የባልንጀርነትን ገመድ የበጠሰ ወንጀል

“ብረት ብረትን ይስለዋል፥ ሰውም ባልንጀራውን ይስላል።” የሚል አባባል መልካም ጓደኝነት ለመጥቀስ ጥቅም ላይ ይውላል። መልካም ጓደኝነት በዕጣ ወይም በሒሳብ ቀመር ተጠቅመን የምናገኘው ነገር ባይሆንም የራሱ የሆኑ መመዘኛዎች ግን ይኖሩታል፡፡ እውነተኛ ጓደኝነት እንደ ወርቅና አልማዝ ብር ነው፡፡

ጓደኞች የችግር ተካፋይ፣ የሐዘን አጋሮች፣ ተስፋ የቆረጠውን ተስፋውን የሚያለመልሙ፣ የወደቀውን የሚያነሡ ከጨለማ ወደ ብርሃን ፣ ከሞት ወደ ሕይወት የሚመልሱ በአጠቃላይ ከጎናችን ሆነው የሕይወት ስንክሣራችንን የሚጋሩ ጓደኞች ዋጋቸው ከወርቅም ከዕንቁም የበለጠ ነው፡፡ አብሮን የዋለ አብሮን ያደረ በተለያየ እንቅስቃሴያችን ውስጥ የምናገኘው ሰው ሁሉ የልብ ጓደኛችን ሊሆን አይችልም፤ ነገር ግን ከእነዚህ ሰዎች መሀል ሃሳቡ ከሃሳባችን፣ ዓላማው ከዓላማችን፣ ሕይወቱ ከሕይወታችን የሚገጣጠመው ብቻ ባልንጀራችን ይሆናል፡፡

የዛሬዎቹ ባለታሪኮቻችን የጓደኝነትን ልክ ከወሬም አልፈው በተግባር የሚኖሩ አብረው ውለው አብረው አምሽተው የሚገቡ ነበሩ። ብዙ ሰዎች በጓደኝነታቸው የሚቀኑባቸው፤ መተማመናቸው የበረታ የጓደኝነት ትስስራቸው የጠበቀ በአጠቃላይ መልካም ጓደኛ መገለጫ ለሌሎች ጥሩ የጓደኞች ምሳሌዎች ነበሩ፡፡

ጓደኝነትን የመሠረቱት ጥቅም ለማግኘት ሆን ብለው አስበው፣ በሽንገላ ከንፈር አንደበታቸውን በማጣፈጥ፣ ለታይታ አልነበረም። የልብ ጓደኝነት ነበራቸው። ጓደኝነታቸውም በዘር፣ በቋንቋ፣ በአንድ አካባቢ ተወላጅነት ላይ የተመሰረተም አልነበረም፡ ፡ የሁለቱ ጓደኝነት በፍፁም ፍቅር ላይ የተመሠረተ ነበር፡፡ መልካም ጓደኛሞች ለችግር ጊዜ ደራሽ፣ በመከራ፣ በሐዘን፣ በደስታ ተካፋይ፣ አማካሪና፣ ገመናን ሸፋኝ የኔ ሰው ነው የሚባባሉም ነበሩ፡፡

በአብዛኛው የእረፍት ቀናቸውን አብረው ነው የሚያሳልፉት። ዛሬም በጠዋት ተገናኝተው ቁርሳቸውን አብረው ፍርፍር በልተው፤ እስከ ምሳ ሰዓት የጋራ ጓደኞቻቸው ከሆኑ ሴቶች ጋር ቆይተው አንደኛው የጥበቃ ሥራ ስለሚሰራ የሥራ መግቢያው ሲደርስ ተሰናብቷቸው ሄዷል።

በኋላም አመሻሽ ላይ መጠጥ መቀማመስ የፈለገው ጓደኛ ካለ መጠጡ ባልንጀራው ከጉሮሮው አልወርድ ቢለው ሥራ ከጨረስክ ና አብረን እናምሽ ብሎ ይጠረዋል። ሀብቴ መዝገቡ የተባለው የፊኒሽንግ ሥራ ላይ የተሰመራው ወጣት ዓለሙ ታረቀኝ አምባው የተባለውንና በጥበቃ ሥራ የሚተዳደረውን ጓደኛውን ከጠራው በኋላ ሥራ የቆየው ዓለሙ ምግብ አዞ እራታቸውን አብረው በልተው ጃንቦ ድራፍት እየጠጡ ነበር ያመሹት።

