መጪውን ጊዜ ብሩህ ለማድረግ

ሰው የህልሙ ፈጣሪ እንደሆነ በርካታ ጠቢባን ይናገራሉ። በዚያው ልክ ሰው የመከራው ፈጣሪም እንደሆነ የሚናገሩ ጥቂቶች አይደሉም። ሀገር በዜጎች ሃሳብ፣ በትውልድ የበጎነት ስንቅ እንደምትፈጠር ሁላችንንም የሚያግባባ የጋራ መረዳት አለ። በዚህ መረዳት ውስጥም ከዓለም የገዘፈች ኢትዮጵያ የምትባልን ሀገር ፈጥረን እናውቃለን።

ከትላንት መለስ ብለን አሁንን ስንቃኝ ግን ትግላችን እንደ በፊቱ ለአብሮነት ሳይሆን የብቻ ቤትን ለመሥራት የምንፈራገጥ ነው የሚመስለው። ደግሞም እውነት ነው ተንፈራግጠን ከአምና የተለዩ መልከ ውይብ ማንነትን ፈጥረናል። ይህ አሁናዊ መልካችን እየሆነ ነው።

አሁን አሁን የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ የመጀመሪያው ጥያቄ እስከመቼ በሞትና ጦርነት ውስጥ እንኖራለን? መቼ ነው ከዚህ አዙሪት የምንወጣው? ለምንድነው ከንቱ ድካም የማይደክመን? የሚሉት እንደሚሆኑ በልበ ሙሉነት ለመናገር እደፍራለሁ። ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት እየከፈልነው ያለው ያልተገባ ዋጋ ነው።

የአንድ ሀገር ሕዝቦች ፈተና ካለመግባባትና ከእርስ በርስ ግጭቶች የሚነሱ ናቸው። ለዚህ ሃሳብ አጽንኦት ለመስጠት በሀገራችን የተነሱትን የዜጎች መፈናቀል፣ ስደት፣ ርሀብ፣ ተረጂነት፣ የኑሮ ውድነት፣ የስጋት እንቅስቃሴ፣ የጸጥታ ችግር ሌላም ሌላም መጥቀስ ይቻላል። እኚህ ማህበራዊ ፈተናዎች ባለመግባባትና ቁጭ ብሎ ባለመነጋገር ጉልበት/ጦርነት መር በሆነ አስተሳሰብ የተፈጠሩ ስለመሆናቸው የማይረዳ የለም።

በዚህ መንገድ እስካሁን የበላይነት በሚንጸባረቅበት የአሸናፊነት መንፈስ ውስጥ ያለንን ከማጣትና ከመጣል ባለፈ የተቀዳጀነው ድል የለም። ዛሬም ድረስ የትላንትና የከዛ ወዲያ የአፋችንን ፍሬ እየበላን ነው። ”ሞትና ሕይወት በአፍህ ቃል/በምላስ ውስጥ እንደሆኑ ታላቁን መጽሐፍ ቅዱስ ጨምሮ የተለያዩ የእውቀት አፎች ይነግሩናል። ግን አውቀንና ተረድተን ራሳችንን ከስቃይ ትውልዱንም ከጥላቻ አልታደግነውም።

እስካሁን ያሸነፍንባቸውም ሆኑ የተሸነፍንባቸው የወንድማማቾች ግፊያዎች ዛሬ ላይ ማናችንም ከፊት አላቆሙንም። አቁመውናል? ስለእውነት እናገራለሁ አላቆሙንም። ይልቅ ማንም ያልከፈለውን የመከራና የስቃይ ዋጋ እያስከፈሉን ነው። አሁናዊ ስቃዮቻችን፣ አሁናዊ መለያየቶቻችን አሸናፊና ተሸናፊ በሌለው የእርስ በርስ ግጭቶችን የመጡ ናቸው።

ሀገርን መታደግ ሕዝብን መታደግ ነው። ሕዝብን መታደግ ደግሞ ትውልድን መታደግ ነው። እኚህ ሁሉ ልዩ መሳይ አንድ ዓይነት መልኮች ወደቀደመ ኢትዮጵያዊ መልክና ክብራቸው እንዲመለሱ ሄደን ሄደን የምንወድቅበት ሳይሆን ሄደን ሄደን የምንደርስበት የአብሮነት ምኩራብ ያስፈልገናል። ይሄ እንዲሆን ሀገር ባቀና የጨዋነትና የአንተ ትብስ ልማዳችን ተረከዝ እስከመያዝ በሚያደርስ የክብብር መንፈስ ውስጥ በመነጋገር ወጥተን የምንገባበት የእርቅና የተግባቦት እውቀት ያስፈልገናል።

