በርካታ ሀገራት በከርሰ ምድር ውስጥ ያለውን ማዕድን በአግባቡ አውቀው፣ ለይተውና አልምተው መጠቀም በመቻላቸው ማደግና መበልጸግ እንደቻሉ መረጃዎች ያሳያሉ። ይህ ዕውነታ በኢትዮጵያም ተመሳሳይ መሆኑ ዕሙን ነው። ኢትዮጵያ ለኢኮኖሚ እድገት የማይተካ ሚና ያለውን የማዕድን ሀብት በአግባቡ ለማወቅና አልምቶ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችላትን ጉዞ ከጀመረች ሰነባብታለች። በተለይም ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ መንግሥት ለሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ትኩረት ከሰጠባቸው አምስት ዘርፎች መካከል አንዱ ማዕድን ነው። በመሆኑም ሀብቱ ያለበትን አካባቢ የመለየትና የማጥናት ሥራ ሲሰራ ቆይቶ በአሁን ወቅትም ማዕድን የማልማት ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ኢትዮጵያ ያላትን የማዕድን ሀብት ለመለየትና ለማልማት በምታደርገው ጥረት ከውጭ ሀገራት የሚገቡ ማዕድናትን በሀገር ውስጥ መተካትና የተለያዩ ማዕድናትን ወደ ተለያዩ ሀገራት በመላክ ለሀገሪቷ የውጭ ምንዛሪን ማምጣት ተችሏል። ሀገሪቷ ያላትን የማዕድን ሀብት አጥንተው መለየት የቻሉና አልምተው ጥቅም ላይ በማዋል እነሱም ተጠቅመው በሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ የላቀ ድርሻ እያበረከቱ ያሉ የዘርፉ ተዋናዮች በርካቶች ናቸው።
ከእነዚህም መካከል ‹‹ዋዳፍ ኢትዮጵያ›› የማዕድን ሥራዎች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት አንዱ ነው። ድርጅቱ የተለያዩ ማዕድናትን አልምቶ ለገበያ እያቀረበ ይገኛል። ድርጅቱ በሶስት ዋና ዋና ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ሲሆን፤ እነሱም ማዕድን ፍለጋ፣ ምርመራና ማዕድን ማውጣት ናቸው። ድርጅቱ በማዕድን ፍለጋ ከፍተኛ ትኩረት አድርጎ በመሥራት በዘርፉ የተገኙ መረጃዎችን ቀምሮ በቀጣይ ለሚመጣው ትውልድ ማሻገር እንዳለበት ያምናል።
የድርጅቱ መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ገመዳ ወርቁ ይባላሉ። አቶ ገመዳ፤ በኦሮሚያ ክልል ሰበታ ከተማ ተወልደው አርሲ አካባቢ አድገዋል። እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በግብርና ሥራ የሚተዳደሩ ወላጆቻቸውን በእርሻ ሥራ እያገዙ አድገዋል። ገና በለጋ ዕድሜያቸው የግብርና ሥራን ጠንቅቀው የሚያውቁት አቶ ገመዳ፣ የሕይወት አጋጣሚ ከውትድርናው ዓለም አድርሷቸዋል። በውትድርና ውስጥ በቆዩበት ጊዜ ታዲያ ለመሬት ያላቸው ዕውቀትና ቁርኝት ይበልጥ ተጠናክሮ ወደ ማዕድን ዘርፍ እንዲገቡ በር የከፈተላቸው መሆኑን ነው ያጫወቱን።
መሬት የሰጠናትን አንድ ፍሬ አብዝታና አባዝታ በብዙ እጥፍ የምትመልስ ባለውለታ መሆኗን በግብርና ሥራቸው ጠንቅቀው የሚያውቁት አቶ ገመዳ፤ ለ18 ዓመታት ሀገራቸውን በውትድርና ባገለገሉበት ወቅት ደግሞ በወታደራዊ ሳይንስ የመሬት ገጽታን የማወቅና የመረዳት ዕድል አግኝተዋል። ‹‹መሬት ለተጠቀመባት እናት፤ ላልተጠቀመባት ደግሞ ጠላት›› እንዲሉ፤ የእናትነት ባህሪ ልጇን በጉያዋ ሸሽጋ የምታኖር አሳልፋ የማትሰጥና ለሕይወትዋ የማትሳሳ እንደመሆኗ በተመሳሳይ መሬትም በውስጧ ያለውን ሀብት ሸሽጋ በመያዝ ለሚጠቀምባት እናት ናት›› በማለት ነው የመሬትን ጠቀሜታ ያስረዱት።
