ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት

 አብዛኞቹ የዓለም ሸማቾች የሀገር ውስጥ ምርት የመሸመት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ጥናቶች ያመለክታሉ። ከእነዚህ መካከል የሀገር ውስጥ ምርትን በመሸመት ታዋቂ የሆኑት አውስትራላውያን ናቸው። የህንድ እና የጣሊያን ዜጎችም ከአውስትራሊያ ቀጥለው የሚጠቀሱ ሕዝቦች ናቸው።

ከአውስትራሊያ ሸማች ሕዝብ 74 በመቶ የሚሆኑት ሙሉ ለሙሉ ምርቶችን ከሀገር ውስጥ ካምፓኒ የመሸመት ፍላጎት አላቸው። ከህንዳውያን 72 በመቶ ፤ ከጣሊያናዊያን 69 በመቶ የሚሆኑ ደግሞ የሀገር ውስጥ ምርትን የሚሸምቱ ናቸው።

ይህ የሀገራቱ ሕዝቦች የሀገር ውስጥ ምርትን የመሸመት ፍላጎት መነሻው ፤ ከሀገር ፍቅር ስሜት እና በሀገራቸው ውስጥ እነርሱ የሚሸምቷቸውን ምርቶች የሚሠሩ ሠራተኞችን እና ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት፤ ለማበረታታት እና እንዲያድጉ ከማሰብ እንደሆነ በዘርፉ የተካሄዱ ጥናቶች ያመላክታሉ።

ወደ እኛ ሀገር ስንመጣ እውነታው የተገለቢጦሽ ነው። ኢትዮጵያ ከምታመርተው በላይ ወደ ሀገር ውስጥ የምታስገባቸው ምርቶች ከፍተኛ ናቸው። ይህም ሕዝቧ ከሀገር ውስጥ ምርት ይልቅ የውጭ ምርትን የመሸመት ሰፊ ዝንባሌ እንዳለው የሚጠቁም ስለመሆኑ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ዜጎች የራሳቸውን ሀገር ምርት መሸመታቸው የሀገር ውስጥ አምራቾችን እንደሚያበረታታ ለመገመት ብዙም የሚከብድ አይደለም። በአንድ ሀገር ውስጥ የሚመረተው ምርት በሀገር ውስጥ ገበያ ከሌለው የሚያድግበት ዕድል ውስን መሆኑም እንዲሁ የሚታወቅ ነው።

አንድ አዲስ ምርት በሀገር ውስጥ ገበያ ሽያጭ ቀስ በቀስ ማደግ ካልቻለ እና ምርቱን በጥራትም ሆነ በብዛት ካላሳደገ በዓለም ደረጃ የመታወቅ፣ ተወዳዳሪ ሆኖ ገበያ የማግኘት ዕድሉ አነስተኛ ስለመሆኑ ገበያ ላይ የተካሄዱ ጥናቶች ያመለክታሉ።

ይህ የሀገር ውስጥ ምርትን መግዛት እና የሀገር ውስጥ ካምፓኒዎችን የማበረታታት ጉዳይ ሲጠቀስ፤ ለብዙ የሀገር ውስጥ ካምፓኒዎች ውድቀት በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ መነሻው የካምፓኒው ክፍተት ብቻ ሳይሆን የሀገሩ ዜጎች አለመሸመትም በምክንያትነት ሊነሳ ይችላል።

በተለይ በአነስተኛ ደረጃ በማምረት ቀስ በቀስ ገቢ እያገኙ በሂደት ማደግን አስበው የሚነሱ አምራች ዜጎች፤ ምንም እንኳ ምርቱ ጠቃሚ ቢሆንም፤ የሀገር ውስጥ ምርትን የሚሸምት አለመኖሩ እና ሸማች ማጣታቸው ያመረቱት ምርት አገልግሎት ላይ እንዳይውል እና ታዋቂነትን እንዳያገኙ ያደርጋቸዋል።

የገበያ ሁኔታው አመቺ ካልሆነ እና ገዢ ከጠፋ እነርሱም አማራጭ ገበያን አግኝተው ከማደግ ይልቅ ሥራቸው ሙሉ ለሙሉ ተጎድቶ ለኪሣራ የሚጋለጡበት ሁኔታ መኖሩ እና ሥራቸውን አቋርጠው ሠራተኛ መበተናቸው የማይቀር ነው። ይህንን ታሳቢ በማድረግም የሀገር ውስጥ ምርት በመሸመት አምራቾች እንዲበረታቱ ብዙ ሥራ መሠራት እንዳለበት እየተነገረ ይገኛል።

በርግጥ የሀገር ውስጥ ምርትን የመግዛት ዝንባሌ አምራችን ብቻ ሳይሆን ዜጎችም በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች፣ ምርቶችን በሚፈልጉት ዝቅተኛ ዋጋ እንዲያገኙ ይረዳቸዋል። በተለይ ለሸማች መሠረታዊ የሆኑ ምግብ፣ ልብስ ወይም ሌሎች ከመጠለያ ጋር የተገናኙ የቤት መሥሪያ ግብዓቶች እና የቤት ውስጥ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎችን አግኝተው በቀላል ዋጋ እንዲገዙ እና እንዲጠቀሙ ይረዳቸዋል።