መጠጡ ሲደጋገምና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የግንባታ ሥራ በመቀዛቀዙ የገቢያቸው መቀነስ ሆድ ስያስብሳቸውና ስለ ጉዳዩ ሲወያዩ ያመሻሉ። ከዛ ሀብቴ “አንተ የምትጠብቀው ያላለቅ ሕንፃ ላይ ሥራ መኖሩን እያወክ ሳትነግረኝ ቀረህ” ይለዋል። ዓለሙም ባለማስተዋል ችላ ያለው መሆኑን ነግሮት ይቅርታ ቢጠይቀውም ሀብቴ ግን በስድብና በዘለፋ ምቀኝነት ነው በማለት ቃላት ይወራወሩ ጀመር።

ከቃላት ምልልስ በኋላ ዓለሙ ሥራ ስላለው መሄድ እንደሚፈልግ ተናግሮ ወደ ደጅ ሲወጣ ሀብቴ ተከትሎት ከመሳደብ አልፎ ለድብድብ መጋበዝ ጀመረ። ትዕግስቱ የተሟጠጠው ጓደኛው መለስ ብሎ አንገቱን በማነቅ ይደባደቡ ጀመር።

ገላጋይ ገላግሏቸው ተንፈስ እንዳሉ ነበር ንዴቱን መቆጣጠር የተሳነው ዓለሙ ከመንገዱ ዳር የኮብል እስቶን አንስቶ ግንባሩ ላይ በኃይል የመታው። መጠጥ ያዳከመው ሀብቴም ድንጋዩ እንዳረፈበት ነበር ወደ ኋላው የወደቀው። ወደ ኋላም ሲወደቅ የተቀበለው የአስፓልት ጠርዝ የራስ ቅሉን ክፉኛ በመጉዳቱ የተነሳ ወዲያውኑ ሕይወቱ ሊያልፍ ቻለ።

ወጣት ሀብቴ መዝገቡ

ሰሜን ሸዋ አካባቢ ተወልዶ ያደገ ወጣት ነው። ሀብቴ ገና በአስራዎቹ አጋማሸ እድሜ ላይ ነበር ያገባው። በልጅነቱ የትዳር ዓለምን የተቀላቀለው ወጣት እርሻው ብዙም አልሳካለት ሲል ከባለቤቱ ጋር አዲሰ አበባ ሄደን ያገኘነውን እንሥራ በማለት ከትውልድ ቀያቸው ወጡ። በትምህርት ብዙም የገፉ ስላልነበሩ ከጉልበት ሥራ በቀር ሌላ ሥራ ማግኘት አልቻሉም ነበር።

ከቀን ሠራተኝነት ተነስተው የፊኒሽንግ ሥራ ላይ ባለሙያ እስኪሆኑ ድረስ ለዓመታት ለፍተዋል። ያገኟትን አጠራቅመው ለወላጆቻቸው ገጠር ቤት ሰርተዋል። ከዚህ በኋላ ለራሳችን ጥሪት እንያዝ በማለት ለቤታቸው ደፋ ቀና ማለት በጀመሩበት ወቅት ነበር የግንበታ ሥራ መቀዛቀዘ የጀመረው።

ትንሽ ጥሪት ይዘን ልጅ እንወልዳለን በማለት በእቅድ የሚመሩት ባልና ሚስት የሥራ መጥፋት ሁኔታው ከእቅድ ውጭ ስላደረጋቸው ይበሰጫጩ ነበር። በፍቅር ሲመሩት የነበረው ቤታቸው በውሃ ቀጠነ መበጥበጥ ጀመረች። ገና ከሀገራቸው መጥተው አዲስ አበባን እንደረገጡ የተዋወቁት ጓደኛቸው ዓለሙ ታረቀኝ መሀል እየገባ የነበረ ፍቅራቸው እንዲቀጥል ጥረት ያደርግ ነበር።

