የሺናሻ ብሄረሰብ አባላት የባህላዊው ህግ ወይም ሽምግልናን አምነው እና ተቀብለው ለአያሌ ዘመናት እየተዳደሩበት ይገኛሉ። በብሄረሰቡ ዘንድ ዘመናዊ ያልሆነ ነገር ግን ፍርድ በመስጠት አገልግሎት ላይ የሚውሉ ሦስት ደረጃዎች ያሉት ባህላዊ የዳኝነት ስርዓቶች አሉ። እነሱም የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ‘’ቡራ’’፣ የሁለተኛ ደረጃ ፍርድ ‘’ኔማ’’ ፣የሦስተኛ ደረጃ ፍርድ ‘’ፄራ’’ተብለው የሚታወቁ ናቸው፡፡
“ቡራ” አንድ ሽማግሌ ብቻውን ሆኖ የሚፈርድበት የቤተሰብ ባህላዊ ችሎት ነው። የ”ቡራ” ፈራጆች ወይም ሽማግሌዎች የሚመረጡት ከሟችና ከገዳይ ቤተሰብ ውጪ የሆኑና ከገለልተኛ አካል (ወገን) የተወጣጡ ናቸው።
በመሆኑም በሁለቱም ቡድኖች (ከሟች ወገንና ከገዳይ ወገን) ምስጢር ይጠብቃሉ ተብሎ የታመነባቸው መሆን አለበት። ይህ የ“ቡራ” የፍርድ ችሎት መጀመሪያ ደረጃ ግጭት መፍቻ እንደመሆኑ መጠን የቅርብ ጊዜ ወይም ትኩስ የሆነ አለመግባባቶችና የግድያ ግጭቶችን የሚያይ ነው። ይህ የግጭት አፈታት ዘዴ እንደአስፈላጊነቱ ሊታይ የሚችል እንጂ ቋሚ አይደለም።
በ‘’ቡራ” ደረጃ ፍርድ ላይ ፈራጅ ሆኖ የሚሾመው ወይም የሚመረጠው ግለሰብ የብሄረሰቡን ባህላዊ ጉዳዮች በደንብ አድርጎ የሚያውቅ፣ ግጭቶችን በመፍታት ዙሪያ በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለው፣ ለእውነት ሲል የሚፈርድ መሆን አለበት። ይህ ፈራጅ የመጀመሪያ ዳኝነት እንደመሆኑ መጠን የበዳይን ጥፋት ተመልክቶ በራሱ አቅም የማይፈታ ከሆነ በቀጥታ የሚፈርድ ሳይሆን ወደ ሌላ ሁለተኛ ደረጃ ፍርድ እንዲሄድ የሚያደርግበት አካሄድ አለው።
“ኔማ” ደግሞ ሦስት ሽማግሌዎች በጋራ ሆነው የሚፈርዱበት ባህላዊ ችሎት ነው። እነዚህ ፈራጆች ከማህበረሰቡ ጋር የጠበቀ ቁርኝት ያላቸው፣ ለገዳይ ወይም ለሟች ወገን የማያዳሉ፣ ከማህበረሰቡ ዘንድ ታማኝና ተቀባይነት ያላቸው፣ እንዲሁም የማህበረሰቡን ባህል ጠንቅቀው የሚያውቁና በባህሉ መሰረት በተለያዩ ምክንያቶች በሰዎች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶችን በመፍታት ወይም በማስታረቅ ከፍተኛውን ድርሻ የያዙ ሊሆኑ ይገባል። ‹‹ኔማ›› በዘመናዊው ህግ ይግባኝ እንደ ማለት ነው። በቡራ ፍርድ አንድ ሰው ቅር ከተሰኘ የተፈረደው ፍርድ ሚዛናዊነት የያዘ አይደለም በማለት ወደ ‘’ኔማ” ፈራጅ ይግባኝ በማለት ፍርዱ በ“ኔማ” ፈራጅ እንዲታይለት ትክክለኛ ዳኝነት የሚጠይቅበት የፍርድ አካሄድ ነው።
ሦስተኛ ደረጀ ዳኝነት ደግሞ ‹‹ፄራ›› በመባል የሚታወቅ ነው። ይህ ባህላዊ ችሎት በአንድ ሰው የሚመራ የዳኝነት ችሎት ዓይነት ሲሆን የመጨረሻውና ይግባኝ የማይጠየቅበት የዳኝነት ስርዓት ነው። ይህ ችሎት በይግባኝ ሰሚ ችሎት ‹‹ኔማ›› የአንድን ሰው ጥፋት ለመፍታት የማይቻለውና ጥፋቱ ካቅማቸው በላይ በሚሆንበት ጊዜ ወደ ‘’ፄራ” የፍርድ ችሎት እንዲሸጋገር ያደርጋሉ። በፄራ የፍርድ ችሎት ፈራጅ ሆኖ የሚሾም ሽማግሌ በስነ ምግባር የታነፁ፣ ታማኝና ቁቡሉነት ያላቸው፣ ፍርዱ እውነትን መሠረት ያደረገ፣ የብሔረሰቡን ባህል ጠንቅቀው የሚያውቁ መሆን መቻል አለባቸው።
በአብዛኛው ጊዜ ባህላዊ መንገድ ግጭት የሚያስወግዱ ወይም የሚፈቱ ሽማግሌዎቸ ፍርድ የሚሰጡት በማህበረሰቡ በተመረጡ ሽማግሌዎች አማካይነት ነው። በመሆኑም የሽናሻ ብሄረሰብ በዳይ (ገዳይ) እና ተበዳይ (የሟች ወገን) ፄራ ለመምረጥ ነፃ ናቸው። በዚህም መሰረት የፄራ
