«የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ወንድማማችነትን በማጠናከር ሀገራዊ አንድነትን የሚያጎለብት ነው» – አቶ ኃይሉ አዱኛ የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ

አዲስ አበባ፡- የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል መከበሩ እንደሀገር በሕዝቦች መካከል ወንድማማችነትን በማጠናከር ሀገራዊ አንድነትን የሚያጎለብት ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ገለጹ፡፡

18ኛውን የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን በዓልን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀው 35ኛው ጉሚ በለል የውይይት መድረክ «ብዝሃነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት» በሚል መሪ ሃሳብ ትናንት ተካሂዷል።

በመድረኩ የተገኙት አቶ ኃይሉ አዱኛ እንደተናገሩት፤ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል በሕዝቦች መካከል ወንድማማችነትን በማጠናከር ሀገራዊ አንድነትን የሚያጎለብት በመሆኑ ያጋጠሙ የተለያዩ ችግሮችን በጋራ ለመቅረፍ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡

የፌዴራሊዝም ሥርዓት በኢትዮጵያ ለሚገኙ ሕዝቦች ባህል፣ ቋንቋና እምነት ዕውቅና ሰጥቷል ያሉት አቶ ኃይሉ፤ በተለይም ራስን በራስ ለማስተዳደርና በጋራ ሀገርን ለመምራት ያስቻለ ሥርዓት መሆኑን ጠቁመዋል።

ሕገ-መንግሥቱ የጸደቀበት ኅዳር 29 ቀን የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በመሆን የሚከበር በመሆኑ በሕዝቦች መካከል ለመቀራረብና ለመተዋወቅ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ብለዋል፡፡

የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ባህል፣ ቋንቋና እምነት ማሳደግ እንዲችሉ ማድረጉን ጠቅሰው፤ ሕገ-መንግሥቱ ዜጎች ልዩነታቸውን አክብረው በጋራ እንዲኖሩ የሚያስችል ሰነድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደሀገር በሕዝቦች መካከል የመረዳዳትና የመቀራረብ ባህልን ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁመው፤ ልዩነትን በማጥበብ በሀገራዊ ግንባታ ጉዳዮች ላይ በጋራ መሥራት ያስፈልጋል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የሕዝቦችን የጋራ አቅም፣ ሀብትና ዕውቀት በመጠቀም አቃፊ ትርክትና አሳታፊ የሀገር ግንባታ ማከናወን እንደሚያስፈልግ ተናግረው፤ በአብሮነት ልማቱን ለማፋጠን የምሁራን ድርሻ ማጉላት ይገባል ሲሉ አመልክተዋል፡፡

የበዓሉ መከበር የሕዝቦችን ባህል ቋንቋና ማንነትን ለመጠበቅ እንደሚያስችል የገለጹት አቶ ኃይሉ፤ በሀገሪቱ ያጋጠሙ ችግሮችን በጋራ በመቅረፍ የትውልዱን መጻኢ ጊዜ ብሩህ ለማድረግ መሥራት ይገባል ብለዋል።

የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል መከበር ወንድማማችነትን እንዲጠናክር በማድረግ ሀገራዊ አንድነት እንዲጎለብት ያስችላል ያሉት ኃላፊው፤ በዓሉ ወንድማማችነትንና ሀገራዊ አንድነት ለማጠናከር የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በውይይት መድረኩ የኦሮሚያ ክልል ምክትል አፈ ጉባኤ ኤሊያስ ኡመታን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የፌዴራሊዝም ምሁራን እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን ኅዳር 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You