አንድ ወታደር ሲንቀሳቀስ የሚንቀሳቀስበት መልክዓ ምድር ምን እንደሚመስል ጠንቅቆ ማወቅ አለበት የሚሉት አቶ ገመዳ፤ በዚሁ ጊዜ የመሬትን ስሪትና ይዘት የማወቅና የመመርመር አጋጣሚያቸውን አስፍተዋል። የዕለት ውሏቸውን የመመዝገብ ልምድም አዳብረዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ በአንድ ወቅት አፋር አካባቢ የገጠማቸው ክስተት እጅግ አስገርሟቸዋል። ጊዜው ምሽት ነው፤ ግዳጅ ላይ እያሉ ይወድቃሉ፤ በዚህ ጊዜ ታዲያ ያነገቡት ክላሽ ከድንጋይ ጋር ሲላተም የተፈጠረው እሳት ከባድ ነበር። በወቅቱ ክፉኛ ድንጋጤ ውስጣቸውን ቢያርደውም ለማረጋገጥ ደግመው በማላተም ብልጭታውን አስተውለዋል። ከዚህ ጊዜ ጀምረው ታዲያ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸውን በመመዝገብ አካባቢያቸውን ሲያስተውሉ ቆዩ።
በዚሁ ጊዜ አፈራማ፣ ድንጋያማ፣ አለታማ ወይም ጥቁር ድንጋይ ያለባቸውን አካባቢዎች በመለየት የዕለት ውሏቸውን ይመዘግቡ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ገመዳ፤ ሀገሪቷ ዕምቅ የሆነ የማዕድን ሀብት ያላት ስለመሆኗም በዚሁ ጊዜ ተረድተዋል። ከመረዳት ባለፈም ይህንኑ ወደ ቢዝነስ ለመቀየር ባደረጉት ጥረት ዋዳፍ የማዕድን ልማት ሥራዎች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅትን አቋቁመው የተለያዩ ማዕድናትን በመፈለግ፣ በመመርመርና በማውጣት ሥራ ላይ ትኩረት በማድረግ ሥራቸውን ቀጥለዋል።
አካባቢያቸውን ለማወቅና ለመረዳት የነበራቸው አጋጣሚና ተነሳሽነት ከጥረታቸው ጋር ተደምሮ የማዕድን ዘርፉን መቀላቀል የቻሉት አቶ ገመዳ፤ የማዕድን ፈቃዳቸውም ብዙ ጊዜያቸውን በውትድርና ባሳለፉባቸው አካባቢዎች ነው። ይህም ለሀገር ማገልገል መልሶ የሚከፍል መሆኑን በተግባር ማየት የቻሉበት እንደሆነ ገልጸው፤ ከዚህ አንጻር እያንዳንዱ ሰው የተሰጠውን መክሊት አውቆ በትክክለኛና በቅንነት ሀገሩን ማገልገል ከቻለ እራሱን ጠቅሞ ሀገርንም ወደ ከፍታ ማምጣት እንደሚቻል አስገንዝበዋል።
በማዕድን ልማት አምስት ዓመታትን ያስቆጠሩ ሲሆን፤ በዚሁ ጊዜ ውስጥ በ14 የተለያዩ የማዕድን ዓይነቶች 28 የማዕድን ፈቃድ አግኝተዋል። ከእነዚህ መካከልም የድንጋይ ከሰል በዋነኝነት የሚጠቀስ እንደሆነ አቶ ገመዳ ሲያስረዱ፤ ድርጅታቸው ዋዳፍ የማዕድን ሥራዎች ሀገሪቷ ከዚህ ቀደም የውጭ ምንዛሪ በማውጣት ወደ ሀገር ውስጥ ታስገባ የነበረውን የድንጋይ ከሰል ለማልማት ብቻ አራት ፈቃዶችን አግኝተዋል። ከአራቱ ፈቃዶች መካከልም በሁለቱ የከሰል ድንጋይ ፈቃዶች ውጤታማ ሥራ እየሠራ እንደሆነ ነው። በዚህም የውጭ ምንዛሪ ከሀገር እንዳይወጣ ማዳን ተችሏል።
በሀገር ውስጥ እየለማ ያለው የድንጋይ ከሰል ከውጭ ይገባ ከነበረው በብዙ እጥፍ የተሻለና ጥራት ያለው ስለመሆኑ የጠቀሱት አቶ ገመዳ፤ በሀገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች ከፍተኛ የሆነ የድንጋይ ከሰል ክምችት መኖሩን ጠቅሰው፤ ድርጅታቸው ዋዳፍ ኢትዮጵያ የማዕድን ሥራዎች በኦሮሚያ ክልል ሁለት ቦታዎች፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልልም እንዲሁ ሁለት ቦታዎች እና በደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች አርባ ምንጭ አካባቢ የድንጋይ ከሰል በስፋት እያመረተ መሆኑን ይገልፃሉ።
የድንጋይ ከሰልን በስፋት እያመረተ የሚገኘው ዋዳፍ ኢትዮጵያ የማዕድን ሥራዎች ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ 67 ሺ ሜትሪክ ቶን የድንጋይ ከሰል ማምረት የቻለ ሲሆን፤ ይህም ወደ ገንዘብ ሲለወጥ አምስት መቶ ሁለት ሚሊዮን ብር የሚደርስ ነው። ምርቱን በሀገር ውስጥ በማልማት ለዚሁ ተግባር ይወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ከማዳን ባለፈ ድርጅቱ ለኮሪያና ለባንግላዴሽ የድንጋይ ከሰል ማቅረብ የሚያስችለውን የቅድመ ዝግጅት ሥራውን አጠናቅቋል። ይህም የውጭ ምንዛሪን ወደ ሀገር ውስጥ በማምጣት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ምሰሶ እንደሚሆን ይታመናል።