በእለቱም ማልደው በመገናኘት ብዙ ከተመካከሩ በኋላ የሀብቴ ባለቤትና ሌሎች አብረው ሆነው ሀብቴና ባለቤቱን በማስመማት ደግም ፀብ እንዳይኖር በመመካከር ነበር የዋሉት። የጥበቃ ሥራ የሚሰራው ዓለሙም እነ ሀብቴን ተሰናብቶ ወደ ሥራው ሲሄድ የሀብቴ ባለቤትና ጓደኞቿ ወደቤት ተመለሱ። ሀብቴም ሥራ ፍለጋ ዞር ዞር ሲል ቆይቶ አመሻሸ ላይ አንድ መጠጥ ቤት በመግባት አንድ ሁለት ለማለት ቢሞክርም ከልብ ጓደኛው ተነጥሎ መጠጣት አልሆን ሲለው ደውሎ ይጠራውና አብረው ያመሻሉ። እንግዲህ ከሞቀታ በኋላ ነው ሆድ የባውን ብቅል ያወጣዋል ይሉት ነገር ተቀስቅሶ ጓደኛሞቹን ግጭት ውስጥ የከተታቸው።

ወጣት ዓለሙ ታረቀኝ

የወሎ ላስታ አካባቢ ተወላጅ ነው። ዓለሙ ታረቀኝ አምባው እድሜው ሃያ ሲሆን የትምህርቱ ደረጃ 6ኛ ክፍል እና ሥራውም ጥበቃ ነበር። ትሁት ለጓደኝነት ሟች የሚባል ዓይነት ሰው ነበር። በጣም የዋህ ከመሆኑ የተነሳ በትንሽ ነገር የሚከፋ በትንሽም ነገር የሚደሰት ዓይነት ሰው ነው።

ነገሮችን በዝምታ ለማለፍ የሚጥር ቢሆንም ታግሶ ታግሶ ሲበቃው ግን ማንም የማይዘው ያልታወቀ ዓይነት ባህሪ የሚያሳይ ቁጡ ሰው ሆኖ ይቀየራል። ለመናደድ ጊዜ የሚፈጅበት ይህ ወጣት ከንዴት ውስጥ ለመውጣትም ሲታገል መመልከት የተለመደ ነበር።

በእለቱም ከጓደኛው ጋር ባልረባ ነገር እሰጣ ገባ ውስጥ ቢገቡም ነገሩን ለማብረድ ደጋግሞ ይቅርታ ሲጠይቅ ነበር። ምንም እንኳን ጓደኛው ይቅርታውን ተቀብሎ ሊተወው ባይፈልግም ለሰላም ሲል ታግሶ ቆይቷል።

ከቆይታ በኋላ ግን ትእግስቱ ተጠናቀቀ፤ ንዴቱ ገንፍሎ ወጥቶ ከቁጥጥር ውጭ ሆነ። ያን ጊዜ ያለምንም መስፈርት በፍቅር ብቻ የመሰረቱት ጓደኝነት ተናደ። ገበና ከታቼ የልቤ ሰው የተባባሉት ጓደኞች የአንዱ ሕይወት በሌላው እጅ እንዲጠፋ ሆነ። ለታላቁ ባልንጀራነት ማብቂያው ወንጀል ሆነ።

ፖሊስ

ምሽቱን ከደስታ ወደ ሀዘን የቀየረው አጋጣሚ እንደተፈጠረ ነበር የፀጥታ ኃይሎች በቦታው የደረሱት። እጅግ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ ፊቱ በሙሉ በደም የተሸፈነውን ወጣትና ፤ በንዴት ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ ነፍስ ያጠፋውን ባልንጀራውን ፊት ለፊት ተፋጠው ያገኟቸዋል። ያኔ አንዱን ወደ ሆስፒታል አንዱን ደግሞ ወደ ፖሊስ ጣቢያ በመውሰድ ምርመራቸውን ይጀምራሉ።

የእምነት ክህደት ቃል

‹‹እኔና ሟች ሀብቴ መዝገቡ የረጅም ጊዜ ጓደኛሞች ነን። በእለቱም ከባለቤቱ ጋር ተጋጭተው ስለነበር ለመመካከር በሚል በጠዋት ነበር የተገናኘው። የተገናኘንበት ሻይ ቤት ቁርስ ፍርፍር አብረን በልተን ሁለታችንም ሥራ ስላልነበረን አብረን ቁጭ ብለን እስከ ስድስት ሰዓት የሟች ባለቤትና ለሎች በጋራ ከምናውቃቸው ሴቶች ጋር ስንጫወት ነበር የቆየነው።