የሀገር ውስጥ ምርትን መሸመት ለዜጎች ወጪ የመቆጠብ እድልን የሚፈጥር ጭምር ነው፤ ይህ የሀገር ውስጥ ምርትን በመግዛት የተገኘው የቁጠባ ገንዘብ ለሌላ ዓላማ መዋሉም በራሱ ሸማቹ የሚያገኛው ሌላኛው ጥቅም ይሆናል። ከሸማች እና ከአምራች በተጨማሪ የሀገር ውስጥ ምርትን ገበያን ማስፋት ነጋዴዎችንም በእጅጉ የሚጠቅም ነው። ከሌሎች ሀገሮች ምርቶችን በመግዛት ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የሚያወጡትን የመርከብም ሆነ የጉምሩክ እና ሌሎችም አጠቃላይ የትራንስፖርት ወጪዎችን ይቀንስላቸዋል።

በሀገር ውስጥ የሚመረተው ምርት ለመጓጓዣ የሚያስወጣው ወጪ አነስተኛ መሆን፤ ያለምንም የዓለም አቀፍ ነጋዴ የዋጋ ውድድር በቀላሉ ገዝቶ ማከፋፈል አስመጪ የነበረ እና ጅምላ ሻጭ ነጋዴውንም የሚያበረታታ እና በቀላሉ ከውጭ ከሚመጣው በቀነሰ ዋጋ እንዲያከፋፍሉ እና የተሻለ ገቢ እንዲያገኙ የሚያስችላቸው ነው።

ይህ የሀገር ውስጥ ምርትን መሸመት አምራች ዜጎችን ፣ ሸማቾችን እና አስመጪ ነጋዴዎችን ለመርዳት ብቻ ሳይሆን ሀገርንም በእጅጉ የሚጠቅም ስለመሆኑ አጠያያቂ አይደለም። በዓለም ደረጃ ብዙ ግለሰቦች የሀገራቸውን አምራች ሰዎች የማበረታታ ፍላጎት ያላቸው በመሆኑ፤ ለሀገራቸው ምርት ቅድሚያ በመሥጠታቸው ግለሰቦች ብቻ ሳይሆኑ ሀገራቸውም በከፍተኛ ደረጃ እየጠቀሙ ስለመሆኑም ይነገራል።

ሀገር እንድትጠቀም ከሚያስችሉ ምክንያቶች መካከል ዋነኛው የውጭ ምንዛሬን ማዳን ነው። ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ በመግባት ለገበያ የሚቀርቡት ምርቶች በውጭ ምንዛሬ የሚገቡ በመሆናቸው ያንን ለማዳን እና ሀገርን ከወጪ ለመታደግ ትልቅ መንገድ መሆኑም እየተጠቆመ ነው።

ዜጎችም ሆኑ ሀገራት የሚያገኙትን ጥቅም ታሳቢ በማድረግ፤ ሀገራት በተለያዩ መንገዶች ‹‹የሀገራችሁን ምርት ግዙ›› እያሉ ያበረታታሉ። የኢትዮጵያ ልማት ኢንተርፕራይዝም ከቀጣዩ ወር ከታኅሣሥ ጀምሮ ብዙዎች በሀገር ውስጥ የተሠሩ ምርቶችን መግዛት እንዳለባቸው ለማስታወስ እና ይህም ሁሉንም እንደሚጠቅም ለማስገንዘብ ‹‹ ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት ›› የሚል መሪ ሃሳብ በመያዝ ቅስቀሳ ለመጀመር መሰናዶ እያደረገ ይገኛል።

ነገር ግን እዚህ ጋር የሀገር ውስጥ ምርት ከመሸመት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጉዳዮች አሉ። አንደኛው ከጊዜ ወደ ጊዜ የምርት ጥራትን ማሳደግ ሲሆን፤ ሌላኛው ከውጭ ከሚገዛው ይልቅ በዝቅተኛ ዋጋ ሊሸመት የሚቻልበት ሁኔታን መመቻቸት ነው። ምርቱ ያለ ብዙ ውጣ ውረድ በቅርብ ርቀት እና ያለ ብዙ ጥበቃ በቀላሉ መገኘት እንደሚኖርበትም እየተነገረ ይገኛል።

ስለዚህ ሸማቾች የሀገር ውስጥ ምርትን መሸመት ላይ ሲያተኩሩ፤ አምራቾች ደግሞ በስፋት ጥራቱ የተጠበቀ ምርት ለማቅረብ ሲሠሩ፤ ነጋዴውም ከሌሎች ሀገሮች ምርቶችን በማስመጣት ላይ መጠመዱን ሲያቆም፤ አከፋፋይም ሆነ ጅምላ ሻጭ በሀገር ውስጥ የተመረተውን ምርት በስፋት በማሰራጨት በቀላሉ የአምራቾችን እና የራሱን ገቢ ያለ ብዙ ውጣ ውረድ የተሻለ ለማድረግ ሲጥር ሀገር ተጠቃሚ ትሆናለች።

ዜጎች ተጠቃሚ ሆነው ሀገር እንድታድግ ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት።

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን   ኅዳር 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You