የጥርስ ምርመራ ማድረግ ባህል ሊሆን ይገባል

አዲስ አበባ፡- ዜጎች ከመታመማቸው አስቀድሞ የጥርስ ምርመራ ማድረግን ባህል ሊያደርጉ ይገባል ሲሉ በአለርት ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የጥርስ ሕክምና ማዕከል አስተባባሪ ስመኝ አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ከአለርት ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የጥርስ ሕክምና ማዕከል ጋር በመተባበር ለድርጅቱ ሠራተኞች ነፃ የጥርስና የአፍ ምርመራ አገልግሎት እንዲያገኙ አድርጓል።

በሆስፒታሉ የጥርስ ሕክምና ማዕከል አስተባባሪ ስመኝ አሰፋ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደተናገሩት፤ የጥርስን ጤንነት ለመጠበቅ በትንሹ በዓመት ሁለት ጊዜ ሐኪም ጋር መታየት ይገባል፡፡

በርካታ ሰዎች ጥርሳቸው የመጨረሻው የጉዳት ደረጃ ላይ ሲደርስ ወደ ሕክምና ተቋም ይመጣሉ ያሉት ዶክተር ስመኝ፤ ይህም ከጥርስ ጉዳት አልፎ ለተጓዳኝ የጤና ችግሮች፣ ለአፍ ጠረን ችግርና ለሥነ-ልቦና ጉዳት እንደሚያጋልጣቸው አስረድተዋል።

በአፍ ውስጥ የምግብ ትርፍራፊ ከዋለና ከአደረ ለጥርስ ህመም እንደሚያጋለጥ ገልጸው፤ በዓመት ሁለት ጊዜ ሐኪም ጋር በመታየት፣ ጠዋትና ማታ ጥርስን በማጽዳትና ቫይታሚን ሲ ያላቸውን ምግቦች በመመገብ የጥርስን ጤንነት መጠበቅ እንደሚቻል አመልክተዋል።

ዜጎች ከመታመማቸው በፊት የጤና ክትትል ማድረግን ባህል ማድረግ እንዳለባቸው አንስተው፤ ለኢፕድ ሠራተኞች ነፃ ቅድመ ምርመራ አገልግሎት የተሰጠው ሌሎች ዜጎች ከመታመማቸው በፊት ምርመራ ማድረግን ባህል እንዲያደርጉ ለማስገንዘብ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የደንበኞች አገልግሎት ባለሙያ ትንሳኤ ደገፉ በበኩሉ፤ በተደረገው ነፃ የጥርስ ምርመራና የግንዛቤ ማስጨበጫ አገልግሎት ከመታመማችን በፊት ወደጤና ተቋም ሂደን ክትትል ማድረግ ያለውን ጠቀሜታ ተረድተናል ብሏል።

በቀጣይም ሳልታመም ወደጤና ተቋም እየሄድኩ ክትትል ከማደረግ ባለፈ በአካባቢዬ የሚገኙ ሰዎች ከመታመማቸው በፊት የጤና ክትትል እንዲያደርጉ ግንዛቤ እፈጥራለሁ ሲል ተናግሯል።

በኢፕድ የዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ክፍል ኃላፊ ወይዘሮ ብርሃኔ ደመቀ በበኩላቸው፤ የተቋሙ ሠራተኞች የጥርሳቸውን ጤና ለመጠበቅ ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ከአለርት ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የጥርስ ሕክምና ማዕከል ጋር በመተባበር ነፃ የጥርስና የአፍ ምርመራና ሕክምና አገልግሎት ተሰጥቷል፡፡

የአለርት ሆስፒታል ላደረገው ትብብር አመስግነው፤ በቀጣይም ለተቋሙ ሠራተኞች በተለያዩ የሕክምና ዘርፎች የሚሰጠው ግንዛቤ ማስጨበጫና የቅድመ ምርመራና ሕክምና አገልግሎት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል፡፡

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን ኅዳር 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You