የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የማሻሻያ አዋጅ በሙሉ ድምጽ ጸደቀ

-አዋጁ በልዩ ልዩ አማራጮች የይዘት ተደራሽነትን ለማስፋት ያስችላል

አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የጀመራቸውን የሪፎርም ሥራዎች ለማጠናከር፣ የይዘት ሥራዎችን ተደራሽነት ለማስፋት እና የመንግሥት የፋይናንስ እና ንብረት አስተዳደር መርሆዎችን የተከተለ አሠራር ለመዘርጋት የሚያስችለው አዋጅ ጸደቀ። አዋጁ፤ ድርጅቱ በልዩ ልዩ አማራጮች የይዘት ተደራሽነቱን እዲያሰፋ የሚያደርግ መሆኑም ተገልጿል፡፡

6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ጉባዔ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ማቋቋሚያ አዋጅ ማሻሻያን መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል። አዋጁ ለተቋሙ በህትመት ተደራሽነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ በተጨማሪነት በልዩ ልዩ የይዘት ማስተላለፊያ አማራጮች እንዲሰማራ የሚፈቅድለት ነው።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ፤ ድርጅቱ እስካሁን ያለውን አቅም  እያዳበረ እንዲሄድ በተጨማሪም ዘመኑ ከደረሰበት ቴክኖሎጂ አኳያ የመልቲ ሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም የጀመራቸውን ሥራዎች እንዲተገብር ማድረጉ ጠቃሚ መሆኑን አንስተዋል።

በተወሰነ ሀብት ቴክኖሎጂን በመጠቀም ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ መፍጠር ተገቢ መሆኑንም ከቋሚ ኮሚቴውና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት በማካሄድ ምላሽ እንዲያገኝ መደረጉንም አቶ ታገሰ አመልክተዋል።

ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ እውነቱ አለነ፤ ተቋሙ በኢትዮጵያ ሕትመት ሚዲያ ዘርፍ ከፍተኛ ልምድና እውቀት ያለው መሆኑን አንስተዋል።የሚበረታቱ በርካታ የሪፎርም ሥራዎች መሠራታቸውንም ጠቁመዋል።

በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያው እጅግ መዘመን ምክንያት የህትመት ሚዲያው ሊገጥመው የሚችለው ፈተና ቀላል ባለመሆኑ በህትመት ዘርፍ ብቻ መቀጠሉ አዋጭ አለመሆኑን አንስተዋል።

‹‹አዲሱ የሚዲያ ዘመን ላይ ነን።ወቅቱ ከኢንተርኔት ጋር የተያያዘ በመሆኑ የመጡ አዳዲስ ለውጦች አሉ፣ ሂደቱም የሚዲያ መዋሃድ እንዲፈጠር፣ የሚዲያ ድንበርም እንዲጠፋ አድርጓል›› ሲሉ አንስተዋል።

ሁሉም ሚዲያዎች የተዋሃዱበት ዘመን ተፈጥሯል ያሉት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ፤ ይህ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ፈተናም ዕድልም አምጥቷል ብለዋል፡፡

በዚህም ድርጅቱ ከህትመት ሥራው ሳይወጣ ሌሎች አማራጮችን እንዲጠቀም ማድረግ ተገቢ ነው ያሉት የተከበሩ አቶ እውነቱ፤ የሌሎች ሀገራት ልምድና ተሞክሮም የሚያሳየው ይህንኑ የተደጋገፈ ሥርዓት መሆኑንም በማንሳት አብራርተዋል።

በመሆኑም ኅብረ ብሄራዊ አንድነት እና ብሄራዊ መግባባት እንዲመጣ ድርጅቱ ከፍተኛ ልምድ ካካበተበት የህትመት ሚዲያ ሥራ በተጨማሪ የተለያዩ የይዘት የማሰራጫ አማራጮችን መጠቀም እጅግ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።

ድርጅቱ ካለው ባህሪ የተነሳ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የግዢና የፋይናንስ ሥርዓትን ተከትሎ ማከናወን እና ሂሳቡን ማስመርመር ለተቋሙ ትልቅ ፈተና እየሆነ በመምጣቱ የመንግሥት የፋይናንስና ንብረት አስተዳደር መርሆዎችን የተከተለ የራሱን አሠራር እንዲዘረጋ በአዋጁ ተደንግጓል። በዚህም የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ማሻሻያ አዋጅ ማሻሻያ ቁጥር 1308/2016 ሆኖ በሙሉ ድምጽ ጸድቋል።

ምክር ቤቱ በተጨማሪም የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአፍሪካ መድሃኒቶች ኤጀንሲ ማቋቋሚያ ስምምነት ረቂቅ አዋጅን ለማጽደቅ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብም መርምሮ አጽድቋል።

የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ወርቀሰሙ ማሞ ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳቡን ሲያቀርቡ እንዳሉት፤ የአፍሪካ ኅብረት አባል ሀገራት ጥራቱ፣ ደህንነቱና ውጤታማነቱ የተረጋገጠ መድሃኒት ለአፍሪካ ሕዝብ ጤና እና ደህንነት አስፈላጊ መሆኑን በማመን የአፍሪካ መድሃኒቶች ኤጀንሲን ማቋቋማቸውን ተከትሎ ኢትዮጵያም ስምምነቱን ተቀብላ ማጽደቋ አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።

የኤጄንሲው መቋቋምና ስምምነቱ መፈረሙ በአፍሪካ እየተከናወኑ ያሉ የመድሃኒት ቁጥጥር አሠራር ሥርዓቶችን ለማስተባበር፣ የኅብረቱ አባል ሀገራት፣ በክፍለ አህጉር ደረጃ የሚገኙ የኢኮኖሚ ማኅበረሰቦችን እንዲሁም የክፍለ-አህጉራዊ የጤና ተቋማትን ጥረት ለማጠናከር እንደሚያግዝም ነው ያብራሩት።

የቁጥጥር መመሪያ ማቅረብና ህመምተኞች በጥንቃቄ፣ ጥራቱን በጠበቀና ፍቱንነቱ በተረጋገጠ የመድኃኒት ምርቶችና የጤና ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል በመሆኑ እንዲሁም ለሕዝቡ ጥራቱና ደህንነቱ የተጠበቀ መድሃኒት እንዲዳረስ የሚያስችል መሆኑን በማመን ቋሚ ኮሚቴው በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል።

ዘላለም ግዛው

አዲስ ዘመን   ኅዳር 21ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You