እውነት ግን የአዲስ አበባ ወንዞች ሽታ በ29 ቢሊዮን ብር ይጸዳ ይሆን? እኔ ያ ጉድ ሽታ በ29 ትሪሊየን ራሱ የሚጸዳ አይመስለኝም። እውነት አፍንጫዬን ሳልይዝ አልፍ ይሆን? በነገራችን ላይ የአዲስ አበባ ወንዞችን ማጽዳት ራሱን የቻለ የጤና መከላከል አጀንዳ ነው። ስለዚህ ከውበት ጋር ብቻ ሳይሆን የሚያያዘው ከጤና ጋር ነው። መቸስ እንግዲህ ዋናው ነገር ጤና አይደል?
የሆነውስ ሆነና ግን የፕሮጀክቱ ትኩረት ወንዞች ላይ ብቻ ነው ወይስ? ኧረ ወንዞች ራሱ ከተሠሩ ተመስገን ነው። የአዲስ አበባ ቆሻሻ ወንዝ ዳር ብቻ አይደለም፤ በጎዳና ዳር፣ በአስፋልት ዳር ይባስ ብሎም በመንደር መሃል ሁሉ ነው።
የዚህ ሁሉ ምክንያት ድህነትና መሃይምነት ነው። ‹‹መሃይምነት›› የሚለው ቃል ከባድ ቢሆንም እየመረረን የምንውጠው ሀቅ እንጂ ምንም የሚስተባበል ነገር የለውም። መሃይማነት ሲባል ቀለም ያልቆጠረ ማለት አይደለም፤ ከ15 ዓመት በላይ በትምህርት ያሳለፈ ከዩኒቨርሲቲ የወጣ መሃይም አለ።
ሱፉንና ከራቫቱን ግጥም አድርጎ አስሮ መንገድ ዳር የሚሸና አይታችሁ አታውቁም? ታዲያ ይሄን መሃይምነት ከማለት ውጭ ምን የሚሽሞነሞን ቃል ያስፈልጋል? የቆሻሻ ገንዳ እያለ ቆሻሻ ከቤቱ አውጥቶ ሜዳ ላይ የሚረጭ ሰው ታዲያ ምን ሊባል ነው?
እስኪ አስተውሎታችንን ወደ ዛሬ ሳምንት እንመልሰው። የዛሬ ሳምንት እሁድ በመላ አገሪቱ የተጠራ የጽዳት ዘመቻ ነበር። በሥራ ምክንያት አዳማ ነበርኩ። የሄድኩበት ጉዳይ ለቅዳሜና እሁድ የታሰበ ቢሆንም በጽዳት ዘመቻው ምክንያት ቅዳሜ እንዲያልቅ ተደረገ። እሁድ በጠዋት ወደ አዲስ አበባ መጣን። ኧረ ወዲያ እቴ! ገና ቃሊቲ ስደርስ ነው ግምቴ ሁሉ እንደከሸፈ ያየሁት።
አዲስ አበባ ከጫፍ እስከ ጫፍ በጽዳት ዘማቾች ተጥለቅልቃ መግቢያም አይኖርም ብየ ነበር። ምንም ነገር ሳላይ መስቀል አደባባይ ደረስኩ። በቃ ከዚህ በኋላማ ምንም አይኖርም ብየ ወደ ቤቴ ሄድኩ። በእርግጥ ቤት ከገባሁ በኋላ በቴሌቭዥን ትንሽ አይቻለሁ። ልብ ብላችሁ ከሆነ ግን አወጣጡ እንደተባለው አይደለም። በመሥሪያ ቤት ደረጃ የወጡ እንጂ ህዝብ ‹‹በነቂስ ወጥቶ›› የሚባል አይደለም። ህዝብ ለምን አልወጣም?
መሃይምነታችን እዚህ ጋ ነው። ነገሩን ከፖለቲካ ጋር አያይዘነዋል። የተጠራው በጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ ነው። ለዚህም ይመስላል የጽዳት ዘመቻውን መውጣት መንግሥትን መደገፍ መስሎ ታየን! ቆይ ግን ለበጎ ከሆነ ብንደግፍስ ምን ችግር ነበረው? ይህን ያባባሱት ደግሞ የፌስቡክ አርበኞች ሆኑ። ገና የጽዳት ዘመቻ ጥሪ ሲደረግ ብሽሽቅ ተጀመረ። እውነት አሁን አካባቢን ለማጽዳት የአይዲዮሎጂ ክርክር ያስፈልግ ነበር? የፌዴራሊዝም ሥርዓት ካልፈረሰ የሚያሰኝ ነበር?
በዕለቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አካፋ ይዘው ሲያጸዱ ታይቷል። ግማሹ ሲያመሰግን ግማሹም እንዴት በአገሪቱ ውስጥ ስንት ችግር እያለ እሱ አካፋ ይዞ ያጸዳል? ተብሏል። በነገራችን ላይ የዚያን ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባያጸዱ ኖሮ ምን ያደርጉ ነበር? የነበሩ ችግሮችን ሁሉ የዚያን ቀን ይቀርፉ ነበር?
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያጸዱት ለአርዓያነትና ለማነቃቃት እንጂ እርሳቸው አጽድተው ያልቃል ተብሎ እኮ አይደለም። በነገራችን ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በፊት አንድ ቅናት ነበር። ብዙዎች ሲሉ እንደምትሰሙት የውጭ አገራት መሪዎችን በጣም እናደንቅ ነበር። ከህዝብ ጋር እንዲህ አድርገው፣ ታች ወርደው እንዲህ አደረጉ፣ የኛዎቹ ህዝብ ያለበት አይደርሱም እየተባለ ይወራ ነበር። አሁን የዚያን አይነት መሪ ሲገኝ ነገሩ ተገልብጦ እንዲህ ሆነ!
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያንን ማድረጋቸው ጥሩ ነገር ነው። ነገሩ ከፖለቲካ ጋር የሚገናኝበትን መንገድ ባስበው ባስበው አልገባህ አለኝ። ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ አካባቢውን ቢያጸዳ መንግሥትን መደገፍ ነው ማለት ነው? እረ አይመስለኝም ራሱን ማጽዳት ማለት ነው።
የአዲስ አበባ ቆሻሻ በፕሮጀክት ይጸዳል ብሎ ማመን ከባድ ነው። ያለን እንዲህ አይነት ማህበረሰብ ነው። ፖለቲካው የተበላሸ፣ የማህበረሰቡ አስተሳሰብ የተበላሸ፤ ታዲያ ይሄ ነገር ያስኬዳል ብላችሁ ነው?
የአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን የብዙ ከተሞቻችን ችግር ይሄው ያለመሰልጠናችን ችግር ነው። አንድ ሰው ቢያጸዳ መቶ ሰው ያቆሽሻል፤ ታዲያ ይሄ እንዴት ነው በአንድ ፕሮጀክት አዲስ አበባን ጽዱ የሚያደርግ? አዲስ አበባን ጽዱ የሚያደርጋት ከዚህ በላይ ሰዎቿ ቢሰለጥኑ ነበር።
እያስቸገረ ያለው እኮ እስካሁን የቆሸሸው ብቻ አይደለም፤ እሱንማ በአንድ ሳምንት (ኧረ በአንድ ቀን) ዘመቻ ማስወገድ ይቻል ነበር። ችግሩ በዚያው ልክ ቆሽሾ የሚያድረው እኮ ነው። እነዚህ አሁን የምናያቸው ወንዞች እኮ ሲፈጠሩ ቆሻሻ ሆነው ተፈጥረው አይደሉም፤ እኛው ነን እንዲህ ያበለሻሸናቸው፤ ታዲያ እኛ ካልተለወጥን ምን ዋጋ አለው?
መጋቢ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁ ብዙ ጊዜ በዲስኩራቸው ላይ ‹‹ህዝብ ይሳሳታል›› እያሉ ይናገራሉ፤ ትክክል ናቸው። መንግሥት የህዝብ ቁጣ እንዳይነሳብኝ ሲል ለማባበል ‹‹ህዝብ አይሳሳትም›› እያለ ይስበክ እንጂ ህዝብ ግን ድብን አድርጎ ይሳሳታል፤ እንዲያውም ከመንግሥት ስህተት ይልቅ የህዝብ ስህተት ይከፋል።
በሩ ላይ ያለውን ቆሻሻ ለማጽዳት ኢህአዴግን ደስ አይበለው ብሎ አልወጣም ማለት መሳሳት አይደለም? አካባቢን አጽድቶ እኮ ኢህአዴግን እንደፈለጉ መናገር ይቻላል አይደል? ይሄ አላጸዳም ብሎ የወጣ ህዝብ ኢህአዴግን ጎዳው ማለት ነው? አይ ጅልነት! ያ ራስ የሚያዞር ሽታ የሚጎዳው አንተኑ ድሀውን ነው እንጂ ባለሥልጣናት እኮ ዓለም አቀፍ ሆቴል ውስጥ ነው የሚውሉት።
አዲስ አበባን ለማጻድት የእውቀት ዘመቻ (ይቺ ቃል የደርግ ስለሆነች ኢህአዴግ አይወዳት ይሆን እንዴ!) ቢደረግ ጥሩ ነው። ምክንያቱም እንደምናየው ነው፤ ሰው የራሱን አካባቢ ለማጽዳት እንኳን አልቻለም። ስለዚህ የእውቀት ዘመቻ ቢደረግ!
አዲስ ዘመን ግንቦት 18/2011
ዋለልኝ አየለ