ከአምናው… የመማር አብነት፤

 በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)

የዓምናው አደገኛ ቀውስ እንዳይደገም የማዳበሪያ ግዥው በጊዜ እየተከናወነ መሆኑ ይበል የሚያሰኝ ነው። ሌሎች ተቋማትም እንዲህ ካለፈው ፈተናቸው ትምህርት ቢወስዱ ሀገር አሳሯን ባልበላች። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ማዳበሪያም ሆነ ሌላው የግብርና ቴክኖሎጂ በጊዜው ለሚገባው እንዲቀርብ ማድረግ ሥራው ቢሆንም በልኩ አበጀህ። ደግ አደረግህ ሊባል ይገባል። እንደ ሀገር እየተቸገርን ያለነው የዓምና የካች ዓምና ስህተት ላይ እንደ ዝሀ ዘጊ እየተመላለስን ነውና። እንደ ዜጋ “ድሮ ቀረ” የቁጭታችን አዝማች የሆነው ለዚህ ሳይሆን ይቀራል።

ገበሬው ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ተጠቀም፣ አልጠቀምም ከሚለው ውዝግብ ወጥቶ ተጠቃሚ ሲሆን ደግሞ በወቅቱ በሚፈልገው መጠን ማቅረብ ፈተና ሆነ። ባለፈው ዘግይቶ በመግባቱና ዕጥረት በመከሰቱ ገበሬው ጅራፉን እየገረፈ ሰልፍ ለመውጣት ከመገደዱ ባሻገር ፖለቲካዊ አጀንዳ እስከመሆን ደርሶ ነበር። ለኮንትሮባንድ ንግድ መዳረጉም አይዘነጋም። በዚህ የተነሳ ቁጥሩ ቀላል ያልሆነ ገበሬም ያለማዳበሪያ ለመዝራት ተገደደ። ይህም በዘንድሮው ምርት ላይ ቅናሽ ማሳየቱ አይቀርም።

በእንቅርት ላይ ቆረቆር እንዲሉ በዚህ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት እንዲሁም በአቅርቦትና በፍላጎት መካከል ያለው ሰፊ ልዩነት ሳይጠብ ማዳበሪያ በበቂ ሁኔታና በወቅቱ ባለመቅረቡ ሰው ሰራሽ የምርት ዕጥረት ይከሰታል። ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ግን የተፈጥሮ ማዳበሪያ ላይ በስፋት ቢሠራና እንደ ሀገርም ኢኮኖሚዋ ግብርና ላይ የተመሠረተ ስለሆነ የማዳበሪያ ፋብሪካ የመገንባት ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት ቢሰጠው ከዚህ አዙሪት በዘላቂነት ሰብሮ መውጣት ይቻላል።

ለ2016/17 ዓም የምርት ዘመን እስካሁን ከ14 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ግዥ መፈጸሙ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የማዳበሪያ ዋጋ ጭማሪ ቢኖርም የአርሶና ከፊል አርብቶ አደሮችን አቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት መንግሥት በየዓመቱ ከፍተኛ ድጎማ እያደረገ መሆኑን፤ በዚህም ባለፉት ሶስት ተከታታይ ዓመታት ብቻ የ52 ቢሊዮን ብር ድጎማ ማድረጉን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶክተር) ዋቢ አድርጎ የኢትዮጵያ ፕሬስ ኤጀንሲ ዘግቧል።

መንግሥት ገበያን ለማረጋጋት ከፍተኛ ድጎማ እያደረገ ይገኛል። በ2014/ 15 ምርት ዘመን 15 ቢሊዮን ብር፤ በ2015/16 ምርት ዘመን 21 ቢሊዮን ብር እንዲሁም በ2016/17 ምርት ዘመን 16 ቢሊዮን ብር፤ በድምሩ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት የ52 ቢሊዮን ብር ድጎማ አድርጓል። መንግሥት ይሄን ያህል ግዙፍ የሀገር ሀብት አውጥቶ የሚደጉመው ማዳበሪያ በትክክል ለገበሬው እንዲደርስ ስርጭቱ የዓምናውን አይነት ሳንካ እንዳይገጥመው ከሕገ ወጥ ነጋዴዎችና ከሌቦች መጠበቅ አለበት።

