ቱሪዝም ሚኒስቴር የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማበረታታት፣ በዲጂታል አማራጭ የመስህብ ሀብቶችን ለቀሪው ዓለም ለማስተዋወቅ እየሠራ እንደሆነ በተለያዩ ጊዜያት በሚያወጣቸው መረጃዎች ይገልፃል። ከዚህ ባሻገር ዘርፉን ያነቃቃል ያላቸውን ፎረሞች፣ ንቅናቄዎች እንዲሁም ውይይቶች በተደጋጋሚ ሲያደርግ ይስተዋላል። በያዝነው የ2016 በጀት ዓመት ደግሞ ከመስከረም 29 እስከ ጥቅምት 28 የቆየ ሀገር አቀፍ የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ አውደ ርዕይ አዘጋጅቶ ነበር።
በአውደ ርዕይው የመንግሥትና የግሉ የቱሪዝም ዘርፍ ባለድርሻዎች ተሳትፈውበታል። ክልሎች ያላቸውን የባህል፣ የታሪክ፣ የቱሪዝም እንዲሁም የተፈጥሮ መስህቦችን ለሀገር ውስጥና ለዓለም አቀፍ ጎብኚዎች በአካልና በዲጂታል አማራጭ የማስተዋወቅ አጋጣሚውን አግኝተዋል። በአንድ ወር ቆይታ ጊዜ ውስጥ የክልላቸውን ሀብቶች በመድረኩ ተገኝተው ካስተዋወቁት ውስጥ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ይገኝበታል። የዝግጅት ክፍላችንም በስፍራው 170 ሺህ ታዳሚ ተገኝቶ በጎበኘው አውደ ርዕይ የቱሪዝም ሀብቶችን ካቀረበው የክልሉ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ተወካይ አቶ ሽመልስ አድሬ ጋር ቆይታ በማድረግ የሚከተለውን መረጃ አሰናድቷል።
የባህልና ቱሪዝም ቢሮው የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሽመልስ አድሬ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በርካታ የታሪክ፣ የባህል፣ የተፈጥሮ ቅርስ የሚገኝበት እንደሆነ ይናገራሉ። ክልሉ ለአንድ ወር በቆየው የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ አውደ ርዕይ ላይም እነዚህን ሀብቶች ለበርካታ ሺህ ጎብኚዎች እንዳስተዋወቀ ይገልፃሉ። ከሌሎች ክልሎች የዘርፉ አንቀሳቃሾች ጋርም የልምድ ልውውጥ ከማድረግ ባሻገር ቀጣይነት ያለው ግንኙነት መፍጠሩን ይናገራሉ።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልና በውስጡ የሚኖሩ ብሄረሰቦች በርካታ መስህብና እሴቶች ባለቤት ናቸው ፤ የሚሉት አቶ ሽመልስ ከዚህ ውስጥ የቤኒሻንጉል ብሄረሰብ ባህላዊ እሴቶችን በምሳሌነት ያነሳሉ፤ በክልሉ ነባር ከሆኑ ብሄረሰቦች መካከል አንዱ የሆነው ቤኒሻንጉል ታሪካዊ ባህላዊ እና ሌሎች በርካታ እሴቶች ባለቤት መሆኑንም ይገልፃሉ። ከዚህ መካከል በማህበራዊና የባህል ሥርዓታቸው ውስጥ የሚታወቁበት በእንግዳ አቀባበላቸው መሆኑን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ የቤኒሻንጉል ብሄረሰብ እንግዳን የሚወድ፣ የሚያከብር እንግዳው ከየትም ይምጣ ሁሉም ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ዙምባራ
ክልሉ በታዋቂው የትንፋሽ መሣሪያ ዙምባራ የታወቃል። ለአንድ ወር በቆየው የሳይንስ ሙዚየም አውደ ርዕይም ላይ ይህ የሙዚቃ መሣሪያ ለእይታ ቀርቦ የብዙሃንን ቀልብ መሳብ ችሎ ነበር። በቤኒሻንጉል ብሔረሰብ ውስጥ በዋናነት የትንፋሽና የምት የሙዚቃ መሣሪያ የሚጨፈረው በደስታና በጥጋብ ወቅት እንደሆነ አቶ ሸመልስ አድሬ ይናገራሉ፡፡ መሣሪያዎቹ በተለያየ መጠን የተሠሩ ቁጥራቸው አስራ ሁለት ነው፡፡ የሙዚቃ መሣሪያው ዜማ የሚኖረውና ትርጉም የሚሰጠው አስራ ሁለት የመዝሙሩ ቡድን አባላት ሲሟሉለት ብቻ ነው፡፡ ሲጨፈር ፆታና እድሜ አይገደብም፡፡
