የመመሪያው ተፈጻሚነት የሁሉንም አካላት ርብርብ ይሻል!

በከተማችን ከፍተኛ የሕዝብ ቅሬታ ምንጭ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ «የጫኝና አውራጅ ማኅበራት» ጉዳይ እንደሆነ የሚታወቅ ነው። ማኅበራቱ በየአካባቢው ያሉ ሥራ አጥ ወጣቶችን በሕጋዊ መንገድ ወደ ሥራ በማስገባት ለራሳቸው፤ ለቤተሰባቸው እና ለሀገራቸው አምራች ዜጋ እንዲሆኑ ታስበው ወደ ተግባር የገቡ ናቸው።

እነዚህን በከተማዋ የሚገኙ ሥራ አጥ ወጣቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኩል የተወሰደው እርምጃ በወቅቱ ከጭነት ማውረድና መጫን ጋር በተያያዘ ይፈጠሩ የነበሩ ያልተገቡ ውጣ ውረዶችንና አለመግባባቶችን ሕጋዊ በማድረግ፤ ሥርዓት ማስያዝ እንደሚችልም በብዙዎች ዘንድ ታምኖበት ነበር።

ሁኔታዎች ግን ከታሰበው ይልቅ ወደ አልታሰበው እያመሩ፤ ነዋሪዎችን ላልተፈለገ ወጪና እንግልት ዳርገዋል። በየአካባቢው ለጸጥታ መደፍረስና ለአምባጓሮ ምክንያት ሆነዋል። በየሰፈሩም በማኅበራቱ ስም ለሕግና ለሥርዓት ተገዥ ያልሆኑ የመንደር የጎበዝ አለቃዎችንም ፈጥሯል።

የከተማዋ ነዋሪዎች በንብረታቸው ላይ የማዘዝ ሕጋዊ መብታቸውን ተነፍገው፤ በየሰፈሩ የተፈጠሩ የጎበዝ አለቆች በወደዱትና በፈቀዱት መንገድ ለመስተናገድ የተገደዱበት ሁኔታ ተፈጥሮ ቆይቷል። ችግሩም በጸጥታ አካላት ሳይቀር በቂ ትኩረት ባለማግኘቱ ነዋሪዎች ለከፋ ችግር ተዳርገው ቆይተዋል።

ችግሩ በተለይም በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ የማኅበራትና የጋራ ቤቶች አካባቢ ጎልቶ ሲስተዋል የቆየ ነው፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች በተለያዩ ምክንያቶች ቤት ለመቀየር የሚገደዱ የከተማዋ ነዋሪዎች ከሚያስወርዱት /ከሚያስጭኑት ዕቃ ዋጋ የበለጠ የሚጠየቁበት ሁኔታም መፈጠሩም የችግሩን አሳሳቢነት የሚያመላክት ነው።

ዕቃዎችን ባልነው ዋጋ፣ ያለእኛ ማውረድ አይቻልም የሚሉት በማኅበር ስም የሚንቀሳቀሱ የየመንደር የጎበዝ አለቃዎች፤ ለሚሰጡት አገልግሎት ዋጋ ለመተመን ምንም ዓይነት ይሉኝታ የሌላቸው፤ ከምንም በላይ በማስፈራራትና በማስጨነቅ የጠየቁትን ለማስከፈል ራሳቸውን ያዘጋጁ ናቸው።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ በአዲስ አበባ አንድ ሺህ 78 በሕጋዊ መንገድ እና 550 ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የተደራጁ የጫኝና አውራጅ ማኅበራት ይገኛሉ። ሕጋዊዎቹን ትተን ሕገወጦቹን ብቻ እንኳን ለማየት ብንሞክር ችግሩ የቱን ያህል የገነገነ እንደሆነ አመላካች ነው።

ይህንን የነዋሪዎችን ችግር ለዘለቄታው ለመፍታት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፤ የጫኝና አውራጅ ማኅበራት የአገልግሎት አሰጣጥን ለመከታተልና ለመቆጣጠር የሚያስችል አዲስ መመሪያ ተግባራዊ ማድረጉን የከተማዋ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ሰሞኑን አስታውቋል፡፡

እንደ ቢሮው ከሆነ፤ አዲሱ የመተዳደሪያ መመሪያ በጫኝ እና አውራጅ ሥራ ላይ ይነሳ የነበረውን ችግር በመፍታት ማኅበረሰቡ ሰላማዊና የንብረት ደህንነት የተረጋገጠ አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችል ነው፡፡

ማኅበራቱም በመመሪያው መሠረት ማኅበራቱ በተደራጁበት ዓላማ ብቻ በመሥራት ለማኅበረሰቡ ስጋት ሳይሆን የሰላማዊ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል፤ ሥራቸውን ሕግና ሥርዓት በተከተለ መልኩ መሥራት ከቻሉ ከኅብረተሰቡ ጋር የሥራ አጋርነት በመፍጠር ተጠቃሚ መሆን የሚያስችላቸውም ነው፡፡

መመሪያው ማኅበራትን ከማደራጀት ጀምሮ ከአገልግሎቱ ላይ የሚያጋጥሙ ቅሬታዎችን የሚፈታ፣ የሕግ ተጠያቂ የሚያሰፍን፣ ያለአግባብ ክፍያንና አስገዳጅ አሠራርን የሚያስቀር እንደሆነም አመልክቷል፡፡

አስተዳደሩ የጫኝና አውራጅ ማኅበራት ተጠሪነታቸው የከተማዋ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ እንዲሆን ከማድረግ ጀምሮ፤ ለማኅበራቱ የሚተዳደሩበት አዲስ መመሪያ አዘጋጅቶ ወደ ሥራ መግባቱ ለችግሩ የሰጠውን ትክረት አመላካች ነው። የነዋሪዎችን ቅሬታ ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት የሚገልጽ ነው።

መመሪያው ከሁሉም በላይ የነዋሪዎችን በንብረታቸው የማዘዝ ሕጋዊ መብት ብቻ ሳይሆን፤ ለሚፈልጉት አገልግሎት መክፈል የሚገባቸውን ክፍያ የራሳቸውን አቅም ታሳቢ አድርገው መክፈል የሚያስችላቸውን አቅም የሚያጎናጽፋቸው ሊሆን ይገባል ።

ችግሩ አብሮን ለረጅም ጊዜ ከመቆየቱ የተነሳም በተለይም በየአካባቢው የነበሩ የጎበዝ አለቆች ሲሄዱበት የነበረው ሕገወጥ መንገድ፣ ሕጋዊ የሆነ ያህል ተቀብለውት የነበረ በመሆኑ የመመሪያው አፈጻጸም አልጋ በአልጋ ሊሆን እንደማይችል ይታመናል።

ከዚህ የተነሳ በተለይም የጸጥታ ተቋማት ችግሩ በአንድም ይሁን በሌላ በከተማዋ ሕጋዊነት ከማስፈን ጋር የተያያዘ የጸጥታ ጉዳይ ጭምር በመሆኑ ለመመሪያው ተፈጻሚነት ራሳቸውን በበቂ ደረጃ ማዘጋጀት እና ቁርጠኛ መሆን ይጠበቅባቸዋል!

አዲስ ዘመን ህዳር 21/2016

Recommended For You