ይሄን ያህል ድጎማ ተደርጎለት የሚመረት ምርት ለሸማቹ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲደርስ የግብይት ሥርዓቱን ማስተካከልም ይገባል። ካለበለዚያ ድጎማው ትርጉም ያጣል። ለአምራቹም ለሸማቹም ሳይሆን የስግብግብ ነጋዴና የደላላ ሲሳይ ሆኖ ይቀራል። እየሆነ ያለውም ይህ ነው። ምርቱ ለገበያ ሲውል የተደጎመውን ያህል ቅናሽ የማይኖረው ወይም ተመጣጣኝ የማይሆን ከሆን ትርጉም ያጣል።

12016/17 ምርት ዘመን የሚውል 19 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እንደሚገዛ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ እስካሁን የ 14 ነጥብ 79 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ መፈጸሙን፤ ከ19 ነጥብ አራት ሚሊዮን ኩንታል ውስጥ ስምንት ነጥብ ሁለት ኩንታል የዩሪያ አፈር ማዳበሪያ መሆኑንና ቀሪው 11 ነጥብ 19 ሚሊዮን ኩንታል ኤን. ፒ. ኤስ መሆኑን ጠቅሰዋል። ይህ ባለፈው ዓመት ከተገዛው 12 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል አንጻር ከፍተኛ ጭማሪ እንዳለውም አስታውቀዋል።

ባለፈው ዓመት የመጀመሪያዋ መርከብ ታህሳስ 18/2015 ዓ.ም መድረሷን ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ በዚህ ዓመት 51 ሺህ 420 ሜትሪክ ቶን ዩሪያ የጫነች የመጀመሪያዋ መርከብ ጥቅምት ወር ላይ ጅቡቲ ወደብ ላይ መድረሷንና ይህም በማዳበሪያ አቅርቦት ታሪከ የመጀመሪያው እንደሆነ፤ ለ2016/17 የምርት ዘመን እስከ ህዳር 19 ቀን 2016 ዓ.ም 207 ሺህ 295 ሜትሪክ ቶን የዩሪያ ማዳበሪያ ጅቡቲ ወደብ መድረሱንና ከዚህ ውስጥም 104 ሺህ 304 ሜትሪክ ቶን ዩሪያ ወደ ሀገር ውስጥ መጓጓዙን ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ከህዳር 21 እስከ ታህሳስ 4 ቀን 2016 ዓ.ም 174 ሺህ 500 ሜትሪክ ቶን ኤን.ፒ.ኤስ ቦሮን የጫኑ ሶስት መርከቦች ወደ ጅቡቲ እንደሚደርሱ፤ ቀድሞ የነበረውን የግዢ መመሪያ መቀየር፤ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ቦርድ በአዲስ መልክ እንዲደራጅ

ማድረግ እና የቴክኒክ ኮሚቴ እንዲቋቋም ማድረግ፣ የተለያዩ የግዢ አማራጮችን በመጠቀም ግዥ ማከናወንን ጨምሮ በርካታ ተግባራት በሚኒስቴሩ እንደተፈጸሙም አስታውቀዋል።

በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም ሆነ በሌላ አካል ተፈጥሮ የነበረን ስህተት ዘንድሮ እንዳይደገም የተሄደበት ርቀት ይበል የሚያሰኝ ነው። ይህ ከስህተትና ከድክመት የመማር ቁርጠኝነት ለሌሎች ተቋማት በአርዓያነት ሊወሰድ ይችላል። የዘንድሮውን የማዳበሪያ ስርጭት ከሕገ ወጦች ለመከላከል የዓምናውን ክፍተት ለይቶ መፍትሔ ማስቀመጥ ግድ ይላል። የዓምናውን መለስ ብሎ ማስታወስ ያሻል።

ሕገ ወጥ የግብይት ሥርዓቱ ሲድህ ሲድህ በማንደራደርበት በሀገራችን የዓይን ብሌን ማዳበሪያ ላይ ደርሷል። የህልውናችን መሠረት ፣ የግብርናችን የጀርባ አጥንት የሆነው ማዳበሪያ ላይ እጁን አስገብቷል። መቼም አይደፈርም። አይነካም። አይሞከርም። ብለን በምንተማመነው የማዳበሪያ ግብይትና ስርጭት እጁን ማስገባት ከቻለ ነገ ተቋሞቻችንና መዋቅሮቻችንን እንደማይቆጣጠር ምን ዋስትና አለን።

