ፍላጎትና ገበያ ያልተጣጣሙበት የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና

በኢትዮጵያ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት እና ሥልጠና መሰጠት የተጀመረው ከ1940ዎቹ አካባቢ ጀምሮ እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ። ተቋማቱ ከተከፈቱባቸው ከተሞች መካከል ደግሞ አዲስ አበባ በቀዳሚነት ትጠቀሳለች። ከዚህ ጋር ተያይዞም ተቋማቱ የገበያውን ፍላጎት መሠረት ያደረገ ሥልጠና እና ትምህርት መስጠት እንዳለባቸው ይነገራል። የሚሰጠው ሥልጠና ገበያው የሚፈልገው ወይም ገበያ መር ካልሆነ ብክነት እንደሆነም ይታመናል። ይህም ቀጣሪ የሚፈልገው እንዲሁም ራሱ ተቀጣሪው ግለሰብ ወጥቶ በሙያው ሥራ ቢጀምር ገበያ ሊያገኝ ይችላል ወይ? የሚለውን ጥያቄ ይመልሳል።

ሠልጣኞች የሚሰለጥኑት በሁለት መልኩ ሲሆን፤ አንደኛው ቀጣሪዎች ተቀጥረው እንዲሠሩ እና የራሳቸውን ሥራ እንዲፈጥሩ በሚያስችላቸው መልኩ ነው። ለመቀጠር የማያስችላቸውን ሥልጠና ብቻ ከወሰዱ ግን ትርፉ ብክነት ይሆናል። የሥራ አጡን ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ያበዛዋል። በዚህም ሳቢያ ማኅበራዊ ቀውስ እንዲከሰት ከማድረግ ባለፈ፤ ሰዎች ወደ ወንጀል ሥራ እና ሀገርን ሊጎዱ ወደሚችሉ እንቅስቃሴዎች እንዲገቡ ይገፋፋቸዋል። መዋዕለ ነዋይም ይባክናል።

ይህንን ሁሉ ችግር ለመፍታት ነው የሚሰጠው ሥልጠና የግድ የገበያውን ፍላጎት መሠረት ያደረገ መሆን አለበት የሚባለው። ከዚህ አንጻር በአዲስ አበባ እየተሰጠ ያለው የትምህርት እና ሙያ ሥልጠና የገበያ ፍላጎትን መሠረት ያላደረገ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን አስታውቋል። ባለሥልጣኑ በተለያዩ ምሁራን ባስጠናው ጥናት መሠረት በከተማዋ በአብዛኛው ገበያ ተኮር ፍላጎትን መሠረት ያደረገ የትምህርት እና ሥልጠና ሥርዓት መከተል እንዳለባት ቢታወቅም እየተሰጠ ያለው የትምህርት ሥልጠና ግን ክፍተት ያለበት ነው ተብሏል።

ባለሥልጣኑ ‹‹ጥናት እና ምርምር ለትምህርት እና ሥልጠና ጥራት›› በሚል ርዕስ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ጥናቱን ያቀረቡት ዶክተር ገነነ አበበ እንዳሉት፤ በከተማዋ የሚሰጠው የቴክኒክ እና ሙያ ሥልጠና የገበያውን ፍላጎት የሚያሟላ አይደለም። የሙያ ደረጃ ሥርዓተ ትምህርቱ፣ የማሰልጠኛ መሳሪያዎች እና የመመዘኛ መሳሪያዎች በአብዛኛው የገበያውን ፍላጎት ሙሉ በሙሉ አያንፀባርቁም።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳኘው ገብሩ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፣ መሥሪያ ቤቱ በአዋጅ ከተሰጠው ሥልጣን እና ኃላፊነት እንዲሁም ተግባራት መካከል ጥናት እና ምርምሮችን አድርጎ የባለሥልጣኑ ዋና የትኩረት አቅጣጫ የሆነውን የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ እንዲሁም ‹‹ሠልጣኖች ምን ያህል ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት አግኝተዋል?›› ብሎ ምዘና ማካሄድ እና ውጤታቸውን መስጠት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፤ ይህንኑ ተግባርም እያከናወነ ይገኛል።

ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ከትምህርት ቢሮ እና ከቴክኒክና ሙያ ቢሮዎች ጋር በቅርበት ይሰራል። ጉድለቶች እንዲሟሉ፤ በጥንካሬዎች ላይ ደግሞ መቀጠል እንደሚገባ አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ በዓመት አራት ጊዜ የጥናት እና ምርምር ሥራዎችን ያከናውናል። ከነዚህ መካከል በ2015 ዓ.ም የተጠናው ፍላጎት ተኮር የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና አንዱ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ ያወሳሉ።

