አዲስ አበባ፡- ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት መሠረታዊ ነፃነቶችና መብቶች ላይ አግባብ ያልሆኑ ገደቦችን የሚጥል ድርጊት መሆኑን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በዓለም ለ32ኛ እንዲሁም በኢትዮጵያ ለ18ኛ ጊዜ «መቼም፣ የትም በምንም ሁኔታ ፆታዊ ጥቃትን ዝም አንበል!!» በሚል መሪ ቃል ለሚከበረው የፀረ- ፆታዊ ጥቃት ቀን የተዘጋጀ ንቅናቄ ማስጀመሪያ ፕሮግራም ሰሞኑን ተከናውኗል፡፡
በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶችና ሕፃናት ዘርፍ የሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ወይዘሮ ዘቢደር ቦጋለ እንዳሉት፤ ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት መሠረታዊ ነፃነቶችና መብቶች ላይ አግባብ ያልሆነ ገደቦችን የሚጥል ድርጊት ነው፡፡
እንደ ወይዘሮ ዘቢደር ገለጻ፤ የሴቶች ጥቃት በሰላምም ሆነ በጦርነት ወቅት በግልም ሆነ በማኅበራዊ ሕይወት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚያሳድር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሕጎች የተረጋገጡ ነፃነቶችና መብቶች ላይ አግባብ ያልሆኑ ገደቦችን የሚጥል ጭምር ድርጊት ነው።
በሴቶችና በሕፃናት ላይ የሚፈጸም ማንኛውም ዓይነት አካላዊ፣ ወሲባዊም ሆነ ሥነልቦናዊ ጥቃት ኢኮኖሚያዊ ችግር የሚያስከትል የሰብአዊ መብት ጥሰት ስለመሆኑም ወይዘሮ ዘቢደር ጠቁመው፤ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርስ ጥቃት አካላዊ፣ አእምሯዊ ጤንነት እና ደህንነት በሁሉም የሕይወታቸው ደረጃ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል ብለዋል፡፡
የ16ቱ የፀረ-ፆታዊ ጥቃት ቀናት በዓለም አቀፍ ደረጃ ፆታን መሠረት ያደረገን ጥቃት ለማስቀረት የሚደረግ ዓለምአቀፍ ትግል አካል በመሆኑ ቀናቶቹ በዓለም አቀፍ ፀረ-ፆታዊ ጥቃት ቀን ተብለው እንዲታሰቡ ስለመደረጉም ወይዘሮ ዘቢደር ጠቅሰዋል፡፡
ይህም የተደረገው በሴቶች ላይ በኃይል የሚፈፀመውን ጥቃትና ሰብአዊ መብት ያላቸውን ቁርኝት ለማገናዘብ እና ጥቃቱ የሰብአዊ መብት ጥያቄ መሆኑን ለማሳየት ነው ብለዋል፡፡ በዚህም ወንዶች ነጭ ሪቫን በማድረግ ከኅዳር 16 ጀምሮ ለአስራ ስድስት ቀናት በሴቶች ላይ ማንኛውም ዓይነት ጥቃት ላለመፈፀም ቃል የሚገቡበት ሂደት ስለመኖሩም ተጠቅሷል፡፡
ዘኢኮኖሚስት ኢንተለጀንስ ዩኒት በሚባለው ተቋም የተደረገ ዓለምአቀፍ ጥናት እንዳመለከተው 38 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች በቀጥታ ጥቃት ሲደርስባቸው 85 በመቶ ደግሞ በዲጂታል ቴክኖሎጂ አማካኝነት ጥቃት /online Violence/ እንደሚደርስባቸው ተመልክቷል።
በቴክኖሎጂው ዘርፍ በሚሠሩ ሴቶች ላይ የተደረገ ዓለም አቀፍ ጥናት እንዳመለከተው 44 በመቶ የሚሆኑ የሴቶች ማኅበራት መሥራቾች በ2020 በሥራ ቦታ ላይ ጥቃት አጋጥሟቸዋል፤ ከነዚህም 41 በመቶዎቹ ሴቶች ወሲባዊ ትንኮሳ ደርሶባቸዋል ይላል።
ዳግማዊት ግርማ
አዲስ ዘም ህዳር 22/2016