበርካታ ችግሮች የተጋለጠ ነበር። ያወረሰውም ዕዳ ለትውልድ የሚተላለፍ ሆኗል።

አዲስ ዘመን፡- ሜቴክ ከተሰጠው ተልዕኮ አፈንግጦ እንዴት ወደ ምዝበራ ሊገባ ቻለ?

አምባሳደር ሱለይማን ደደፎ፡- በሂደት በሜቴክ ውስጥ ያለው አመራር ከተሰጠው ኃላፊነት በማፈንገጥ የራሱን ኢምፓየር መመስረት ጀመረ። ለመንግሥታዊ አሰራር፤ ለሕግና ደንብ ለመገዛት ፍቃደኛ አልነበረም። አመራሩ በመንግሥት ለመታዘዝ አለመፈለግና ጭራሹኑም ከመንግሥት በላይ የመሆን ፍላጎት አደረበት። በተግባርም አዋለው።

አመራሩ ለራሱ በሚጠቅመው መልኩ ሕግና አሰራሮችን መተርጎም፤ ሕግን በራስ እጅ ውስጥ የማስገባትና አንዳንዴም የራስን ህሕ የማውጣት አካሄዶችን ይከተል ነበር። የንብረት አያያዝ፤ አጠቃቀም፤ ግዢ ሥርዓት ሁሉ ከመንግሥት መመሪያ ውጭ ይፈጸም ነበር። የውጭ ምንዛሬ የሚገኝበትም ሆነ የገንዘብ ዝውውር የሚካሄድበት መንገድ ፍጹም ሕገ ወጥ አካሄድን የተከተለ ነበር። በአጠቃላይ በሂደት ተቋሙ የተሰጠው ተልዕኮ ከሽፎ የሕገ ወጦች መናኸሪያ እና የዘረፋ ተቋም ለመሆን በቃ ።

በተዘረጋው የዘረፋ ሰንሰለትም ግለሰቦች፤ ቡድኖች እራሳቸውን የሚያበለጸጉበትና እንደፈለጉ የሀገርና ሕዝብ ሀብት እያፈሱ የሚሰጡበት ተቋም ወደ መሆን ተሸጋገረ። ከዛም አለፍ ብሎ ከተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ግዢዎችንና ኮንትራቶችን በትዕዛዝ በመቀበል ለግል ጥቅማቸው ያውሉ ነበር። ጭራሽ ተቋሙ የሚከተለው በትዕዛዝና በማስፈራራት የተወሰደ ኮንትራትና ግዢ ውል የማይፈጸምበትና ስምምነትም የማይፈረምበትን አካሄድ ነበር።

ተቋሙ ኮንትራቶችን የሚወስደው ውል ቢፈራረምም እንደማይከሰስና ተጠያቂነትም እንደሌለበት ተፈርሞለት ሆነ። በዚህ አካሄድም ከእያንዳንዱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ኮንትራቶችን ወስዶ መና አስቀርቷል። ተቋሙ እንደ ንጉስ የማይከሰስ ስለሆነ የወሰደውን ኮንትራት ባይፈጽም የሚጠይቀው አልነበረም። አሁን ሜቴክ የተፈራረማቸውን ሰነዶች ስንመለከት ‹‹ሜቴክ የወሰዳቸውን ኮንትራቶች በወቅቱ ባይፈጽም በድርድር ይፈታል እንጂ በህግ አግባብ አይጠየቅም›› የሚሉ ውሎች ቤቱን ሞልተውት ተገኝተዋል።

ሜቴክ ሲፈራረማቸው የነበሩ ውሎች ከሕገ መንግሥቱ በላይ ሥልጣን የሰጠው ነበር። በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ማንኛውም ሰው፤ ባለሥልጣን፤ ቡድን፤ ተቋም ላጠፋው ነገር ይከሰሳል። ሁሉም አካል ከሕግ በታች ነው። ሜቴክ ግን ማንም አይከሰውም፤ ጥፋት ቢያጠፋም ለምን አጠፋህ ብሎ የሚጠይቀው አልነበረም። ይህ ደግሞ ሀገሪቱ የምትከተለውን ሕገ መንግሥትንና እሱን ተከትለው የወጡ ሕጎች የሚጥስና ተቋሙንም አይነኬ ያደረገ ነበር።