ከጨረታ ፣ ከግዥ ፣ ከማጓጓዝ እስከ ስርጭት በየደረጃው ባለ የመንግሥት መዋቅር ይሳለጣል ብለን በምናምነው የማዳበሪያ ግብይት ካች ዓምና እና ከዚያ በፊት ጥቂት ሕገ ወጦች አልፎ አልፎ የታዩበት ባለፈው ዓመት ግን እልፍ አእላፍ ሆነው ሲራኮቱበት ታዝበናል።

ስድ የተለቀቀው ሕገ ወጥ የግብይት ሥርዓት ከሕዝባችን 85 በመቶ የሚሆነው ዜጋችን ኑሮውን በመሠረተበት ፤ ለሀገሪቱ ጥቅል ብሔራዊ ምርት ድርሻው 47 በመቶ በሆነው ግብርና አንገት ላይ ሸምቀቆውን እያስገባ ነው ። በጊዜ አደብ እንዲገዛ ካልተደረገ በመሠረታው የፍጆታ ሸቀጣ ሸቀጦች ላይ እንዳደረገው ሸምቀቆውን ስቦ ያንቀዋል። ይህን አደረገ ማለት በ126 ሚሊዮን ሕዝብ እና በሀገር ጉሮሮ ላይ ቆመ ማለት ነው።

በተለይ ከአለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ወዲህ ያለአፈር ማዳበሪያ ግብርና የሚታሰብ አይደለም። መሬቱ ማዳበሪያ ለምዷል። ገበሬው መሬቱ ባልጓል። ያለማዳበሪያ በጀ አይልም ይለዋል። ይህን የተረዱ የሕገ ወጥ ግብይቱ ተዋናዮች ገበሬው መሬቱ ጦም ከሚያድር የተጠየቀውን እንደሚከፍል እርግጠኛ ስለሆኑ በግብይት ሰንሰለቱ ሰርገው በመግባት ከሙሰኛ አመራር ፣ የልማት ጣቢያ ሠራተኛና ሥነ ምግባር ከጎደላቸው ከሕብረት ሥራ ማህበራት አመራሮች ጋር በመመሳጠር ፤ እንዲሁም ዓምና የተፈጠረውን የአቅርቦት መዘግየትና መስተጓጎል እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም መንግሥት በከፍተኛ ድጎማ ለገበሬውን ያቀረበውን ማዳበሪያ በሁለትና በሶስት እጥፍ እስከ መቸብቸብ ደርሰዋል ።

ያለው ውስን ማዳበሪያ በወቅቱ እንዳይከፋፈል በማድረግና ሰው ሰራሽ እጥረት በመ ፍጠር ቀውስ ፈጥረዋል። ሕገ ወጥ የግብይት ሥርዓቱ መንግሥት በወቅቱ ማዳበሪያን ካለማቅረቡ ጋር አብሮ የማዳበሪያ እጥረቱ ተባብሶ በሀገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ገበሬውን ሰልፍ እስከማስወጣት ደርሷል። ለሴራ ትንተና በር ከመክፈቱ ባሻገር ወደ መልካም አስተዳደር ችግርነት ተሸጋግሯል። ሕገ ወጥ የግብይት ሥርዓቱ ሀገሪቱ በሌላት የውጭ ምንዛሬ አቅም ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጭ አድርጋ የገዛችውን ማዳበሪያ እንደ ዘይቱና ሲሚንቶው ለመቆጣጠር ዕንቅስቃሴ መጀመሩን ታዝበናል።

ባለፈው ዓመት ምንድን ነው የሆነው፤ ዘንድሮም እንዳይደገም መለስ ብለን እንቃኝ። በኦሮሚያ ክልል ከ2 ሺህ 300 ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ በሕገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር መያዙን የክልሉ ሕብረት ሥራ ኤጀንሲ ማስታወቁን ፤ የኤጀንሲው ምክትል ሃላፊ መስፍን ረጋሳ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት ፤ ሕገ-ወጦች በክልሉ የተፈጠረውን የማዳበሪያ እጥረት ባልተገባ መልኩ ለመጠቀም ተንቀሳቅሰዋል።