እንዲህ ካልሆነ የምንደርስበት ሩቅ የለም። እንዲህ ካልሆነ የምንደርስበት ህልምና ራዕይ የለንም። ፍቅርና አንድነትን ባጎደለ ምኞትና ህልም ውስጥ የሚመጣ የተሀድሶ ለውጥ የለም። ሀገራዊም ሆኑ ግለሰባዊ ለውጦች በፍቅር ጀምረው በአንድነት የሚያበቁ ናቸው። ተለያይተንና ተራርቀን ንፋስ የገባባቸው ቀዳዳዎቻችን እንዲጠቡ የፍቅር አፎችና የእርቅ አንደበቶች ያሹናል። እንዴትም ብናስብ እንደ እኛ የተቀራረበ ሕዝብ የለም። የታሪኮቻችን መነሻና መድረሻ የአብሮነት ደማቅ ስምን የታከኩ ናቸው።

‘ጊዜ የሰውን ልጅ አይቀይረውም’፤ ይሄን እውነት ለመረዳት ዝግ ማለት ግድ ይሆናል። በአሁኑ ሰዓት ዓለም በዚህ አስተሳሰብ ውስጥ ሁለት የተለያዩ ጽንፎችን የምታራምድ ናት። ሰው እንደተረዳው ነው። ማንነቱ፣ ታሪኩ፣ ሕይወቱ፣ ህልሙ ሳይቀር ይሄን እውነት ተደግፎ የቆመ ነው። ምን ለማለት ፈልጌ ነው.. በየትኛውም የሕይወት መንገድ ላይ በጽናትም ሆነ በእንግድጋዴ የምንራመደው በገባን ልክ ነው።

ብዙዎቻችን ዘመንን በተመለከተ ሁለት ዓይነት አረዳድ አለን። ‹ጊዜ የሰውን ልጅ ይቀይረዋል› የሚልና ‹የሰው ልጅ ጊዜን ይገዛዋል› የሚል። በምንም የሕይወት ደረጃ ላይ እንሁን ሁላችንም ከዚህ እውነት ጀርባ የቆምን ነን። ከሁሉም የሚልቀው እውነት ጊዜ በሰው ልጅ ቁጥጥር ስር ነው የሚለው ነው።

ይሄ እውነታ የገባቸው በጊዜ ውስጥ የሚቀይሩት ታሪክ፣ ማንነት፣ ባህል፣ ሥርዓት የላቸውም። ማንነታቸውን ተቀብለው ወደፊት የሚራመዱ እግረ ለሞች ናቸው። ይሄ እውነታ ያልገባቸው ግን ትላንትን እየናቁ ዛሬን የሚያደንቁ፣ ታሪክና ማንነታቸው ኋላቀር እየመሰላቸው ምንም ባላወቁትና ባልተረዱት የሚደናበሩ ናቸው።

ይሄን እውነት ወደእኛ ስናመጣው ብዙ የትዝብት አክርማን መምዘዝ እንችላለን። ዓለም በሌለው ክብርና ነጻነት ውስጥ የቆምን፣ የሰላምና የአብሮነት ደሴት ተብለን የተደነቅን ሕዝቦች ስለምን ዛሬ ሌላ ሆንን? ከኢትዮጵያዊነት ውጭ ሌላ የማናውቅ፣ ተጨማሪ ስምና መጠሪያ የሌለን ሕዝቦች ዛሬ ስለምን በማይረቡ እልፍ ስሞች ተከበብን?።

ተመካክሮ በጥቅምት እኩሌታ ወራኤሉ የከተመ፣ ተግባብቶና ተስማምቶ በኦጋዴንና በካራማራ የቆመ ሕዝብ ስለምን ዛሬ ሰላም ራቀው? ባህር ማዶ ተሻግሮ ስለሌላው ሰላም የሞገተ፣ ስለሌላው ነጻነት የተከራከረ ሕዝብ ስለምን ሰላም ናፋቂ ወጣው? ሊቀ ነብያት ሙሴን ያበረቱ ዮቶራዊ አፎች፣ የግሪክ ጸሐፍቶች በድርሰቶቻቸው ያሞካሿት ኢትዮጵያ ስለምን ዛሬ ክብር ራቃት?።

“ኢትዮጵያዊ መልኩን ነብር ዠንጉርጉርነቱን” አይቀይርም ሲል አምላክ በቃሉ ያወሳት ምድር፣ “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደእግዚአብሔር ትዘረጋለች” ሲል የእምነቷን አጽናፍ የመሰከረ ቅዱስ ቃል ያላት ሀገር አሁን ምን አገኛትና ከተመሰከረ ማንነቷ ጋር ተጋጨች? ስለሀገሬ ጥቂቱን ተናገርኩ እንጂ ጥንተ ብኩርናዋንና ገናናነቷን የሚናገሩ እልፍ የታሪክ ሰነዶች አሉ። ዛሬ ለምን፤ ስለምን ቀለልን? ስለምን ከክብራችን ተንሸራተትን?

