
አዲስ አበባ:- የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር ኢትዮጵያ ልማትና ብልጽግናን ለማሳካት በምታደርገው ትግል ወሳኝ ድርሻ አለው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ28ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ28) ላይ ንግግር አድርገዋል።
በንግግራቸው የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራ ከኢትዮጵያ አልፎ ለዓለም ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ወሳኝ ድርሻ እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገልጸዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቁ የደን ልማት ፕሮጀክት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መርሐ-ግብሩ የአካባቢ ጥበቃና ልማትን ከማሳደግ ባለፈ ለበርካቶች የሥራ ዕድል የፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብርን በማጠናከር ለጎረቤት ሀገራት ጭምር የተለያዩ ችግኞችን በማከፋፈል መሥራቷን ጠቁመው፤ መርሐ-ግብሩ በአፍሪካ ለሚገኙ ሌሎች የልማት የትብብር ሥራዎችም መጠናከር ግብዓት እንደሚሆን አመላክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኮፕ28 ጉባኤ ጎን ለጎን ከተለያዩ ሀገራት መሪዎች ጋር በሁለትዮሽ ትብብር ጉዳዮች ላይ ገንቢ ውይይት አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከቤልጂየም ጠቅላይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ዴ ክሮ ጋር በሀገራቱ ሁለትዮሽ ትብብር ጉዳዮች ዙሪያ ላይ ተወያይተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኮፕ28 ጉባኤ አስቀድሞ ከቤልጂየም ጠቅላይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ዴ ክሮ ጋር በኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ መካነ ርዕይ (ፓቪሊዮን) ተገናኝተዋል፡፡
ሁለቱ መሪዎች በወቅታዊ የሀገር ውስጥ እና ሁለትዮሽ ትብብር ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጋር ተወያይተዋል፡፡
መሪዎቹ ከኮፕ28 ጉባዔ ጎን ለጎን ባደረጉት ውይይት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ታሪካዊ ወዳጅነት ይበልጥ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኮፕ28 ጉባኤ ጎን የኩባውን ፕሬዚዳንት ሚግዌል ዲያዝ-ካናልን በኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ መካነ ርዕይ (ፓቪሊዮን) ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡
ሁለቱ መሪዎች የዓለም የአየር ጠባይ ለውጥ ኃላፊነትን፣ የሁለትዮሽ ትብብርን እና የብሔራዊ ልማት ጉዳዮችን የተመለከተ ውይይት አድርገዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከእንግሊዝ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር ጋር ተወያይተዋል።
በ28ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ በመሳተፍ ላይ የሚገኙ የዓለም ሀገራት አዲስ የአየር ንብረት አደጋ ፈንድ ስምምነት አጽድቀዋል፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ኅዳር 22 ቀን 2016 ዓ.ም