ከሜቴክ ጋር ውል የሚገቡ ተቋማት ወደ ሥራ የሚገቡት መጀመሪያውኑ ስምምነት ሲያደርጉ ሜቴክን እንደማይከሱ ፈርመው ነው። ይህን የሚያደርጉት ደግሞ ወደው አይደለም፤ ተገደው ነው። የሚደርሳቸው ማስፈራርያም ከሥራ መሰናበት ብቻ ሳይሆን ሕይወትንም እስከማጣት የሚያደርስ ነበር። በፀረ መንግሥትነት፤ በፀረ መከላከያነትና በፀረ ሜቴክነት ተከሰው መቀመቅ ሊገቡ ይችላሉ።

አዲስ ዘመን፡- ከሕግ ውጭ እነዚህን ሥራዎች ሲፈጽም የሚጠይቀው አካል አልነበረም ?

አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ፡- ችግሩ የነበረው ከአናቱ ነው። የሜቴክ አመራሮች ይህን ሁሉ ሕገ ወጥ ተግባር ሲፈጽሙ የነበረው ከአናቱ የነበሩ አመራሮችን በመተማመን ነበር። ከተቀማጭ ገንዘብ ላይ ገንዘብ ለግለሰቦች ያለዋስትና የሚሰጥበት ሀገር የለም። በኢትዮጵያ ግን ያለምንም ማስያዣ ገንዘብ እንደልብ ከባንክ ይወጣ ነበር። የሜቴክ አመራሮች በሙሉ የበላይ ኃላፊዎችን በመተማመን በገሃድ ሲፈጽሙት የቆዩት ተግባር ይህንን ነው። የሜቴክ አመራሮች ከንግድ ባንክ፤ ከልማት ባንክ እና ከሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ዶላር አዘው እና በሻንጣ ይዘው ወደ ውጭ ሀገር የሚወጡበትና በውጭ ባንኮችም የፈለጉትን ያህል ዶላር የማስቀመጥ መብት ነበራቸው።

የሜቴክ አመራሮች በሙሉ የራሳቸው አሠራር አላቸው፤ የራሳቸው ፋይናንስ አላቸው፤ የራሳቸው አካሄድ አላቸው። በአጠቃላይ ኢትዮጵያን የግላቸው አድርገው ሲመዘብሯት ኖረዋል። በዚህም ሀገሪቱ እስካሁን ተከፍሎ ያላለቀ እና ለትውልድ የሚተርፍ እዳ አሸክመዋታል። ትውልድም የእነዚህን ሰዎች ጦስ ተሸክሞ ዕዳ ሲገፈግፍ ይኖራል።

አዲስ ዘመን፡- ከሜቴክ ውስጥ የአሁኑ ኢትዮ ኢንጂነሪንግ እንዴት ወጣ ?

አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ፡- የለውጡ መንግሥት እንደመጣ በመጀመሪያ ከተቃወማቸውና ስር ነቀል ለውጥ ያስፈልጋቸዋል ብሎ አቋም ከወሰደባቸው አሰራሮች ውስጥ የመጀመሪያው የሜቴክን መዋቅር እና አሰራር ማፍረስ ነው። ይህን ሕገ ወጥ አሰራር ሲሰሩ የነበሩትን ወደ ሕግ ከማቅረብ ጀምሮ በስሩ የነበሩ ተቋማትን ለሁለት በመክፈል አዲስ አደረጃጀት ለመፍጠር ተችሏል። ወታደራዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን በመከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ ማካተት የመጀመሪያው ሲሆን፤ ቀሪዎቹን ለሕዝብ የዕለት ተዕለት አገልግሎት የሚሰጡትን ተቋማት በአንድነት በማደረጃት ኢትዮ ኢንጂነሪንግ የሚል ስያሜ እንዲሰጣቸው ተደረገ።

ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ዘጠኝ ተቋማትን በማቀፍ የተቋቋመ ግዙፍ ተቋም ነው። ኢትዮ ፕላስቲክ፤ አዲስ ማሽን መለዋወጫ ፋብሪካ፤ አቃቂ ቤዚክ ሜታልስ ኢንዱስትሪ፤ ቢሾፍቱ ኦቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ፤ አዳማ የግብርና ማሽነሪዎች ማምረቻ ፋብሪካ እና ደብረ ብርሃን ላይ የሚገኘው የኮንስትራክሽን ዕቃዎች ማ ምረቻ ይገኙበታል ።

አዲስ ዘመን፡- ከሜቴክ ወደ ኢትዮ ኢንጂነሪንግ የነበረው ሽግግር ምን ይመስላል?

አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ፡- እጅግ ከባድ ነበር። ሜቴክ በቀውስ ውስጥ የነበረ ተቋም በመሆኑ ሽግግሩም ቀውስ የነበረበት ነው። ሜቴክ ሀብትና ንብረቱ የማይታወቅ፤ ዕዳው የማይታወቅ፤ ተጠያቂነት የሌለበት ተቋም ነበር። እናም ይህንን አጣርቶና አደራጅቶ ለሀገርና ለሕዝብ የሚጠቅም ተቋም ማድረግ እጅግ ፈታኝ ቢሆንም፤ በዚህ እልህ አስጨራሽ ጥረት ውስጥ ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የሚባል አዲስ ተቋም ሊወለድ ችሏል።

በሜቴክ ውስጥ የነበሩት ተቋማት ግዙፍ ነበሩ። ቢሆንም በአሰራር ብልሹነት የመከኑ ስለነበሩ እነዚህን ተቋማት ወደ ምርታማነት ለመመለስ እጅግ ፈታኝ ነበር። ተቋማቱን በአዲስ አደረጃጀትና አመለካከት ጭምር የተነቃቁና አትራፊ እንዲሆኑ ለማድረግ ወደ አራት ዓመታት ፈጅቷል።

አሁን ፈታኝ ከሆኑብን ጉዳዮች አንዱ ሜቴክ በነበረበት ወቅት የወሰዳቸውን ኮንትራቶች በአግባቡ ባለመጨረሱ  የተለያዩ አካላት ተቋሙን መክሰስ ጀምረዋል። ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ባልፈጸመው ወንጀል በሜቴክ ምክንያት እየተከሰሰ ነው። ሜቴክ ይከተለው በነበረው አሰራር የደላላ ባህሪን ተላብሶ ይስራ ስለነበረ ከአንድ ተቋም ሥራዎችን ይወስድና እንደ ደላላ ሆኖ በሰብ ኮንትራት አካሄድ ሥራውን አሳልፎ ለአንድ ተቋራጭ ወይም ድርጅት ይሰጣል። ያም ድርጅት የሚከታተለው አካል ስለሌለ ሥራውን በአግባቡ ሳያከናውን ገንዘቡን ወስዶ ይጠፋል። በዚህ ሁኔታ በርካታ ተቋማት ገንዘባቸው ተበልቶ ቀርቷል። በዚህ የተነሳ በርካታ የክስ ፋይሎች እየመጡ ነው።

ለምሳሌ ግዙፍ የሆነውን ያዩ የማዳበሪያ ፋብሪካን እገነባለሁ ብሎ ሥራውን ከኬሚካል ኮርፖሬሽን ከወሰደ በኋላ ሜቴክ እራሱ መሥራት ሲገባው ተክል ብርሃን አምባዬ ለተባለ ድርጅት አሳልፎ ሰጥቷል። ሆኖም በብዙ ቢሊዮን ብር የፈሰሰበት ይህ የማዳበሪያ ፋብሪካ ሳይሰራ መክኖ ቀርቷል። ያዩ ማዳበር እና ሌሎች መሰል ዕዳዎችም ሊከፈሉ የማይችሉ ስለሆኑ በኦዲት ተረጋግጦ ከ65ቢሊዮን ብር በላይ ለመንግሥት ቀርቦ እንዲሰረዝ ተደርጓል። ይህ ለኢትዮጵያ ትልቅ ኪሳራ ነው። ከድሃ እናት መቀነት፤ ከድሃ አርሶ አደር ኪስ፤ ከጉሊት ቸርቻሪ እናት ኪስ የወጣ ገንዘብ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ይሄ 65 ቢሊዮን ብር ንብረት ላይ የዋለ ነው ወይስ በግለሰቦች በጥሬው የተወሰደ?