ጥያቄዎቻችን ወደ አንድ አቅጣጫ ነው የሚመሩን..የጥንቱን ባህል ስለመሳት፣ መጤ በሆኑ አጉል አስተሳሰቦች ስለመወሰድ፤ የቱን ያህል በከፋ ራስ ወዳድነት እና ጽንፍ ረገጥ አስተሳሰብ መወሰዳችንን ነው የሚያሳብቁት። ታሪክ ማጣመምን፣ እውነትን መሸሽን ነው የሚነግሩን። በትርክት መሽመድመድን፣ በሀሰት መለያየትን ነው የሚጠቁሙን። ተነጋግሮ አለመግባባትን፣ ተወያይቶ አለመስማማትን ነው የሚነግሩን። ለፍቅርና ለይቅርታ የተዘጉ ልቦቻችንን ነው የሚያስታውሰን። ከባህልና ከሥርዓት ያፈነገጠ ጊዜ ወለድ ማንነታችንን ነው የሚያንጸባርቁብን።

እስከ መቼ አንቀላፍተን፣ እስከ መቼ የራሳችን ጠላቶች ሆነን እንዘልቀዋለን? የጦርነት ነጋሪት ስንጎስም፣ አታሞ ስንመታ እዚህ ደርሰናል። እስኪ ደግሞ በፍቅር ድካሞቻችንን እንርሳ። ተነጋግረንና ተፈቃቅደን ችግሮቻችንን ካልፈታን የጥንቱን አብሮነት የምንመልስበት ሌላ ሁነኛ መላ የለንም።

ከድካሞቻችን ለመበርታት ብቸኛው መዳኛችን እርቀ ሰላም ነው። በእርቅ ሰላም ማውረድ ለእኛ አዲስ ነገራችን አይደለም። ስናስታርቅና ስንመክር፣ ስንገስጽና ስናስተቃቅፍ የኖርን ለዘመናዊው ዓለም ፋና ወጊ የሆንን የሥርዓት ቀደምቶች ነን። ልባችንን በእልህና በክፋት ዘግተነው እንጂ ለዛውም ከወንድሞቻችን ጋር፣ ለዛውም አብሮ ከበላና አብሮ ከተዋለደ ሕዝባችን ጋር መተቃቀፍ አይከብደንም ነበር።

አሁን ላይ የሰላም መንገዶቻችንን የዘጉብን የኃይል አስተሳሰቦች ዘመን አመጣሽ ወይም ደግሞ ከዚህ የተሻለ ስም የሚሰጣቸው ናቸው። እንጂማ ማንና ምን እንደነበርን የምናውቅ ነን። ጥንተ መሠረታችን ፍቅርን አምጦ የወለደ ማህጸን፣ አንድነትን አቅፎ ያሳደገ ክንድ ነው። ጥንተ ማንነታችን አብሮነትን እሽሩሩ ያለ፣ ኢትዮጵያዊነትን ያስቀደመ ሃሳብ ነው። ዛሬ በጥላቻና በመለያየት ቆሽሸን የቆምንው አንደበቶቻችን እብለትን፣ እጆቻችን ግፍን፣ ልቦቻችን ጥላቻን ስለተለማመዱ ነው።

በጥላቻ የቆመ ትውልድ እንደ ሎጥ የክብር መንገድ የለውም። በመለያየት የቆመ ሕዝብ እንደ አብረሃም የበረከት ቤት የለውም። ሎጥ ከሰዶም ሲወጣ፣ አብረሃም ከካራን ሲጠራ በፍቅር ልብ በኩል ነው። እኛም የፍቅር ልብ ያስፈልገናል። ከድህነትና ከኋላቀርነት ብሎም ጦርነት እያስከፈለን ካለው አበሳ ለመራቅ ምክክርን እንደሁነኛ አማራጭ ልንቀበለው ግድ ይለናል።

ልዩነት ለምን ተፈጠረ ሳይሆን ልዩነትን እንዴት ማጥበብ እንዳለብን ማወቁ ነው የሚበጀን። ለውይይት ቢሮውን የከፈተ ባለሥልጣን፣ ለምክክር ፖለቲካውን ያዘጋጀ ፓርቲ ለሀገር ጥፋት የሚሆንበት ምንም ምክንያት የለም። ለእርቅና ለተግባቦት የተዘጋጀ ማህበረሰብ የልዩነት ድጦች አዳልጠው አይጥሉትም።