እንደ ሥራ አስኪያጁ ማብራሪያ በቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት ውስጥ የሚሰጠው ሥልጠና ለሀገር ግንባታ ወሳኝ ነው። አብዛኛው ዜጋ የሚፈራው ከቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት ነው። ተቋማቱ ተገቢው ትኩረት ካልተሰጣቸው የሀገር እድገት የሚታሰብ አይደለም። የሀገር እድገት እንዲያድግ ከተፈለገ ለሙያው ትኩረት መስጠትና ተማሪዎችን ማብቃት ይጠይቃል። ጥናቱ እንዳመላከተው ግን ብዙ መሰናክሎች እንዲሁም ብዙ ጉድለቶች እንዳሉ ነው። በአጭሩ የትምህርት ስብራት መኖሩን እና ስብራቱን ለመጠገን ደግሞ የቴክኒክን ሙያ ቢሮ ዋናው ሥራው ቢሆንም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መሥራትን ይጠይቃል።

አቶ ታደለ አየለ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክ እና ሙያ ሥልጠና ቢሮ የሥልጠና እና አካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ናቸው። እንደ እርሳቸው ገለፃ የቴክኒክና ሙያ ስትራቴጂ ገበያ መር እንዲሆነ ያዛል። እንደ ቢሮም ክፍተቶችን ለመለየት በየሁለት ዓመቱ ጥናት የሚያደርግ ሲሆን፤ በኢንደስትሪ አካባቢ ያሉ ችግሮች መቅረፍ እንዳለባቸው ይታመናል። ከቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት የሚወጣው የተማረ ኃይል የኢንደስትሪውን አቅም ሊያሟላ እንደሚችል በማመን የቀረውን ጥናት በግብዓትነት ተጠቅሞ የማስተካከል ሥራ ይሠራል።

አቶ ዳኘው በበኩላቸው እንደሚናገሩት፣ ኢንዱስትሪዎች ይህንን ሥራ ለመንግሥት ብቻ ወይም ለአንድ ተቋም የመተው አዝማሚያ ይታይባቸዋል። በተግባር ልምምድ ላይ ከፍተኛ እንቅፋት የሚፈጥሩ ሲሆን፤ በጋራ ተግባብቶ መሥራት ያስፈልጋል። አንዳንድ ተማሪዎች ፍላጎት ላይ መሠረት ያደረገ ሥልጠና ለመውሰድ ፈቃደኛ ሲሆኑ አይስተዋልም ወይም ፍላጎቱ የላቸውም። ተማሪዎቹ በሀገር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንደሆኑ የጥናቱ ግኝትን እና ምክረ ሃሳቦችን በማጤን መሥራት ያስፈልጋል።

ከብቃት ምዘና ጋር በተያያዘ በመዲናዋ በተአማኒነትና ብልሹ አሠራር በኩል መሻሻሎች መኖራቸውን ዶክተር ገነነ ተናግረው የተሻሻለ ነገር የታየ ቢሆንም አሁንም የበለጠ መሠራት እንዳለበት ይጠቁማሉ። ከሴቶች ተሳትፎ አንጻርም በሚገባ አበረታች ሥራ መሠራቱንና የተለየ ፍላጎት ላላቸው ለአብነትም የማየት፣የመስማት፣ የእንቅስቃሴ እና የመሳሰሉት ችግር ላለባቸው ተማሪዎች ፍላጎታቸውን ለማሟላት ተመሳሳይ ሥራዎች መሠራታቸውን ይጠቅሳሉ። ይሁን እንጂ ገና ብዙ ሥራ መሥራት እንደሚጠይቅ በጥናቱ ግኝት ለማወቅ ተችሏል። የተግባር ልምምድ ጋር በተያያዘ አሁንም የተወሰነ ክፍተት መኖሩ እንደታየ ይናገራሉ።