አምባሳደር ሱለይማን ደደፎ፡- ገንዘቡ በግለሰቦች አማካኝነት ከባንክ ወጥቷል። ነገር ግን ምን ላይ እንደዋለ አይታወቅም። ኦዲት ሲደረግም በዚህ ገንዘብ የተገዛ ዕቃ ወይም ንብረት የለም። ስለዚህ ይህ 65 ቢሊዮን ብር ዕቃ የገዙበት ይሁን ወይም የተከፋፈሉት የሚታወቅ ነገር የለም።

አንዳንድ ዕቃዎች ተገዙም ቢባል ጥቅም የሚሰጡ አይደሉም። ለምሳሌ አምስት ሺ ትራክተሮች ተገዝተው አንድም ቀን አገልግሎት ሳይሰጡ ዝም ብለው አዳማ ላይ ተቀምጠዋል። እነዚህ አምስት ሺ ትራክተሮች ለአንድም ቀን አልሰሩም። ትራክተሮቹ የተገዙት ከየቦታው ተለቃቅመው ነው። ከተገዙት ውስጥ የአንዳንዶቹ ትራክተሮች ፋብሪካ ከተዘጉ ዓመታት ተቆጥረዋል። መለዋወጫ እንኳን የላቸውም። ስለዚህም ብክነቱ በቃላት ከሚገለጸው በላይ ነው።

ሜቴክ በሀገር ውስጥ ያለውን ነዳጅ የማይጠቀሙ ሁለት አውሮፕላኖችን ገዝቶ ያስገባ ድርጅት ነው። ለእነዚህ አውሮፕላኖች የሚሆን ነዳጅ በሀገር ውስጥ ስለሌለ በከፍተኛ ብር የተገዙት እነዚሁ አውሮፕላኖች ያለምንም ጥቅም ተቀምጠዋል። እነዚህ አውሮፕላኖች አንድም ቀን በረው አያውቁም። ኢትዮ ኢንጂነሪንግም እንደንብረት የሚረከባቸው አይደሉም።

በተመሳሳይም ሕዳሴ ግድብ ላይ ተፈጽሞ የነበረው ግፍ አንዱ የሜቴክ ቅሌት ነው። ብቃትና ዕውቀቱ ሳይኖረው ሕዳሴን የሚያክል ግዙፍ ፕሮጀክት እሰራለሁ ብሎ ተነስቶ ሥራውን ከማጓታት ባሻገር በርካታ ሚሊዮን ብሮች ባክኖ እንዲቀር አድርጓል። ሆኖም እንደ አጋጣሚ ሆኖ የመንግሥት ለውጥ በመምጣቱ የሕዳሴ ግድብ ከውድቀት ተረፈ እንጂ እንደሜቴክ አካሄድ የሕዳሴ ግድብ መክኖ መቅረቱ ሳይታለም የተፈታ ነበር።

በአሁኑ ወቅት የማዳበሪያ ጉዳይ ኢትዮጵያን እየፈተነ ያለና የአርሶ አደሩም የዕለት ተዕለት ጥያቁ ነው። ሜቴክ ያባከነው 65 ቢሊዮን ብር በርካታ የማዳበሪያ ፋብሪካ ይገነባ ነበር። ከዛሬ ስምንት ዓመት በፊት በ65 ቢሊዮን ብር ትላልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶችን መገንባት ይቻል ነበር። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ሳስበው የድህነታችን ሚስጥር አባካኝነታችን እንደሆነ ይሰማኛል። የደሃ ሀገር እና ሕዝብን ገንዘብ በዚህ መጠን ማባከን እንደሀገር ውድቀት ነው።

ሆኖም ሀገርና ሕዝብ መቀጠል አለባቸውና ቀደም ሲል የተሰሩ ስህተቶች እንደሀገር እያረምን እየሄድን ነው። በተለይም እንደ ተቋም እጅግ ፈታኝ የነበረው የምዝበራና የሌብነት አስተሳሰብን ማስወገዱ ነው። በሜቴክ ውስጥ እጅግ የገነገነ የሌብነትና የምዝበራ አስተሳሰብ ነበር። ከታች እስከ ላይ ድረስ ሰርቶ ከማደግ ይልቅ በምዝበራ የመበልጸግ ሜቴካዊ አስተሳሰብ ነበር። ዛሬም ይህ አስተሳሰብ ሙሉ በሙሉ ተወግዷል ብለን አፋችንን ሞልተን ባንናገርም፤ አሁን በትግል ነገሮች በመለወጥ ላይ ናቸው።