ሌላው ከብሄረሰቡ ልዩ ተኩረት የሚስበውና ለእይታ ማራኪ የሆነው የቤት አሠራር ሥርዓት እንደሆነ ይናገራል። በቤት አሠራር መሰረት በቤኒሻንጉል አብዛኛዎቹ ሁለት ጎጆዎችን ይሠራሉ፡፡ ጎጆዎቹም አልሀልዋና ሹልጽጺዎ ይሏቸዋል፡፡ ሽንጺጺዎ የሴቶች መዋያና ዋና መኖሪያ ቤት ሲሆን ሴቶች ምግብን የሚያበስሉትም በዚሁ ቤት ውስጥ መሆኑን ዳይሬክተሩ ይገልፃሉ፡፡
ከቤት አሠራር ሥርዓቱ ባሻገርም በክልሉ የሚገኝ ጎብኚ በማህበራዊ ህብረቶችና አደረጃጀቶች ተማርኮና ትምህርት ወስዶ ይመለሳል። በደስታም ሆነ በኀዘን በእርሻም ሆነ በቤት ሥራ በአንድ ሰው ጉልበት ሊሠራ የማይቻለውን ወይም አንድ ሰው ብቻውን ሊሠራው የማይችለውን ለማከናወን ባህላዊና ማህበራዊ ህብረቶች እንዳላቸው አቶ ሽመልስ አድሬ ይናገራሉ፡፡ የመረዳዳት ሥርዓቱም ሌላ ትኩረት የሚስብ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ አታምባ ወይም እቁብ በመባል እንደሚጠራ ይገልፃሉ፡፡ ብሔረሰቡ ውስጥ የሚተማመኑ ሰዎች ያለምንም የውል ሰነድ በቃል ብቻ ገንዘብን አዋጥተው የሚረዳዱበት ዘዴ እንደሆነ ነው የሚናገሩት፡፡
አቶ ሽመልስ አድሬ ስለ ቤኒሻንጉል ብሄረሰብ የአመጋገብ ሥርዓትም ያነሳሉ። እርሳቸው እንደሚሉት ቤኒሻንጉሎች የአመጋገብ ሥርዓታቸው በአብዛኛውን ተመሳሳይ ሲሆን ተወዳጅ ምግባቸው ገንፎ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ እንደዚሁም በቱርኮች እንደመጣ የሚነገረው “ቄንቄስ” /ባሚያና ዌካ/ በእንግሊዞች አጠራር ኦክራ የሚባለው ለወጥ መሥሪያነት የሚያገለግል የአትክልት ዘር በብሔረሰቡ ዘንድ ከሁሉ የበለጠ ተወዳጅ ባህላዊ ምግብ መሆኑን ያነሳሉ፡፡ ቄንቄስ የሚሠራው ከስጋ፣ ከዓሳ፣ ከሽሮ ጋር ወይንም ብቻውን ተዘጋጅቶ ከገንፎ ጋር ወይንም በእንጀራ እንደሚበላ ያስረዳሉ፡፡ ሳይበላሽ ለረዥም ጊዜ (እስከ ሶስት ዓመት) መቆየት እንደሚችል የሚያስረዱት ዳይሬክተሩ ጎብኚዎች በክልሉ በሚያደርጉት ቆይታ ከሚያገኟቸው ጣፋጭ ምግቦች መካከል አንዱ እንደሚሆንም ያነሳሉ፡፡
ብሄረሰቦችና የቱሪዝም ሀብቶች
የባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተሩ አቶ ሽመልስ አድሬ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በርካታ መስህቦች እንዳሉት ይናገራሉ። ከእነዚህ ውስጥ በክልሉ በነባር ነዋሪነት የሚታወቁት ብሄረሰቦች ታሪካዊ፣ ባህላዊ እሴቶች እንደሆኑ ይናገራሉ። በምሳሌነትም የጉሙዝ ብሄረሰብ የባህል እሴቶችን ይጠቅሳሉ።
ብሄረሰቡ በጋራ የመኖር ፣ በጋራ የመሥራት ፣ በጋራ የመብላትና በጋራ የመጠጣት አኩሪና አስደሳች ማኅበራዊ ሕይወትን የታደለ መሆኑን የሚያነሳው አቶ ሽመልስ አድሬ አስደማሚ ባህል ፣ ማራኪ ታሪክና መንፈሳዊና ባህላዊ ቁሳዊ ቅርሶች እንዳሉት ያስረዳሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ዴሞክራሲያዊ የምርጫና አስተዳደር ሥርዓት እንደ ቱባ እሴትነት ያነሳሉ። ቆሚያ (ባህላዊ የትንፋሽ የሙዚቃ መሣሪያ) ከተመረጡ የዛፍ አይነቶች የሚሠራና ልዩ ዝግጅቶች ላይ የሚጠቀሙት እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡
ሌላው ኤፂፃ የሚባልና (በሴቶች እግር ላይ የሚታሰርና ለዘፈን ማድመቂያነት የሚያገለግል ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያ) እንዳለ ይናገራሉ። ሴቶቹ እግራቸውን በማንሳት በለመዱት ስልት ደጋግመው መሬቱን ሲመቱ እርስ በእርሱ እየተጋጨ ማራኪ ድምጽ የሚያወጣና የተወዳጅ ባህላዊ ሀብት መሆኑን ይናገራሉ። በሌላ በኩል ሲያያ የሚል ስያሜ ያለውና (የቤት ውስጥና ውጪ መገልገያ እቃ አይነት) መኖሩን ገልጸው ሴቶች በግራና በቀኝ ትከሻቸው ወይም አንዱ ላይ በማሳረፍ እንደ ሚዛን የሚጠቀሙበት ከገመድና ከእንጨት የሚዘጋጅ የዕቃ መሸከሚያ ነው) መሆኑን ያነሳል። በብሄረሰቡ የቱሪስቶችን ቀልብ የሚስብ ሀብቶችና እሴቶች መኖራቸውን አንስቶ ክልሉ የእነዚህ ሁሉ መገኛ እንደሆነ ያስተዋውቃል።
አቶ ሽመለስ በክልዩ የሺናሻ፣ የማኦ፣ የኮሞና ሌሎች ብሄረሰቦች ቱባ እሴት፣ ባህላዊ ሀብት እንዲሁም ለረጅም ዘመናት የቆየ አብሮ የመኖር ታሪክ የያዙ ብሄረሰቦች መገኛ እንደሆነ ይገልፃል። የአመጋገብ፣ የኀዘን፣ የደስታ ጊዜ ሥርዓት እሴቶች በስፋት በብሄረሰቦቹ እንደሚገኝ ይገልፃል። ባህላዊ ጭፈራዎች፣ ዘፈኖች፣ ጌጣጌጦችና አልባሳት ውብ መልከዓ ምድርና ሌሎች ታሪኮች መገኛ ክልል ነው። በተፈጥሮ ስብጥር፣ በሥነ ምህዳርና በሀገር በቀል ጥንታዊ እፅዋት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልና በውስጡ የሚኖሩ ብሄረሰቦች መገለጫ መሆኑን የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተሩ ይናገራሉ።
ጉባ- የውሃ ቱሪዝም የዓባይ ግድብ
በውሃ ቱሪዝሙ ላይ ሌላው የኢትዮጵያን የመዳረሻ ተመራጭነት ያሰፋል ተብሎ የሚጠበቀው የግዙፉ የሃይል ማመንጫ የሆነው የታላቁ የዓባይ ግድብ ነው። ይህ ግድብ መገኛው ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በጉባ ወረዳ ነው። ግድቡ የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦትና ሽፋን ከማሳደጉም ባሻገር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንደሚኖረው ከወዲሁ ተገምቷል። ከዚህ ውስጥ አንዱ ደግሞ ግድቡ ሲጠናቀቅ በሚፈጥረው ሰው ሠራሽ ሃይቅ ደሴቶች እንዲሁም ሌሎች የመዝናኛ ሥፍራዎች አማካኝነት “የውሃ ቱሪዝም” ፕሮጀክት እንደሚኖር ነው። አቶ ሽመልስም ይህንኑ ያጠናክራሉ።
የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተሩ አቶ ሽመልስ ታላቅ ራዕይ በተሰነቀበትና የኢትዮጵያ የጀርባ አጥንት እንደሚሆን የሚጠበቅው የዓባይ ግድብ የሚገኘው በክልሉ መሆኑን ያስረዳሉ። የጉባን ተራራ ተንተርሶ በሰፊው በሚንጣለለው ሰው ሰራሽ ሃይቅ ከ70 በላይ ደሴቶችን ፈጥሮ የጎብኚዎች መዝናኛና መናፈሻ እንደሚሆኑ ያስረዳሉ። ይህ እውን ሲሆን ለክልሉ የቱሪዝም መዳረሻነት ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ይገልፃሉ። ግድቡ ሰው ሰራሽ ሃይቅ የዓሳ ሀብት በማምረት መጠቀምና የቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራ የማድረግ እንቅስቃሴ እንዳለም ይገልፃሉ።