አቶ አየለ በበኩላቸው እንደሚናገሩት አካቶ ትምህርትን በተመለከተ ለአካል ጉዳተኛ ምቹ እንዲሆን ከማድረግ ባለፈ የሪሶርስ ማዕከላት (ከሥልጠና ወጥተው ልምምድ የሚያደርጉበት) ቦታ ተዘጋጅቷል። የሙያ መረጣን አስመልክቶ ለሴቶች፣ለአካል ጉዳተኞች ነጥቡን ዝቅ ከማድረግ በተጨማሪ ቅድሚያ በመስጠት ልዩ ትኩረት እንዲያገኙ ይደረጋል። በአጠቃላይ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር የአካል ጉዳታቸውን ዓይነት በመለየት ወደ ሙያ ሥልጠናው እንዲገቡ ይደረጋል።

የትብብር ሥልጠና በቴክኒክ እና ሙያ ሥልጠና ተቋማት ላይ በመሠረታዊነት ይሰጣል። የተግባር ልምምዱ በኢንደስትሪ ውስጥ እንዲሰጥ ይፈለጋል። አሁን ላይ ኢንደስትሪዎች ጠቀሜታውን እያወቁት ነው። ነገር ግን አንዳንድ ዘርፎች ላይ በተለይም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ ማሽኖች ለተለማማጆች ተላልፈው ተሰጥተው ቢሰባበሩ ‹‹ማን ይተካልናል?›› የሚል ስጋት አለ። ችግሩን ለመፍታት የቴክኒክ እና ሙያ ሥልጠና አዋጁን መሠረት አድርጎ እንዴት ማካካስ እንደሚቻል እና ሌላ የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት እንደሚገባ ምክረ ሃሳብ ቀርቧል። በተወሰነ መልኩ ፍላጎት እና አቅርቦት መኖሩ ጥናቱ በማመላከቱ ይህንንም ከአምራች ኢንደስትሪዎች እንዲሁም ከአገልግሎት ሰጪ ቀጣሪዎች ጋር ቀጣይነት ያለው ምክክር፣ ውይይት እና በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግ ዶክተር ገነነ ያብራራሉ።

ባለሥልጣኑ ችግሩን ለመፍታት ለመዛኞች እንዲሁም ለኢንዱስትሪ እና ለተቋማት አሰልጣኞች ስታንዳርድ አውጥቶ በዛ መንገድ ስለመሰራቱ መከታተል አስፈላጊ መሆኑን ዶክተር ገነነ ይጠቁማሉ። የሙያ ደረጃ፣ ሥርዓተ ትምህርት፣ የማሰልጠኛ መሳሪያዎች እና ሌሎችም ሲዘጋጁ የገበያውን ፍላጎት መሠረት አድርገው እየተሰጡ ስለመሆናቸውም ፍተሻ ማድረግ እንደሚገባ ይጠቅሳሉ። ተቋማቱም ሥልጠና ለመስጠት በሚያስችላቸው ቁመና ላይ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ በጥናቱ ላይ በመፍትሔነት ከቀረቡት ሃሳቦች መካከል ተጠቃሽ መሆኑን ያስረዳሉ።

ዶክተር ገነነ ጨምረው እንደሚያስረዱት በአዲሱ የትምህርት እና ሥልጠና ፖሊሲ ላይ የተለያዩ አማራጮች ተቀምጠዋል። በተለይም የተግባር ልምምድን በተመለከተ ሰልጣኞች ሊማሩ ከሚገባቸው ጋር ተያይዞ ከሚማሩት ጋር የተዛመደ መሆን ይኖርበታል። በኢንደስትሪዎች ውስጥ እየተሰጡ ያሉ እና ኢንደስትሪው በትክክል ሊያሰለጥኑ የሚችሉ ትክክለኛ አሰልጣኞችን መመደባቸውን ከዚህ በተጨማሪም በተግባር ልምምድ ጊዜ የክትትል ሥራዎች መሠራታቸውን መከታል ያስፈልጋል።

በአሁን ወቅት ከቴክኒክ እና ሙያ ሥልጠና ትምህርት ቤቶች የሚወጡትን መፈለግ ብሎም የመቅጠሩ ነገር ከዚህ ቀደም ከነበረው ጋር ሲነጻጸር መሻሻሎች ታይተውበታል። ይሁን እንጂ አንዳንዴ ከተቀጠሩ በኋላ ከእውቀት፣ ከሙያ በተጨማሪ የአመለካከት ክፍተት መኖሩ ታይቷል። እንዲሁም ኢንዱስትሪዎች ሰልጣኞቹን ከቀጠሯቸው በኋላ የሰዓት አጠቃቀም፣ የሥራ ፍላጎት አናሳ መሆን በሰልጣኞቹ በኩል እንደ ችግር ይነሳል። በቀጣሪው በኩል ደግሞ በቂ የሚባል ክፍያ ስለማይከፈላቸው ለቆ የመውጣቱ ነገር በስፋት መታየቱ በጥናቱ ተመላክቷል።

