መንግሥት ለሰላማዊ ውይይት ሁልጊዜም በሩ ክፍት ነው

– በሸኔ ላይ የተጠናከረ ርምጃ እየተወሰደ ነው

አዲስ አበባ፡- አሸባሪው ሸኔ ከሚፈጽመው የሽብር ተግባር ተቆጥቦ ወደ ሰላማዊ መንገድ የሚመጣ ከሆነ መንግሥት ሁልጊዜም ለሰላም በሩ ክፍት መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ፡፡ ቡድኑ የቀረበለትን የሰላም አማራጭ ወደ ጎን ብሎ በሽብር ተግባሩ በመቀጠሉ መንግሥት የሕግ የበላይነትን የማስከበር ኃላፊት ስላለበት በቡድኑ ላይ ርምጃ እየወሰደ መሆኑንም ገለጸ፡፡

የቢሮ ኃላፊው አቶ ኃይሉ አዱኛ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰው ሸኔ ሽብር ቡድን በተከፈተው የፖለቲካ ምህዳር ባለመጠቀም ኃይልን መሠረት ያደረገ የትጥቅ ትግል አንስቶ ባለፉት ዓመታት በሰው ሕይወትና በብረት ላይ የተለያዩ ጉዳቶችን አድርሷል፡፡ መንግሥትም ቡድኑ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመጣ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡

ሆኖም ቡድኑ የሰላም አማራጮችን ወደ ጎን ትቶ በሽብር ተግባሩ በመቀጠሉ ጠንካራ ርምጃ እየተወሰደበት ይገኛል ብለዋል፡፡

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ብዙ ጥረቶች መደረጋቸውን ያስታወሱት አቶ ኃይሉ፤ በፖለቲካ ምህዳሩ ብልሽት ምክንያት ከሀገር ተሰደው የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ ሀገር እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡

ሸኔም የተከፈተውን ሰላማዊ የትግል ሜዳ ከመጠቀም ዓላማዬን በትጥቅ ትግል አሳካለሁ በማለት በሰላማዊ ዜጎች ላይ የተለያዩ ጉዳቶችን ሲያደርስ መቆየቱን አንስተው፤ መንግሥት በኦሮሞ ባህል መሠረት ችግሮች እንዲፈቱ በሀገር ሽማግሌዎች፣ በአባ ገዳዎችና በሀደ ስንቄዎች አማካኝነት እርቅ ለመፍጠር ጥረት አድርጓል። ሆኖም ቡድኑ በአባገዳዎች የቀረበለትን ሰላም ጥሪ ወደ ጎን ትቶ ሦስተኛ ወገን በተገኘበት ካልሆነ አልደራደርም በማለቱ መንግሥት ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት በሁለት ዙር ንግግር ተደርጓል፡፡

ሽብር ቡድኑ አሁንም ወደ ሰላማዊ መንገድ መመለስ ፍላጎት ስለሌለው ንግግሩ ፍሬ እንዳያፈራ አድርጓል፤ በሽብር ተግባሩም ቀጥሏል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

መንግሥት የሕግ የበላይነትን ማስፈን የዜጎችን ደህንነት ማረጋገጥ ኃላፊነት ስላለበት የክልሉና የፌዴራል ፀጥታ ተቋማት በቡድኑ ላይ ርምጃ እየወሰዱ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም ቡድኑ ተቆጣጥሯቸው የነበሩ ቦታዎችን የማስለቀቅ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡

በመሬት ላይ እየወሰደ ባለው ርምጃ የተደናገጠው ሽብር ቡድኑ በሰላማዊ ዜጎች ላይ አሰቃቂ ርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል ያሉት ኃላፊው፤ በዚህም በአርሲ ዞን ሼካ ወረዳ በወሰደው ጭካኔ የተሞላበት ርምጃ ብዙ ዜጎች ገድሏል፡፡ ቤት ንብረታቸውንም አቃጥሏል፡፡

እንደ ቢሮ ኃላፊው ገለጻ፤ ቡድኑ አሸባሪ ካስባሉት ጉዳዮች አንዱ የራሱን የመደራደር አቅም ከፍ ለማድረግ ሰላማዊ ዜጎቸ ላይ ያነጣጠረ ርምጃ መውሰዱ ነው፡፡

በተጨማሪም ዜጎች ሠርተውና አምርተው ኑሯቸውን በአግባቡ እንዳይመሩ የእርሻ ግብዓቶችን እንዳያገኙ፣ እንዳይጠቀሙና የእርሻ ሥራቸውን በወቅቱ እንዳያከናውኑ እንቅፋት እንደሚፈጥር ጠቁመው፤ የተመረተው ምርት በአግባቡ እንዳይሰበሰብ ለማድረግም ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም መንግሥት የዜጎችን ደህንነትና ሰላማዊ እንቅስቃሴ የማረጋገጥ ኃላፊነት ስላለበት በቡድኑ ላይ ርምጃ እየወሰደ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

በተሠራው ሥራም ባለፈው ሳምንት ከምሥራቅና ምዕራብ ወለጋ ቡኖ በደሌን ለማጥቃትና ለማውደም የተንቀሳቀሰውን የሽብር ቡድን በተወሰደበት ርምጃ ሙትና ቁስለኛ ሆኗል ያሉት አቶ ኃይሉ፤ ሕዝቡም መረጃ በመስጠትና በተለያዩ መንገዶች ከመንግሥት ጎን መሆኑን አረጋግጧል፡፡

ሕዝቡ ቡድኑ ወደ ሰላማዊ መንገድ ይመጣል በሚል ተስፋ አድርጎ ነበር ያሉት ቢሮ ኃፊው፤ መንግሥት ለሰላም ካለው ቁርጠኝነት ወደ ስምምነት ለመምጣት ብዙ ርቀት ሄዶ ጥረት አድርጓል፡፡ ሽብር ቡድኑ ለድርድር ይዞ የቀረበው የጋላቢዎቹን አጀንዳ ነው፡፡ ይህ የሀገርን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ የሚጥል ስለሆነ ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡

በዚህም ድርድሩ የሚፈለገውን ውጤት ስላላስገኘ የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅና የሕግ የበላይትን ለማረጋገጥ አስፈላጊው ሁሉ ዋጋ እንደሚከፍል ጠቅሰው፤ ቡድኑ ተገዶ ወደ ሰላም እንዲመጣ የሚያደርግ ጠንካራ ሥራ ይሠራል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በተሳሳተ መረጃ ሽብር ቡድኑን የተቀላቀሉ ወጣቶች ወደ ሰላማዊ ሁኔታ እየተመለሱ መሆኑን አመልክተው፤ በቀጣይነትም ሕዝቡን በማስተባበር ቡድኑ የዜጎች ስጋት ከማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ የሚያስችል ርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

መንግሥት ለሰላም የዘረጋው እጁ ዛሬም አልታጠፈም ያሉት አቶ ኃይሉ፤ የሽብር ቡድኑ ከሽብር ተግባሩ ተቆጥቦ ወደ ሰላማዊ ውይይትና ንግግር ከተመለሰ መንግሥት ለሰላም ሁልጊዜም በሩ ክፍት ነው ብለዋል፡፡

ፋንታነሽ ክንዴ

 አዲስ ዘመን ኅዳር 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You