በዚህም ከ ሁለት ሺህ 330 ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ መያዙን ጠቁመው ፤ በድርጊቱ የተሳተፉ 30 ግለሰቦች በሕግ እንዲጠየቁ መደረጉን ፤ በክልሉ በዘርፉ የሚፈፀመው ሕገ -ወጥነት የአፈር ማዳበሪያ እጥረት ያስከተለ ሲሆን ፤ አርሶ አደሮችም ማዳበሪያ በኩንታል እስከ 11 ሺህ ብር ለመግዛት መገደዳቸውን አብራርተዋል:: በክልሉ የሚገኙ አርሶ አደሮች በበኩላቸው ፤ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ሕገወጦች በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑን ጠቅሰው ፤ ከችግሩ ስፋት አንፃር አሁንም ያልተደረሰባቸው መኖራቸውን ፤ የምዕራብ ሸዋ ዞን ም/አስተዳዳሪ ተካልኝ ይማሙ በበኩላቸው የዞኑ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ጭምር በሕገ-ወጥ ተግባር ላይ ተሠማርተው በመገኘታቸው ርምጃ መውሰዱን አረጋግጠዋል ።

በአማራ ክልል እንዲሁ 400 ኩንታል ማዳበሪያ በሕገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወርና ሲሸጥ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ዋልታ የዘገበ ሲሆን እንደሁም በተመሳሳይ ሁኔታ በሲዳማና በሌሎች አካባቢዎችም ባልተለመደ ሁኔታ ሕገ ወጥ የማዳበሪያ ዝውውሩ ተባብሶ መስተዋሉ ዜጎችን እያሳሰበና ስጋት ላይ እየጣለ ይገኛል። አልቀመስ ባለው ፣ ሸማቹን ባማረረውና ኑሮውን ባመሰቃቀለው የኑሮ ውድነት ላይ ሌላ ቤንዚን እንዳያርከፈክፍ፤የኑሮ ውድነቱና የዋጋ ግሽበቱ አሁን ካለበት የከፋ እንዳያደርገው ብዙዎችን እያስጨነቀ ይገኛል።

ከዓመት ዓመት ክንዱ እየፈረጠመ የመጣው ሕገ ወጥ የግብይት ሥርዓት ነገ የህልውናችንና የሰላማችን ስጋት መሆኑ አይቀርምና መንግሥት ነገ ዛሬ ሳይል ሥርዓት ሊያሲዘው እና በግብይት ሥርዓቱ የሕግ የበላይነትትን ሊያረጋግጥ ይገባል። መንግሥት መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶችን ፣ ነዳጅንና ማዳበሪያን በብዙ ቢሊዮኖች እየደጎመ በሌለ የውጭ ምንዛሬው ቅድሚያ ሰጥቶ እያስገባ ሕገ ወጥ የግብይት ሥርዓቱ ግን አመድ አፋሽ እያደረገው እና ከሕዝብ ጋር እያቃቃረው ስለሆነ አበው ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ መንግሥት ከዳተኝነት አባዜ ወጥቶ ሕገ ወጥ የግብይት ሥርዓቱን በፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ታግዞ ሊያስተከክለው ይገባል ።

የግብይት ሥርዓታችን ጤናማ ቢሆን ኑሮ የዋጋ ግሽበቱም ሆነ የኑሮ ውድነቱ እዚህ ደረጃ ባልደረሰ። የሀገራችንን የዋጋ ግሽበት የተለየ የሚያደርገውም እሴት በማይጨምሩ ሕገ ወጦች የታነቀ መሆኑ ነው። ይህ ማለት ግን የፍላጎትና የአቅርቦት አለመጣጣም ፤ ዓለምአቀፉ የዋጋ ግሽበትና የዩክሬን በራሽያ መወረር ለዋጋ ግሽበቱም ሆነ እሱን ተከትሎ ለመጣው የኑሮ ውድነት አስተዋጽኦ የለውም ማለት አይደለም። ዝቅ ብዬ ዋቢ ያደረግሁት አስደንጋጭ ጥናት እንደሚያትተው ደላላው ወይም የሕገ ወጥ ግብይቱ ተዋናይ በሀገራችን ለሚስተዋለው የዋጋ ግሽበት 60 በመቶ ድርሻ አለው ። መንግሥት ይሄን አጉራ ዘለል የግብይት ሥርዓት ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ ሳይባባስ አደብ ቢያስገዛ የዋጋ ንረቱን 60 በመቶ የመቀነስ ዕድል አለው ማለት ነው።

የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ባለፈው ዓመት አንድ አስደንጋጭ የጥናት ውጤት ይፋ አድርጓል። ኢትዮጵያ ምግብ ውድ ከሆነባቸው የአፍሪካ ሀገራት ከቀዳሚዎቹ ተርታ መሰለፏንና ከዓለም 8ተኛ ደረጃ ፤ ከዚምባቡዌ ቀጥላ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ያለባት ሀገር እንደሆነች አርድቶናል። አጠቃላይ የዋጋ ግሽበቱ 49.1 በመቶ ሲሆን የምግብ የዋጋ ንረት ከፍተኛውን ድርሻ ይዟል:: ይህም ከክልል ክልል የተለያየ ሲሆን በአማራና ደቡብ ክልል ያለው የዋጋ ግሽበት ከሀገራዊ ምጣኔው ከፍ ያለ ነው::

ከተቀረው ዓለም የሀገራችንን የኑሮ ውድነት ለየት የሚያደርገው ማለትም ከፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን ባሻገር እሴት የማይጨምሩ ደላሎች በገበያ ሰንሰለቱ ከማሳ እስከ ገበያ መሰግሰጋቸው ፤ መንግስትም ተገቢውን ቁጥጥርና የእርምት ርምጃ አለመውሰድ የዋጋ ንረቱን አባብሶታል ይላል ጥናቱ:: በዚህም ምክንያት ምርት አምራቹ ከሚሸጥበት 58 በመቶ ዋጋው ከፍ ብሎ ሸማቹ ጋር እንዲደርስ አድርጓል::

ይህ ማለት ዛሬ በሀገራችን ከሚስተዋለው የዋጋ ግሽበት 60 በመቶ ያህሉ የተከሰተው በደላሎች አማካኝነት መሆኑን ጥናቱ ያመላክታል። በሕግና በሥርዓት ሊስተካከል በሚችል የግብይት ሰንሰለት ሸማቹ ምን ያህል ፍዳውን እያየ መሆኑንም ቁልጭ አርጎ አሳይቶናል። የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከስንት ውትወታ በኋላ ሕገ ወጥ ደላላን ከግብይት ሰንሰለቱ የሚያስወጣ መመሪያ አዘጋጀሁ ቢለንም ሥራ ላይ ባለመዋሉ የሀገሪቱ የግብይት ሰንሰለት የደላላ መፈንጫ እንደሆነ ቀጥሏል።

በኢትዮጵያ በሕገ-ወጥ መንገድ በሚካሄደው የግብይት ሥርዓት ሀገሪቱ በየዓመቱ አስከ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር የሚደርስ ገቢ እያጣች መሆኑን ፤ በዓለም ታዋቂ ከሆነው የምጣኔ ሀብታዊ መፅሄት “ዘ-ኢኮኖሚስት” ጋር በመተባበር በተዘጋጀውና በአህጉራዊ የንግድ እንቅስቃሴ ችግሮች ፣ መንስኤዎቻቸውና መፍተሄዎቹ ዙሪያ በመከረ ጉባዔ ላይ መመልከቱ የችግሩን አሳሳቢነት ያረጋግጣል። በኢትዮጵያ ከሚካሄደው አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ግብይት ሥርዓት ውስጥ 40 በመቶ ያህሉ በሕገ-ወጥ መንገድ በሚገቡ ምርቶች የተያዘ ነው።

በዚህም ሀገሪቱ ከግብይቱ ሥርዓቱ ማግኘት የነበረባትን ዘጠኝ ቢሊዮን ብር በየዓመቱ ታጣለች ። ይህ ገቢ ለ72 ሺ ዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር ሀገራዊ ኢኮኖሚውን በከፍተኛ መጠን ያግዝ ነበር ተብሏል። እንደ ኢዜአ ዘገባ 45 በመቶ የትንባሆ ምርቶች ፣ 48 በመቶ የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች እንዲሁም 30 በመቶ መድሃኒት በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ በመግባት ገበያውን የሚያውኩት ቀዳሚ ሸቀጦች ናቸው። በዚሁ ሕገ ወጥ የግብይት ሥርዓት አማካኝነት ወደ ሀገር የሚገቡ ጊዜ ያለፈባቸው መድሃኒቶችም የህብረተሰቡን ጤና ስጋት ላይ የሚጥሉ መሆናቸውንም ጥናቱ አመልክቷል።

ሻሎም !

አሜን ።

አዲስ ዘመን ኅዳር 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You