በከተማዋ በሚገኙ አንዳንድ ሰልጣኞች ላይ የቴክኒክ እና ሙያ ሥልጠና ትምህርት እንደ ጊዜ ማሳለፊያ እና ሌላ ዕድል እስከሚያገኙ ድረስ ያለፍላጎታቸው የሚማሩ መኖራቸው በጥናቱ አማካኝነት ታውቋል። ተግባራዊ ልምምድ ሳይወስዱ እንደወሰዱ ተደርጎ ‹‹ደብዳቤ ፃፉልን፡›› የሚሉ ሰልጣኞችም አልጠፉም። ስለዚህም በተማሪዎች በኩል ለቴክኒክ እና ሙያ ትምህርት ያለው ዝቅተኛ አመለካከት ሙሉ በሙሉ ተቀርፏል ብሎ መናገር አይቻልም።

በተመሳሳይ በማኅበረሰቡ በኩል የአስተሳሰብ መዛባት አለ ያሉት አቶ አየለ፤ የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመጠቀም ተማሪዎች አማራጭ አጥተው ሳይሆን መርጠውት እንዲመጡ ኅብረተሰቡ እንዲያውቀው እየተሠራ ነው ሲሉ ይገልፃሉ። ከትምህርት ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን ተማሪዎች ገና ወደ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ከመምጣታቸው በፊት የግንዛቤ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ይጠቁማሉ። በተጨማሪም ከተቋማቱ ወጥተው የራሳቸውን ድርጅት ከፍተው እና በተለያዩ ቦታዎች ላይ ተቀጥረው እየሠሩ ያሉ ሰዎችን በመገናኛ ብዙኋን የማስተዋወቅ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ያስረዳሉ።

በአንዳንድ ሠልጣኞች በኩል ሥልጠናውን የማይፈልጉበት ምክንያት ‹‹እስከ ደረጃ አምስት ከተማርን በኋላ ለማደግ አያስችለንም።›› የሚል ይሁን እንጂ በአዲሱ የትምህርት እና ሥልጠና ፖሊሲ መሠረት ተማሪዎቹ ጠንክረው ከተማሩ እስከ ደረጃ ስምንት (ከፔኤች ዲግሪ ጋር እኩል ) ለመድረስ እንዲቻላቸው ሁኔታዎች እንደተመቻቹላቸው ይጠቅሳሉ። በማኅበረሰቡ፣ በቀጣሪዎች እንዲሁም በሠልጣኞች የተወሰነ መሻሻሎች ቢኖሩም ብዙ መሥራትን እንደሚጠይቅ ይገልጻሉ።

አቶ አየለ በበኩላቸው እንደሚሉት በአሁን ወቅት በቴክኒክ እና ሙያ እስከ ደረጃ ስምንት መማር የሚቻልበት ሁኔታ በመፈጠሩ በሙያ የተደገፈው ትምህርት ለመማር የሚያስችል አሠራር ተዘጋጅቷል። በ2015 ዓ.ም የአስራ ሁለተኛ ክፍል ውጤትን አስመልክቶ በርካቶች ውጤት ያላመጡ መሆናቸው እንደ መልካም ዕድል መቆጠር አለበት። ወደ ዩኒቨርሲቲ የገባ ብቻ አይደለም በትምህርት ዘርፍ መቀጠል የሚችለው። ቴክኒክ እና ሙያ ሌላ አማራጭ ነው። ተማሪዎች ወደ ተቋማቱ የመግባታቸው ነገር የሰፋ በመሆኑ በቴክኒክና ሙያ ተቋማት ላይ ምንም የሚፈጥረው ጫና የለም። ከዚህ ጋር ተያይዞም ከደረጃ አንድ እስከ አምስት ሥልጠና ለመስጠት በቂ ዝግጅት ተደርጓል።

የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ እንደሚገልጹት፤ ገበያን መሠረት ያደረገ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ለሀገር እድገት ወሳኝ መሆኑን በመረዳት ባለሥልጣኑ በቀጣይ በግኝቱ መሠረት ችግሮችን ለይቶ የቁጥጥርና የድጋፍ ሥራዎችን ይሠራል።

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን   ኅዳር 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You