እንደ ማጠቃለያ
የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተሩ አቶ ሽመልስ አንድሬ እንደሚሉት ለአንድ ወር በቆየው የሳይንስ ሙዚየም የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ሀገር አቀፍ አውደ ርዕይ ከላይ የተዘረዘሩትን ሀብቶች ለበርካታ ሺህ ጎብኚዎች ማስተዋወቅ ተችሏል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በባህል፣ በታሪክ፣ በተፈጥ ያሉትን የቱሪዝም መስህቦች ተደራሽ የማድረግ እድል የከፈተ አውደ ርዕይ ነበር።
በሳይንስ ሙዚየም የነበረው መድረክ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የቱሪዝም ሀብቶችን ከማስተዋወቅ ባሻገር ከአቻ ክልሎችና ከልዩ ልዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከመጡ ተቋማት ጋር እንዲተዋወቁና ልምድ እንዲለዋወጡ እንደረዳቸውም ዳይሬክተሩ ይናገራሉ። መሰል መድረኮችም ቀጥለው የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ቱሪስቶች የኢትዮጵያን ሀብቶች እንዲያውቁ ቢደረግ የሚፈለገው ለውጥ እንደሚመጣ ይገልፃሉ። በአካል ከመቶ ሺህ ዎች በላይ ተገኝተው በጎበኙበት ወቅት ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመሄድ ጉብኝት ለማድረግ ቃል የገቡ መኖራቸውንም ገልጸውልናል።
የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሀብቶች፣ አዳዲስ መዳረሻዎች እና የዘርፉን ጅምር ሥራዎች በኤግዚቢሽን እና ፎረሞች የማስተዋወቅ ሥራ ከቅርብ ጊዜ ውስጥ እያደገ መምጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ። በተየለይ ትላልቅ ኤግዚብሽኖችን በመክፈት በዲጂታል አማራጭ ተደራሽ ማድረግም እየተለመደ መጥቷል። ለምሳሌ የቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን እና ሌሎች በግል የሚሰሩ “ማይስ ኢትዮጵያን” የመሰሉ መድረኮች የሀገሪቱን ሀብቶች ከመጠበቅና ከማልማት ባሻገር አስተዋውቆ ጎብኚዎችን ለመሳብ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዙ ናቸው። ከዚህ አኳያ ጅምር እመርታዎች እየታዩ ሲሆን የኢትዮጵያ ቱሪዝም እድገት እስኪረጋገጥና ኢትዮጵያም የዓለም ተመራጭ መዳረሻዎች መካከል ቀዳሚ እስክትሆን መቀጠል ይኖርበታል።
ከመስከረም 29 እስከ ጥቅምት 28/2016 ዓ.ም በቆየው የሳይንስ ሙዚየም የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ አውደ ርዕይ ላይ በርካታ ተሳታፊዎች ቀርበው ነበር። በቆይታውም በአካል 170 ሺህ የሚጠጉ በዲጂታል አማራጭ ደግሞ ዘጠኝ ሚሊዮን አካባቢ የሚደርሱ ጎብኚዎች እንደጎበኙ መረጃዎች አመልክተዋል። በአውደ ርዕይው ተሳታፊ ከሆኑ ተጋባዦች መካክል የሁሉም ክልሎች ባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች ይገኙበታል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ህዳር 23/2016