
አዲስ አበባ፡- የፌዴራል ሥርዓቱ ለሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች እውቅና በመስጠት ሁሉም ዜጋ የባህል፣ የቋንቋ እንዲሁም የማንነት መገለጫዎቹን እንዲያዳብር እያደረገ መሆኑን የሕገ መንግሥትና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ገለጹ፡፡
ኃይለየሱስ ታዬ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ለብሔር ብሔረሰበቦች እኩል መብት ተሰጥቶ በጋራ ቀኑን ማክበር መቻል በራሱ የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ያስገኘው ትሩፋት አንዱ መሆኑን መገንዘብ ይገባል።
ለሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች እውቅና በመስጠት እኩል መብት መሰጠቱ የባህል፣ የቋንቋ እንዲሁም የማንነት መገለጫዎች እንዲዳብሩ አስችሏል ያሉት ዶክተር ኃይለየሱስ፤ በዓሉ በየዓመቱ መከበሩ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚና ኢንቨስትመንት መነቃቃት እንዲሁም ለቱሪዝም ዘርፍ ማደግ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
ህብረ-ብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓት ብዝሃ ማንነት መገለጫቸው ለሆኑ ሀገራት የተሻለ አማራጭ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ፌዴራሊዝም የሕዝቦችን እኩልነት፣ አንድነትና ትስስር በማጠናከርና የሕዝቡን ዴሞክራሲያዊና ንቃተ ሕገ-መንግሥት በማሳደግ ጠንካራ ሀገር የመገንባት ሚና እንዳለው አመልክተዋል፡፡
በሀገራችንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአተገባበር ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን በማስተካከል ብሔር ብሔረሰቦች በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻሉን አብራርተዋል፡፡
በዓሉ በየዓመቱ መከበሩ በብዝሃነት ውስጥ አንድነት እንዲጠናከር እንዲሁም በብዝሃነት ውስጥ ያለው አንድነት
ምንያህል ጠቀሜታ እንዳለው መገንዘብ የሚቻልበት መሆኑን ዶክተር ኃይለየሱስ ጠቁመዋል፡፡
ዘንድሮ ለ18ኛ ጊዜ ለሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ሰፊ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመው፤ በዓሉ በሰላም እንዲከበርና የበዓሉ ዓላማ እንዲሁም የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር ለተለያዩ አካላት ስልጠናዎች ሲሰጡ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
የፌዴራሊዝም ሥርዓት የብሔር ብሔረሰቦች የማንነት መገለጫ፣የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፍላጎት ለማስተናገድ ከፍተኛ ድርሻ አለው ያሉት ዶክተር ኃይለየሱስ፤ የፌዴራሊዝም አስተምህሮቱ ለብሔር ብሔረሰቦች እኩል መብት የሰጠ ቢሆንም በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ ካልተቻለ የራሱ የሆነ ጉዳት እንዳለው ተናግረዋል፡፡
የፌዴራል ሥርዓቱን በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ ግጭቶች የፌዴራል ሥርዓት አድርጎ የሚነሳው ነገር ተገቢ አለመሆኑን ገልጸው፤ ይልቁንም የሀገሪቱ የፌዴራሊዝም ሥርዓት ለማንነቶች፣ ብዝሃነት እውቅና በመስጠት በብዝሃነት ውስጥ የሚተገበር ህብረ-ብሔራዊ ፌዴራል ሥርዓት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በቀጣይ በህብረ ብሔራዊ ፌዴራል ሥርዓት ዙሪያ የተስተካከለ አመለካከት በመያዝ፣ የብሔር ማንነትና ሀገራዊ ማንነቶች አስተሳስሮ በመሄድና ብዝሃነት በአግባቡ በማስተናገድ የፌዴራል ሥርዓቱ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ለማስቻል መሠራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
የዘንድሮ 18ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ “ብዝሃነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሃሳብ በመጪው ኅዳር 29 ቀን 2016ዓ.ም ይከበራል፡፡
ልጅዓለም ፍቅሬ
አዲስ ዘመን ኅዳር 23 ቀን 2016 ዓ.ም