የሩዋንዳና የደቡብ አፍሪካን የብሔራዊ ምክክር አውድ ስንቃኝ መነሻው የልዩነት ጽንፍ ሆኖ መድረሻው ደግሞ ሀገራዊ ውጥንቅጥ ነበር። በሄዱበት ሁሉን አካታች የምክክርና የውይይት ቅብብሎሽ ችግራቸውን ቀርፈው ሀገራቸውን ወደሰላማዊ ይዞታዋ መመለስ የቻሉበትን ሁኔታ ማስታወስ ይቻላል። በእኛም ሀገር ተመሳሳይ ነገር ስለመንጸባረቁ የኮሚሽኑ ዓመታትን የዘለቀ ዝግጅት ጥቁምታን የሚሰጥ ነው።

በሰፊ መድረክ፣ በሰፊ ተሳትፎ ሰፊዋን ሀገራችንን ከአስተሳሰብ ጥበት ለማውጣት እየተሰራ ያለው ሥራ የሚደነቅ ነው። በእንዲህ ዓይነቱ አካታችና አሳታፊ፣ ገለልተኛና ነጻ መድረክ ፊት ካልሆነ ወደ ሰላም የሚያስገባን ቀዳዳ እንደሌለም የሚታመን ነው። ለአንድነት በአንድነት ስንቆም ሰፍተን እንደምንገዝፍ ብዙ ያለፉ ታሪኮቻችን ምስክሮች አሉን። ከእኛ የማሰብና የመዋሃድ አቅም አንጻር ሲታዩ ችግሮቻችን እዚህ ግቡ የሚባሉ አይደሉም። የሰላም መንገዶቻችንን የዘጉብን እውቀት ማነስ ሳይሆን ለፍቅር አለመሸነፋችን ነበር።

ታሪክና እሴት፣ ወግና ልማድ የሳተ ፖለቲካ ለሀገር አይበጅም። በታላላቅ ባህልና ሥርዓት ውስጥ በቅለን ፍሬ አልባ ዛፍ የሆነው ርካብ በሳተ ርምጃችን ነው። ሀገር በመገንባት ሂደት ውስጥ ትልቁ ብቃታችን ሊሆን የሚገባው በምንም የማይሸራረፍ የአብሮነት መንፈስ ነው። ቀጣይ በሚኖረን የእርቅና የተግባቦት መድረክ ላይ እንዲህ ዓይነቱን መንፈስ በማራገብ ልዩነቶቻችንን ማጥበብ እንችላለን።

ሕይወት የአረዳድ መልክ ነው። እየኖርን ያለነው በተረዳንውና በገባን ልክ ነው። አረዳዳችንን ከኃይል ይልቅ ለሰላም፣ ከጥላቻ ይልቅ ለፍቅር እስካላስገዛን ድረስ ህልሞቻችን ፍሬ አይቋጥሩም። በአንዳንድ ትርክቶችና አንድነት ጠል ቡድኖች ከመነሻችን ሸሽተን ሌላነትን እየተለማመድን ነው። ከእውነታ የራቀ አረዳድ ትርክት ከማድመጥ ባለፈ ትርክት የማጥራት አቅም የለውም። በሀሰትና በማስመሰል እውቀት ጥራዝ ነጠቆች ሆነን ትውልዱን እየመረዝን ያለነው ባልገባን እውቀት ነው።

በወሬ ሳይሆን በተግባር፣ በትርክት ሳይሆን በታሪክ ሀገር እንፍጠር። በጥላቻ ሳይሆን በፍቅር፣ በመለያየት ሳይሆን በማበር ትውልድ እንታደግ። መጪውን ጊዜ ብሩህ የሚሆነው በዚህ ለሁላችንም በሚበቃና፤ ሁላችንን በሚበጅ እውነትና እምነት፣ ሃሳብና ተግባር ስንቃኘው ብቻ ነው።

ልዩነት ለምን ተፈጠረ ሳይሆን ልዩነትን እንዴት ማጥበብ እንዳለብን ማወቁ ነው የሚበጀን። ለውይይት ቢሮውን የከፈተ ባለሥልጣን፣ ለምክክር ፖለቲካውን ያዘጋጀ ፓርቲ ለሀገር ጥፋት የሚሆንበት ምንም ምክንያት የለም። ለእርቅና ለተግባቦት የተዘጋጀ ማህበረሰብ የልዩነት ድጦች አዳልጠው አይጥሉትም

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን   ኅዳር 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You