ነገር ግን የሌብነት ጉዳይ ከተነሳ በሜቴክ ውስጥ ብቻ ሳይሆን አሁንም እንደሀገር ትልቅ ችግር አለ። የሌብነትና በአቋራጭ የመክበር አስተሳሰብ የትውልዱ በሽታ ነው ማለት ይቻላል። ስለዚህም ሀገር እንድትድን የሚፈልግ ዜጋ በሙሉ በዚህ ጉዳይ ላይ ሊያስብበት ይገባል። ሌብነት ላይ በዘመቻ ትልቅ የባህል አብዮት አካሂደን ችግሩን ከስር መሠረቱ ካልነቀልነው በስተቀር እንደ ሀገር ሊያጠፋን የሚችል ችግር ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የራሱ የሆነ አኩሪ ባህል ያለው ሕዝብ ነው። ሌብነትን የሚጸየፍና ብሎም የሚቆጣ ነው። ስለዚህም ዘረፋን፤ ሌብነትንና በአቋራጭ መክብርን እንደ ሕዝብ ተነስተን ልንዋጋው የሚገባ ጉዳይ ነው። ሌብነት አስነዋሪ ነው፤ ማጭበርበር አስነዋሪ ነው፤ የሕዝብ ሀብት ማባከን አስነዋሪ ነው፤ የራስ ያልሆነን ንብረት መወሰድ አስነዋሪ ነው። ስለዚህም እነዚህን አስነዋሪ ተግባራት መዋጋት ለፖሊስ ወይም ለአንድ የሕግ አካል የምንተወው ሳይሆን ሁላችንም በአንድነት በመቆም ልንዋጋው የሚገባ የሀገር ጠላት ነው።

በአዲስ መልክ የተቋቋመው ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕም በዚህ ላይ ትግል እያደረገ ነው። በተለይም ተቋሙ ከሜቴክ የሌብነትና የምዝበራ አስተሳሰቦች የጸዳና በአንጻሩም ሌብነትና ብልሹ አሰራሮችን የሚጸየፍ ሠራተኞች እንዲኖሩት የተለያዩ ስልቶችን ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።

አዲስ ዘመን፡- ከሜቴክ ወደ ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ሲሸጋገር የዓላማ ለውጥ አድርጓል?

አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ:- የዓላማ ለውጥ አላደረገም። ሜቴክም ቢሆን እኮ በወረቀት ላይ ያለው ዓላማው የሚናቅ አይደለም። ዋነኛ ዓላማውም ከላይ እንደገለጽኩት የሀገሪቱን የኢንዱስትሪ ዘርፍ መምራት ነው። በሀገር ውስጥ የማይመረቱና በሕዝብ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ክፍተትን መሙላት ነው። ጥናትና ምርምር በማድረግም የሀገሪቱ ኢንዱስትሪዎች ዘመናዊ አሰራርን እንዲከተሉና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማድረግ ነው። እነዚህ አላማዎች ደግሞ የሚደገፉና ሀገርንም ወደፊት የሚያራምዱ ናቸው።

ስለዚህ ሜቴክ ቀድሞ ስለያዛቸው እኛ ልንወስዳቸው አንችልም አንልም። እኛ ያደረግነው የአሰራር፤ የአስተሳሰብ፤ የአካሄድ ለውጥ ማድረግ ነው። ኢትዮ ኢንጂነሪንግ በሕግ ጥላ ስር ሆኖ በሕግ የሚመራ፤ ተጠያቂነት ያለበት፤ ሲያጠፋ የሚቀጣ፤ የሚከሰስ፤ ተቋም ሆኖ እንዲቀጥል ማስቻል ነው። የተሰጡትን ሀገራዊ ተልዕኮዎች የሚወጣና ኢንዱስትሪውንም በዕውቀት የሚመራ ተቋም እንዲሆን ማስቻል ነው።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮ ኢንጂነሪንግ በአሁኑ ወቅት ምን ያህል ውጤታማ ነው ?

አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ፡- ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ከመጣበት ጊዜ ጀምሮም ቢሆን ሜቴክ ያሳረፈበት ጠባሳ ከባድ በመሆኑ ፤ ላለፉት አራት ዓመታት በኪሳራ ውስጥ ቆይቷል። እስካለፈው አጋማሽ ድረስ ዘጠኙም ፋብሪካዎች ኪሳራ ውስጥ ነበሩ። በተለይም ተቋማቱ በአግባቡ ሲመሩ ስላልቆዩና የማሽነሪዎችም እርጅና ስላለ በፍጥነት ወደ ውጤታማነት መለወጥ አዳጋች ነበር። ሠራተኛውም ቢሆን በሚፈለገው መልኩ ውጤታማ አልነበረም። የጥሬ ዕቃ እጥረት አንዱ ችግር ነበር።

ካሉን ዘጠኝ ፋብሪካዎች ስድስቱ ከውጭ በሚገባ ጥሬ ዕቃ ላይ የተመሰረቱ በመሆናቸው፤ የውጭ ምንዛሬን የሚሹ ናቸው። አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ እንደ ሀገር ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ያለብን በመሆኑ፤ እነዚህ ፋብሪካዎች ከውጭ ጥሬ ዕቃ ለማግኘት ተቸግረዋል። ባላቸው አቅምም ለማምረት አልቻሉም። ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ሜቴክ ያሳረፈበት ጠባሳ የከፋ ቢሆንም፤ በስሩ ያሉት ትልልቅ ተቋማት ከብዙ ጥረት በኋላ ካለፈው ዓመት ወዲህ ትርፋማ መሆን ጀምረዋል።

ከብዙ ጥረት በኋላ ካለፈው ዓመት ሁለተኛ አጋማሽ ጀምሮ ትርፋማ መሆን ጀምረዋል። ባለፈው የ2015 በጀት ዓመትም ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ወደ 480 ሚሊዮን ብር ማትረፍ ተችሏል። አጠቃላይ ሀብታቸውም ወደ ሁለት ቢሊዮን ብር ደርሷል። ይህ በቂ አይደለም። ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግዙፍ ተቋም ከመሆኑ አንጻር ገና ብዙ ማትረፍና ለሀገሪቱንም የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ አርአያ ሊሆን የሚገባው ነው።

ሆኖም ኢትዮ ኢንጂነሪንግ የነበሩበትን መሰናክሎችና ውጣ ውረዶች አልፎ ማትረፍ እንደሚችል አረጋግጧል። ይህንንም ከግምት ውስጥ በማስገባት በ2016 በጀት ዓመት አጠቃላይ ምርቱን 15 ቢሊዮን ብር ለማድረስና የሁለት ቢሊዮን ብር ዓመታዊ ትርፍ ለማስመዝገብም አቅዷል። በተለይም መንግሥት ለአቅርቦት የሚሆን የዶላር ብድር ስለተፈቀደለት ከውጭ የሚገቡ ጥሬ ዕቃዎችን በቀላሉ በማስመጣት ፋብሪካዎቹ በሙሉ አቅማቸው እንዲሰሩ ለማድረግ እንሞክራለን።

ከቻይና ገበያ በተጨማሪ የአውሮፓ ገበያን በመጠቀም ጥሬ ዕቃዎች የሚገቡበት ሁኔታ ይመቻቻል። ጥሬ ዕቃ የምናገኝባቸውን የገበያ አማራጮች ማስፋት አለብን በሚል በአሁኑ ወቅት ከአንዳንድ የአውሮፓ ገበያዎች ጋር ግንኙነት ማድረግ ጀምረናል። ለምሳሌ ቀደም ሲል ጀምሮ የጣሊያን ምርቶች በጥራትም ሆነ በጥንካሬ በኢትዮጵያ ተወዳጅ ምርቶች ነበሩ። ጥራት እና ጥንካሬ ያላቸው የጣሊያን የጭነት መኪናዎች፤ አውቶቡሶች በኢትዮጵያ ለዘመናት አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተዋል። እነሱን ለማስመለስ እንቅስቃሴ ጀምረናል። በተመሳሳይም የጀርመን፤ የኔዘርላንድ አውቶቡሶች በኢትዮጵያ ተመራጮች ናቸው። እነዚህን ለማስገባት ድርድር ላይ እንገኛለን።

ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ የርካሽ ዕቃዎች ማረገፊያ ሆና ቆይታለች። አነስተኛ ዋጋ በሚል ሰበብ በሚወጣ ጨረታ ለሀገርና ለሕዝብ የማይመጥኑ ዕቃዎች ኢትዮጵያን አጨናንቀዋታል። በየቦታው ሶስት ዓመት እንኳን ሳይሰሩ የሚቆሙ መኪኖች፤ አውቶቡሶች፤ በርካታ ናቸው። ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚቀርቡ ቁሳቁሶች አንድ ጊዜ አገልገለው የሚወረወሩ ናቸው። በአጠቃላይ ስታንዳርድ አጥተናል። ለጥራት ያለን አመለካከት ተዛብቷል።

