ኢትዮጵያ በአራት ወራት ከወጪ ንግድ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አገኘች

አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ወራት ከወጪ ንግድ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ማግኘቷን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በሚኒስቴሩ የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ በላይነሽ ረጋሳ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በ2016 በጀት ዓመት አራት ወራት አጠቃላይ ለውጭ ገበያ ከቀረቡ ምርቶች ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል፡፡

ሚኒስቴሩ ወደ ውጭ ገበያ ከላካቸው የጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎች፣ የብርዕና አገዳ ሰብሎች፣ የጫት ምርት፤ የቁም እንስሳት፣ ደንና የደን ውጤቶች ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል፡፡

የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ለአፈጻጸሙ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የገለጹት የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚዋ፤ የተገኘውን ውጤት በሌሎች ዘርፎች ላይ ለማሳካት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡

በጫት ምርት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ አዳዲስ አሠራሮች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆናቸውን ጠቁመው፤ በተለይም ጫት ላኪዎች በሕጋዊ መንገድ ወደ ውጭ እንዲልኩ በማድረግ እንደ ሀገር የሚታጣውን ገቢ ማዳን መቻሉን አስረድተዋል፡፡

በግብይት ሥርዓቱ የኦንላይን አገልግሎት ተግባራዊ በመደረግ ላይ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም የውጪ ኮንትራት ምዝገባ አፈጻጸምና የኤክስፖርት መላኪያ ፍቃድ አሠጣጥን ጊዜ ቆጣቢና ቀላል ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

ምርት ላኪ ድርጅቶች በወቅቱ ኮንትራት ገብተው ለዓለም አቀፍ ገበያ ማቅረብ እንዲችሉ ክትትልና ድጋፍ በመደረግ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴና የኮንትሮባንድ ንግድ ላይ የተጠናከረ ክትትል መከናወኑን አመልክተዋል።

በዘርፉ የኮንትሮባንድ ንግድ መስፋፋት፣ የቅባት እህሎች የወጪ ምርት አቅርቦት እጥረት መኖራቸውን ጠቅሰው፤ በኤክስፖርት ምርቶች ላይ አላስፈላጊ ታክስ መኖርና የክፍያ ኬላዎች መበራከት የወጪ ንግድ ገበያው እንዳያድግ ምክንያት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በዘርፉ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታትና ገቢን ለማሳደግ በምርቶች ላይ የክትትልና ድጋፍ ሥራዎች መሠራታቸውን የገለጹት በላይነሽ፤ አገልግሎት አሠጣጡን ቀልጣፋና ወጪ ቆጣቢ ለማድረግ የሪፎርም ሥራዎች መሠራታቸውን አስረድተዋል።

በቀጣይ የኮንትሮባንድ ንግድ ቁጥጥርን ማጠናከር፣ የድንበር ላይ ንግድን ወደ ሕጋዊ መንገድ የማስተሳሰር ሥራዎች እንደሚሠሩ በመግለጽ፤ የገበያ መዳረሻዎችን ማስፋትና ነባር የገበያ መዳረሻን ማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የበይነ መረብ የወጪ ንግድ ግብይትን ማዘመን፣ የወጪ ንግድ ፈቃድ አሰጣጥ ሥርዓትን ማሻሻል እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ በተለይም ዓለም አቀፍ፣ ቀጣናዊና የሁለትዮሽ የንግድ ትስስር ተግባራትን ማጠናከር ትኩረት እንደሚሰጣቸው አመልክተዋል፡፡

አማን ረሺድ

አዲስ ዘመን ኅዳር 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You