ለሲሚንቶ ምርት ግብዓት የሚሆነው የድንጋይ ከሰል ከዚህ ቀደም ከውጭ ሀገር የሚገባ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ገመዳ፤ በአሁኑ ወቅት በሀገር ውስጥ እየተመረተ መሆኑን ጠቅሰው ድርጅታቸው ዋዳፍም ሲሚንቶ አምራች ለሆኑ ፋብሪካዎች ለአብነትም ለዳንጎቴ፣ ለሙገርና ለሌሎችም በስፋት እያቀረበ እንደሆነና እስካሁን ያላቸው ግብረ መልስም ጥሩና የሚያበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።
ድርጅቱ ከድንጋይ ከሰል በተጨማሪም በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ ኩርሙክ ወረዳ የወርቅ ሳይቶች ያሉትና ወርቅ ማምረት የሚያስችለውን የቅድመ ዝግጅት ሥራ ያጠናቀቀ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ገመዳ፤ ወርቅም አንዱ የሀገሪቷ ሀብት እንደመሆኑ በዚህም ሰፋፊ ሥራዎችን በመሥራት በአሁን ወቅት የምርመራ ፈቃድ ጨርሰው ማሽኖችን በመትከል ወደ ምርት ሊገቡ ጫፍ መድረሳቸውን ነው የገለጹት። ከከበሩ ማዕድናት መካከል የሚጠቀሰው ኮፐርንም እንዲሁ እያመረቱ ሲሆን ፍሎራይት የተሰኘውን ማዕድን ማልማት የሚያስችላቸውን የዝግጅት ሥራም አጠናቅቀዋል።
ዋዳፍ ኢትዮጵያ የማዕድን ሥራዎች በፍለጋ ካገኛቸው ማዕድናት መካከል ተጠቃሽ የሆነው ሌላኛው ማዕድን ማይካ ነው። ይህ ማዕድን የሚገኘው በሱማሌ ክልል ሲሆን ለዚህም አስፈላጊውን ጥናት በማድረግ ሙሉ ምርመራ አድርጎ ወደ ሥራ ገብቷል። ታይኦሊን የተባለ ማዕድንም እንዲሁ በሀገሪቱ ጥሩ ክምችት ስለመኖሩ በጥናት ተረጋግጦ መልማት የሚችልበትን የቅድመ ዝግጅት ሥራ በማጠናቀቅ ወደ ሥራ የገባ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ገመዳ፤ ኢትዮጵያ በማዕድን ዕምቅ ሀብት ያላት መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚሁ ዘርፍ ጠንካራ ሥራ በመሥራት ሀገር እንድታድግ ሕዝቦቿም ከድህነት እንዲወጡ ማድረግ ይቻላል ብለዋል።
የማዕድን ፍለጋ ሥራ ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅ ትልቅ ኢንቨስትመንት መሆኑን በመጥቀስ ባሳለፉት አምስት የማዕድን ፍለጋ ዓመታት ድርጅቱ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉን የጠቀሱት አቶ ገመዳ፤ ከዘርፉ ከሚገኘው ገቢ በበለጠ ማዕድኑ መኖር አለመኖሩን መለየት በራሱ ትልቅ ስኬት ነው ይላሉ። ምክንያቱም ለመጪው ትውልድ ትክክለኛውን መረጃና ዳታ ሰርቶ ማስተላለፍ ያስፈልጋል። ትውልዱም ባገኘው መረጃ የተወሰነ ጥረት በመጨመር ዘርፉን ማሳደግ እንደሚችል ጠቅሰው፤ ለዚህም ድርጅታቸው ዋዳፍ ኢትዮጵያ የማዕድን ሥራዎች ለማዕድን ሥራ ትልቅ ትኩረት በመስጠት በተለይም በማዕድን ፍለጋ፣ በምርመራና በማውጣት ሥራ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