ጥራት ያለውን እቃ እየተውን ተልካሻ ዕቃ በመረጥን ቁጥር ድህነትን እናባዛለን እንጂ አናተርፍም። ርካሽ ዕቃ እያሳደደን በሄድን ቁጥር ሀብትን እያባከንን እንሄዳለን። ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ዕቃዎች በሙሉ ርካሽ ስለሚሆኑ ብዙም አገልግሎት ሳይሰጡ ከጥቅም ውጭ ይሆናሉ። ነገር ግን እንደ ሀገር የምናወጣው ገንዘብ ውድ ዕቃዎችን ጭምር ለመግዛት የሚያስችለን ነው። የሚወጣው ገንዘብ በርካሽ ዋጋ ልክ አይደለም። ሌብነቱ ተጨምሮበት፤ ማጭበርበሩ ታክሎበት ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ዕቃዎች ሊገዛ የሚችል ገንዘብ ነው እየባከነ ያለው።

በሀገር ውስጥ ያሉ በርካታ የመንግሥትም ሆነ የግል ፋብሪካዎች የሚገጥሟቸው ማሽኖች በአውሮፓ ለረጅም ዘመናት ያገለገሉና ዘመን ያለፈባቸው ናቸው። በርካቶችም በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዲሸጡ ውሳኔ የተላለፈባቸውና የማምረት አቅማቸውም የተዳከመ ነው። ሆኖም በደላላ አማካኝነት እነዚህ ማሽኞች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ተደርገው ብዙም ሳይሰሩ ይቆማሉ፤ ለመለዋወጫም በርካታ ዶላሮችን ያስወጣሉ።

በእኛ እጅ እንኳን ከ10 በላይ ፋብሪካዎች በዚህ ዓይነት መልኩ ያረጁ ማሽኖች የተገጠሙላቸው ናቸው። ዓይነታቸው የማይታወቁ፤ ምን እንደሚሰሩ የማይታወቁ እንዲሁ ተገዝተው ቁጭ ያሉ አሮጌ ማሽኖች በእኛው ድርጅት ውስጥ አሉ። እዚህ ከገቡ ጀምረው አንድም ቀን ያልተንቀሳቀሱ ማሽኖች አሉ።

አጠቃላይ እንደ ሀገር ጥራት አጥተናል። የትምህርት ሥርዓታችን ጥራት የለውም። አስተራረሳችን ጥራት የለውም። አኗኗራችን ጥራት የለውም። ንግድ ሥርዓቱ ጥራት የለውም። ይህ እንደ ሀገር አሳሳቢ ነው። ጥራት ያለው ዜጋ ካልተፈጠረ ደግሞ ጥራት ያለው ምርት ማምረት የሚታሰብ አይደለም። ጥራት ያለው ዕቃ አምርቶም መጠቀም አይቻልም። ስለዚህም ኢትዮጵያውያን ለጥራት ትኩረት መስጠት አለብን። ኢትዮጵያም በጥራት ከሚታወቁ ሀገራት ተርታም መሰለፍ አለባት። የራሳችንን የምርምርና የጥናት ሥራዎች በማጠናከር ጥራት ያላቸውን ምርቶች አምርተን ቢያንስ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ማዋል አለብን ብለን እየተንቀሳቀስን ነው።

ስለዚህም ኢትዮጵያንና ሕዝቧን የሚመጥኑ ዕቃዎች እንዳይገቡ የተደረገበት መንገድ የሚያስቆጭ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥራት ያለው ነገር አይወድም ያለው ማን? ይህ እንደ ሀገር ሊያስቆጨን የሚገባ ጉዳይ ነው። ስለዚህም ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የሀገሪቱን የጥራት ደረጃ ከፍ ሊያደርጉ የሚገቡ መገልገያዎችን ለማምረትና ወደ ሀገር ውስጥም ለማሰገባት የበኩሉን ጥረት ያደርጋል።

አዲስ ዘመን፡- ቀጣይ የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ዕቅድ ምንድን ነው ?