ሽማግሌ ሲመረጡ መሟላት የሚገባቸው ጉዳዮች ከአባት፣ ከአያት፣ ከቅድመ አያት ያገኙት የግጭት አፈታት፣ የምርቃት እውቀት ያላቸው፣ ወንጀል ነክ ጉዳዮችን በማየት ከፍተኛ የሆነ ልምድ ያላቸው፣ ምክንያታዊ የሆነ፣ ሃሳቡን በነፃነት መግለፅ የሚችልና የማሰብ ችሎታ ያላቸው መሆን አለባቸው።
ይሄ ደምን በባህላዊ የግጭ መፍቻ የዳኝነት መንገድ ማድረቅ ከሽናሻ ብሄረሰብ ውጪም ሌሎቹም ይጠቀሙበታል። የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቋንቋና የባህል እሴቶች ልማት ዳይሬክቶሬት ያወጣው አንድ ጽሑፍ “አበጋር” በመባል የሚታወቅ በወሎ ብሔረሰቡ ስለሚዘወተር ዕርቅ ዓይነት እንዲህ አስነብቧል፡፡ አበጋር ባህላዊ የግጭት መፍቻ ስርዓቱ ተቋም መጠሪያ ስያሜ እና የዳኛነት ስርዓቱን የሚከውኑ ግለሰቦች የማዕረግ ስም ነው፡፡
አበጋር በሚኖሩበት አካባቢ ማህበረሰብ ውስጥ የሚከሰቱ የተለያዩ ግጭቶችን የመፍታትና የማስታረቅ ስልጣንና ይሁንታ ያገኙ ሰዎችን የያዘ ተቋም ነው፡፡ ተቋሙ ከአነስተኛ ግጭት እስከ ከፍተኛው የግድያ ወንጀል ድረስ ያሉ ግጭቶችን በየደረጃው የመፍታት ስልጣን አለው፡፡ ይህ ተቋም ወንዶች ብቻ የሚሳተፉበት ነው፡፡
የአበጋርነት ማዕረግ በሁለት መንገድ ይገኛል። የመጀመሪያው ከዘር የሚወረስ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በመመረጥ ይገኛል፡፡ በዘር የሚገኘው አበጋርነት ከጥንት ጀምሮ ከአባት ወደ ወንድ ልጅ በቅብብሎሽ የሚወረስ ነው፡፡ ወንድ ልጅ የሌለው አበጋር ለሴት ልጁ ማውረስ አይችልም። ነገር ግን አበጋሩ ለመረጠው የወንድሙ ወይም ለእህቱ ወንድ ልጅ ማውረስ ይችላል፡፡ አበጋሩ የሚተካውን አካል የመምረጥ እና የማብቃት እንዲሁም ዕድሜው መድረሱን ያረጋግጣል፤ ተተኪው አበጋር የማመዛዘን ብስለቱ እንዲያድግ እና ትክክለኛ ፍርድ እንዲሰጥ ዕድሜው 30 እና ከዚያ በላይ መሆን ይኖርበታል፡፡
ሁለተኛው የአበጋርነት ማዕረግ ደግሞ በመመረጥ የሚገኝ ነው፡፡ ከአካባቢው ማህበረሰብ መካከል ተደማጭነት፣ ተቀባይነት፣ የሚከበር እና ተግባቢነት ያለውን ግለሰብ ማህበረሰቡ በመምረጥ እና በመሰየም የሚሰጠው ማዕረግ ነው፡፡
የተመረጠው አበጋር በተለያዩ ሁኔታዎች የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት ካልቻለ ሌላ የሚመረጥ ሲሆን የመተካት ስልጣን ያለው የአካባቢው ማህበረሰብ ነው፡፡ በዘር እንደሚገኘው የአበጋርነት ማዕረግ ለወንድ ልጁ ወይም ለሌላ አካል ስልጣኑን ማውረስ ወይም ማስተላለፍ አይችልም፡፡ አበጋር የሰላም አባቶች ናቸው። ደም የተቃባን ያስታርቃሉ ፣ ደም ያደርቃሉ፡፡
አብዛኛው የወሎ ህዝብም የሃይማኖት ልዩነት ሳይገድበው በአበጋር ይዳኛል፡፡ አበጋሮች ወይም ሽማግሌዎች የሟች እና የገዳይን ቤተሰብ ያቀራርባሉ፡፡ የአበጋርን የሰላም፣የእርቅ ጥሪ አልቀበልም የሚል አይኖርም፤ ቢኖርም ከህብረተሰቡ ይገለላል፡፡ የአበጋር የእርቅ ስነ ስርዓት በሁሉም ህብረተሰብ ይከበራል፡፡
በአጠቃላይ አበጋር የዘመመ ጎጆን ፣ የፈረሰ ትዳርን ያቃናል፡፡ እነዚህ ባህላዊ ዳኝነቶች እና የእርቅ ስነ ስርዓቶች ሊጎለብቱ እና ሊያድጉ ይገባል፤ ምክንያቱም ዘመናዊውን የፍትህ ስርዓት ያግዛሉ። ባህላዊ እሴቶች በማንኛውም ማህበረሰብ ዘንድ ችግር ፈቹ ሆነው ዘመንን ተሻግረዋል። ዛሬም ግጭቶችን በመፍታት እያገለገሉ ናቸው። ስለዚህ እኛም ለባህላዊ እውቀቶች እና ግጭት አፈታቶች ትኩረት ይሰጥ እንላለን፡፡ ሰላም!
አዲስ ዘመን ግንቦት 18/2011
አብርሃም ተወልደ