የማዕድን ልማት በባህሪው ብዙ የሰው ኃይል የሚፈልግ ባይሆንም ዋዳፍ ኢትዮጵያ የማዕድን ሥራዎች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በተለያዩ የቢሮ አገልግሎት ሥራዎች 30 ለሚደርሱ ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ከቢሮ ሠራተኞች ባሻገር ድርጅቱ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ባሉት 13 ሳይቶች በእያንዳንዳቸው 50 ጊዜያዊና ቋሚ ሠራተኞች አሉት። በእያንዳንዱ ሳይት የሚገኙ 50 ሠራተኞች፣ በተለያዩ የሥራ መስኮች የተሰማሩ ሲሆን፤ በዋናነት ባለሙያ የሆኑ ተመራማሪዎች፣ ፎርማኖችና ኦፕሬተሮች ይገኛሉ። ድርጅቱ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችን ጨምሮ በድምሩ 680 ለሚደርሱ ሠራተኞች የሥራ ዕድል በመፍጠር ኢኮኖሚያ አበርክቶ እያደረገ ይገኛል።
ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድም የተለያየ አበርክቶ እያደረገ ያለው ዋዳፍ ኢትዮጵያ በተለይም ማዕድ በማጋራት ብዙ አቅመ ደካሞችን መድረስ ችሏል። ቢሮው ከሚገኝበት አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ለሚገኙ አቅመ ደካሞች ማዕድ የማጋራቱን ተግባር በበዓላት ወቅት ይከውናል። በማምረቻ ቦታዎችም እንዲሁ የአካባቢውን ማህበረሰብ በመመገብ ድጋፍ ያደርጋል። ከዚህ ባለፈም ያዘመሙ ጎጆዎችንም የማቅናት በጎ ሥራ እየሠራ የሚገኝ ሲሆን፤ ጅማ ዞን ዴዶ ወረዳ ላይ ለአራት አባወራዎች ቤት ለመሥራት ዕቅድ ይዞ አንዱን ቤት አጠናቆ አስረክቧል።
በቀጣይም ይህንኑ ተግባር አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የጠቀሱት አቶ ገመዳ፤ በአካባቢው ትምህርት ቤትና መንገድ ለመገንባት እንዲሁም ንጹህ የመጠጥ ውሃ ለማውጣት ዕቅድ ይዘው እየተንቀሳቀሱ ሲሆን፤ በአሁን ወቅትም በማምረቻ አካባቢዎች ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች መብራትና ውሃ ማጋራት ችለዋል። መንግሥት ለሚያደርጋቸው ጥሪዎችም እንዲሁ ምላሽ በመስጠት ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ እንደሆነ ተናግረዋል።
ድርጅቱ በቀጣይ የማዕድን ሥራዎቹን አጠናክሮ በመቀጠል ማዕድኑን በጥሬው ለገበያ ከማቅረብ ይልቅ እሴት በመጨመር ያወጣውን ማዕድን ለመጨረሻ ተጠቃሚ ተደራሽ የማድረግ ዕቅድ አለው። ይህን ዕቅድ ለማሳካትም አስፈላጊ የሆኑ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እየሠራ እንደሆነ አቶ ገመዳ ገልጸዋል። እሳቸው እንዳሉት በተለይም የማዕድን ዘርፉ የብዙ አካላት ፍላጎት ያለበት እንደመሆኑ ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ያስፈልጋል። ለዚህም ነው መንግሥት በአሁን ወቅት ለማዕድን ዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑ የሚበረታታ ነው። በቀጣይም ሀገሪቷ ተዝቆ ከማያልቀው የማዕድን ሀብቷ ተጠቃሚ መሆን ትችላለች።
በማዕድን ዘርፉ በርካታ ችግሮች የሚያጋጥሙ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ገመዳ፤ ሰዎች ራዕያቸውን ለማሳካት የሚገጥማቸውን ማንኛውንም ችግር በጽናት ማለፍ እንዳለባቸው ጠቅሰው በተለይም በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋለው የሰላም መደፍረስ ለማዕድን ዘርፉ ብቻ ሳይሆን ለማንኛውም ሥራ እንቅፋት መሆኑን ተናግረዋል። ይሁንና አልጋ በአልጋ የሆነ ሥራ ባለመኖሩ ማንኛውንም ችግር አቅም በፈቀደ መጠን በመቋቋም የጀመሩትን ሥራ ወደፊት የሚያራምዱ እንደሆነ ገልጸው፤ እያንዳንዱ ማህበረሰብም ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ ነገሮችን በጥንቃቄ መከወን እንዳለበትም አሳስበዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘም ህዳር 22/2016