ከዛ በኋላ ተለያይተን ከቆየን በኋላ ሟች ደወሎ የት ነው ያለኸው አብረን እንጠጣ ብሎ ስሄድ ድራፍት እየጠጣ አገኘሁት። እኔ ስደርስ ምግብ አዘዝኩና አብረን ምግብ ከበላን በኋላ ድራፍት ጠጣን። እኔ ጥበቃ ስለሆንኩ ልሂድ ሥራ አለኝ ብዬ ተነሳሁ።

ከዛ በድርጅታቸሁ ሥራ እያለ ለምን አልነገርከኝም በማለት መቆጣት ጀመረ፤ ሥራው የፊኒሽንግ ሥራ ስለነበር ባለማስተዋል ለጓደኛዬ ስላልነገርኩት ተጸጽቼ ይቅርታ ጠየኩት። ቢሆንም ግን እሱ እየተናደደ ሲናገር አንድ አንድ ስንባባል ቆይተን ተጣላን፤ ተያይዘን መደባደብ ጀመርን፡፡ ከዛ ዞር ብዬ ድንጋይ በማንሳት ግንባሩን ስለው ወደኋላ ስለወደቀ አስፓልቱ መቶት ሊሞት ችሏል።›› በማለት ተጠርጣሪውም በወንጀል ምርመራ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 127(2) መሠረት የወንጀል ድርጊቱን መፈፀሙን ለፖሊስ የእምነት ክህደት ቃሉን ሰጥቷል።

የፎረንሲክ ምርመራ

አስክሬኑ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊንየም ሜዲካል ኮሌጅ የፎረንሲክ ሜዲስንና ቶክሲድ ትምህርት ክፍል በመሄድ ምርመራ የተደረገለት ሲሆን በቁጥር ጳሆ 8/3257 በቀን 18/06/14 በሟች ሀብቱ መዝገቡ የተሰጠው የአስክሬን ምርመራ እራስ ቅሉ ላይ በደረሰው ጉዳት መሞቱን የሚያስረዳ መረጃ ለፖሊስ ቀርቧል።

ፖሊስም የሰው ምስክሮችን፤ የተከሳሽ የእምነት ክህደት ቃልንና የሰነድ ማስረጃ ማለትም የፎረንሲክ ምርመራውን በማጠናቀር ለፌዴራል አቃቤ ሕግ ልኳል።

የፌዴራል አቃቤ ሕግ ክስ

ከሳሽ የፌዴራል አቃቤ ሕግ፤ ተከሳሽ ዓለሙ ታረቀኝ አምባው እድሜ 20 አድራሻ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09 የቤት ቁጥር አዲስ ወንጀሉ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 540 ስር የተደነገገውን መተላለፍ ሲሆን የወንጀሉ ዝርዝር በዚህ መልኩ ቀርቧል።

የወንጀሉ ዝርዝር ተከሳሽ ሰውን ለመግደል በማሰብ በቀን 30/05/14 ከምሽቱ በአራት ሰዓት አካባቢ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ልዩ ቦታው ኮዬ ፈጬ ፕሮጀከት ቢ ተብሎ የሚጠራው ቦታ ላይ ሟችን ግንባሩ ላይ አንድ ጊዜ ወርውሮ በመምታት በራስ ቅሉ ላይ በደረሰው ጉዳት ምክንያት ሕይወቱ እንዲያልፍ ያደረገ በመሆኑ በፈፀመው ተራ ሰው የመግደል ወንጀል ተከሷል።

ውሳኔ

 ተከሳሽ ዓለሙ ታረቀኝ የተከሰሱበት ተራ ሰው የመግደል ወንጀል በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ በ24/8/15 በዋለው ችሎት ክስና ማስረጃውን ከሕግ ጋር አገናዝቦ በሰጠው ውሳኔ መሠረት በ10 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኗል።

ለታሪኩ መነሻ ሃሳብ እንድናገኝ የተባበሩን የአዲስ አበባ ፖሊስ የመዝገብ ቤት አባላትን በዝግጅት ክፍላችን ስም ከልብ እናመሰግናለን።

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘም ህዳር 22/2016

Recommended For You