አምባሳደር ሱለይማን ደደፎ፡- ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ተዘርዝረው የተሰጡትን ኃላፊነቶች በአግባቡ እንዲወጣ ማድረግ ነው። የሀገሪቱን የኢንዱስትሪ ዘርፍ መምራት ዋነኛው ተልዕኮው ስለሆነ እሱ ላይ ጠንክሮ ይሰራል። በሀገር ውስጥ የማይመረቱና በሕዝብ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ክፍተርን መሙላት አንዱ ዓላማው ስለሆነ በዚህ ዘርፍም ውጤት ለማምጣት ይጥራል። ከዚህም አልፎ ለውጭ ገበያ አዳዲስ ሞዴል ያላቸውን መኪናዎች የማቅረብ ዕቅድ አለው። ጥናትና ምርምር በማድረግም የሀገሪቱ ኢንዱስትሪዎች ዘመናዊ አሰራርን እንዲከተሉና ተወዳዳሪ እንዲሆኑም ለማድረግ ይሰራል።

እነዚህን ተልዕኮዎቹን ለማሳካት ከወዲሁ የጀመራቸው ሥራዎች አሉ። ከጥቂት ወራት በኋላ ሞጆ ላይ በ50ሚሊዮን ዶላር ትልቅ የትራክተር ፋብሪካ መገንባት እንጀምራለን። በአፍሪካ ደረጃም ትልቅ ሊባል የሚችል ነው። ፋብሪካው ትራክተር የሚገጣጥም ሳይሆን ትራክተሩን ለማምረት የሚያስችሉ ዕቃዎችን የሚያመርት እራሱን የቻለ ፋብሪካ ነው። ይህ ፋብሪካ የትራክተር ሞተር ጭምር የሚያመርት ነው።

ባሉን ፋብሪካዎችም ሻንሲ የመሥራት አቅም እያዳበርን በመሆኑ፤ ሞተር ማምረት ከቻልን መኪና የማምረት አቅም ላይ እንደርሳለን። ከእኛ አቅም በላይ የሚሆኑትን ደግሞ ለሌሎች የሚሠሩ አካላት በመስጠት ሥራውን ለውጤት እናበቃለን። በውጭ ሀገራት ያሉ በርካታ ፋብሪካዎች ሁሉንም ነገር እራሳቸው አያመርቱም። ለመለስተኛ ተቋማት እንዲሠራላቸው ይሰጣሉ። ለምሳሌ ቦይንግ በኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲሠራ የሰጠው የአውሮፕላን ክፍል አለ። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ወቅት እያመረተ ለቦይንግ በማስረከብ ላይ ይገኛል። ገቢም በማግኘት ላይ ይገኛል።

ኢትዮ ኢንጂነሪንግም መኪናና ትራክተሮችን በራሱ ለማምረት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል። ይህ የትራክተር ፋብሪካ ለግብርና አገልግሎት የሚውሉ ፓንፖችን ጭምር የሚያመርት ነው።

ኢትዮጵያ በግብርና የምትተዳደር ሀገር በመሆኗ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ትራክተር ያስፈልጋታል። በተለይም እያደገ የሚሄደውን ሕዝብ ቁጥር ለመመገብና ግብርናዋን ዘመናዊ ለማድረግ ሰላሳ አርባ ሚሊዮን ትራክተሮች ያስፈልጉናል። አሁን በተጨባጭ ያሏት የትራክተሮች ቁጥር በመላ ሀገሪቱ 100ሺ ትራክተር የሚሞላ አይመስለኝም። በዚህ የትራክተር ቁጥር ደግሞ ምርታማ ሆና ሕዝቧን መመገብ አትችልም። ከፍተኛ የምግብ እጥረት ያጋጥመናል። ይህ ደግሞ ለሀገሪቱ አደጋ ነው።

ተገዝተው በሚመጡ ትራክተሮች ብቻ የኢትዮጵያን ግብርና ማዘመን አይቻልም። ስለዚህም ኢትዮጵያ የራሷን ብራንድ መትከል ስለሚገባት በሚሊየን የሚቆጠር ትራክተር የሚያመርት ፋብሪካ መገንባት አለበት ብለን ወደ ተግባር በመግባት ላይ እንገኛለን።

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ አመሰግናለሁ።

አምባሳደር ሱለይማን ደደፎ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን   ኅዳር 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You